Tidarfelagi.com

ከተረቶች ጀርባ “አበው”

ልጅ እያለሁ ጅብ እና ሌባ አንድ ይመሱሉኝ ነበር። “ጅቡን እንዳልጠራው!”፣ “ሌባው ይሰርቅሃል!”… እየተባልኩ ነው ያደኩት። ጅብንም ሆነ ሌባን አይቻቸው አላውቅም ነበር። እንድፈራቸው ሲባል ብቻ የተሰገሰጉብኝ እሳቤዎች ግን አንድ አይነት አስፈሪ ምስል ፈጥረውብኝ ስለነበር ሌባም ሆነ ጅብ አንድ ነበሩ። አድጌ ነገሮችን ሳገናዝብ የተገለፀልኝ ቀዳሚ እውነት፣ ጅብ ሌባ አለመሆኑ ብቻ ነው። (ምናልባት ሌባ ጅብ ሊሆን ይችላል።)

ጅብ ለሌባ እና ሙሰኛ መገለጫ መሆኑ ይደንቀኛል። ይህ ምስኪን እንስሳ ምን አድርግ ነው የሚሉት?! አያ ጅቦ እውነት የሚባለውን ሰምቶት ይሆን?! ጅብን ከተላመዱት እኮ የገቢ ምንጭ ሊሆን ይችላል። (ሐረር ውስጥ እንዳለው የጅብ አልማጅ።) ጅብ ሆዳም አይደለም። የጣመህን መብላትም “ጅብ” አያሰኝህም። የመያሳዝነው ከእንስሳዎች ሁሉ ተነጥሎ የጣመውን ስለበላ እንዲህ መብጠልጠሉ መሠረት አልባ ጥላቻ ማትረፉ ነው።

ጅብ ከተነሳ አህያም አንድ ምስኪን ስመ ጥፉ ነው።መቼስ፣ “በአህያ ቆዳ የተሠራ ቤት ይፈርሳል ጅብ የጮኸ እለት” ሲባል ሰምታችሁ ይሆናል። አህያ በጅብ መበላቷን መሠረት ያደረገ የአበዎች ብሂል እንደሆነ አታጡትም። አህያ በመሠረቱ ሰርዶ በል ናት። ጅብም ሥጋ በል። እንዲህ ከሆነ ሥረ-መሠረቱ “በመብል” ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አንዳች መግባባት ይፈጥራል። ሰው ሰርዶ በል አይደለም። ሰርዶም ሰው በል አይደለም። ታዲያ ስለምንስ እንዲህ ማለት ከበዳቸው?! “በሰርዶ የተሰራ ቤት ፣ ይፈርሳል አህያ የጮኸ እለት” … ሰርዶ ሕይወት እንደሌለው የማያስብ ስጋ በል የፈተለው አባባል በእንስሳት ይላከካል። እናም አህያ ሆኜ እጮኻለሁ። ጅብ የሚበላኝ ሰርዶ መስዬው ነው!!!

እነሆ እንደዛሬው ተረቶች በካርቱን ፊልም ሳይተኩ ቀድሞ ተወለድኩ። የቢልጮ ታረክ ሲነገረኝ በፍርሃት እየተንቀጠቀጥኩም ስሰማ አደኩ። እንደ ቢልጮም ብልጥ ለመሆን ስመኝ እድሜዬ ገፋ። ዜማዬም ከተረቱ የተቀዳ የቢልጮ ክፋት ማሳረገያ እስኪሆንም ድረስ ሰለጠንኩበት። “እኔ ቢሊጮ፣ ተንበላልጬ፤ የልጇን ሥጋ፣ አበላሁ ልጬ…”

ብልጦች ያለምክንያት አልበዙም! አድጎም የማያመዛዝን አዕምሮ ልጅ ሆኖ በሰማው ተረት ይመራል እንዲል “ሼክስፒር” (..ያው እርሱ አይልም አይባልም ብዬ ነው) ጅብ ከመሆን ብልጢቷ ጦጣን ሊኖራት ሲሞክር “አያ ጅቦ!” ተብሎ በሸገር የሚነገርበት ይሆንና ያርፈዋል። የብልጠት ብልጥነት ዝቅጠት መውረድ፣ የመውጣት ደረጃ እንዳልሆነም ሲገባኝ “ቢልጮን” ለዘመናት ከኖረበት አናቴ ዳግም እንዳይበቅል አድርጌ ላጨሁት። መነጠርኩት። አሁን ቢልጮ እኔ ዘንድ ያለው የክፋት መምህር ተመስሎ ብቻ ነው። ተረቱም ተራ። አያሌ ቢሊጮዎች ግን በዙረያዬ አሉ። የልጅ ሥጋን ለእናት በማብላት ብልጥነት የሰለጠኑ።

በቢልጮ ተረት እየተንጰረጰርክ ካደክ እነዚህ የሕይወት ገፅታዎች በአንተ ላይ ቢንፀባረቁ አትደረም፡-

1- በመጀመሪያ በቢልጮ ታምናለህ
2- የቢልጮ ታሪክ እውነት መሆኑን ታውቃለህ
3- ቢልጮ አንተ ትሆናለህ
4- ቢልጮ ባትሆንም እንኳን እርሱን ትመስላለህ

አንዳንዴ አበው የሚናገሩትን አያውቁም። ያው ተረትም ከአበው ወይም ከእመው (በጥቂቱ) አናት ላይ አይወርድም። በርግጥ እነዚህ አባባል እና ተረቶች ከብዙ ሳንሱር በኋላ በእኛ እድሜ የደረሱት ጥቂት እውነት ከብዙ ጥቅስ በልጦም ሊሆን ይችላል። “ለአህያ ማር አይጥማትም” ሲሉ ስሰማ ግን እቆጫበራለሁ። ኧረ ማነው ከአበው መካከል የሰርዶን ጣዕም ቀምሶ እንደ አሕያዋ አጣጥሞ የሚሰለቅጥ?! እኔ ለአሁን አህያ ብሆን እንዲህ የምል ይመስለኛል። “የሚጥመኝን የማውቀው እኔ! ሰርዶ በልቶ ለማያውቅ ሰው ማር ባጥመው ጉዳዬ ነው?!”

የሚጥምህን ካወቅክ ይበቃል። ባልጣመህ ላይ ማውራት ግን ጣፍጧቸው ያጣጣሙትን ሌሎች ስሜት አለመረዳት ነው።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *