በአንዲት “ሊቃውንት” በሚበዙባት ደብር ውስጥ የኒህ የሁለቱ ሊቃውንት ፀብ ለያዥ ለገናዥ አስቸጋሪ ሆነ። በቃላት ምልልስ የጀመረው የመሪጌታ ቀፀላ ኤፍሬም እና የቀኝጌታ በፍርዱ ሄኖክ ፀብ፤ እጅጉን ብሶበት በምዕመናኑ ፊት ከዓውደ ምህረቱ ስር ለድብድብ ተጋበዙ።
በቅርብ የተገኙት፤ ከቅዳሴ የወጡት ቆራቢ ምዕመናን ገላግለው፤ የቤተልሄም መግቢያ ላይ ለተሰበሰቡት ሠሙነኛ ቀዳሾች አስረከበው፤ ወደየቤታቸው ሄዱ።
ንዴትም ትግልም ያልበረደላቸው ሁለቱ “ሊቃውንት” ገላጋይ ካህናቱ እጅ ላይ ሲደርሱ ጭራሽ ባሰባቸው። ገላጋዮቹ እነ ቀሲስ መርከቡ፤ መገላገሉ ከአቅማቸው በላይ ሲሆንባቸው፤ ግራ እና ቀኝ በሀይል ጎትተው በመለያየት የደብሩ አስተዳዳሪ አባ ምናሴ ዘንድ፤ ከንባብ ቤታቸው ይዘዋቸው ሄዱ።
አባ ምናሴ እጅጉን መንፈሳዊ አባት ናቸው። ፀብ ግን አይወዱም። በሌላ የማያደርጉትን ክፉ ውሳኔ በፀበኛው ላይ ለመፍረድ አይግደረደሩም።
እድሜያቸውን ሙሉ በንባብ ያደከሙት ዓይናቸው መነጽር ከተቆጣጠረው ሰንበት አለ። ዛሬም፤ እህል እንኳን ባፋቸው ሳይዞር ከቅዳሴ እንደወጡ ንባባቸውን ተያይዘውታል።
በድንገት የንባብ ቤታቸው በር ተከፍቶ፤ ፀበኞቹን የያዙት ካህናት ግልብጥ ብለው ገቡ። “…እግዚአብሄርን ፍሩ እናንተ ሰዋች…” አሉ ቀሲስ መርከቡ፤ ነገሩ ፀብ እና ግልግል መሆኑን ለአባ ለማሳወቅ።
አባ ምናሴ ንባባቸውን ገድፈው የሁሉንም ሁኔታ ሲያጤኑ፤ ለድብድብ ሲጋበዙ የነበሩት መሪጌታ… እና ቀኝጌታ… እንደተደበደበ ሰው ምስኪን መስለው ቆሙ።
“ምንድነው ጉዳዩ ቀሲስ?” አሉ አባ። “ታውደ ምረቱ ቲደባደቡ፤ ምዕመናን ገላግለው ተቤተልሄሙ ደጃፍ ድረስ አመጡልን። እህ… ወዲ ብንል ወዲያ፤ ይባሱኑ ነፍስ ሊጠፋፉብን ሆነ። እንግዲህ ‘ሚፈሩት አሶን ነው። ይዳኙ ብለን ተዚ በግድ አጋዝናቸው”
አባ ምናሴ ተናደዱ። መሪጌታ ቀጸላ ቸኮል ብሎ ክሱን ማቅረብ ጀመረ። “ሁል ግዜ ባጠገቡ ሳልፍ፣ ባጠገቡ ላለው ሰው በጆሮው አንድ ነገር ሹክ እያለ…” ቀኝጌታ በፍርዱ ጣልቃ ገብቶ የራሱን ክስ ይተነትን ገባ። “…አባታችን መቼም ስለኔ ባህሪ እሶም ቢሆኑ የሚመሰክሩ ነዎት። እሱ ግን የማይለኝ የለም ተየካህኑ ፊት…” አባ ምናሴ ክስ የመስማት ትዕግስት የላቸውም። ቶሎ አሰናብተው ወደ ንባባቸው ለመመለሰ ቸኮሉ።
እንደ ማጨብጨብ ብለው ንትርኩን አስቆሙ። “ሁለታችሁንም የአንድ ወር ቀለባችሁን ለቅጣት ቆርጫለው” ሁለቱም አጉተመተሙ። “ነገር ግን፤ ያንዳችሁ ስተት ካንዳችሁ ሊበልጥ ስለሚችል፤ የበለጠ ጥፋተኛ የሆነውን ለይቼ የሁለተኛውን ወር ቀለብ እንዲታጎልበት አደርጋለሁ… እናንተን መቼስ እዚህ ቀጥቶ ማስተማር እንጂ ማን ይረግማል?” ሁለቱም በመጠኑ መስማማት ይታይባቸዋል።
“አባታችን! ተምን አርገው ነው እሳ እጥፋተኛውን አሁን ባሁን ሚገልጡት?” ቀሲስ መርከቡ ንዝንዙ ይዘልቅ ከሆነ ደጀ ሰላሙ እንዳይዘጋባቸው በማሰብ ችኮላቸውን በዘዴ ገለጡ።
አባ ምናሴ ደግሞ ከማንም በላይ ለንባባቸው ቸኩለዋል። ምግብ አላማራቸውም። “ማልዳ ነገ፤ እጣነ ሞገሩን አድርሳችሁ፤ ጥፋት ተሰርቶብኛል ያላችሁትን በሙሉ አንድም ሳታስቀሩ በጽሁፍ ይዛችሁልኝ ኑ። ከደጀ ሰላም ስትመለሱ ብዙ ጥፋት ያገኘሁበትን ለይቼ ውሳኔውን አሳውቃለው። በሉ አሁን ሂዱ” ብለው አሰናበቱ። ካህናቱ አጠር ባለው ግልግል ተደስተው እጅ እየነሱም፤ እጃቸውንም እየተሳለሙ ወጡ።
በንጋታው ጠዋት መሪጌታ ቀጸላ እና ቀኝጌታ በፍርዱ፤ መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ጨርሰው፤ የጫሩትን የክስ ደብዳቤ ይዘው ወደ አባ ምናሴ ሄዱ።
ተራቸውን በስርዓት እየጠበቁ፤ የያዙትን ደብዳቤ ለአባ እየሰጡ፤ ጉልበታቸውን፣ የእጃቸውንም መዳፍ እየሳሙ፣ እየተሳለሙ፣ ፈጠን እያሉ ከንባብ ቤታቸው እየወጡ ወደ ደጀ ሰላማቸው ሄዱ።
አባ ምናሴ ሶስት ገጽ የሚሆነውን የመሪጌታ ቀጸላን የክስ ደብዳቤ ቀረብ አርገው ስራቸውን ጀመሩ።
ደብዳቤውንም በጀርባው ገልብጠው፤ የመጨረሻውን ገጽ፤ የመጨረሻ አርፍተ ነገር፤ መጨረሻ ቃል ጀምረው ሽቅብ ማንበብ ጀመሩ።
በእጃቸው በያዙት ብዕር የስዋስው፤ የቃላት እና የሆሄ ግድፈት ያገኙባቸውን ቦታዎች እያሰመሩ ምልክት በማድረግ ማስታወሻ መያዝ ጀመሩ። ከታች የጀመሩትን እርማት እስከ ላይ አድርሰው፤ የገጹን ስራ ሲጨርሱ የስህተቶቹን ብዛት የቅጠሉ ጫፍ ላይ ቆጥረው በጽሁፍ አሰፈሩ።
እንዲህ እንዲህ እያደረጉ፤ የሁለቱንም አርመው ጨረሱ።
ከደጀ ሰላም የተመለሱት ሁለቱም ከሳሾች ከነአጃቢዎቻቸው አባ ምናሴ ንባብ ቤት ተሰብስበው ገቡ። ፍርዱም ብይኑም ጊዜ እንደማይፈጅ የተገነዘቡት ካህናት ንባብ ቤቱን ሞልተው እንደቆሙ የአባን ቃል ይጠባበቃሉ።
“እንደተለመደው፤ ሁለታችሁም ብዙ አጥፊዎች ናችሁ። በመምህርነታችሁ ከናንተ የማይጠበቅ ብዙ ስታችሁ ስታበቁ፤ እናንተ ስትጣሉ አስታራቂ የሆነውን ምዕመን ትመጻደቁበታላቹ። ይኸው ስህተታችሁን ወስዳቹ ተፀፀቱበት” ብለው የክስ ደብዳቤዋቻቸውን ገፋ አደረጉላቸው።
ሁለቱም ወረቀቶቻቸውን ተቀብለው ለመመልከት ቢሞክሩም በጭራሽ ሊገባቸው አልቻለም። “ለማንኛውም ብዙ ስህተት የተገኘው ተመሪጌታ ቀጸላ ዘንድ ስለሆነ፤ የሁለተኛውም ወር ቀለብ የሚታጎለው በርሱ ላይ ነው”
ካህናቱ በሙሉ ወረቀቶቹን ከበው መመልከት ሲጀምሩ ነገሩ ቶሎ የገባቸው ቀሲስ መርከቡ “አባታችን! እህሳ ፍሬ ነገሩን መርምረውት ነውን?” አባ የመጨረሻዎቹን ቃላት መናገር ጀመሩ “ፍሬ ነገሩ፣ ያው ወቀሳ ነው! ትችት ነው! ሲበዛ ደግሞ የራስ ውዳሴ ነው! ምን ሊያደርግልኝ እሱን ላንብብ ቀሲስ? ማንበብም ማረምም የጀመርኩት ገልብጬ ከመጨረሻው ነው። ዎናው በነዚህ ጥቂት ገጾች ስህተቱ የበዛ ጥፋት በብዛት አያጣም ብዬ ነው።…
“ቃሉን ባንፈጽም እንኳን ቃላቱን እስኪ ልክ እንሁን!”
አባ ፍትህ ሰጡ፣ ያለ ተቃውሞ ሁሉም ተበተኑ።
……..
……..
……..
የኔንም ስህተት በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በገፍ ታገኛላችሁ።
Photo by Muluken BirhanuComposed by Girma Berta for more photos follow him @gboxcreative on instagram