Tidarfelagi.com

ኦነግና ኢህአዴግ በአንድ ቀን ጦርነት (ክፍል አምስት)

(እውነተኛ ታሪክ)

ያ የኦነግ ወታደር አስደንግጦኝ “ወደቤት” ስገባ ትቶኝ የነበረው ፍርሃት እንደገና ተቀሰቀሰብኝ። ልቤም እንደ ቃልቻ ድቤ “ድው ድው.. ድው… ድው….” ማለት ጀመረ። “ምን ዓይነት ቀን ነው?” አልኩ ለራሴ። የአክስቴ ልጆችም እንደኔው ተሸብረዋል። “ወዴት መሄድ ይሻላል?” በማለት መነጋገር ስንጀምር “ሙበጀል” የሚባለው ትልቁ ልጅ “ቆይ ትንሽ ፋታ ይስጡን! ወታደሮቹ ከዚህ ቦታ ሲሄዱልን እኛ ከብቶቹን ይዘን ወደ “ደሞ” እንሄዳለን” አለን (ደሞ ከሰፈሩ በስተደቡብ ዝቅ ብሎ የሚገኝ የእርሻ ስፍራ ነው። እዚህ ያሉት እርሻዎች ከበቆሎ በስተቀር ሌላ እህል አይመረትባቸውም። አትክልትና ፍራፍሬ ግን ዓመቱን በሙሉ ይለቀምበታል። ጫትና ቡናም በገፍ አለ)።

ሁላችንም ሙበጀል በሰነዘረው ሃሳብ መስማማታችንን ገለጽን። ይሁንና ከደቡብ በኩል ቤቱን ያጠሩት የኦነግ ወታደሮች ከአሁን አሁን ወደፊት (ወደ ሰሜን አቅጣጫ) ይንቀሳቀሳሉ ብለን ስንጠብቅ ከርቀት የሚመጣ የተኩስ ድምጽ ተሰማን። እያደር ድምጹ እየጎላ መጣ። “እንደገና ጀመሩ እንዴ” በማለት ጆሮአችን አንቅተን ስንጠብቅ በሩጫ የሚሮጡ ሰዎች የእግር ኮቴ መሰማት ተጀመረ። ቀስ በቀስም ኮቴውም እኛ ዘንድ ደረሰ። ብዙ ወታደሮች “ግርርር” እያሉ እኛ ወዳለንበት ቤት ጀርባ ሲሮጡ ሰማን (እንዲህ አይነቱ ሩጫ በኦሮምኛ “ዲዲቻ” ይባላል)። ከርቀት የሚሰማው የተኩስ ድምጽም እኛ ዘንድ ደረሰ።

ከቤቱ ውስጥ ብንሆንም ኦነጎች ከቤቱ ጀርባ ወረድ ብሎ ካለው የ“ረውዳ” መስክ መድረሳቸው ታውቆናል። ነገር ግን እነርሱ እየሮጡ የተኩሱ ድምጽ ከነርሱ መራቁ አደናገረን። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን ተኳሹ ሃይል ገና ወደኛ እየደረሰ መሆኑን ተረዳን። ይህ ሃይል እንደ በፊተኛው የሚሮጥ ሳይሆን ቀስ ብሎ እያዘገመ ነው ወደ ላይ (ወደ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ) የሚተኩሰው። የነርሱ ተኩስ በቅርበት ሲሰማን ከወዲያኛው ጫፍ የሚተኮሰው ደግሞ ከርቀት ይሰማ ነበር። እነዚያዎቹ ኢህአዴጎች መሆናቸው ነው እንግዲህ!!

የኦነግ ወታደሮች ተኩሳቸውን እያጦዙ ከአክስቴ ቤት ጀርባ በዝግታ አለፉ። የኢህአዴጎቹ ተኩስም እየገዘፈ መጣ። ኢህአዴጎቹ የአክስቴ ከብቶች ከሚያድሩበት ስፍራ ሲደርሱ እንደ በፊቱ ጉዞአቸውን ገትተው ቦታ ቦታቸውን ያዙ። የተኩስ መአት በአካባቢው ላይ ዘነበ። “ክላሽ”… “ኤም-14.”. “ፋል” እና ሌሎች በስም የማላውቃቸው ጠመንዣዎች እንደጉድ ተንፈቀፈቁ። ግርኖቭ መትረየስ “ዶግ…ዶግ…ዶግ…ዶግ…ዶግ…ዶግ…ዶግ….ዶግ….ዶግ…..ዶግ….” እያለ አስገመገመ። አየሩ በባሩድ ሽታ ተበከለ።

በቤቱ የነበርነው ሰዎች መሬቱ ላይ በደረታችን ተለጠፍን። ፍርሃትና ሽብር ነገሠ። “ኒጊስቲ” የምትባለው የአክስቴ ልጅ እምባዋን እያዘራች አለቀሰች። የኔም ነፍስ ልትወጣ ከደረቴ አልፋ ጉሮሮዬ ላይ ደረሰች። አክስቴ ግን እንደበፊቱ “ከብቶቼን” ትል ነበር።
*****
ሁለተኛው ውጊያ ከሃያ ደቂቃ በላይ የቆየ አይመስለኝም (የጀመሪያው አርባ ደቂቃ ያህል ቆይቷል)። የተኩሱ ብዛትና ግዝፈት (intensity) ግን ከበፊተኛው በጣም ይበልጣል። በተለይም ድምጸ-ጎርናናው ግርኖቭ መትረየስ ከሁለቱም በኩል ፋታ ሳይሰጠው ነው የተተኮሰው። ሁለቱም ወገኖች ያለ እረፍት ያንደቀድቁታል።

ከሃያ ደቂቃ በኋላ ተኩሱ ቆመ። ኢህአዴጎቹ በድጋሚ በከፍተኛ ድምጽ እያወሩ ወደ መጡበት አቅጣጫ ተመለሱ። ኦነጎች በበኩላቸው ከላይ እየሮጡ የመጡበትን መንገድ ትተው ከቤቱ በስተምስራቅ አቅጣጫ ያለውን መንገድ (ውጊያው ከመጀመሩ በፊት የኦነግ ወታደሮች በሰልፍ ሲመጡ ያየንበትን መንገድ) በመያዝ በፉከራና በዲዲቻ ወደ ሰፈሩ ውስጥ ገቡ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ “ጣቢያ” ከሚባለው የመንደሩ ገበሬዎች ማህበር ጽ/ቤት አቅጣጫ የተኩስ ድምጽ ተሰማ። ይህ ተኩስ ቀስ በቀስ እየራቀ ወደ “አባ ያያ” ተራራ ደረሰ።

ለአስራ አምስት ደቂቃ ያህል በነበርንበት ሁኔታ ቆየን። ከዚያም አክስቴ ከብቶቼን ማየት አለብኝ ብላ ተነሳች። “እባክሽ እንዳትወጪ” ብለን ብንለምናትም ልናስቆማት አልቻልንም። አክስቴ በዋናው በር ወጥታ በቅድሚያ ከቤቱ ጀርባ ሄደችና ስፍራውን ቃኘች። በአካባቢው ዝር የሚል ወታደር እንደሌለ ካረጋገጠች በኋላ ወደኛ ተመልሳ “አሁን ሄደዋል መሰለኝ” አለችን። እኛም ተነስተን ወደ ውጪ ወጣንና ከግድግዳው ስር ቆምን።

አክስቴ ከብቶቹን ስታይ ሁሉም ደህና ሆነው አገኘቻቸው። “ተመስገን ያ አላህ! እነርሱ ናቸው ያሳሰቡኝ” ብላ ለፈጣሪ ምስጋና አደረሰች። ከአክስቴ ቤት ፈንጠር ብሎ ባለው ቤት የሚኖሩት የዘመዳችን ልጆች ወደኛ መጥተው በውጊያ መሀል ስለነበሩበት ሁኔታ ያወጉን ጀመር። እኛም ስለተኩሱ፣ ስለፍርሃታችን፤ ስለንግስቲ ለቅሶ፣ ስለ አክስቴና ከብቶቿ ወዘተ… አወራናቸው። በመሀሉ ግን አክስቴ “ወይ ዲምቱ ቲያ!” ብላ ጮኸች (“የኔ ቀዮ” እንደማለት ነው)።

አክስቴ ወደነበረችበት ስፍራ ዞር ስንል “ዲምቱ” የምትባለው ላም በአፍንጫዋ ደም እየመለሰች ነው። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ደሙ በሆዷ በኩል መጣ። በዚህም ዲምቱ በጥይት መመታቷን አረጋገጥን። ሆኖም ደሙ በሁለት በኩል መምጣቱ ግራ አጋባን። በተለይም በሆዷ በኩል የሚፈሰው ወፍራም ጥቁር ደም ስለነበረ ዋናው ምት እርሱ መሆኑ አጠራጠረን። ጥይቱ በየት በኩል ነው የገባው?… በፍጹም ለማወቅ አልተቻለም።

ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ግራጫ መልክ ያለው ወይፈን (ዲቢቻ) በሆዱ ላይ መድማት። “እንዴ!” አለች አክስቴ በጩኸት። “ከብቶቼ አንድ በአንድ ሊያልቁብኝ ነው እንዴ!” በማለት አማረረች። በዐይኗ እምባ ግጥም ብሎ ሞላ። በዚህን ጊዜ ሶስቱ ልጆቿ አስፈላጊ ያሉትን እርምጃ ወሰዱ። “ሰዎቹ ከተመለሱ ከብቶቹ እዚሁ ማለቃቸው ነው። ስለዚህ እየነዳናቸው ከዚህ ሰፈር መጥፋት አለብን” ተባባሉ።

በዚህም መሰረት ኢዘዲን፣ ነጋሺ እና ሙበጀል የሚባሉት ልጆች ከብቶቹን እየነዱ ከሰፈሩ ጠፉ። እኔ፣ በድረዲን እና ኒጊስቲ ከአክስቴ ጋር በቤቱ ውስጥ ቀረን።
*****
የኦነግና የኢህአዴግ ተዋጊዎች ከዚያ በኋላ እየተታኮሱ እኛ ወደነበርንበት ቤት አቅራቢያ አልተመለሱም። ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ውጊያው የሚካሄድበት ስፍራ የሰፈሩ ሰሜናዊ ጫፍ ሆኗል። በዚህም ሳቢያ የአካባቢው ህዝብ ፋታ አግኝቶ መንቀሳቀስ ጀመረ። በርካታ ሰዎች ከብቶቻቸውን እየነዱ “ዲኪቻ” እና “መተሙራ” ወደሚባሉት የገጠር ቀበሌዎች ነጎዱ። በሰፈሩ ከቀሩት መካከል እጅግ የሚበዙት ከቤታቸው ፊት ለፊት ቆመው ተኩሱ ወደሚመጣበት አቅጣጫ ያንጋጥጣሉ። እኛም ከአክስቴ ቤት ራቅ ብሎ በሚገኝ ገላጣ ስፍራ ላይ ቆመን ወደ “ጋራ አባ ያያ” እንመለከታለን።

በዚህ ሁኔታ እስከ ጠዋቱ አራት ሰዓት ከቆየን በኋላ አክስቴ ጠራችንና ቁርስ ሰጠችን። ቁርሳችንን እንደበላን እኔና በድሩን ወደ አያቴ ግቢ ሸኘችን። እርሷና “ኒጊስቲ” ግን “በኋላ እንመጣለን” ብለው በቤቱ ውስጥ ቀሩ። እኛም ይሁን ብለን ወደ አያቴ ግቢ ሄድን።

ታዲያ ወደ አያቴ ግቢ ሳንደርስ በርካታ የኦነግ ወታደሮች “አዴሌ” ከሚባለው አቅጣጫ በመምጣት ከአያቴ ግቢ ፊት ለፊት በሚያልፈው “ከራ ጉዳ” (ትልቁ መንገድ) የተባለ ጎዳና ወደላይ ሲያልፉ አየንና ከግቢው መግቢያ ላይ ቆም አልን።፡

እነዚያ ወታደሮች ከ130-140 ሰዎች ያህል ይመስሉኛል። መሪያቸው ቀይ ባለጎፈሬ ሰው ነው። ስሙን በወቅቱ ባላውቀውም በኋላ ላይ ሰዎች ሲነግሩኝ “ጃሌ ዱሜሶ” ነው ብለውኛል (የኦነግ ሰዎች አዘዦቻቸውን “ጃሌ” እያሉ ነው የሚጠሩት። “ጓድ” እንደማለት ነው)። “ዱሜሶ” ምክትል የሻለቃ አዛዥ ነበር። ያነገተው ታጣፊ ክላሽ በጫፉ ላይ ሳንጃ አለው። በእጁም ቴሌግራም ይዟል። እነዚያ ወታደሮች በኦነግ ደንብ መሰረት በአንድ ሰልፍ ብቻ ነበር የሚጓዙት። ዱሜሶ ደግሞ ከነርሱ ጎን ሆኖ ነው የሚሄደው።
*****
ጦርነቱ አላቆመም። ገና ቀኑን ሙሉ ይቀጥላል። በማግስቱም ስፍራ ቀይሮ ይቀጥላል (እኔ እርሱን አልተረከውም)። ወደ ቀጣዩ ወግ ከማለፋችን በፊት ግን ወደ ኋላ ልመልሳችሁ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ያኔ በልጅ አዕምሮዬ ሳይገቡኝ ቀርተው ከጊዜ በኋላ ያወቅኳቸውን አንዳንድ ነገሮች ላወሳ እፈልጋለሁና።

የኢህአዴግ ወታደሮች በቅድሚያ ውጊያውን የከፈቱት በጋራ ጉራቻ መሆኑ ተረጋግጧል። ያ “ጋራ ጉራቻ” የሚባለው ተራራ እኔ ከነበርኩበት ስፍራ ሶስት ኪሎሜትር ተኩል ያህል ይርቃል። “ጋራ አባ ያያ” የሚባለው ትልቁ ተራራ ደግሞ በሰሜን አቅጣጫ አንድ ኪሎሜትር ተኩል ያህል ይርቀኛል። ኢህአዴጎች በዚህም ጋራ ስር የነበሩትን የኦነግ ወታደሮችን አጥቅተው ወደታች እንዲገፉ አድርገዋቸዋል። ታዲያ ኢህአዴጎች በሁለቱ ስፍራዎች እየተዋጉ ማንም ሳይጠብቃቸው ከአክስቴ ቤት አጠገብ እንዴት ተገኙ….?።

ለዚህ የሚሆን እርግጠኛ መልስ የለኝም። ይሁንና ለእውነታው የቀረበ ግምታዊ መልስ ይኖረኛል። ከብዙ ምንጮች ለማረጋገጥ እንደተቻለው ኦነግ “ጋራ ጉራቻ” ከሚባለው ተራራ ወዲህ ብቻ ሳይሆን ከጀርባውም በኩል (በገለምሶ አቅጣጫ) ያስቀመጠው ሀይል ነበር። ታዲያ ያ ሀይል ሳይጠበቅ በኢህአዴግ ጦር ተጠቃ። በመሆኑም ብዙዎቹ ተዋጊዎች በቀላሉ ተማረኩ (እንደገና እንመለስበታለን)። ከጋራው ወዲህ ያለው የኦነግ ሀይል ግን የተኩስ ድምጽ መስማት ሲጀምር በየአቅጣጫው እየተበታተነ ወደ ተራራው ግርጌ ወረደ። እርሱን ተከትሎ ደግሞ ኢህአዴጎች በጋራ አባ ያያ በኩል ያለውን ሀይል አጠቁት። ያ የኦነግ ሀይል የሚችለውን ያህል ከተዋጋ ከኋላ ግማሹ ከርሱ ተገንጥሎ ከሰፈሩ ውስጥ ገባ። ኢህአዴጎች የዚህን ሀይል አካሄድ በርቀት አይተው ከርሱ በላይ (በሰሜን ምዕራብ በኩል) በማለፍ በቆረጣ ስልት ሊከቡት ፈለጉ። በዚህም መሰረት በአክስቴ ግቢ በስተሰሜን ምስራቅ በኩል መጡ።

ይሁንና ኢህአዴጎች ውጥናቸውን ከግብ ሳያደርሱ እነርሱ የሚከታተሉት የኦነግ ጦር በሼኽ ፊኒንሳ ከሚመራው ሌላ ጦር ጋር ተቀላቅሎ ጠበቃቸው። ይህ የሼኽ ፊኒንሳ ጦርም ኢህአዴጎቹን ሲያይ ተኩስ ጀመረ። በዚህም ሳቢያ የአክስቴ ግቢ የጦር ሜዳ ሆነ። ኢህአዴጎች አመጣጣቸው ከ“ጋራ አባ ያያ” ያፈገፈገውን አነስተኛ ጦር ለመክበብ እንጂ ከሼኽ ፊኒንሳ ጦር ጋር ለመፋለም አልነበረም። የሼኽ ፊኒንሳ ጦር ገትሮ ሲይዛቸው አድፋጩ ሀይል እነርሱ ለከበባ ካሰማሩት በላይ መሆኑን ስለተረዱ ወደ ኋላ ተመለሱ።

ኢህአዴጎች ለሁለተኛ ጊዜ ወደስፍራው መምጣታቸው ደግሞ በዚያ የነበረው የኦነግ ጦር በሌላ አቅጣጫ እየተዋጋ ከነበረው ሃይል ጋር እንዳይቀላቀል በሚል ይመስለኛል። ይሁንና ኦነጎቹ አሁንም አይለው ወደኋላ መለሷቸው። ቢሆንም ኢህአዴጎቹ በቅድሚያ ተራሮቹን በመያዛቸው ከዚያ ላይ ማንም ሊነቀንቃቸው አልቻለም። ኦነጎችም ባልጠበቁበት ሰዓት ተራሮቹን በመነጠቃቸው ወደፊት ለመግፋት አልቻሉም። በኔ ግምት ኦነጎች ተራሮቹን ባይነጠቁ ኖሮ፤ ከተነጠቁ በኋላም መልሰው ቢይዟቸው ኖሮ በሁለቱ ሀይሎች መካከል ሲደረግ የነበረው ውጊያ ሌላ መልክ በያዘ ነበር።
*****
በጣም ያስገረሙኝ ነገሮች አሉ።

ሁለቱ ሃይሎች ውጊያውን ያደረጉበት የአክስቴ ግቢ ከአንድ ሺህ ካሬ ሜትር የሚበልጥ ስፋት የለውም። ኢህአዴጎች በሁለቱም ጊዜያት የአክስቴ ከብቶች ከሚያድሩበት ስፍራ ነበር ያደፈጡት (ከውጊያ በኋላ ሄደን ስናይ ስፍራው በ“ቀለህ” ተሞልቷል)። ይህ ስፍራ ከቤቱ ግድግዳ አራት ሜትር ብቻ ቢርቅ ነው። ኦነጎች ደግሞ ከአክስቴ ግቢ ትንሽ ዝቅ ብሎ በሚገኘው የረውዳ መስክ መግቢያ ላይ ነው ያደፈጡት። በመካከላቸው ያለው ርቀት 100 ሜትር የሚሞላ አይመስለኝም።

የአክስቴና የልጇ ቤት ሁለቱ ሀይሎች ባደፈጡባቸው ቦታዎች መካከል ነው ያሉት። ሁለቱ ቤቶች የሳር ክዳን የለበሱ መሆናቸውን ቀደም ብዬ ተናግሬ ነበር። ታዲያ ለሁለት ጊዜያት በስፍራው የጦፈ ውጊያ ተካሂዶ ቤቶቹ እንዴት ነው ያልተነኩት?…. በተለይ ኢህአዴጎቹ ከፍ ካለ እየተኮሱ እነርሱ የሚተኩሱት ጥይት የአክስቴ ቤት ጣሪያ ላይ ወድቆ ለምን አላቀጣጠለውም?…. ወይንስ ጥይቱ ከጣሪያው ላይ እያረፈ ሳሩን ማቀጣጠል ስለተሳነው ነው ቤቱ ያልተቃጠለው…?

ይህ ዘወትር የሚያስደንቀኝ ጉዳይ ነው። በውጊያው የተተኮሱት ጥይቶች የቤቱን ግድግዳ ጠዝጥዘውታል። በሁለቱም በኩል ያሉት የቤቱ ግድግዳዎች በክብ ነጠብጣቦች ተሞልተዋል። በዚህም ሳቢያ በቤቱ ምርጊት ላይ የተቀባው የበራሳ አፈር ተዥጎርጉሮ “ቀይ ቆቅማ” ዶሮ መስሏል። ጥይቶቹ ላይ ላዩን ከመነካካት ውጪ ግድግዳውን ጥሰው አልመጡም። “ጥይት ግድግዳን አይበሳም” ሲባል ሰምቼ ስለነበር እርሱ አላስደነቀኝም። የጣሪያው አለመነካት ግን በጣም አስገርሞኛል። በተጨማሪም ሁለቱ ሀይሎች ለውጊያው ቦምብ አለመጠቀማቸው ሁሌ ያስደንቀኛል። ሌላው ቀርቶ ከአስራ ስድስቱ የአክስቴ ከብቶች መካከል በጥይት የተመቱት ሁለቱ ብቻ ነበሩ።

በየጊዜው በዜና ማሰራጫዎች “የእገሌ ሰፈር በጦርነት ወደመ” ሲባል እንሰማለን። ነገር ግን ተዋጊዎቹ ቤቶችና መንደሮችን ሆን ብለው ካላጠፉት በስተቀር ውጊያው በመደረጉ ብቻ ሰፈሩ የሚወድምበት ዕድል ጠበብ ያለ መሆኑን ከዚያ ቀን ውሎዬ ተምሬአለሁ።

(ይቀጥላል)

አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 15/2007

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *