Tidarfelagi.com

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል ስድስት)

ክፍል ስድስት፡ ለይላ ኻሊድ በዓለም ህዝብ ፊት 

በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች መካከል ብዙዎቹ ስለአውሮፕላን ጠለፋ ሰምተዋል። ይሁን እንጂ ጠላፊዋ ሴት ስትሆንባቸው በጣም ነበር የተደናገሩት። ይህም የሆነው በዘመኑ ወንዶች እንጂ ሴቶች በአውሮፕላን ጠለፋ ሲሳተፉ ስላልታየ ነው። በዚህም የተነሳ ተሳፋሪዎቹ ከመደናገጥ ይልቅ ወደ አግራሞት ነበር ያደሉት። ጠላፊዋ የድርጅቷን የፖለቲካ ዓላማዋ እያብራራች ስትገልጽላቸው ደግሞ ያደንቋት ጀመር።

ለይላ ኻሊድ የአውሮፕላኑን አብራሪ እየመራች ጉዞዋን ቀጠለች። አውሮፕላኑ የሜዲትሪያኒያንን ባሕር ሲያቋርጥ ግን የትውልድ ከተማዋ ናፍቆት ተቀሰቀሰባት። በመሆኑም አብራሪውን “የተወለድኩት በሐይፋ ከተማ ነው። ሆኖም ለረጅም ጊዜ አላየኋትም። ስለዚህ ከተማዬን ማየት እንድችል አውሮፕላኑን በዚያ በኩል አሳልፈው” በማለት አዘዘችው። አብራሪውም እንደተባለው አደረገ። ለይላም የሐይፋ ከተማን ከሀያ ዓመታት በኋላ ከሰማይ ወደታች ቁልቁል አየቻት። ለተወሰኑ ደቂቃዎችም በኃላፊነት የምትመራውን አደገኛ ኦፕሬሽን ዘንግታ ከተማዋን እያየች አነባች።

ከሽርፍራፊ ሰከንዶች በኋላ ግን ደነገጠችና ከትካዜዋ ነቃች። አትኩሮቷንም ሰብስባ ወደ ኦፕሬሽኑ ተመለሰች። ታዲያ አብራሪው የለይላን ሁኔታ ሲያይ ከልቡ ነበር ያዘነላት። በመሆኑም ትእዛዞቿን በምንም መልኩ ለመጣስ አልደፈረም። ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላም አውሮፕላኑን በደማስቆው የሐፊዝ አል አሳድ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ አሳረፈው።
—–
አውሮፕላኑ ወደ ደማስቆ እንደሚመጣ ለሶሪያ ባለስልጣናት ተነግሮ ስለነበረ ብዙ መደናገጥ አልተፈጠረም። አውሮፕላኑ ሲያርፍ ደግሞ PFLP ያሰማራቸው ተጨማሪ ኮማንዶዎች ለይላንና ጓደኞቿን ለመርዳት ወደ ውስጥ ገቡ። ለለይላም ዛሬ በብዙ ፎቶግራፎች ላይ ታጥቃ የምትታየውን AK-47 (ክላሽኒኮቭ) ጠመንጃ አመጡላት።

በአውሮፕላኑ ይጓዙ የነበሩ ተሳፋሪዎችን ማንነት ለማጣራት በተደረገው ፍተሻ ግን አምባሳደር ይስሐቅ ራቢን በአውሮፕላኑ ውስጥ እንደሌሉ ታወቀ። በዚህም የPFLP አመራሮች የተሳሳተ መረጃ እንደደረሳቸው ተረዱ። ለወደፊቱ ጥንቃቄ ለመውሰድ ወሰኑ። ቢሆንም አውሮፕላኑ በለይላ ኻሊድ መሪነት መጠለፉ ታላቅ ዜና በመሆኑ የPFLP መሪዎች በአፈጻጸሙ በጣም ነበር የተደሰቱት።

ከግማሽ ሰዓት በኋላ የተጠለፈው አውሮፕላን በደማስቆ ስለማረፉ በሶሪያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ተነገረ። በርካታ ጋዜጠኞችና ወሬ አነፍናፊዎችም ወደ አየር ማረፊያው መጡ። ለይላ ኻሊድ ከአውሮፕላኑ ሳትወርድ ከጋዜጠኞቹ ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አደረገች። የዓለም ማህበረሰብ የፍልስጥኤምን ህዝብ ስቃይ እንዲመለከትና ለህዝቡ የነፃነት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ማሳሰቢያ ሰጠች። በአውሮፕላኑ ውስጥ የታገቱት ተሳፋሪዎች በነፃ እንደሚለቀቁም አስታወቀች። “አውሮፕላኑ ግን የእስራኤል አውራ ረዳትና የፍልስጥኤም ህዝብ ቀንደኛ ጠላት የሆነችው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊስቶች ንብረት ነው፣ ስለዚህ በዚሁ ሜዳ ላይ እያለ ይቃጠላል” በማለትም አከለች።

ለይላ ኻሊድ ከPFLP አመራር በተሰጣት ትእዛዝ መሠረት በተከታዮቹ ቀናትም ወደ አየር ማረፊያው ከመጡ ጋዜጠኞች ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጋለች። ታዲያ ለይላ ከጋዜጠኞቹ ጋር ስትነጋገር ስለትግሉ እንጂ ስለራሷ ግድ አልነበራትም። ወደ ጠለፋው የገባችውም በግንባሩ ስለታዘዘች እንጂ ራሷን ለማስተዋወቅ አልነበረም። ይሁን አንጂ ለጋዜጠኞች መግለጫ በምትሰጥበት ወቅት ብዙዎች ፎቶ ሊያነሷት ተረባረቡባት። ከነዚያ ፎቶዎች ሁሉ እጅግ ታሪካዊና ዝነኛ ለመሆን የበቃው አንድ ታዋቂ ጋዜጠኛ በካሜራው ያስቀረው ፎቶ ነው።

ጋዜጠኛው ኤዲ አዳምስ ይባላል። ኤዲ ለአሜሪካው አሶሼትድ ፕሬስ ተቀጥሮ የሚሰራ “ፎቶ-ጆርናሊስት” ነበር። ኤዲ “አንዲት ፍልስጥኤማዊት ወጣት አውሮፕላን ጠለፈች” በሚለው ዜና ተገርሞ ነበር ወደ አየር ማረፊያው በፍጥነት የመጣው። ለይላን ፊት ለፊት ሲያገኛት ደግሞ ልበ ሙሉነቷ እና ዓላማዋን የገለጸበችበት መንገድ በጣም አስደንቆታል። በመሆኑም በካሜራ እይታ ውስጥ ስትገባለት በጋዜጠኝነት ዓለም ታዋቂ ከሆኑት ፎቶግራፎች መካከል አንዱን አንስቶ ለአሶሼትድ ፕሬስ ላከው። በማግስቱም ፎቶዋ በበርካታ የአውሮጳ እና የአሜሪካ ጋዜጦች ላይ ወጣ። የግራ ኃይሎች ፎቶውን እያባዙ በዓለም ዙሪያ በስፋት አሰራጩት። በዚህም ሁኔታ ያ ታሪካዊ እንደ ቼ-ጉቬራ ፎቶግራፍ ታዋቂ ለመሆን በቃ።

አሜሪካ እና የተለያዩ የዐረብ ሀገራት አውሮፕላኑን ከቃጠሎ ለማትረፍ ሞክረው ነበር። ነገር ግን ለይላ እና የPFLP መሪዎች ከቃላቸው ፍንክች የማይሉ ሆነው ነው የተገኙት። በማሳሰቢያቸው መሠረትም በአውሮፕላኑ ይጓዙ የነበሩትን ተሳፋሪዎችና ሰራተኞችን በሰላም ከለቀቁ በኋላ አውሮፕላኑን አቃጠሉት። ትዕይንቱም የወቅቱ ግንባር ቀደም ዜና ሆኖ በተለያዩ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተላለፈ።
—–
ለይላ ኻሊድ ጠለፋውን ከካሄደች ከሰላሳ አንድ ዓመታት በኋላ (በነሐሴ ወር 2000) “Aviation Security” ከተባለ መጽሔት ጋር ቃል-ምልልስ ስታካሄድ ትዝታዋን እንዲህ በማለት ገልጻለች።

“ከአውሮፕላኑ ውስጥ ስገባ አንዲት ህፃን አየሁ። ህፃኗ ቆንጅዬ እና ደስተኛ ናት። ከእናቷ ጎን ቁጭ ብላ ትስቃለች። በለበሰችው ቲ-ሸርት ላይ “Let us be friends” የሚል ጽሑፍ ተጽፏል። የርሷን ደስተኛነት ሳይ የልጅነት ዘመኔ ትዝ አለኝ። በልጅነቴ ምንም ሳላጠፋ ወራሪዎች ከተማችንን ይዘው ቁም ስቅላችንን ሲያሳዩን ትዝ አለኝ። ንፁሐን ጎረቤቶቻችን ፍልስጥኤማዊ በመሆናቸው ብቻ የተገደሉበት ትዕይንት ትዝ አለኝ። ከቤተሰቦቼ ጋር እየደበደቡ ከቤታችን ካስወጡን በኋላ ከከተማችን ሲያባርሩን ያደረብኝ ስሜት ትዝ አለኝ። ልጅነቴን እንደዚያች ህፃን በደስታ ለማሳለፍ አልቻልኩም። በወራሪዎች ደባ በልጅነቴ ወደ ስደተኛ ካምፕ ገብቼ አራት ዓመታትን በሰቀቀንና በችግር አሳልፌአለሁ። አስር ዓመት ከሆነኝ በኋላ ነው ታላቅ እህቴ መጥታ ከካምፑ ያስወጣችኝ። ታዲያ በአውሮፕላኑ ውስጥ ያገኘኋትን ደስተኛ ልጅ እያየሁ በውስጤ እንዲህ አልኩ።

“ሚሚዬ! ፈጣሪ በሰጠሽ ፀጋ መደሰትሽ ያኮራል። እኔም በዛሬው ዕለት ከባድ ኃላፊነት ተሸክሜ ከአጠገብሽ የተገኘሁት ፍልስጥኤማዊያን ህፃናት እንዳንቺ ደስተኛ ሆነው እንዲያድጉ ስለምፈልግ ነው”
(ይቀጥላል)
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 8/2010
በሸገር ተጻፈ።

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል ሰባት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *