ማደግ በመሰለኝ ረግረግ ውስጥ የጠፋች ልጅነቴን አፋልጉኝ – ማወቅ በመሰለኝ ጥልቅ ውስጥ የተደበቀች ልጅነቴን አፋልጉኝ – ከድቅድቅ ጽልመት ውስጥ የዘነጋሁዋትን እውነት አፋልጉኝ…
~
ዕድሜ የሥጋ ኑረት መስፈሪያ እንጂ የውዷ ሕይወት መግለጫ አይደለም… ሕይወቴ ልጅነቴ ነው… ዕድሜ ደግሞ የልጅነቴን ንጽሕና የነጠቀኝ ቀበኛ…
~
ልጅ እያለሁ ፍርድ አልነበረኝም… ከልክነትና ስህተት ጋር ፈጽሞ አንተዋወቅም ነበር… ከመሆን ጋር በጥልቅ ትስስር ውስጥ ነበርኩ… ልክነትና ስህተት ማደጌ ውስጥ ያጎነቆለ አጥር ነው… ከኑረት ወንዝነት ጋር ከመፍሰሴ አናጥበው በልክና ስህተት ኩሬ ውስጥ ያቆሩኝ ‘ያደጉ ሰዎች’ ናቸው… በልጅነቴ ሙቀት ውስጥ የነበረኝን ስክነት ትልቅ መሆን አለብህ በሚል ኩሸት የነጠቁኝ ትልልቅ ሰዎች ናቸው… ልክነትና ስህተትን በማላውቅበት ዘመን ከሁሉ ጋር እንደ አንድ እኖር ነበር… አድጌ መስመር ሳበጅ ግጭት ውስጥ ገባሁ… ‘ልክ አይደለህም – ልክ ነህ’ ውዝግብ ገነባሁ… መስፈርቴ ግን ከግል ተሞክሮዬ የተጨለፈ አልነበረም… ከሌሎች ግንዛቤ የተቀዳ እንጂ… እናም አድግ ብዬ ከራሴ ተፋታሁ… ልጅነቴን አፋልጉኝ…
~
ልጅ ሳለሁ ሚዛን አልነበረኝም … በጎ መጥፎ ብዬ አላውቅም… የደስታዬ ጅረት የሆነን ከመቀበል እንጂ ሁነቱን ከመመዘን ፈልቆ አያውቅም… ይሄ መጥፎ ያኛው በጎ ነው ያሉኝ ታላላቆቼ ናቸው… በበጎነትና መጥፎነት ሚዛን ትላልቆች ሁሉ እንደማይስማሙ ያወቅሁት አድጌ ነው… ልጅነቴን አፋልጉኝ…
~
ልጅ ሳለሁ ደረጃ አልነበረኝም… ከፍታና ዝቅታ የኑረቴ አካል አልነበሩም… ጌታና ሎሌ፣ አለቃና ምንዝር፣ ዲታና ምስኪን፣ አዋቂና ማይም አላውቅም ነበር… ‘በማደግ እውቀት’ ነው ደረጃዎቼ የተሰሩት… ከልጅነቴ ፍራሽ ላይ ነው የማደጌ ቅራቅንቦዎች የበቀሉት… ልጅነቴን አፋልጉኝ…
ልጅ እያለሁ ስለ ጊዜ አላውቅም ነበር… የትናንት ጸጸትና የነገ ስጋት ውሎ አዳሬን አያውቁትም… ደስታዬ ከቅጽበታት ምንጭ የሚቀዳ ነበር… በእኔ ውስጥ እዚህና አሁን መኖር እንጂ ፔንዱለማዊ መባከን አልነበረም… አስቤ አላውቅም ነበር… ሃሳብ የሚባለውን መርዝ የረጩብኝ ከልጅነቴ ያፋቱኝ ታላቆቼ ናቸው… ፈጽሞ ተጨንቄ አላውቅም ነበር… የሰርክ እንቦቃቅላዊ ሳቄ የከሰመው ታላላቆቼ የጭንቀት አዚም ካደረጉብኝ በኋላ ነው… የማግኘት ተብሰልስሎት ስጋዬን ጨርሶት አያውቅም… የማጣት ስጋት ልቤን ሰቅዞኝ አያውቅም… የኔ የምለው አልነበረም… የእነእከሌ ነገርም ታስቦኝ አያውቅም… ሁሉ የሁሉአዊው ነውና እንዳፈተተኝ ስጠቀመው ኖሬያለሁ… ልጅነቴን አፋልጉኝ…
~
ልጅ ሳለሁ ድንበር አልነበረኝም… ከዚህ ወዲያ – ከዚያ መለስ ብዬ አላውቅም… ቤተሰብ.. ቀዬ.. ሰፈር.. ሃገር.. ወገን.. ብሔር.. ሐይማኖት.. የሚባሉ ክፍልፋዮችን አላውቅም ነበር… ሰው ብቻ ነበርኩ… የስጋ መገለጥ በጎበኘኝ ጊዜ ከዚህ ውጭ አንዳችም ልክና ልኬት አልነበረኝም… ቤተሰቦቼ ‘የእኛ ልጅ ነህ’ ከማለታቸው በፊት የእኔ የምለው ቤተሰብ አላውቅም ነበር… ሰፈሩ ‘የእኛ ሰፈር ልጅ’ እስኪለኝ ድረስ ሰፈርተኝነት ጎብኝቶኝ አያውቅም ነበር… ስም እስኪሰጡኝ ስም አልባ ነበርኩ… የሆነው ሁሉ ከፍቃድና ፍላጎቴ ውጭ ሆነ… ብሔር ሰጡኝ… ሃገር ሰጡኝ… ‘ከዚህ ውጭ ውልፊት ብትል’ ብለው ግድግዳ አበጁልኝ… ከእስከ-አልባው ሕዋ አባልነቴ ሰረዙኝ… አንዱንም ፈልጌው አልሆንኩም… ፈልገው ያልሆኑትን ነው አስገድደው ያሆኑኝ… ልጅነቴን አፋልጉኝ…
~
ልጅነቴ ውስጥ ያልተነካካ ውበት ነበር… ድንግል ውበት… ‘ውበት ማለት ይህ ነው’ እስኪሉኝ ከሁለንታ ውስጥ ውብ ያልሆነ ስለመኖሩ አስቤ አላውቅም ነበር… ዓይኖቼ ያረፉበትም ሆነ ምናቤ የደረሰበት ሁሉ ውብ ነበር…
~
ልጅነቴ ነፃነት ነበረች… ማደግ እስራት ሆኖብኛል… ሃፍረት፣ መሸማቀቅና ይሉኝታን የገመደብኝ እስራት… ከአስተሳሰብ ባርነትና ከአዕምሮ እስርቤት ያልወጡ እነርሱ ግና ‘ከወህኒ ስትገባ ብቻ ነው ነፃነት ሚጎድለው’ ይሉኛል…
~
ልጅነቴ ውስጥ ፍቅር ብቻ ነበር… ከፍልቅልቅ ሳቅ ውስጥ የምሰማውን የደስታ ሙዚቃ ሽርደዳን ቀላቅዬ እንድሰማበት ያሰለጠኑኝ እነርሱ ናቸው… ከሌሎች ርህራሄ ጥግ አዛኝ ልብን ሳይሆን ተንኮል እንድፈልግ ያሰሉኝ እነርሱ ናቸው… ከአብሮ ማዕዴ ጥርጣሬን፣ ከጉርብትናዬ ቂምን፣ ከባልንጀራዬም ሴራን እንዳሻትት የገፋፉኝ እነርሱ ናቸው… አለመግባባቴን በጠብ – ኩርፊያዬንም በግጭት እንድትረጉም ያጸኑኝ እነርሱ ናቸው… የልጅነቴ ቀበኞች!!… ልጅነቴን አፋልጉኝ…
————————————————
ውዴ ሆይ…
__________________________________
በኩርፊያችን ማግስት ጀርባ ለመስጠት ከፈጠነው አዋቂነት ይልቅ በንጹህ ልብ የሚፈላለገውን የልጅነት ድምጽ ሰምተን እንታረቅ!!…