Tidarfelagi.com

ስንት ጊዜ ሆናችሁ?

መሃል አዲስአባ…ሸገር ላይ እያላችሁ..

የእንቁራሪቶች ድምፅ በደንብ ከሰማችሁ
በክር የታሰረ ጢንዚዛ ካያችሁ
የማርያም ፈረስን መንገድ ካገኛችሁ
በእፉዬ ገላ ‹‹ያዘኝ አትያዘኝ›› ከተጃጃላችሁ…

ስንት ጊዜ ሆናችሁ?

ሱዚ የሚዘሉ
ፔፕሲ የሚራገጡ
ሸክላ እየፈጩ በርበሬ ነው የሚሉ
ሙሽራ ሙሽራ – እቃ እቃ እቃ እቃ የሚጨዋወቱ
ጢቢ ጢቢ ሰርተው- እየተጫወቱ- የሚፈነድቁ -ሴት ልጆች ካያችሁ

ስንት ጊዜ ሆናችሁ?

በኮባ ጠመንጃ የሚተኳኩሱ
ኳሷን ከስልክ እንጨት ድብን አርገው አስረው ቴዘር የሚመቱ
በሽቦ መኪና የሚወዳደሩ
መሬትን ቆፋፍረው ብይ የሚጫወቱ
ልጆችን ካያችሁ

ዛፉን ተፈናጥጠው ሆምጣጤ የሚያወርዱ
ከአመት እስከ አመት እርግብ የሚያረቡ
በሌሊት ተነስተው ለእግር ኳስ ቡድን ስፖርት የሚሰሩ ፈርጣማ ጎረምሶች
ሰፈር ውስጥ ካያችሁ

ስንት ጊዜ ሆናችሁ?

አዲሳባ መሃል የአሞራ ክንፍ ቪላ
የቀይ ሸክላ ውብ ቤት በአይናችሁ ካያችሁ
ሰንሰልና ሃረግ አጥር ሆነው ቆመው በጎን ካለፋችሁ

ላላ ያለ ጉንጉን ሁለት ቦታ ከፍላ የተሰራች ጉብል ከገጠመቻችሁ…
‹‹አትሸኟትም ወይ መሄዷ አይደለም ወይ›› እያሉ ሲዘፍኑ ካንጀቷ ምታለቅስ ሙሽራ ካያችሁ
ፅዋ ተሸክመው እያሸበሸቡ ወይ እየዘመሩ የሚጓዙ ሴቶች
መንገድ ካገኛችሁ
ስንት ጊዜ ሆናችሁ?

በድፎ ዳቦና በሚሪንዳ ብቻ ልደቱን የሚያከብር ትንሽ ልጅ ካያችሁ
‹‹በሙሽራ ቀሚስ›› እየፈነደቀች ወዲህ ወዲያ የምትል ትንሽ ልጅ ካያችሁ
በሚያበራ ጫማ- ወይም በ‹‹ኦክስጅን ባግ›› ጓደኛ የሚያቀና ህፃን ልጅ ካያችሁ

ስንት ጊዜ ሆናችሁ?

በውይይት ታክሲ በረድፍ ተቀምጣችሁ ከተጓጓዛችሁ
ለአንዲት ነገር ብቻ መርካቶ ሸመታ ጎራ እንኳን ካላችሁ
አምስት ሳንቲምና ስሙኒ ካያችሁ
እሱ እንኳን ቢጠፋ የአንድ ብር ወረቀት ከኖረ በእጃችሁ

ስንት ጊዜ ሆናችሁ?

በናና የተፈላ ሻይ ፉት ካላችሁ
ሽልጦን ከወዳጅ ከተካፈላችሁ
አሹቅ አነባብሮን መክሰስ ካረጋችሁ
ቤት የተዘጋጀ- የሰነፍ ገብስ ቆሎ ዝግን ካረጋችሁ
ከጎረቤት ጋር ሰብሰብ ብላችሁ ቡና ከጠጣችሁ…

ስንት ጊዜ ሆናችሁ?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *