ለምኖርበት ህንፃ የፅዳት ተጠሪ ስለሆንኩ በየወሩ እየዞርኩ ለሠራተኞች የሚከፈለውን ደሞዝ መዋጮ እሰበስባለሁ።
ቅዳሜ እንደተለመደው እየዞርኩ የአንዷን ጎረቤቴን አፓርትማ አንኳኳሁ።
ከፈተች።
ከእሷ ቀድሞ ከቤቷ ውስጥ የወጣው ትኩስ እንጀራ ሸታ አወደኝ።
የትኩስ እንጀራ ነገር አይሆንልኝም። ቁንጣን ይዞኝ ‹‹ማር እንኳን አልልስም›› ብዬ እንኳን የማልጨክንበት ነገር ቢኖር ትኩስ እንጀራ ነው።
ሳይርበኝ ሆዴ ተላወሰ።
ምግብ ሳያሰኘኝ ሞረሞረኝ።
‹‹ሄይ…የፅዳት ነው አይደል…?.›› ስትለኝ ወደራሴ መለስ አልኩና፣
‹‹አዎ…የፅዳት ብር እየሰበሰብኩ ነው..….ውይይ….ትኩስ እንጀራ ነው የሚሸተኝ አይደል?›› አልኳት፤ ከተናገርኩት ውስጥ ‹‹ትኩስ እንጀራ ነው የሚሸተኝ አይደል?›› የሚሉት ቃላት ያለ ፈቃዴ ከአፌ ስለወጡ እያፈርኩ።
መልስ ሳትሰጠኝ ብሩን ለማምጣት መሰለኝ ወደ መኝታ ቤት ገባች።
እኔ እዚያው በሩ ደፍ ላይ ወደ ውስጥ ሳልገባም፣ ወደ ውጭ ሳልወጣም ቆሜ ትኩስ እንጀራውን ማማግ፣ በአፍንጫዬ መመገብ ጀመርኩ።
አንዳንድ ጠረኖች የሉም? የሰከንድ ስብርባሪ ሳይፈጅባቸው አስርት አመታት ወደኋላ የሚወስዷችሁ? በልጅነታችሁ ያሸተታችሁት አበባ፣ በልጅነታችሁ የበላችሁት ማስቲካ፣ በልጅነታችሁ የተቀባችሁት ቅባት፣ ዳግም ስታገኙት በቅፅበት ጊዜን ሽሮ መልሶ ልጅ አድርጓችሁ አያውቅም?
የእንጀራው ሽታ እዛው በቆምኩበት ልጅ አደረገኝ።
በዚህ ሂሳብ ሳስበው የራበኝ እንጀራ አልነበረም።
ውል ያለኝ ልጅነቴ ነው። የራበኝ ትዝታዬ ነው።
እናቴ እንጀራ ጋግራ ስትጨርስ እንጎቻ ሰርታልኝ በበርበሬ የምትሰጠኝ ።
ትንሽ ሳለሁ ዘወትር ቤታቸው ተልኬ በሄድኩ ቁጥር እንጀራ ሲጋግሩ ከገጠመኝ ‹‹የኔ ኮረሪማ…ነይ ይሸትሻል ›› ብለው ቆረስ አድርገው የሚያጎርሱኝ እማማ እምወድሽ ።
የዘመን ናፍቆት ነው ሆዴን የሞረሞረው።
ባለ እንጀራዋ ጎረቤቴ በርካታ ሰውነቷን እየጎተተች ብሩን ይዛ ተመለሰች።
‹‹ይሄው›› አለችኝ ‹‹በይ ሂጂ እንጂ ምን ቀረሽ?› አይነት አስተያየት አይታኝ በሩን ልትዘጋው እየዳዳት።
‹‹ትኩስ እንጀራ በጣም ነው የምወደው›› አልኳት። (ማነው እንዲህ ፈጣጣ ያደረገኝ? ሥነምግባሬ ወዴት ገባ? )
‹‹ተይ አንጂ…? እኔ ደሞ ስጠላ…የሚጠባበቀው ነገር ያስጠላኛል›› አለችኝ በሩን አጥብቃ እንደያዘች።
‹‹በሚጥሚጣም ቢሆን አትወጂም…? እኔ ግን ነፍሴ ነው..አሁን ሲሸተኝ ምን ትዝ እንዳለኝ ታውቂያለሽ…›› (ምነው እንዲህ ቀላዋጭ ሆንኩ ግን?)
አረፍተነገሬን ሳልጨርስ ፈጠን አለችና፣ ‹‹አይ እኔ እንጀራ ካደረ ነው የምወደው….››በሩን መዝጋት እየጀመረች ነው።
ይሄን ጊዜ በመሃላችን ምቾት የሚነሳ ዝምታ ሰፈነ።
ሳላውቀው አይኔ እምባ ያቀረረም መሰለኝ።
የእማዬ ትኩስ እንጎቻ በሚጥሚጣ፣ የእማማ የምወድሽ የማይዘጋ በር ትዝ ብሎኝ እምባዬ ሊያመልጠኝ መሰለኝ።፡
ምን ሆና ነው?
ስስት ነው? (ቁራሽ እንጀራ ልትሰስት የሚገባት ሰው አትመስልም። ብትሰስትስ? ብበላ አንድ መሶብ ሙሉ እንጀራ አልበላ! ለምንስ በፍጥነት በሩን እላዬ ላይ መዝጋት ፈለገች? ብቻዋን ለመሆን ብትቸኩልስ? ብቆይ አንድ ሳምንት አልቆይ….)
ይህች በእድሜ አርባ ቤት ያለች ሴት ምን ያህል ተንጋዳ ብታድግ ነው እንዲህ ያለውን ነውር የምታደርገው?
በዝግታ የምትዘጋው በሯ እኔ ላይ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ሕይወታችን ላይ፣ እኔ ላይ ብቻ ሳይሆን ልማድና ጉርብትናችን ላይ ለዘልአለም የሚጠረቀም ታላቅ በር መሰለኝ።
ከስጥ ላይ ሊበላ እጁን ሲዘረጋ እንደተመታ ልጅ ሽምቅቅ አልኩ።
እግሬ ጎማ ኖሮት እየተነዳሁ በፍጥነት ብጠፋ እየተመኘሁ… ሀገሬ ላይ ሆኜ ሃገሬ እየናፈቀችኝ፣ ወደ ቤቴ ተራመድኩ።
ኢትዮጵያዊያን ልማድና ወጋችን፣ መተሳሰባችን፣ ማህበራዊ ሕይወታችን እና ጉርብትናችን በብዙ ተፈትኖ አልፏል።
ቢሆንም …
‹‹እንኳን በአንድ ምጣድ- ቢጋገር በመቶ፣
ይሸታታል ትቅመስ፣
ይሸተዋል ይቅመስ -ማለት ድሮ ቀርቶ›› ተብሎ የተተረተው ለርሃብ እና ለቸነፈር ጊዜ እንጂ መካከለኛ ገቢ ኖሯቸው በአፓርትመንት ውስጥ ለሚኖሩ ጎረቤታሞች ነው ብዬ አስቤ ግን አላውቅም።