Tidarfelagi.com

‹‹ቢልልኝ››

(መታሰቢያነቱ፡ ‹‹ለምወድሽ››)

….ዛሬስ ልቤ ወጌሻ የሚፈልግ ይመስለኛል፣ የኔ ጌታ። ልቤን የሚያሽ ወጌሻ ፈልግልኝ እስቲ..ስብራቱን የሚያቃና።

‹‹አስራ አራት አመት ካልወለዳችሁ ከዚህ ወዲህ የመውለድ እድላችሁ ዜሮ ነው›› ነው ያለው ሀኪማችን?

ከዚያ ሁሉ ምርመራ፣
ከዚያ ሁሉ ምልልስ፣
ከዚያ ሁሉ ተስፋ በኋላ፤

‹‹አስራ አራት አመት ካልወለዳችሁ ከዚህ ወዲህ የመውለድ እድላችሁ ዜሮ ነው›› ነው ያለው ሀኪማችን?

ቆሽቴም ይነዳል። መላ አካላቴ ይግማል። ደሜ እንደ ትኩስ ሽሮ ሲንተከተክ ይሰማኛል።

ልክ እንዲህ እንዲህ ሲያደርገኝ ‹‹አምላኬ ሆይ፣ በዚህ አለም ላይ ስኖር ልቀይር የማልችለውን ነገር እንድቀበል፣ ልቀይር የምችለውን ነገር ደግሞ እቀይር ዘንድ የሚያስችለኝ ጥንካሬ ስጠኝ። ከዚህ በላይ ግን በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት እንድረዳ አስተውሎት ስጠኝ›› እልና መለስ እላለሁ። ረጋ። ረገብ። ቀዝቀዝ።

የኔ ጌታ፣

ቢልልኝ፣ ልጅ ልወልድልህ እፈልጋለሁ።

ግማሽ እኔ፣ ግማሽ አንተ የሆነ ልጅ ፈጥረን ብንኖር ደስ ይለኛል።

እግዜር አንተ እና እኔን አዋህዶ በተአምር አንድ ልጅ ቢያደርገን እሻለሁ። የሁለታችንን ነፍስ እና ስጋ በአንድ ሰው ላይ መርጎ ተአምሩን ቢያሳየኝ እናፍቃለሁ።

ዘርህን አራብቶ እኔ ውስጥ ቢያበቅለው፣
ከአንተ ገንጥሎ እኔ ውስጥ ቢያፀድቀው እጅግ እመኛለሁ።

‹‹አይኑ እኔን..ፀጉሩ ያንተን ነው የሚመስለው›› እያልን ብንሳሳቅ እወዳለሁ።

ይሄን የምመኘው የተጋባ ሁሉ ልጅ መውለድ ስላለበት አይደለም።
መደበኛ የሕይወት ኡደት ውስጥ እንድንሰለፍም አይደለም።

እናት እና እህቶችህ በተጋባን ወር ጀመሮ ልሙጥ ሆዴን በገምጋሚ አይኖቻቸው መቀላወጥ ስለጀመሩ አይደለም።
ያጋቡን ቄስ ‹‹ሊጥ የሌለው ቡሃቃ›› ብለው በአሽሙር ስለወጉኝም አይደለም።
ያገኘን ሁሉ የትዳር ጊዚያችንን በግማሽ እያካፈለ፤ ‹‹ልጆቻችሁስ?›› እያለ ስለሚያሳቀቀኝም አይደለም።
የሀገር ጠበል፣ የሀገር መድሃኒት፣ የሀገር አዋቂ ያልፈታው ያልተፈታ የዘር ህልም አንፍዞኝም አይደለም።

ልወልድልህ የምፈልገው አንተን የመሰለ ሰው በዚህ አለም ላይ መደገም ስላለበት ነው።

ቅጂህ ስለሚያሰፈልግ ነው።

አንተን የሚመስልን ሌላ ሰው በመፍጠር ሂደት ውስጥ የመሳተፍ መባረክን አጥብቄ ስለምፈልግ ነው።

ለዚህ ነው ቢልልኝ ልወልድልህ የምፈልገው።

የኔ ጌታ፣

ሰው የሆንኩት እኮ ባንተ ነው።
መኖር የጀመርኩት እኮ አንተን ካገኘሁ ነው።

ለዚህ ነው ያንተን ዘር ከማብቀል ለበለጠ አላማ ልታጭ የማልፈልገው።
እና ደግሞ ለትዳራችን የልጅ ሃውልት ማቆም ካልቻልኩ፣ ሰዎች እንደሚሉት ጥለኸኝ እንዳትሄድና እንዳልሞት ስለምፈራም ነው።

መኖር የጀመርኩት አንተን ካገኘሁ ነው አላልኩህም?

ጥለኸኝ ስትሄድ እሞታለኋ……ሙትት…::

እናም ልወልድልህ እፈልጋለሁ..።

ለትዳራችን የልጅ ሃውልት ለማቆም፣
ለእቅዳችን ያለመዛነፍ፣
ውጥናችንን ከስርዝ ድልዝ ለማዳን፤

ልወልድልህ እፈልጋለሁ።

ላንጠገን እንዳንሰበር፣ ላንገኝ እንዳንጠፋ ስል..፣
ያላፈራነው ፍሬ የትዳራችንን ዛፍ እንዳይመርዘው፣
ማጭድ ሆኖ እንዳይቆርጠው…፤

ቢልልኝ ልወልድልህ እፈልጋለሁ።

ትዳር በልጅ ትሩፋት ካልሆነ በመዋደድ ብቻ አይቆምም ስለሚሉኝ፣
ያልበቀለው ዘራችን ከስራችን እንዳይነቅለን ስለምፈራ፣

ልወልድልህ እፈልጋለሁ።

….ግን ባይሆንልኝስ…? ሀኪሙ እንዳለው ልጅ ሳይሆን የማይሰምር ምኞት ብቻ ታቅፌ ብቀርስ?

መጨረሻችን ከዚህ ድንግዝግዝ አልፎ ይታይሃል?
መድረሻችንን ከወዲሁ ማየት ይቻልሃል?

ባላላቆጥነው ጭቃ ተዳልጠን ድፍት ስንል፣
ያልቆፈርነው ጉድጓድ ውስጥ ስንገባ ታየህ?

ወይስ ለሁለት የጀመርነው ጉዞ ሁለት እንዳለን ሲፃና?

የኔ ጌታ…ምን ይታይሃል?

….ዘመናይ ጓደኞቼ ‹‹ጉዲፈቻ አሳድጊ›› ይሉኛል።

ያልገባቸው ምን መሰለህ..?

እኔ ልጅ አይደለም የምፈልገው። ያንተን ልጅ ነው የምፈልገው።

አንተን ነው መድገም የምፈልገው።

አላማዬ፤ ባልፈጠርነው ልጅ ማእበል የትዳራችን ጀልባ እንዳይመታ ማድረግ ነው።

…የኔ ጌታ፣

እግዜሩ ግን ምነው እንዲህ ሆዱ ጨከነ?

አንተ እኮ ወልዶ ከብዶ የቀለለ በበዛበት ዘመን ልጅ የሌለህ ጥሩ አባት ነህ።
እኔ እኮ ወልዳ የምትጥል በበዛችበት ዘመን ያልወለድኩ ግሩም እናት ነኝ።

ታዲያ እግዜሩስ ለምን ጨከነ?

ለምን የአመታት ልመናችንን ጆሮ ዳባ ልበስ አለ..?

ምናልባት አልተመረቅን ይሆን…?

ስላልተመረቅን ይሆን ያልለመለምነው?

ተረግመን ይሆን የተቀሰፍነው…?

ግን ምን አጥፍተን?

አንተ እኮ ወልዶ ከብዶ የቀለለ በበዛበት ዘመን ልጅ የሌለህ ጥሩ አባት ነህ።
እኔም ብሆን ወልዳ የምትጥል በበዛችበት ዘመን ያልወለድኩ ግሩም እናት ነኝ።

….ብቻ የኔ ጌታ…

ልጅ በዝቶ እንቅፋት በሆነበት ሀገር ልጅ መከልከላችን የእግዜር ምፀት ይመስለኛል።
ያላጠናንበትን ፈተና እየተፈተንን ይመስለኛል::

ግን ቢልልልኝ ብወልድልህ እመኛለሁ።

ይሄንን መልካምነትህን፣ ይሄንን ደግነትህን፣ ይሄንን አይደገሜነትህን ….
በራስህ ልጅ ብደግመው እላለሁ…

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *