Tidarfelagi.com

ስለ ፍቅር ሲባል!

<በዘመኑ በመፈጠሬ እኮራለሁ> ብል ታበይክ እሚለኝ እሱ ማነው?ፍቅር እና ትዕቢት ባንድ መንበር አብረው እንዳይቆሙ እናውቃለንና።

ዳሩ ግን ሰውየው በፊደል ቆጠራ የልጅነት ዘመኔ አቡጊዳ ብሎ በዜማ ሀሁ እንደለከፈኝ አለ።ነፍስ ባላወቀ ቦላሌ ባላንጠለጠለ የልጅነት ዘመናችን ነፍሷ በሰማይ ካለ አብሮ አደጌ ካዲሴ እና ከእህት ሚጡ ከወንድሟ ቢኒያም ጋር ሃሜትን በማያውቅ ጮርቃ ዘመናችን <ለማንልማሽ እኔ አንቺን ፍቅሬ>ን ተኮላትፈን ስንዘፍን አድገናል።ነገረ አቡጊዳና የመልዕክተ ዮሐንስ የቄስ ትምህርት ቤት ውሏችን በያኔው የብራና ልባችን ውስጥ እንዳይፋቅ ሆኖ ተከትቧል።የቄስ መምህራችን ነጭ ፂም፣<የንታዋ እራበነ እራበነ፣ትንሽ አለንጋ ያቅምሱነ ያቅምሱነ> ዝማሬአችን፣በልጅነት የየዋህ ልቡና ብዙ ሆነን እንደ አንድ እነ ራሄል እና ሜላትን ያፈቅርንበት ትዝታችን፣በዜማ አክናፍ ከነ <ልጅነት አላት> <እንደ ቢራቢሮ> እና <ሄዋን እንደዋዛ> ጋር እንደተገመደ ለአፍታም ሳይደበዝዝ ዛሬም ድረስ አለ።በከረመ ትዝታና ፍቅር አናት ላይ ማን ሊሰለጥን ይቻለዋል?
.
ልቤን የረታት የፍቅር እና አድናቆት ሰበዙ ከዛ ዘመን ይጀምራል።በጃህ ያስተሰርያል ከከነፉ የትውልዱ ልጆች አንዱ ነኝ።ለካሴቱ መግዣ ኩርማን ፍራንካ ባልነበረኝ የተማሪነት ዘመኔ ጎረቤት ቤት ወዳለ ቴፕ ጆሮዬን ወርውሬ፣ለአቅመ ፖለቲካ ግንዛቤ ባልደረሰ ልቦናዬ መረብ ምላሽ ባለው አፍቃሪ የዳህላክ ዜማ እተክዝ ነበር።

<ካስተማርሽው ፍቅርን በጊዜ
አይሻለሁ ወይ በሱ ጊዜ!>

ዳህላክ ደሴቱ ስር በማዕበል ለተያዘችው የህፃኑ ነፍስ ስጨነቅ ስጨነቅ!የፍቅር ነገር!
.
የሶስት ትውልድ ታሪክን ባልመረመረ ልጅነቴ በጃህ ያስተሰርያል ፍቅር መወድቄ እውነት ነው።<እስኪ ተዋደዱ ይያያዝ እጃችሁ> ሲል ልቤን ይነዝረኝ ነበር።ለክፋትና ተንኮል እንጂ ለፍቅር ጥሪ መጎልመስ አነበብኩ አወቅኩ ማለት ግድ አልነበረምና።<ለካ ሰው አይድንም በደገመው መፅሃፍ> እንዲል።
.
ከእስራ ምዕቱ በኋላ በእስር ዘመኑ ስቃዩን እያሰብኩ በሃዘን ብዙ ተብሰልስያለሁ ።

ስራው ራቅ አርጎ የሰቀለው የኔና የትውልዴ አብሪ ኮከብ ነው።ስሜቴ ከስኬቱ ጋር ከፍ ሲል ከሃዘኑ ጋር ሲያጎነብስ ኖራል።ጉዞው/ጉዟችን/ ከዚህ አለም ኑባሬ ምክንያት እና ከኑረታችን ደማቅ ምስጢር ከፍቅር ጋር ነው።ከዛን ዘመን ጀምሮ እስከ አሁኗ ቅፅበት ድረስ ይህቺን ፩ እውነት /ፍቅርን/ ያሰተማረኝ ታላቅ ወንድሜ ነው።ወንድሜ ስል ከእውነት ነው።ከእናት ማህፀን ያልተፈለቀቀ ሁላ ወንድም አይባልም እንዳንል አይን አፋሩ ባህል እና ብሂላችን <መወለድ ቋንቋ ነው> እያለ አሳድጎናልና።
.
ጦርና ጋሻ ሳይዙ የሚሊዮኖችን ልብ መግዛት ለጥቂቶች የታደለ ፀጋ ነው። የእሱ ጦር ግን ዜማ ነው።ዜማና ምሳጤ እንደ ሊቁ ያሬድ እግርህ ላይ የተሰካን ጦር እስከርመሳት ያደርስሃል።ጋሻው የአንድነት ጥሪው ነው።ይሄ ጥሪ ከመቶ አመት በፊት በዘመነ አድዋ አልጋው ላይ ከሚስቱ ጋር የተሰየመን አባወራ አስፈንጥሮ ያስነሳ፣ነፃነት ፈካሪ አያሌ አያቶቻችንን በዛው እንደወጡ ያስቀረ ሃይለኛ ጥሪ ነው።ዝናሩ ፍቅር ነው።ስለ ፍቅርማ ምን ሊባል ይችላል?
If there is one thing real,That’s love!
.
ሆኖም አንዳንድ ልቦች እንደ አለት ይደነድናሉ።የዜማ ብትል የፍቅር የእውነት ብትል የሰላም ድምፆች አይሰሟቸውም።ልቡናቸው በጥላቻ ጉልጭማ ተቀርቅሯልና።ግያዝነት ድቅድቅ ነው ወዳጄ!።ምን እንላለን?እያዘንላቸው እናልፋለን እንጂ።በዚ ድፍርስ አለም ፍቅርን የሰበከ ሁሉ የፍቅርን ዳረጎት አይበላም።በነ ሄሮድስ እርኩስ ችሎት ፊት መቆም በሃሰት ቀራኒዮ ጫፍ ላይ መውጣትም አለና።

ደሞ እኮ እኛ ስለነሱ ጥላቻ ከደነቀን በላይ እነሱ ስለኛ ፍቅር ይገርማቸዋል።ሰው በመሆን ያገኘነው ፀጋ ምቾት ይነሳቸዋል።እኛ ግን ለልቡና እውነታችን ፍቅር እንዲቀርብ ጥቁሩ ሰው! /ኔልሰን ማንዴላ/ ምስክራችን ነው።

“For Love comes more naturally to the human heart than its opposite”
.
የሆነው ሁሉ ሆኖ ግን እውነት ላትሸነፍ ፍቅር ላትንሻፈፍ ሁሉም ሊያልፍ ሁሉም ሊጠፋ ነገር…<ያስገምታል ስጋ ሞቶ ለሚቀበር> ብለን ጉዟችንን እንቀጥላለን።
.
እንደ ትውልድ ባጋጣሚ የመከራ ቀንበር ባልተፋታት ምስኪን ሃገር ላይ በስጋ በቅለናል።እጣፋንታ ነው!የመጣነውን መንገድ ዞር ብሎ ላየ የተያያዝነው የእብደት ቁልለልት ድንጋጤ ውስጥ ይጥላል።ከፍቅርና አንድነት ጋር ፍቺ የፈፀመ ትውልድ አካል ነን።የነፍሱን አንደበት ያልዘጋ ግን ያስተውል!የሌላውን ጥቁር ሰው! የማርቲን ሉተርን ቃል ያስታውስ።

“We must learn to live together as brothers or perish together as fools.”
.
ብላቴናው እንቅፋት በበዛበት ዘመናችን መንገራገጭ ባልተለየው የትውልድ ጉዟችን የነፍስያችን ጥሪ አስታዋሽ ነው።የህልውናችን ኢማን የረቀቀው ምስጢር የፍቅር አዝማሪያችን ነው።በከፍታና ዝቅጠታችን ጊዜ ሁሉ ከጎናችን ያልጠፋ ካደባባያችን ያልተለየ <ሰዋችን> ነው።
.
ጉዟችን ጉዞው እንደሆነ ሁሉ የሱም ጉዞ ጉዟችን ነው።ሽቅብም ይሁን ቁልቁል በሄደበት ሁሉ እንሄዳለን።<ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ> ብሎ ባሳደገን ቀዬ እየኖርን የሰውን አደራ አንበላም።ወጀቡ ሲመጣ <ቀላል ይሆናል>ን ልንዘምርለት፣ስኬቱ ሲከሰት <አበባ አየሁሽን> ልንደልቅለት ውለታው አለብን።የፍቅር ጥሪ ሁሉ ይመለከተናልና።
.
የፍቅርን ጦር በልቤ ላይ ከሚቸክሉ ስንኞቹ ባንዱ ተሰናበትኳችሁ።

<<ካድማስ እየራቀ ምነው ይሄ መንገድ ያባክነኛል
በየት በኩል ብሄድ ወደ እረፍት አገሬ ቶሎ ያደርሰኛል
ቀስተ ዳመና ነው የለበስኩት ጥበብ የያዝኩት አርማ
አልጠላም ወድጄ የነፍሴ ላይ ፋኖስ እንዳያይ ጨለማ
አንት አብርሃም የኦሪት ስብሃት
የነ እስማኤል የይስሃቅ አባት
ልክ እንዳክሱም ራስ ቀርፀሃት ራሴን
በፍቅር ጧፍ ለኩሳት ነፍሴን
በል አትዛል ቀና ሁን ልቤ
የ’ልሜን ከንኣን እንዳይ ቀርቤ
ሰው ለመውደድ ካልኩኝ ደከመኝ
ያኔ ገና ውስጤን አመመኝ>>

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *