ቀዳሚው የትግል ምዕራፍ
ዶ/ር ጆርጅ ሐበሽ እና ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ በቀዳሚዎቹ ዓመታት አዲሱን ድርጅታቸውን በማስተዋወቅና አባላትን በመመልመል ላይ ነበር ያተኮሩት። በዚህ መሠረት በተለያዩ ሀገራት ወደሚገኙት የፍልስጥኤም ኮሚኒቲዎች ወኪሎቻቸውን እየላኩ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን አስተዋውቀዋል። አባላትን እየመለመሉ በድርጅቱ ህዋሳት ስር አዋቅረዋል። ከተለያዩ መንግሥታት ጋርም ግንኙነት ለመፍጠር ሞክረዋል።
ይሁንና በሁለቱ ዶክተሮች ግንባር ቀደም ተሳትፎ የተመሠረተው “ሐረካ” (የዐረብ ብሄራዊ ንቅናቄ) ከጅምሩ በርካታ መሰናክሎች ነበር የገጠሙት። ከነዚህ መሰናክሎች መካከል ዓይነተኛ ተጠቃሽ የሆነው በ1957 “በዮርዳኖሱ ንጉሥ ሑሴን ላይ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሴሯል” በሚል የድርጅቱ መሪ በሆነው ጆርጅ ሐበሽ ላይ የቀረበው ክስ ነው። ድርጅቱ ክሱን ቢያስተባብልም ተሰሚነት አላገኘም። በዚህም የተነሳ ጆርጅ ሐበሽ ህቡእ ለመግባት ሲገደድ የድርጅቱ መስራች አባል የነበረው አቡ ዓሊ ሙስጠፋ ታስሯል። ድርጅቱም በዮርዳኖስ እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል። በድርጅቱ አባልነት የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎችም ታስረዋል።
የዮርዳኖስ የጸጥታ ኃይሎች እነዚህን እርምጃዎች ከመውሰዳቸው በፊት የድርጅቱ ዋነኛ መሪዎች እነ ማን እንደሆኑ ተረድተው ነበር። በዚያ ወቅት በጸጥታ ኃይሎች እይታ ስር ያልወደቀው ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ ብቻ ነበር። ዋዲ ሀዳድ በተፈጥሮው ቆቅ እና ሁሉንም ነገር ከጸጥታ ኃይሎች ሰውሮ ማከናወን የሚሻ ሰው ነበር። አሁን በህይወት ያሉት የድርጅቱ አባላት “ዋዲ ሀዳድ ማንነቱን ከተለያዩ ሀገራት የጸጥታ ተቋማት በመደበቅ የመኖር ተሰጥኦ የነበረው ጂኒየስ ነበር፣ የዮርዳኖስና የሌሎች የዐረብ ሀገራት የጸጥታ ኃይሎች ለበርካታ ዓመታት የርሱን ማንነት አያውቁም፣ ዋዲ ሀዳድ በህይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ የሌሎችን ትኩረት ሳይስብ ያሰበውን ይፈጽም ነበር” በማለት ይመሰክራሉ።
ዋዲ ሀዳድ በርግጥም የድርጊት ሰው ነበር። ብዙዎች ሁለቱን ዶክተሮች ሲገልጿቸው “ጆርጅ ሐበሽ የጭንቅላት ሰው (ideologue) ሲሆን ዋዲ ሀዳድ ግን የተግባር ሰው (pragmatic) ነው” ይላሉ። ዋዲ እንደዚህ የተባለው ማንነቱን ለመደበቅ በመቻሉ ብቻ አይደለም። የድርጅቱ መሪዎች በችግር በተወጠሩበት ወቅት ልዩ ልዩ ብልሃቶችን እያመነጨ ይታደጋቸው ስለነበረም ነው። ከዚህ ሌላም ዋዲ ሀዳድ ቅልጥፍና የታየባቸውን ኦፕሬሽኖች እያቀደ የመፈጸም ችሎታው ከፍተኛ ነበር። ይህ ችሎታው አስቀድሞ የታየው ከላይ በጠቀስነው መንገድ ድርጅቱ ባልጠነከረበት ዘመን ለዮርዳኖስ የጸጥታ ኃይሎች እመቃ በተዳረገበት ወቅት ነው።
በዚህም መሠረት ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ በዮርዳኖስ የጸጥታ ኃይሎች ተይዞ ወደ እስር ቤት የገባውን አቡ ዓሊ ሙስጠፋን የሚያስለቅቅበትን ዘዴ አጠና። ከዮርዳኖስ መንግሥት እይታ ተገልሎ በህቡእ ለመኖር የተገደደው ጆርጅ ሐበሽ ከሀገሪቱ የሚያመልጥበትንም መንገድ ቀየሰ። ሁለቱን መሪዎች በተመሳሳይ ዕለት ወደ ሶሪያ መውሰድ እንደሚበጅም አመነ። ያሉትን አማራጮች ሁሉ ከገመገመ በኋላም አንድ ኦፕሬሽን ነደፈ።
ኦፕሬሽኑም በተያዘለት እቅድ መሠረት የካቲት 18/1958 ይተገበር ጀመር። በኦፕሬሽኑ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ ከአምስት የድርጅቱ ታጋዮች ጋር ሆኖ በውድቅት ሌሊት አቡ ዓሊ ሙስጠፋ የታሰረበትን እስር ቤት ሰበረውና የትግል ጓዱን አስለቀቀው። በዚያው ቅጽበትም የተወሰኑ ሰዎችን መድቦለት ወደ ሶሪያ ሸኘው። በማለዳ ደግሞ እርሱና ጆርጅ ሐበሽ እንደ በደዊ ዐረብ ለብሰው የዮርዳኖስን ድንበር በማቋረጥ ወደ ሶሪያ ገቡ። ብዙሃኑ የድርጅቱ አባላትም በተከታዮቹ ቀናት ከዮርዳኖስ እየሾለኩ ወደ ሶሪያና ሊባኖስ በመሄድ ከመሪዎቻቸው ጋር ተገናኙ።
ድርጅቱ በሶሪያ ምድር ለአባላቱ የፖለቲካና ወታደራዊ ስልጠና የሚሰጥበትን ካምፕ መሠረተ። ለሁሉም አባላቱ ወታደራዊ ስልጠና ሰጠ። ስልጠናውን ካጠናቀቁት የድርጅቱ አባላት መካከል ብዙዎቹ በዘመኑ በዮርዳኖስ ይዞታ ስር ወደነበረው “ምዕራባዊ ዳርቻ” በመግባት የመንደርደሪያ ጣቢያዎችን መሠረቱ። ከጣቢያዎቹ እየተነሱም የፍልስጥኤም ግዛቶችን በያዙት የእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃቶችን መፈጸም ጀመሩ።
———
ጆርጅ ሐበሽና ጓዶቹ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ድርጅቱን በአዲስ ሁኔታ አዋቀሩ። በ1958 “ፋታሕ” እየተባለ የሚጠራውን “የፍልስጥኤም ብሄራዊ የነፃነት ንቅናቄ”ን ከመሠረቱት እነ ያሲር አራፋት (በትግል ስሙ “አቡ አማር”)፣ ኸሊል አል-ወዚር (በትግል ስሙ “አቡ ጂሃድ”)፣ ሳላሕ ኸለፍ (በትግል ስሙ “አቡ ኢያድ”) እና ማሕሙድ ዐባስ (በትግል ስም “አቡ ማዚን”) ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውንም ስምምነት ፈጸሙ።
በዚህም መሠረት ፋታሕ፣ ሐረካ እና ሌሎች ፍልስጥኤማዊ ድርጅቶች በጋራ በመሆን የህዝባቸውን ትግል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወክለውን “የፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ድርጅት”ን (PLO) በ1964 መሠረቱ:: ይህ የጋራ ድርጅትም የፍልስጥኤማዊያንን ትግል ለዓለም ህዝብ ለማስተዋወቅ ጥረት ማድረግ ጀመረ። የዐረብ ሊግም ለዚህ የጋራ ድርጅት “የፍልስጥኤም ህዝብ ብቸኛ ተወካይ” የሚል እውቅና ሰጠው። በርሱ ስር ያሉት ፍልስጥኤማዊያን ድርጅቶችም በወረራ ወደተያዙት ግዛቶች እየገቡ የእስራኤልን ወታደሮች መውጋታቸውን ቀጠሉ።
(ይቀጥላል)
——-
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 4/2010
በሸገር ተጻፈ።