Tidarfelagi.com

ኢህአፓ፣ መኢሶን እና የሃይሌ ፊዳ የፖለቲካ ህይወት

የመኢሶን መስራች የነበረው ሀይሌ ፊዳ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ታሪክ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ፋኖዎች አንዱ ነው። ይህ ሰው በ20ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ሰፊ አሻራ ጥለው ካለፉት ግለሰቦችም አንዱ ነው። አንዳንዶች የግለሰቡን ሚናና ስራውን እያዳነቁ ጽፈውታል። እንደ ሰማእትም ያዩታል። አንዳንዶች ግን ስሙን በክፉ ነው የሚያነሱት። ለአንድ ትውልድ እልቂት ምክንያት ከሆኑት ግለሰቦች አንዱ እንደነበርም ይናገራሉ። ነገር ግን የሀይሌ ፖለቲካን የመዘወር ችሎታና ርዕዮተ ዓለማዊ ብስለት በየትኛውም ወገን ጥያቄ ውስጥ ገብቶ አያውቅም። የርሱ የዕድሜ ልክ ጠላቶች የሆኑት ኢህአፓዎችም ሆኑ የኋላ ኋላ የርሱ ተቃዋሚ የነበሩት የደርግ አባላት እየጠሉት እንኳ ጠንካራ ጎኑን ሲጽፉለት ተስተውሏል።

ሀይሌ በኖረበት ዘመን ታላላቅ ኩነቶች ተከስተዋል። ከነዚያ ክስተቶች መካከል አንዳንዶቹ በአዎንታዊነታቸው ተመዝግበዋል። “እንደ ቀይ ሽብር” እና “ነጭ ሽብር” ያሉ አሳዛኝና አሳፋሪ ክስተቶችም ተፈጥረዋል። የሀይሌ ስምም ከነዚያ ክስተቶች ጋር የሚነሳበት አጋጣሚ ሞልቷል። በተቃራኒው ደግሞ የሀይሌን ስም ከጥፋተኝነት የመከላከል ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል።
በሀይሌ ፊዳ ማንነት ዙሪያ ጽሑፍ መጻፉ ለአሁኑ ጊዜያችን ብዙም ፋይዳ ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን የያኔውን ታሪክ ማወቅ ለሚፈልጉት ወገኖቻችን ያወቁትን ማሳወቅ የዜግነት ግደታን የመወጣት ያህል ነው። ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ ሀይሌ ፊዳ ከጥር 1966 እስከ ነሐሴ 1969 ድረስ የነበረው ፖለቲካዊ አስተዋጽኦና በርሱ የተመራው ድርጅት የሄደበት አቅጣጫ በመጠኑ ይፈተሻል።

ሀይሌ ፊዳ ኩማ የተወለደው በወለጋ ክፍለሀገር ሆሮ ጉድሩ አውራጃ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ የሳይንስ ፋካልቲ ካገኘ በኋላ ለጥቂት ጊዜ በሀረርጌዋ የደደር ከተማ በመምህርነት ሰራ። ከዚያም በውጪ ሀገር ነጻ ስኮላርሺፕ በማግኘቱ ወደ ጀርመኗ የሀምቡርግ ከተማ ተጓዘ። ሁለተኛ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ በጂኦፊዚክስ ሳይንስ ከሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ከያዘ በኋላ እዚያው ማስተማር ጀመረ። ሀይሌ በውጪ ሳለ ከአንዲት ፈረንሳዊት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዶላታል።

ሀይሌ በማስተማር ሙያው ላይ እያለ በወቅቱ እየተቀጣጠለ በመሄድ ላይ በነበረው የተማሪዎች ትግል ተሳበ። እርሱና ጓደኞቹ በአውሮፓ በነበረው “የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር በአውሮፓ” በኩል በትግሉ ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት ጀመሩ። ነገር ግን በዚህ ቡድንና በዓለም ዙሪያ ተበታትነው በነበሩት ሌሎች የተማሪ ንቅናቄ ቡድኖች መካከል ልዩነቶች ተፈጠሩ። በተለይ አውሮፕላን ጠልፈው በአልጄሪያ ጥገኝነት በተሰጣቸው ዝነኛ የተማሪ ንቅናቄ መሪዎች (ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ እያሱ አለማየሁ ወዘተ..) እና በነሀይሌ ቡድን መካከል የተካረረ ክርክር ተከፈተ። በሰሜን አሜሪካ የነበረውና በርካታ ተማሪዎችን ያቀፈው አንጋፋ ማህበር ከአልጀሪያው ቡድን ጋር ወገነ። እነ ሀይሌም የአውሮፓውን ማህበር አመራር በመቆጣጠር ዓላማቸውን በተማሪው ውስጥ ለማስረጽ ተጣጣሩ። በዚህም የበላይነትን አሳዩ። ከጥቂት ዓመታት በኋላም የአልጄሪያና የሰሜን አሜሪካው ቡድን በህብረት “ኢህአድ” (የኢትዮጵያ ህዝብ አርነት ድርጅት) የተሰኘ ድርጅት በህቡዕ መሰረቱ (በኋላ ላይ ድርጅቱ “ኢህአፓ” ማለትም “የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ” በማለት ስሙን ቀይሯል)። የነሀይሌ ቡድንም መኢሶን (የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ) የተባለ ድርጅት አቋቋመ። በነዚህ ሁለት ተቃራኒ ቡድኖች መካከል ሊደረግ የተሞከረው እርቅና ውህደት ከሸፈ። ድርጅቶቹ እና ሰዎቹም በተቃራኒ የታሪክ አቅጣጫዎች ሄዱ።

የሀይሌ ፊዳ የህይወት መስመር ከመኢሶን ህልውናና የትግል መስመር ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው። እርሱና ድርጅቱ የሄዱበትን ጉዞ ከማየታችን በፊት ከኢህአፓ ጋር የነበራቸውን ልዩነት በትንሹም ቢሆን መፈተሹ አግባብ ይኖረዋል።

በኢህአፓና በመኢሶን መካከል የነበረው ልዩነት እንዴት ተፈጠረ? ይህንን ጥያቄ መመለስ አስቸጋሪ ሆኗል። አንዳንድ ጸሐፍት ለልዩነቱ መፈጠር የሻዕቢያና የጀብሃ እጅ እንደነበረበት ይናገራሉ። ለምሳሌ እነዚህ ጸሐፍት የ“ኢህአፓ” ቡድን የኤርትራን መገንጠል መፍቀዱንና መኢሶን በዚህ ላይ ባለመስማማቱ ልዩነት እንደተፈጠረ ያወሳሉ። አንዳንዶች ደግሞ ነገሩን ከስልጣን ጥመኛነት ጋር ያያይዙታል። ለዚህም የኢትዮጵያ ተማሪዎች ዓለም አቀፍ ማህበርን ለመመስረት በተደረገው ጉባኤ ሁለቱ ቡድኖች የማህበሩን አመራር በድርጅታዊ ስልት ለመቆጣጠር ሲወጥኗቸውና ሲከውኗቸው የነበሩትን ሴራዎች እንደ አብነት ይጠቅሳሉ። በጣም ጥቂት ጸሐፍት ደግሞ ነገሩን ከዘመኑ ሁለት አለም አቀፍ ሶሻሊስት ሀይሎች ጋር ያያይዙታል። ለምሳሌ ኢህአፓ በወቅቱ የሶቭየት ህብረት ደጋፊ ሲሆን መኢሶን ደግሞ የቻይና አብዮት ምሳሌ ተከታይ ነበር።

አራተኛው ጎራ ደግሞ ቡድኖቹ በትግሉ ስልት ላይ ከነበራቸው ሰፊ ልዩነት ሳቢያ የጉዞ መስመራቸውም ሊለያይ እንደቻለ ይገልጻል። ለምሳሌ የኢህአፓ ቡድን “ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረግ የትጥቅ ትግል ጭምር የሀይለስላሴን መንግሥት መገልበጥ አለብን” ሲል መኢሶን ግን “እንዲህ ዓይነት ትግል ባልነቃ ህዝብ ውስጥ ማካሄድ ውጤቱ ታጥቦ ጭቃ ነው፣ ያልነቃ ህዝብ የአድሀሪያን መሳሪያ መሆኑ አይቀሬ ነው፤ ስለዚህ ከትጥቅ በፊት ህዝቡን ማንቃት ይበጃል” ማለቱን ያወሳሉ። ከነዚህ ሁሉ መላምቶች ውስጥ ትክለኛውን ነቅሶ ማውጣት በኔ አቅም የማይታሰብ ቢሆንም የስልት ልዩነትን እንደ ምክንያት ያቀረቡ ተመልካቾች ለእውነታው ይበልጥ የቀረቡ ይመስለኛል።

የ1966 አብዮት ለሁለቱም ወገኖች ድንገተኛ ደራሽ ውሃ ነበር። ማንም ባልጠበቀበት ወቅት ነበር ከተፍ ያለው። አብዮቱ የገዥውን መደብ እንዳስደነገጠው ሁሉ የዘመኑን ታጋዮችም በጣም ነበር ግራ ያጋባው። ሆኖም “ኢህአፓ” ለአብዮቱ ድጋፍ በመስጠት ቀዳሚ ሆኖ ተገኘ። በሀገር ውስጥም በመግባት ህቡዕ ህዋሶችንና የጥናት ቡድኖችን አቋቁሞ ስለነበርም በአባላቱ አማካኝነት ከህዝቡ ጋር በሰፊው መገናኘት ችሎ ነበር።

“መኢሶን” ግን አብዮቱን እንደ ትክክለኛ አብዮት መቀበል ተስኖት እንደነበረ በርካታ ምንጮች ያወሳሉ። መኢሶን “አብዮቱ ትክክለኛ አብዮት ነው የሚባለው በሰራተኛው መደብ አመራር ሰጪነት ሲካሄድ ብቻ ነው” የሚል ትንታኔ እንደሰጠም ምንጮቹ ያወሳሉ። (መኢሶን “የሰፊው ህዝብ ድምጽ” በሚባለው ህቡዕ ልሳኑ አማካኝነት አብዮቱን እንደ ተራ ሁከት የቆጠረበት ርዕሰ አንቀጽ ጽፎ እንደነበርም ይነገራል)። እንዲያም ሆኖ ግን በውጪ ሀገራት ብቻ ተወስኖ የነበረው መኢሶን ነገሩን በቅርበት ለማጤን በሚል ከሚያዚያ 1966 ጀምሮ አባሎቹን አንድ በአንድ ወደ ሀገር ቤት መመለስ ጀመረ።

በሰኔ ወር 1966 የጦር ሀይሎች አስተባባሪ ኮሚቴ (በኋላ ላይ “ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ” በሚል ስሙን የቀየረ) ሲመሰረት ደግሞ ሁለቱ ቡድኖች መደናገር ጀመሩ። አብዮቱ ከፍጹም ንጉሣዊ አገዛዝ ወደ ወታደራዊ ስርዓት የሚያመራ መሰላቸው። በመሆኑም “ዲሞክራሲያ” የተሰኘው የኢህአፓ ልሳን እና የመኢሶኑ “የሰፊው ህዝብ ድምጽ” አዝማሚያው አስፈሪ ነው በማለት ህዝቡን አስጠነቀቁ። አጼ ኃይለ ሥላሴ ከስልጣን የወረዱበትን የመስከረም 2/1967 የኢትዮጵያ ትቅደም አዋጅ ተከትሎም ቡድኖቹ ስልጣን የያዘውን ወታደራዊው ቡድን አወገዙ። ኢህአፓ “ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት ይቋቋም” የሚለውን ተዋቂ መፈክሩን አጠናክሮ ገፋበት። መኢሶን ይህንን አቋም ባይወስድም ህዝቡ አዲሱን ወታደራዊ መንግሥት እንዳይቀበል በልሳኖቹ በሰፋት ጻፈ።

በታህሳስ ወር 1967 ከታወጀው የዕድገት በህብረት የምርትና የዕድገት ዘመቻ በኋላ ግን ነገሮች በከፍተኛ ፍጥነት መልካቸውን ቀየሩ። “ኢህአፓ” በጀመረው “ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት” አቋሙ ቀጠለበት። የመኢሶን አመራር ግን ከደርግ ጋር መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ማጤን ጀመረ። በኋላ ላይም “ለደርግ ሂሳዊ ድጋፍ እየሰጡ አብሮ መስራት ይቻላል” አለ። የኢህአፓን የጊዜያዊ ህዝባዊ መፈክር በመቃወምም “ህዝባዊ መንግሥት ከመመስረቱ በፊት ህዝቡ መንቃት፣ መደራጀትና መታጠቅ አለበት” የሚል አቋም ያዘ። በመሆኑም በሀይሌ ፊዳ የሚመራው የመኢሶን አመራር በጥር ወር 1967 ማብቂያ ላይ ወደ ሀገር ቤት ተመለሰ። መኢሶንም ህቡህ ፓርቲ መሆኑ ቀረ። ከደርግ ጋርም በግልጽ መስራት ጀመረ።

One Comment

  • የማነ ገ/ማርያም commented on July 18, 2017 Reply

    ሠዓሊ በምሰል ይገልጠዋል አቀንቃኝ በድምጡ … ደረሰ የሚለው ቃል አመልካች ሲሆን; በወረቀትና ብዕር ሲገለጥ…(ገለጣህ ፍቅረኛን ያሸፍታል)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *