Tidarfelagi.com

ጠፍታ አገኘችኝ

የደመናው ጽልማሞት በዝናብ ፍርሃትና በቀጠሮ አለማክበር ስጋት መሃል አዕምሮዬን እያላጋብኝ ወደ ታክሲ መያዣው የማደርገውን ግስጋሴ ትቼ ቅርቤ ወዳለ ካፌ ዘለቅሁ… ፒያሳ ነኝ… ከመቀመጤ ሸገር እሪ ብላ አነባች… በጣም ከባድ ዝናብ መውረድ ጀመረ…

“ሸበሌ እንገናኝ” ነበር ያለችኝ… ፍቅረኛዬ ናት… ‘ጥብቅ ጉዳይ’ አለኝ ስትለኝ ቆይታ ስለነበር የዛሬው ቀጠሮ የቀደሙትን እንደማይመስል ጠርጥሬያለሁ… ግንኙነታችን ዓመት ሊደፍን የሚታትር ለጋ ቢሆንም የጅምር ወዘናው ይገረጅፍ ይዟል… በሆነ ባልሆነው መነጫነጭ ጀምራለች… ‘ምን ሆነሻል’ መልስ የላትም…

ቆንጂዬ ናት.. ቆንጆ መረዳት ግን የላትም… አንዳንድ ድርጊቶቿን ቸል የምልበትን ትዕግስት የመውደዴን ጥልቀት ለመጠርጠር ሰበብ ታደርገዋለች… ‘ልታስቀኚኝ አትሞክሪ’ ያልኳት በመፈላለጋችን ማለዳ ነበር… አልሰማችም… ስሜት አልባ ስለሆንኩ አልነበረም እንዲህ ያልኳት… እኔ ብቻ ልወዳት የተፈጠረች እንዳልሆነች አውቃለሁ… ሰውን possess ማድረግ አልወድም… የተደወለላትን ስልክ አናግራ ስታበቃ ከስልኩ ወዲያ ጫፍ ላለው ወንድ ‘እኔም እወድሃለሁ’ ትለውና ዓይኖቼን በዓይኖቿ ትፈትሻለች… የኔ ዓይኖች በተቃራኒው ከወንድሞቿ ከአንዱ ጋር እንዳወራች የሚያምን ርህራሄ ይረጩላታል… ትበሳጫለች… ይባስ ብላ ‘ማን እንደደወለለኝ ታውቃለህ?’… ትለኛለች… እኔ ከስልኩ በፊት የጀመርነውን ወሬ ለማስታወስ በሃሳብ እየተመናተልኩ ሊሆን ይችላል… በፊቴ ‘ካልነገርሽኝ እንዴት አውቃለሁ?’ እላታለሁ… ልማዷን ስለማውቅ ቃል አላባክንም… ‘ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አብሮኝ የተማረ ልጅ ነው… ፌስቡክ ላይ ሲፈልገኝ ቆይቶ ሰሞኑን አገኘኝና ስልክ ተለዋወጥን… በጣም ይወደኛል’… ‘አንቺስ’ አልላትም… ትበሳጫለች… ካፌ ውስጥ ቁጭ ብለን ከፊት ወዳሉ ወንዶች በጉንጮቿ እየጠቆመች ‘ምን ያፈጣሉ’ ትለኛለች… ‘ተወዳጅ ስለሆንሽ ነዋ’ እላታለሁ… ባለመቅናቴ ትታመማለች… ‘ጓደኛዬ በሌሎች ታየች’ ብሎ ቡራ ከረዩ የሚል ወንድ አልወድም… በእርሷ ላይ እምነት የለውም ማለት ነው… ወንዱ ምን አለ አይደለም ቁምነገሩ ሴቷ ምን መለሰች እንጂ…

ከተቀመጥኩበት ካፌ ወደ ውጭ አሻግሬ እያየሁ አስባለሁ… በረዶ የቀላቀለው ወጨፎ ወደውስጥ መዝለቅ ሲጀምር አስተናጋጆቹ በሩን ዘጉት… በረንዳው ላይ አንዲት ስስ ልብስ የለበሰች ልጅ ከዝናቡ ውርጅብኝ ለመሸሸግ ስትሞክር በመስታወቱ አሻግሬ አየሁዋት… ዝናቡ ብስብስ አድርጓታል… የዝናብና ጸሐይ መከለያው ዝቅ ስላልተደረገ ከዝናብ አላመለጠችም… ስቃይዋ እየተጋባብኝ መጣ…

“ምን ልታዘዝ?” አለችኝ አስተናጋጅዋ… ሃሳብ ውስጥ ሆኜ አይደለም በደህናውም ጊዜ ምን ልታዘዝ ሲሉኝ ግራ እጋባለሁ… “እ…” አስተናጋጁዋን ትኩር ብዬ አየሁዋት… “እባክሽ ያቺን ልጅ አስገቢያት” አልኳት ከመስታወቱ ባሻገር እያመለከትኩ… ቀና ብላ አይታት የመጠየፍ ምልክት አሳየች… “አለዚያ በራችሁ ላይ መሞቷ ነው”… የራሷ ጉዳይ ዓይነት ምልክት አሳይታኝ “ምን ልታዘዝህ?” አለችኝ በድጋሚ… “ቀድመሽ እርሷን ታዘዢኝ” አልኳት… አሻፈረኝ አለች… ተነስቼ በሩን ከፈትኩ… ለልጅቱ በምልክት እንድትገባ እየነገርኳት እያለ ሻይ ቡነኞች ‘ብርድ አስገባህብን’ የሚል ጉርምርምታ ጀመሩ… ዝም አልኩ… ልጅቱ ፈራ ተባ እያለች ቀረበችኝ… ከላይ እስከታች ያላቆጣት ዝናብ ሰቀቀን ሆኖባታል… አስገብቻት በሩን ዘጋሁ… የት ትቀመጥ… የካፌው ወንበሮች በዝናብ ለራሰ ሰው ምቹ አይደሉም… አንድ ወጣት ፕላስቲክ ወንበር ላይ ተቀምጦ ስላየሁት ከራሴ ጋ ምቹውን ወንበር ወስጄ ቀየርኩለትና እርሱዋን እዚያ ላይ አስቀመጥኩዋት… ልብስዋን ካልቀየረች በቀር ብርዱ እንደማይተዋት ገባኝ… ትንቀጠቀጣለች… ወደ መታጠቢያው ክፍል ይዣት ገባሁ… ድርጊቴን ከሩቅ የሚያይ ምን ስሜት ሊፈጥርበት እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አይቻልም… ከላይ የለበሰችውን ሸሚዝ ተቀበልኳት… ልጅቱ በግራ መጋባት ውስጥ ሆና ታየኛለች… እንደ ወንድሟ እንድትረዳኝ ሆኛለሁ አልያም ‘በዚህ ሁሉ ሰው መሃል ምንም ሊያደርገኝ አይችልም’ ብላ ተማምናለች ማለት ነው… ሸሚዟን እንድታወልቅ አድርጌ የራሴን ሌዘር ጃኬት ደረብኩላት… ጸጉሯን በትንሹ ለማደራረቅ ሞከረች… ከመታጠቢያው ወጥተን ቦታችን ተቀመጥን… ሸሚዟን ከጀርባዋ አሰጣሁት… የሰው ሁሉ ዓይን እኛ ላይ ነው… እንደዛሬ ዓይን አብረክርኮኝ አያውቅም…

አስተናጋጁዋን ታዘዢን ብዬ ምልክት ሰጠሁዋት… መጣች… “ምን ይምጣልሽ እናት” አልኩዋት ልጅቱን… አንገቷን እንደደፋች ነው… ድምጹዋን ሳታሰማ ምንም አልፈልግም ብላ በእጅዋ ተከላከለች… “ኧረ ማን ይሰማሻል… የሆነ ነገርማ ትወስጃለሽ” ወደ አስተናጋጅዋ ዞሬ “ለሁለታችንም ደረቅ ኬክ ነገር እና ወተት አምጪልን” አልኳት…

ፍቅረኛዬ ጋ ደወልኩ… አታነሳም… ደግሜ ደወልኩ… አታነሳም… እንዲሁ ናት… ፈጥና ኩርፍ ትላለች… “ማሬ በጣም ይቅርታ… ፒያሳ ስደርስ ኃይለኛ ዝናብ መጥቶ ኖሮ አንድ ካፌ ውስጥ ልጠለል ገባሁ… ዝናቡ ሲቆም በቀጥታ ወዳንቺ እመጣለሁ… እባክሽ አትቀየሚኝ” ቴክስት አደረግሁላት… ወዲያው ፃፈችልኝ…

“ብቻህን ነው ወይስ?”… ምን ማለቷ ነው… አጠገቤ ያለችውን እንስት አየሁዋት… ዝናብ ሲቆም የምትለየኝን ሴት

“ምን እያልሽ ነው… የምመጣው ወዳንቺ አይደል እንዴ… ብቻዬን ነው እንጂ”…

“ሃሃሃ”… ብላ ፃፈችልኝ… ማላገጧ ነው…

“ሱሪህን አውልቀህ ስታጠልቅላት ብቻህን እንዳልሆንክ ይገባሃል”… አለችኝ…

ለደቂቃዎች ጭውውውው አለብኝ… ልቤ ከተፈጥሮዋ ውጭ ስትከውን ታዘብኳት… ትንፋሼ ተቆራረጠብኝ… አስተናጋጇ የታዘዘችውን አምጥታ ጠረጴዛ ላይ ስታኖር ነው ብንን ያልኩት… አፌን ደም ደም አለኝ… ለማስመለስ ሁሉ ተናንቆኝ ነበር… ወደ መታጠቢያ ክፍል ሄድኩ… ፊቴን በመስታወት ውስጥ እያየሁ ቆዘምኩ… ስልኳ ላይ ደጋግሜ ደወልኩ… አታነሳም…

ለመረጋጋት እየጣርኩ ወደ መቀመጫዬ ተመለስኩ… ልጅቱ እየጠበቀችኝ ነው… ‘ብይ’ የሚለው ቃል ዘግይቶ ነው የመጣልኝ… ሸረፍ አድርጋ አየችኝ… ከስልክ ጉርጎራዬ በኋላ ጥሩ እንዳልሆንኩ ገብቷታል… ዙሪያዬን በጥንቃቄ ቃኘሁ… ካፌ ውስጥ ብዙ ሰው አለ… ከልጅቱ ጋር እየሆነ ያለውን ማን ነው ያወራብኝ… ቴአትር አዘጋጅቶ ከተመልካች ጋር የሚያይ ክፉ ዳይሬክተር ካፌው ውስጥ ያደፈጠ መሰለኝ… የማውቀው ሰው ዓይኔ ሊገባ አልቻለም… የሆነ ሆኖ ሙሉ ታሪኩን ይሆን የነገሩዋት?… ለእርስዋ ‘ከሴት ጋር’ የሚለው ቃልም በቂዋ ነው… ከፒያሳ ሸበሌ ዝናብ ይዞህ ስትቆም ሩቅ ለወሬ እግር ግን የአፍና ያፍንጫ ያህል ቅርብ ነው…

ታክሲ ውስጥ ነበር የተዋወቅነው… አንድ ወንበር ላይ ነበርን… ሂሳብ ለጠየቃት ረዳት መቶ ብር አውጥታ ስትሰጠው ‘በጠዋት መቶ ብር ስትሰጪ አይደብርሽም?’ ብሎ ያመናጭቃታል… ‘ከሌለኝስ’ ትለዋለች በስጨት ብላ… እንዳጋጣሚ 10 ብር ሰጥቼው መልስ እጠብቅ ኖሮ ‘ግድየለም የኔን መልስ ለእርሱዋ አድርገው’ አልኩት… በረዳቱ ብስጭት ብዙ ተናገረች… ላረጋጋት ሞክሬ ወሬ ጀመርን… ስለ ታክሲ… ስለ አየሩ… የባጥ የቆጡን ስናወራ ቆይተን መውረጃዬ ደርሶ ‘ወራጅ አለ’ ስል እርሷም በአንድ ቃል ይህንኑ እያለች ነበር… ተያይተን ሳቅን… ወርደን ወደ ጉዳይዋ ስታመራ ለሻይ ቡና ባግደረድራትም አልተሳካልኝም… ሴትን በማግባባት በኩል አሪፍ አይደለሁም… ስፈራ ስቸር ‘ሌላ ቀን የታክሲ ቸግሮሽ የድረሱልኝ ጥሪ ብታሰሚ ፈጥኜ እደርሳለሁ’ እያልኩ ቢዝነስ ካርዴን ዘረጋሁላት… እየሳቀች ተቀበለችኝ… ሳቅዋ በጭንቅ እንደሚወጣ የሐምሌ ፀሐይ ነው…

‘በነገራችን ላይ ሃሌታ እባላለሁ’… ጨበጥኳት
‘መቅደስ’ ተሰነባበትን… በሳምንቱ ደወለችልኝ… ደስ አለኝ… እየተገናኘን ማውራት ጀመርን… አለፍን… ተሻገርን… ዛሬ ደግሞ…

ዝናቡ ወደ ካፊያ ተለወጠ… መቅዲ ጋ ደግሜ ደወልኩ… አታነሳም… ቆይታ ዘጋችው… ብስጭት አልኩ… በዚህ መሃል ልጅቱን አየሁዋት… ቶሎ ቶሎ እየበላች ነው… እንደራባት ሳውቅ አሳዘነችኝ…

ከካፌው ስንወጣ የማደርገውን ማሰብ ጀመርኩ… አሁን ሸበሌ መሄድ አዋጭ አይደለም… ጠዋት ቤትዋ መሄድ አለብኝ… የቀረበልኝ ኬክ አልተነካም… ሆዴ በነገር ጠግቧል… ‘ለምን አትበላም’ አለችኝ ልጅቱ በፍርሃት… ‘እ… ግድየለም… አሁን ጥሩ አይደለሁም…’ አስተናጋጅዋን ጠርቼ ሂሳብ ከፈልኩ… ስለመሸ የካፌው ደንበኞች መውጣት ጀምረዋል… ልጅቱ መጨረስዋን ሳረጋግጥ ‘እንሂድ?’ አልኩዋት… ‘እሺ’ ብላኝ ተነሳችና ጃኬቴን አውልቃ ሰጠችኝ… ሸሚዟን ለበሰች… ጠፈፍ ቢልም ገና አልደረቀም… እንደ ጨከንኩባት ተሰማኝ…

ከካፌው ወጣን… “ወደየት ነው የምትሄጂው?” አልኳት ልጅቱን… ለዓመል እንጂ እንደማልሸኛት አውቃለሁ “እ…” ፊቷ ልውጥውጥ አለ… ግራ ተጋብታለች… “ምነው…” አልኳት ደንገጥ ብዬ… “እውነቱን ለመናገር ወዴት እንደምሄድ አላውቅም” አለችኝ… እንባዋ እየወረደ ነበር… “ቆይ ቆይ አታልቅሺ”… በምታለቅስ ሴት ፊት መቆም አልችልም… “ንገሪኝ… ምን ሆነሽ ነው?” … “ከክፍለ ሃገር ነው የመጣሁት… ከነበርኩበት ችግር መሸሼን እንጂ መድረሻዬን አላሰብኩበትም”… “ማልቀስሽን አቁሚና አውሪኝ ፕሊስ… እሺ እኔ ምን ልርዳሽ?” … “አላውቅም… ማደሪያ ወይም መጠጊያ..” … የሆነ ዓይነት ወጥመድ ውስጥ እየገባሁ እንዳለሁ ተሰማኝ… ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ነገሮች ገጥመውኝ በተለያዩ መንገዶች ተወጥቻቸዋለሁ… ሳንቲም በመስጠትና አንዳንዶቹን ሆቴል አልጋ በማስያዝ… ለዚህች ልጅ የሚሻለው መፍትሄ የትኛው ነው… አተኩሬ አየሁዋት… ፊትዋ ላይ ንጽህና ይነበበኛል… ሁለቱም መፍትሔ እርሱዋን ለአውሬ የመስጠት ያህል ከበደኝ… “እኔ ቤት ትሄጃለሽ?”… መልሼ ደነገጥኩ… ጭራሽ ቤት… መቅዲ ይህን ስትሰማ ራሷን ትሰቅላለች… ልጅቱ ፈጥና እሺ አላለችኝም… ፊቷ ግን ‘ምንም ምርጫ የለኝም’ ዓይነት የተስፋ መቁረጥ ቀለም ይታይበታል… “ግድየለም የዛሬን እኔ ዘንድ አርፈሽ ሌላውን ነገ እንነጋገራለን” ድፍረቴ ለራሴም ገርሞኛል…

ታክሲ ውስጥ ገባን… ብስጭት፣ ፍርሃትና ሃዘን እያላጉኝ ነው… ሰፈር ደረስን… ገና አንድ ሰዓት ነው… የኪራይ ቤቴ ባለ አንድ መኝታ ኮንዶሚኒየም ናት… ገባን… የልጅቱ ፊት ላይ ፍርሃት ይነበባል… “አይዞሽ እንደቤትሽ አስቢው” አልኳት… ዙሪያ ገባውን አጤነች… ሶፋ ላይ እንድትቀመጥ ጠቆምኳት…
“ሻወር መውሰድ ትፈልጊያለሽ?” … ድካም አይባታለሁ… ልብሶቿ መጠጥ ከማለታቸው ውጪ እንደበሰበሱ ነው… “እሺ” አለችኝ… ለመታጠቢያ የሚሆኑ ቁሶችና የምትቀይራቸውን ቀለል ያሉ ልብሶች አሰናድቼ “ይኸው 30 ደቂቃ ተሰጥቶሻል፣ እኔ ራት ይዤ መጣሁ” አልኳት… ለመጀመሪያ ጊዜ ፈገግ አለች… በሩን ከውስጥ እንድትዘጋው ነግሬያት ወጣሁ…

ሱፐርማርኬት ለማግኘት አንድ ፌርማታ መመለስ ነበረብኝ… የተወሰኑ ምግቦችን ሸማምቼ ተመለስኩ… ቤት ስደርስ ጨርሳ ነበር… ልብስ ስትቀያይር ተለወጠችብኝ… “አንቺ የቅድሟ ልጅ ነሽ?”… አልኳት… ሳቀች… ያምርባታል… ምግቦቹን የተወሰኑትን ወደ ፍሪጅ ሌሎቹን ጠረጴዛ ላይ አኖርኩ… ከመኝታ ክፍሌ ትርፍ ፍራሽ አውጥቼ የለሊት ልብሶች ሰጠሁዋት… “እንግዲህ ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም፣ ራስሽን አስተናግጂ፣ እኔ በልቼ ነው የመጣሁት” ብያት ወደ መኝታ ክፍሌ ገባሁ…

ስልክ ለመደወል ጓጉቻለሁ… ሰላም ጋ… የመቅዲ ጓደኛ ናት… በመሃከላችን ያለች ብቸኛ ሰው… ከመሸ በመደወሌ ይቅርታ ጠይቄ የተፈጠረውን ነገር በዝርዝር አስረዳሁዋት… ሁሉንም ሰማችኝ… ቀጥተኛ ሰው ስለሆነች ስሜቷን ብቻ ነው የምትከተለው… ጓደኛዬ ናት ብላ ስታደላ ገጥሞኝ አያውቅም… ተረድታኛለች… በጣም ብዙ ነገር አወራን… “መስማት ይኑርብህ አይኑርብህ አላውቅም፣ ግን…” አለች… “ምኑን ሰላም” ልቤ እየነጠረች ነው… “በፌስቡክ ከተዋወቀችው አንድ አውሮፓዊ ጋር ተጋብታ ለመኖር መስማማታቸውንና በዚህ ሳምንት ልትሄድ እንደምትችል ነግራኝ ነበር ትናንት…” ከዚህ በኋላ አልሰማሁዋትም… ጭንቅላቴ እንደ እርጥብ ቆዳ ሲከብደኝ ይሰማኛል… አልጋዬ ላይ ወደቅሁ… ለረጅም ሰዓት ምን እንደተፈጠረ አላውቅም… በመሃል ነቃሁ… ስልኬ ምልክት ያሳያል… ሰላም ደጋግማ ደውላ አላነሳ ስላልኳት መልዕክቶች ልካልኛለች… ማጽናኛዎች ነበሩ… በተለይ አንደኛው መልዕክቷ መቼም የምረሳው አይመስለኝም… “ተቀባብሎ የተቀመጠ ጥይት አለመተኮስ አይችልም… ተዋት”…

ቅዳሜ ጠዋት… ከወደቅሁበት ስነቃ ቤቴ ውስጥ ጉድጉድ የሚል ሰው መኖሩን አወቅሁ… ቁርስ ሰርታለች… ሽታው ቤቴን አውዶታል… ከመኝታ ክፍል እየተጎተትኩ ስወጣ ልብሶቿን አጥባ እየጨረሰች ነበር… ሰላምታ አቀረበችልኝ… ቤቴ ይሄን ወግ አይቶ አያውቅም… ተጣጥቤ ሶፋ ላይ ተዘረፈጥኩ… በተራዬ እንግዳ የሆንኩ መሰለኝ… ቁርስ እየበላን “ሃሌታ እባላለሁ” አልኳት… አተኩሬ ማየት ስጀምር ያየሁዋት ልጅ ውብ ናት የማይበቃት ቆንጆ ሆነችብኝ… ኦው… ቁንጅና ራሱን ነች እንጂ… “ማሕሌት” አለችኝ… ስለራሷ እንድትነግረኝ ገፋፋሁዋት… የራሴን ጉዳይ ለመርሳት ነበር…

እናቷ በልጅነቷ ነበር ያረፉት.. አባቷ ሌላ ሚስት ባለማግባታቸው ለቤቱ ብቸኛ ልጅ ሆና ቆየች… ከጊዜ በኋላ አባት በጠና በመታመማቸው የቤቱ ኃላፊነት እርሷ ላይ ወደቀ… የቤቱ ጥሪት በሕክምና እየተሟጠጠ ሲሄድ የእርሷም ችግር እየገዘፈ መጣ… እያደገች ስትመጣ እርሷን ማግባት አለብን የሚሉ ሰዎች ፈተናዎችን ያደርሱባት ጀመር… አባቷ አረፉ… የለቅሶው ድንኳን ከተነሳ በኋላ ሰዎቹ በግልጽ ጸብ ውስጥ ገብተው ፉክክር በመጀመራቸው የኮሌጅ ትምህርቷን ከመጀመሯ በፊት የምትገባበት ችግር አሳስቧት ጥቂት ቁሶቿንና የትምህርት ማስረጃዎቿን ጓደኛዋ ጋ አኑራ ጠፍታ ወደ አዲስ አበባ መጣች… እዚህ የምታውቀው አንዳች ዘመድ የላትም… ቤተሰቦቿ በአባት የስራ ለውጥ ምክንያት በሄዱባት ከተማ ስለወለዷት ስለዘመዶቿ የምታውቀው በቂ ነገር የለም… እናም ከኔ ጋር ተገናኘች…

የአንዳንድ ታሪክ መቋጫና የሌላኛው መንደርደሪያ መሃል ሌላ መካከለኛ የለም… ማሂ ክረምቱን እኔው ዘንድ ቆየች… መስከረም ሲጠባ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለች… የምችለውን ሁሉ እንደቤተሰብ አገዝኳት… በጥሩ ውጤት የመጀመሪያ ድግሪዋን ያዘች…

አምስት ዓመታት አለፉ…

ያልነገርኳችሁ አንድ ነገር… አንድ ቆንጅዬ ወንድ ልጅ ወልደናል… ዛሬ ደግሞ ልደቷ ነው… ለስጦታ ያዘጋጀውላት ያማረ ፍሬም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ከመስታወቱ ጀርባ አኑሯል…

ኩራዝ ጠፍቶኝ ሳዝን – ፀሐይ አዋለድሽኝ
ባጣሁት ስቸገር – ባለኝ ሰው አ’ረግሽኝ
በሆንኩት ወደድሽኝ – አልታየሽ ጉድለቴ
በመኖርሽ ደምቋል – ኦና ነበር ቤቴ
———————————————

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *