Tidarfelagi.com

“ወዜን አልሸጥም”

በካን ፊልም ፌስቲቫል ላይ ይፋዊ የዕይታ ተሳትፎ በማድረግ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ፊልም ሆኖ የተመረጠው የያሬድ ዘለቀ ዳንግሌ (Lumb) ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ የነበረኝን የሥራ ቆይታ አስታውሼ፣ ከቀረፃው በፊት ስለነበረው የአልባሳት ግዢ ቆይታ ላጫውታችሁ።

ህሊና ደሳለኝ የፊልም ሥራ ውስጥ በአልባሳት ዲዛይነርነት እየታወቀች የመጣች ወጣት ባለሙያ ነች። በዚህ ፊልም ደግሞ የዋናዋ ፈረንሣዊት ዲዛይነር የሳንድራ በርቢ ረዳት ናት። ከእሷ ረዳት መስከረም ወንድማገኝ ጋር ሆነን ሦስታችንም በመኪና አዲስ አበባን ለቀን ያለፈው ዓመት በክረምት ወቅት ጉዞ ወደ ጎጃም አደረግን።

ለፊልሙ የሚያስፈልጉ አልባሳትን ንድፍና ናሙናቸውን በፎቶ የተደገፈ ማብራሪያ ስለያዝን ፣ የሚቀራረብ ልብስ ባየን ቁጥር በየመንገዱ እየቆምን ለመግዛት ጥረት ማድረግ ጀመርን። ልብሶቹ ከተሰበሰቡ በኋላ በዲዛይነሮቹ አማካኝነት ወደ’ሚፈለገው የልብስ አይነት ስለሚቀየሩ በአብዛኛው በዲዛይነሯ የተነደፉ አልባሳት ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው የተለበሱ ፣ ያገለገሉ የገጠር አልባሳት ላይ ትኩረት እናደርግ ነበር።

በዚህ ጊዜ ነበር “ወዜን አልሸጥም” የሚል ፈተና የገጠመን።

ወዝ መሸጥ ምንድነው?

ወዝ ማለት – ላብ ያረፈበት ልብስ ልክ እንደ አንድ የአካል ክፍል የሚቆጠር ማለት ነው – ቆይቶ እንደገባኝ።

እኛ የምንፈልገው የተለበሰ፣ በመጠኑ ያረጀ ወይም ደግሞ ለእድሳት የተለጣጠፉ የአዘቦት የሥራና የክት የገጠር አልባሳትን ነው። በአጭሩ ወዝ የተነከሩ። ብዙ ተለብሰው መነሻ ባህሪያቸውን የቀየሩ። የገጠሩን ነዋሪ ኑሮውን ማንነቱን የሚመስሉት። ከአፈር ጋር ያላቸውን ትግል የሚያሳዩ ማለት ይቻላል። “አንዱ ‘አዋቂ’ ቤት ሄዶ ለባልንጀራው ክፉ ሲመኝ ‘ወዙን አምጣልኝና እሠራልሀለው’ ተብሎ የልብሱን ቁራጭ አዋቂው ጋር ወስዶ አፍዞ አደንዝዞ አስቀረው። እና በምን አምኛችሁ ነው ወዜን የምሸጥላችሁ?” ሲል አንዱ ቆፍጣና ገበሬ አወጋኝ። ጉድ እኮ ነው። አንዱ ምስኪን የለበሰውን ያለ ቅያሪ አውልቆ ግዙኝ ያለበት መንደር ደግሞ፣ በካህን አስወግዘው ሰው ያለ ጨርቅ የሚያስቀሩ ጉዶች መጡ ተብለናል።

በጢስ ዓባይ መንደር ልጆች ዕርዳታ ቅዳሜ ገበያ አሮጌ ልብስ ለብሶ የመጣውን ገበሬ በአዲስ ልብስ እየቀየርነው የተወሰነ ግዢ አደረግን። ትንሽ ቆይቶ ተጨማሪ ገንዘብ መጠየቅና ለአሮጌ ጉርድ ቁምጣ ሙሉ ጋቢ በድርቡ መጠየቅ መጣ። ከጢስ ዓባይ ደግሞ ተሰደድን። እንዲህ እንዲህ እያልን ፈተናውን እየተጋፈጥን እግረ መንገዳችንንም እየተገረምን ፍለጋችንን ቀጠልን።

ከዚህ ቀደም ለፊልም ሥራ ሄጄ የተዋወቁኳቸው ሰዎች ያሉባትና ከባህር ዳር 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው የአለቃ ገብረ ሐና የትውልድ መንደር “ቆራጣ” በመባል የምትታወቀው ቀዬ ትልቅ ተስፋ ይዘን አመራን። የፊልም ሥራን ባህሪ የተረዱ ነዋሪዎች ያሉበት ቦታ በመሆኑ ብዙ ልብሶች ገዛን። “ወዜን አልሸጥም” የሚል ቃል ያልሰማንበት ብቸኛውን መንደር እያደናነቅን፣ በማግሥቱ ስለሚኖሩን በርካታ ግዢዎች ዕቅድ እያወጣን ወደ ባህር ዳር ዘለቅን።

በማግሥቱ ጠዋት የገዛናቸውን ልብሶች ለማሳጠብ ባህር ዳር ላገኘናት አመለ ሸጋ ልብስ አጣቢ፣ አሮጌዎቹ ልብሶች በመታጠብ ብዛት እንዳይበላሹ በመጠኑ ብቻ እንዲፀዱ አስረድተናት ወደ ቆራጣ አመራን። ቆራጣ ስንደርስ የመንደሩ ሰው ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ልብሱንም አዘጋጅቶ ጠበቀን። በደስታ እየመረጥን ዋጋም እየተስማማን ከሰዓት በኋላውን በሙሉ ስንገበያይ ዋልን። ወዙን አምኖ የሰጠንን የመንደሩ ነዋሪ ከፈቃደኝነቱ በላይ ግፊያው መከራ ቢሆንም፣ የምንፈልገውን ያህል ገዝተን በደስታ፣ በጥቋቁር ረጃጅም ላስቲኮች ሰባት ከረጢት ሙሉ “ወዞችን” የራሳችን አደረግን።

ዲዛይነር ህሊና ደሳለኝ አንድ ቀለሙ ለየት ያለ “ጎጃም አዘነ” (ፎጣ) ከርቀት አየች። በጣም ተመኘችው። መኪናችንን አስነስተን ሰውየው ወደሄደበት አቅጣጫ እንደተጠጋን መሣሪያ የያዘ ሰው አስቆመን። ሰውየው የመንደሩ አዲስ ሹም ነው። የተፈጠረው ግርግር በምን ምክንያት እንደሆነ ጠየቀን። አስረዳነው። ሊገባው አልቻለም። ከዚህ ቀደም እዚህ መንደር ፊልም እንደሠራሁ በትህትና ነገርኩት “አይመለከተኝም” አለ። መንገዱን ዘግቶብን ከመኪናው ፊት እንደቆመ ስልኩን አውጥቶ ለወረዳው ኃላፊ እያጋነነ ሪፖርት ማድረግ ጀመረ። ከውስጥ የሚያወራው ሰው ድምፅ አይሰማኝም። ሰውየው ግን “እሺ ጌታዬ”፣ “እሺ ጌታዬ” ይላል። ስልኩን እንደዘጋው ይቅርታ ጠይቆን መንገዱን ለቀቀልን። እኔ ስደሰት ህሊና ግን ተናዳለች። “ጎጃም አዘነ” የለበሰው ገበሬ ተሰውሯል።

ወደ ቆራጣ መንደር የሚያሳጥፈው ብቸኛውን የፒስታ መንገድ እየተውን አስፋልቱን ለማግኘት ወደ ሐሙሲት አቅጣጫ ልንወጣ አስፋልቱ ዳር ስንደርስ ሰባት ታጣቂ ፖሊሶችና ሁለት ሚሊሻዎች መሣሪያቸውን እንደታጠቁ መንገዱን ዘግተው አስቆሙን። ልብሱም እኛም በቁጥጥር ሥር ዋልን። ሁሉም መኪናው ላይ ተጣበው ተጭነው ወደ ሐሙሲት ከተማ አመራን። የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ በሌሎች ታጅበው ጠበቁን። አስረዱ ተባልን ትንታኔ ሰጠሁ። ምክትል አስተዳዳሪው “የአካባቢው ሕዝብ አስተዳደርና የፀጥታ አካላት እንዲህ ዓይነቱን የወረዳችንን ‘ኢሜጅ’ የሚያጠፋ ድርጊት በቀላሉ አንመለከተውም?” በማለት ፖለቲካዊ አንድምታ ሰጡት። ቀጠል አድርገውም፣ “መጪው ዓመት የምርጫ በመሆኑ ‘ሕዝቡ ኑሮው አልተቀየረም’ የሚል መልዕክት የማስተላለፍ አዝማሚያ ያለው ድርጊት በመሆኑ፣ ጉዳዩን ላይ ድረስ የምናጣራው ይሆናል። ልብሶቹን በሙሉ አስረክቡ፤” አሉ።

“ወዜን አላስረክብም” ዓይነት ወኔ መጣብኝ። በስንትና ስንት ልፋት የተገኙ ልብሶች ዕጣ ፈንታ መቃጠል እንደሆነ አንዱ አጃቢያቸው “ከነተባዩ እሳት መልቀቅ ነው” በማለት ሲናገር ሰምቼ ተረዳሁ። “ከነልብሱ እዚህ እቆያለሁ እንጂ ብቻውን አልሰጣችሁም፤” አልኳቸው። ምክትል አስተዳዳሪው ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥተው ሄዱ፡፡ ‘‘ቀበቶህን ፍታ’’ ተባልኩ። ሲመሻሽ ከሰባቱ ላስቲክ ልብሶች ጋር ወደ ወህኒ ወረድኩ። በሕይወቴ የመጀመሪያዬ የሆነውን የእስር ጊዜ ከ11 ታሳሪዎች ጋር ለማሳለፍ ወደ እስር ቤቱ ስገባ በእጅጉ ተገረምኩ። አሥራ አንዱም እስረኞች ያለፍራሽ ወለሉ ላይ የተነጠፈው ላስቲክ ላይ ተኝተዋል። ሰባቱን ላስቲኮቼን ተባይ እንዳያስወጡ ግጥም አድርጌ አስሬ ደርድሬ ምቹ ፍራሽ አደረግኳቸው።

የላስቲኩን ድምፅ የሰሙት እስረኞች በየተራ እየነቁ ከኔ ጋር ማውራት ጀመሩ። የታሰርኩበትን ምክንያት ስነግራቸው መሳቅ ጀመሩ። አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች የገጠር ሰዎች ስለነበሩ “የኔን ወዝ የማትገዛኝ” እያሉ አሳሳቁኝ። አንዳንዶቹም ልሽጥልህ እያሉ ሲያስጎመጁኝ አደሩ። በሕይወቴ የማውቀው ረጅሙ ሌሊት በእስረኞቹ አጫዋችነት በመጠኑም ቢሆን አጥሮልኛል። ሊነጋ ሲል ሸለብ አደረገኝ። ጠዋት በሩ ተከፍቶ የሚጣፍጥ አምባሻ በሻይ መጣልን። እስር ቤቱ በራፍ ላይ ካለው ፍርግርግ አጥር ውስጥ ፀሐይ ለመሞቅ ስንወጣ ስልክ ተፈቅዶልኝ መደወል ጀመርኩ።

ስለጉዳዩ የተገነዘቡ የባህልና ቱሪዝም ኃላፊ ተባብረውኝ፣ ስለሥራችን አስረድተውና ደብዳቤ ጽፈው እኔም ልብሶቹም ከእስር ነፃ ወጣን። የወረዳው አስተዳደር ወዙ ደርቆ “ወዜን” አሳልፌ አልሰጥም ቢልም በስንት ውጣ ውረድ ከቃጠሎ የተረፉ ልብሶችን አስለቅቀን ወደ መንደሩ ላለመመለስ ወስነን ወጣን። አዲስ አበባ ለመመለስ ጉዞ ጀምረን ጥቂት እንደተጓዝን የህሊና ዓይኖች ብርሃን ለበሱ። ቆራጣ የወደደችውና ያመለጣትን “ጎጃም አዘነ” ተመሳሳይ ልብስ አንድ የቆሎ ተማሪ ለብሶ አየች። መኪናውን አስቁመን መንደር ውስጥ ተሯሩጠን ደረስንበት። የእግዜር ሰላምታ ተለዋውጠን የሮጥንበትን ምክንያት አስረዳነው። የቆሎ ተማሪው በጥያቄ ሲያጣድፈን ቆይቶ “ወዜን አልሸጥም” ብሎን እብስ አለ።

ወዝ ያለው!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *