“And in the end it’s not the years in your life that count; it’s the life in your years.” ~ Abraham Lincoln
___
የብዙዎቻችን ምኞት ረጅም ዓመት መኖር ነው… ብዙ ዕድሜ ማስቆጠር… ትልቁ ምርቃታችን ‘ዕድሜ ይስጥህ’ አይደል?… ‘ዋናው ጤና’ ስንልም ከደሕንነት በላይ በሚያሳስበን ረጅም ዓመት መኖር ላይ ተመስጠን ነው…
___
የኑረት መቆርቆር ቢጠን፣ የደስታ ከረጢት ቢያጥጥ፣ ልብ በበደል ቢጠለሽ፣ ደዌ ከፍቶ ቢያንገሸግሽ… የቀጣዩን ቀን ብርሃን ለማየት መጓጓት ያለ ነው… ‘የምን ተስፋ መቁረጥ’ ይላል ሁሉም… ‘የነገን ማን ያውቃል?’…
___
ወጣት ስንሆን ደግሞ የሁልጊዜነት ምኞታችን ራሱን በሌላ መልክ ይገልፃል… በሁሌአዊነት… ረጅም ዓመት ለመኖር የመፈለጋችንን ያህል ሳናውቀው ወጣትነትን ለማዝለቅ እንፍጨረጨራለን… ስሜቱ እጅግ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ጉልምስናን ዘለን የእርጅናን በር ስናንኳኳም አይለቀንም… ልብህ የወጣትነት ዝማሬዋን አለመተዋ እኮ በጎ ነገር ነው… በእርጅና ውስጥ ያለን ‘እጅ መስጠት’ ለመቋቋም ይረዳሃል… የዕድሜ መግፋት ሥጋት ውርዝናን የሙጥኝ አስብሎህ ሲሆን ግን ይገርማል…
___
ልጅ ወልደው ዘላለማዊነትን መቋደስ የሚሹ አሉ… ታሪክ ሰርተው፣ ዝና ሸምተው፣ በጎ ውለው የመቃብርን የዕድሜ ቁጨት ስንዝር ከጋት ለማሻገር የሚታትሩም አሉ… ማንም ሰው ግን ድርጊቱን ‘ዕድሜ ማርዘሚያ’ ነው ብሎ አያምንም… ውስጡ ግና የስሙን ሕላዌ የማስቀጠል ምኞት ማድፈጧ አይቀርም…
___
“Do not act as if you were going to live ten thousand years. Death hangs over you. While you live, while it is in your power, be good.” ~ Marcus Aurelius
___
ለመኖር የመጓጓታችንን ያህል መኖራችን ዋጋ እንዲኖረው እንተጋ ይሆን?… ከውልደት እስከ ሞት የሚዘረጋው የስብዕናችን ተረክ ሁነኛ ልኩስ ምንድነው?…
___
የሆነ ጊዜ ላይ ደርሰህ ከቤተሰብ እስከ ማሕበረሰብ፣ ከመንደር እስከ ሃገር በሚዘረጋው የኑረት ጎዳና ላይ አሻራህን የሚያሳይ አንዳች እውነት ትፈልጋለህ… እናም እንዲህ ብለህ ትጠይቃለህ – ‘በእኔ መኖር ምክንያት ምን ተቀየረ?’… አበርክቶህ ምንም ያህል ቢሆን በተቀበልከው ኖረህ ስታልፍ ለሌሎች የምታቀብለው ተክቶህ እንዲቀጥል ትሻለህና ‘መዋጮዬ ወዴት አለ?’ ማለትህ አይቀርም…
___
ዛሬ የምትኖረውን ኑሮ እንድትኖር ትናንት ዋጋ የከፈሉ ሰዎች ነበሩ… ለነዚህ ሰዎች ወደኋላ ሄደህ ብድር አትመልስ ይሆናል… ወደፊት ሄዶ ዕዳህን የሚከፍል ስንቅ ማኖር ግን ግዴታህ ነው… አልያማ ሰው ኖሮ ካልጠቀመ ሄዶ እኮ አያጎድልም – ባለዕዳነቱን አይሰርዝም እንጂ… አንዳንዱ ግን ይሙት… ምናልባት መኖሩ የከለላት ጸሐይ ለመድመቅ ዕድል ታገኝ ይሆናል…
___
የመኖር ውሉ በራስ ታዛ መድመቅ ብቻ አይደለም… የሌሎችንም ማገር ማጥበቅ እንጂ… በበጎ ቃል – የታመመ ልብ ትፈውሳለህ፣ የጎበጠ ሞራል ታቀናለህ… በፍቅር ኃይል – ቂም በቀል ትሽራለህ፣ ጥላቻን ትንዳለህ… ሰው ነህና ብዙ የምትሰጠው ይኖርሃል…
___
ብቻ… በራስ ዛቢያ ከጦዙበት እልፍ ዓመት ሌሎችን የቀላቀሉበት ክራሞት፣ ለብቻ ከኖሩት የዕድሜ ብዛት ለትውልድ ያኖሩት ጥቂት ብልሃት የበለጠ ዋጋ አለው…
___
ሞትን ለምን እንደምንፈራ አስበህ ታውቃለህ? – ኖረን ስለማናውቅ ነው!!
___
“Even death is not to be feared by one who has lived wisely.” ~ Gautama Buddha
___
.
.
.
ዛሬም ‘ዕድሜህ ስንት ነው?’ ትሉ ይሆን… ምክርና ወቀሳ የሚያበዛ ሰው ስንት አስርት እንዳስቆጠረ መገመት እየቻላችሁ?… ሃሃ…
___
እንኳንም ተወለድኩ እናንተዬ… ማን ይኖርልኝ ነበር?… እህእ…
___
ፍቅርን ከመስጠት በላይ ዕዳ አይኑርባችሁ!!