የታፈኑ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶች ተብላልተው ጉልበት ሆነው ይመጣሉ እንጂ ተዳፍነው አይቀሩም! የብሔር ጥያቄም እንዲያው ነው።
ከዘመነ ኃይለስላሴ በፊት ግዛቶች ራሳቸው በራሳቸው የማስተዳደር አንፃራዊ ነፃነት ነበራቸው።የሚያስተዳድራቸው የራሳቸው ሰው ነበር። ልዝብ ፌደራሊዝም አይነት ነበሩ። ኃይለስላሴ መጥተው ያንን ሰባበሩት። (ዶ/ር ፍስሃ አስፋው እና ፕሮፌሰር መስፍን)
የብሔር ጥያቄ በዘመነ ሀይለስላሴ ሲጀመር፣ በሀይለ ስላሴም ሆነ ከዛ በኋላም የተሰጠው መልስ ዱላ እና ንቀት ነበር። ጥያቄውን እንደ ሀገር አፍራሽ በማየት ሃሳባቸው በሌላ ዘንድ ተደምጦ “ጨዋውን ሕዝብ እንዳይረብሽ ” ብዙ ተለፍቷል።
ያ ስህተት ዛሬ ደርሶ ያስከፍለናል። በፖለቲካ ነፃነት ሊመለስ የሚችለውን ቀላል ጥያቄ፣ በመሪዎች ግትርነት እና አሳጥሮ አሳቢነት ዛሬም ጥያቄ ሆኖ እንታሽበታለን።
ኢህአዴግ ተብየዋም መጥታ በመልሻለሁ ሰው አበላሸችው። ነገር ዓለሙ ሁሉ የብሔር ቋንቋ እንዲሆን አድርጋ፣ ለብሔሮች ጥያቄ ይሄነው የሚባል መልስ አልሰጠችም። ሉዓላዊ ባለስልጣኖች ብሔር ብሔሰቦች ናቸው። በእውነታው ግን ተርዚና የምታህል ስልጣንም የላቸውም። ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አልቻሉም።የብሔር ጥያቄውን ይበልጥ ለመለጠጥ የሚያመች ኢንቫይሮመንት ከመሰራቱ ውጭ አንዳችም የተመለሰ ነገር የለም። የአሁኑ የኢህአዴግ ፖለቲካ ክፋቱ ግለሰብ የሚባል ነገር መኖሩን የሰማም አለመምሰሉ ነው። ብሔርነትን አጉል ለጥጦ፣ ለብሔሮች አንድ የረባ ነገር ጠብ አለማድረጉ በመጨረሻ እራሱን ሊበላው የደረሰ ይመስላል። ቃል መግባት መልስ አይሆንም።
ብዙዎች የብሔር ጥያቄን ይፈሩታል። የዘውግ ፓለቲካ ለማንም አይመችም። በግሌ እኔም አይመቸኝም። ግን፣ የብሔር ጥያቄ መልሱን ካገኘ በሆነ ባልሆነው ዘሎ ልብላህ የሚል አውሬ አይመስለኝም። የሚያስፈራው የአንባገነን መንግስታት መልስ እንጂ የብሔሮች ጥያቄ አይደለም።
የማይሰማው መንግስት ብቻ አይደለም ፣ ሕዝቡም ነው። ታጋዩም ነው። በአሁን እምነቴ አንድ ሰው በብሔሬ ተበድያለሁ ካለ እህ ብሎ መስማት ያስፈልጋል። አልተበደልክም ማለት የሚቻልም የሚያዋጣም አይመስለኝም። አይ በተባለ ቁጥር ሞር አግሬሲቭ እየሆነ እንጂ፣ ከመነጫነጭ መለስከኝ ብሎ አቅፎ የሚስም የሕዝብ ጥያቄ የለም።
አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ የሚያደርጉ ጠንካራ ክሮች ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያ አንድ አይደለችም። ብዙ ናት። ብዙ ባህል፣ ብዙ ቋንቋ፣ ብዙ ሥነልቦና የያዙ ሕዝቦች አሉባት። አንድ አለመሆኗ የሚጎዳት ሁሉንም አንድ ልታደርግ ስትሞክር ወይ ወደ አንዱ ስትዘም እንጂ (እንደ ቲፒኤልኤፍ ፖለቲካ) «እሺ ምን ጎደላችሁ» ብላ ስትሰማ አይደለም። ኢትዮጵያ የሁሉም ሀገር የምትሆነው የሁሉንም ጥያቄ ስትመልስ ነው። አሁን ባለሁ ሁኔታ የሁሉንም ጥያቄ አልመለሰችም። እንኳን የሁሉን የጥቂቶቹን አልመለሰችም። ስለዚህ፣ ኢትዮጵያ የሁሉም አይደለችም።