«ምንድን ናት» ለሚል ጠያቂ ትርጉምሽን ባልፈታም
«ሀገር ሃሳብ ብቻ ነው» የሚል ሞጋች ባልረታም
ሀገሬ ሆይ እወድሻለሁ!
እርግጥ፣
ሲበድሉሽ እንዳላየ፣
ሲገድሉብሽ እንዳልሰማ
ሲተኩሱ እንዳልደማ
ጌቶች ሲቆጡ ለስልሶ
ጫን ሲሉ አፈር ልሶ
ሲያስሩብሽ እንዳልታሰረ
ሲመቱሽ እንዳልነበረ
ሆኖ ማለፉን አውቃለሁ
ቢሆንም እወድሻለሁ።
«የህዝብ ንብረት ነው» ሲባል
«ህዝብ ከየት አባቱ አፈራው ብዬ»
ህሊናዬን አባብዬ
ከካዝናሽ እጄን ዶያለሁ
ቢሆንም እወድሻለሁ!
ሀገር ሰው ነው ባሉኝ ማግስት፣
በእንጀራ መሃል ሰጋቱራ
በበርቤሬ የሸክላ አሻራ
ጨምሬ የሸጥኩ ቢሆንም
እወድሻለሁ አሁንም!
ባህል እና እስቴሽን እወደዋለሁ ባልኩ አፍታ
ብሆንም የፊደል ሽፍታ
ከትዝታሽ ትዝ የማይለኝ
ከዛሬሽ ህብር የሌለኝ
እንደሆንኩ እየገባኝም
እወድሻለሁ አሁንም!
መብላት «ሹም እያሉ ነው»
ያባት ቤት ሲዘረፍ መዝረፍ
በሀገር ንብረት ኑሮን ማትረፍ
የሚል እምነት ሸሽጌ፣ ለተግባሩ ብተጋም
አንቺን እወድሻለሁ ሳልል፣ የመሸው ፈፅሞ አይነጋም!
ለምለሽን ለማጠውለግ ከኛ የፈጠነ ቢጠፋም
ስለመውደድ ስናወሳ ቃላችን ባንቺ ባይከፋም
ብርሃንሽን ለማክሰም ጨለማ መዝራት ባንሰንፍም
እንወድሻለን ዘላለም፣ ከቃላችን ሃባ አንቀጥፍም!
ጉሮሯችን እስኪነቃ፣ አልፎ ሂያጅ እስኪታዘበን
እንወድሻለን ዘላለም፣የፍቅርሽ አርቡ ሳይጠበን
ባለቅኔ ልጆችሽ የተካንን በዘረፋው
እንወድሻለን በሃላል፣ ጠላትሽ ይበሳጭ ይክፋው!
እንደ ሀገሬ ወንድሞቼ፣ እንደ አባት፣ እህቶቼ
እኔ ራሴም እወድሻለሁ፣ እጄን ኪስሽ ከትቼ!!