( የታሪክ መዋቅር እና ሃሳብ- የቼታን ባጋት ‹‹ዋን ኢንዲያን ገርል›› አንዲት ዘለላ ታሪክ)
ቅዳሜ ስምንት ሰአት ተኩል።
አዲሱን ቤቴን ለማደራጀት የቤት እቃዎች መገዛዛት ከጀመርኩ አንድ አመት ሞላኝ። የቀረኝን የመፅሃፍ መደርደሪያ ለመግዛት በባልደረቦቼ ጥቆማ መሰረት ‹‹ፍሎውለስ ፈርኒቸርስ›› የሚባል ቤት መጥቻለሁ። የሱቁ ስፋት የትየሌለሌ ምርጫውም ብዙ አይነት ነው።
– የእንጨት ይሻልሻል የብረት? አለኝ ቀለብላባው የሽያጭ ሰራተኛ። በራሴ አይቼ ልወስን ብለውም ከገባሁ ጀምሮ እየተከታተለ ይነዘንዘኛል።
– ያለውን አይቼ ልወስን…በራሴ አያለሁ…አልኩት በመታከት።
– አዳዲስ ሞዴሎች አስገብተናል። እዚያ ጋር የምታያቸው ከእንጨት የተሰሩት በቅርብ ከብራዚል የመጡ ናቸው። ንፁህ እንጨት ናቸው። ዋጋቸው ትንሽ ቢወደድም የዘልአለም እቃዎች ናቸው። የብረቶቹ…እነዚያ እዛ ጋር ያሉት የቻይና ናቸው። ዋጋቸው ዝቅ ያለ ነው ግን ጥራታቸውም ምንም አይልም…እኔ የምመክርሽ ግን…
– በናትህ በራሴ ልይ! ሳላስበው ጮህኩበት።
በርግጎ ሄደ።
ኡፍፍፍ!
ረጋ ብዬ ከብራዚል መጡ ወዳላቸው የእንጨት መደርደሪያዎች ሄድኩ። ቀልቤን ወደሳበው ሄጄ መነካካት ስጀምር ከኋላዬ በጣም የማውቀው የወንድ ድምፅ ስሜን ሲጠራ ሰማሁ። ደቤ?
ዞርኩ።
ደቤ ነው።
– እንዴት ነሽ? አለኝ በቆመበት ከላይ እስከታች እያየኝ። እንዴት ነሽ አባባሉ ቅርበታችንን የማይመጥን የሩቅ ሰው ድምፀት ነበረው።
ምናባቱ ቆርጦት ነው መጥቶ አቅፎ የማይሰመኝ?
– ደህና ጋሽ ደቤ….በሹፈት መልክ እየሳቅኩ ተጠጋሁት።
ስጠጋው እንደመጠጋት ወደ ኃላ ሸሸት አለና ሊገባኝ ባልቻለ ምክንያት ለተሰበሰበ ህዝብ የሚያወራ ያህል ጮህ ብሎ
– ምን ልትገዢ መጣሽ እዚህ….?እኛ ለልጆቹ አልጋ መቀየር ፈልገን ልናይ ብለን ነው…ነይ ገኒን እና ልጆቼን ላስተዋውቅሽ…. አለ
አመዴ ጨሰ።
ደቤ እና በግምት አርባ አመት የሚሆናት ደርባባ፣ ቀጭን እና ፀጉረ ረጅም ሴት ከትንሽ ልጅ ጋ ወደኔ እየመጡ ነው። ፡ ከልጁ ከፍ የምታለው ሴት ልጅ አንዱ የሚሸጥ ሶፋ ላይ ቁጭ ብላ ከእጆቿ በእጥፍ የሚበልጥ ስልክ እየጎረጎረች ነው።
እኔስ? እኔ ደግሞ ድንገተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ መቀመቅ እንዲያወርደኝ እየተመኘሁ ነው።
– ፍሬሕይወት! እንዴት ነሽ…? ገነት እባላለሁ አለችኝ ሴትዮዋ እጆችዋን በትህትና ለሰላምታ እየሰጠችኝ።
ከድንጋጤዬ ሳላገግም
– ሃ….ገነት! ፍሬሕይወት እባላለሁ አልኩና ጨበጥኳት
– አውቃለሁ….ደብሽ ብዙ ጊዜ ስላንቺ ያወራል እኮ….አለች…ፈገግታዋ የደግ ሰው ነው።
ሁለት የወለደች የማትመስል፣ ቅርፅዋ የተስተካከለና ተረከዝ አልባ ጫማ ብታደርግም ከገመትኩት በላይ ረጅም ሴት ናት። ጠይም ፊቷ ላይ ትንሽ ድካም ቢታይም መረጋጋትና ደግነት የሰፈነበት ቆንጆ ሴት ናት። ረጅም ግን ሳሳ ያለው ፀጉሯ በየመሃሉ ጥቂት ሽበቶች አሉት። ቢሆንም ግርማ እንጂ እድሜ አልጨመረባትም።
– ይሄ ደግሞ ማርኮን ይባላል…ማርኮን ፍሬሕይወትን ሰላም በላት….አለች ፈገግታዋ ሳይጠፋ።
ማርኮን ሚጢጢ እጆቹን ለሰላምታ ዘረጋልኝ። ልቤ ከልክ በላይ እየመታ ጎንበስ ብዬ እንደ ትልቅ ሰው ጨበጥኩት።
– ያቺ ደግሞ አርሴማ ትባላለች… አለ ደቤ ስልክ ወደምትጎረጉረው ትንሽ ልጅ እያመለከተ። ደምጹ ይንቀጠቀጣል።
አርሴማ ለአመል ቀና አለችና ቀኝ እጇን በቻው ቻው አውለበለበችልኝ። ቁርጥ እናቷን ናት።
– አርሴማ…ሰው እንዲዚህ ነው ሰላም የሚባለው? ነይና ሳሚያት! አለች ገነት ባልገመትኩት የቁጣ ድምፅ።
አርሴማ ፍንጥር ብላ ተነስታ መጣችና እጇን ዘረጋችልኝ።
-ሳሚያት አለች ገነት
አርሴማ ልትስመኝ ስትንጠራራ ጎንበስ ብዬ ሁለት ጊዜ አገላብጬ ሳምኳት።
– ጎበዝ የኔ ልጅ! አለች ገነት።
እሺ…ቀጥሎ ምን ሊሆን ነው በሚል እጆቼን ወደ ኋላ አጣምሬ በግራ መጋባት ቆምኩ። ገነትን ላለማየት ሰፊውን ቤት፣ ልጆችዋን እና አልፎ አልፎ ደቤን አያለሁ። የገነትን አይኖች ሽሽት አንዴ አረንዴውን ሶፋ፣ አንዴ ወድጄው የነበረውን መደረደሪያ፣ አንዴ ቀይ በነጩን ምንጣፍ፣ አንዴ ቅድም እየተቅለበለበ ሲረብሸኝ የነበረውን ልጅ አያለሁ።
ምናለ አሁን መጥቶ ከዚህ ሁኔታ ቢገላግለኝ?
ምን ሰበብ ፈጥሬ እግሬ አውጪኝ ልበል?
– ደቤ የባህርዳር ልጅ እንደሆንሽና ለስራ ብለሽ አዲሳባ እንደመጣሽ ነግሮኝ ነበር…አለች ገነት
– አዎ…ገና አንድ አመቴ ነው ከመጣሁ…አልኩ አሁንም አይኖቿን እየሸሸሁ
– ለበአል ቤት ይዘሃት ና ብለው እሱ ልብ የለው ሳይነግርሽ ቀረ መሰለኝ…እንግዳ ሆነሽ ብቻሽን…..
– አረ ችግር የለም…አልኩ ሳላስጨርሳት።
ወሬያችንን በአጫጭር መልሶች የምደመድመው ላውቃት ስለማልፈልግ ነው። ባጭሩ ተገላግዬ ከዚህ ቤት መፈርጠጥ ስለምፈልግ ነው።
– ነውር ነው አረ…. አለች ገነት
ለምን አትተወኝም?
ደቤን አየሁት። በናትህ ከዚህ ጉድ ገላግለኝ በሚል አይን አየሁት።
– እስካሁን የቤት እቃ እየገዛሽ ነው እንዴ? አለ ነገሬ እንደገባው ሁሉ።
(ቤቴን አብጠርጥረህ የማታውቅ ይመስል እንዲህ አይነት ጥያቄ መጠየቅ አግባብ ነው ደቤ? አግባብ ነው ወይ?)
ጭራሽ ወሬ ይቀጥላል እንዴ? ለራሴ ሚስቱ እና ልጆቹ ፊት ከእሱ ጋር በመቆሜ የጥፋተኝነት ስሜት ጥርስ አውጥቶ ሊበላኝ ነው ጭራሽ ወሬ ይቀጥላል?
– እ…አዎ…ቀስ እያልኩ ነው…ይሄ ግን የመጨረሻ እቃ ነው…ለጊዜው….አልኩ እያየሁት
– ቤትሽ የት አካባቢ ነው….? አለች ገነት ረጅም ፀጉሯን በግራ እጇ ከፊቷ እየመለሰች። የሚያንፀባርቀውን የጋብቻ ቀለበቷን አየሁት። አንደኛው ባለ ትልቅ ፈርጥ፣ ሌላኛው ልሙጥ ግን ሰፊ ወርቅ።
– ሰሚት…ሰሚት ኮንዶሚኒየም ነው ምኖረው አልኩ አይኖቼ ቀለበቷ ላይ ተሰክተው
– እንዴ…?እኛም እኮ ታዲያ አያት ነን ያለነው!
(አውቃለሁ ገነት- አውቃለሁ)
– እንዲህ ቅርብ ለቅርብ ሆነን ነው እስካሁን ያላመጣሃት….?
(ወይዘሮ ገነት….በናትሽ…በፈጠረሽ መልካም ሴት አትሁኚ። በናትሽ መልካም ሴት አትሁኚ!)
– በቃ…ለመስቀል እንዳትቀሪ…ደቤ ነግሬሃለሁ…ለመስቀል ይዘሃት እንድትመጣ…አሪፍ የጉራጌ ክትፎ ትበያለሽ….
(ምንም ማድረግ አይቻልም። የዋህና ደግ ሴት ናት። ምንም ማድረግ አይቻልም)
– ኦኬ….እኛ ጨርሰናል…እዚህ የሚረባ ነገር አላገኘንም….ምሳ ለመብላት እዚህ ቃተኛ ልንሄድ ነበር….አለ ደቤ።
ምጤ ገብቶት ሊገላግለኝ በመዘጋጀቱ እፎይታ ተሰማኝና
– አሪፍ….እኔም ደህና ነገር አላገኘሁም…መሄዴ ነበር ኤኒዌይ…አልኩ ቶሎ ብዬ
– ብቻሽን ነሽ አይደል? አለች ገነት ቆሜ የነበርኩበትን ቦታ በአይኗ እያሰሰች
(አዎ..ብቻዬን ነኝ። ብቸኛ ነኝ ገነት)
– አዎ…ግን ቅዳሜ አይደል…ወደቤት ሄጄ ቤት ማፅዳት ምናምን አለብኝ…አልኩ ደቤን እያየሁ
– ውይ በቃ ምሳ አብረን እንብላና ትሄጃለሻ? እ? ያ ምስኪን ፈገግታዋ ፊቷ ላይ ተመልሶ ተሳለ።
ወደ ላይ ሊለኝ ፈለገ።
(ደቤ- አረ ከዚህ ጉድ አውጣኝ በናትህ?)
– አይ…ፕሮግራም ካላት ትሂድ ገኒ…አለ ድምጹ የሱ አይመስልም
– የምን ፕሮግራም? ቤት ማፅዳት? ነይ…ምሳ በልተን ትሄጃለሽ…እንሸኝሻለን በዛውም….አለች ገነት ልጆችዋን በግራ እና በቀኝ ይዛ።
ወሰነች ማለት ነው? ድምፅዋ ውስጥ ሰለዚህ ጉዳይ ከዚህ በላይ አልወያይም አይነት…ቅድም አርሴማን ‹‹ነይ ሰላም በያት›› ያለችበት አይነት ትእዛዝ ነበረበት። በአንድ ጊዜ ለስላሳም ጠንካራም የሆነችው እንዴት ነው?
ምርጫ እንደሌለው ሰው ከኋላዋ ሱክ ሱክ እያልኩ መከተል ጀመርኩ። ደቤ ካጠገቤ ይራመዳል። በሚስቱ እና በልጆቹ እና በእኛ መካከል ያለው ክፍተት ሰው አያስገባም። ቢሆንም ድምፄን ዝቅ አድርጌ ፣ በሹክሹክታ እንዲህ አልኩት
– ደቤ…በማርያም…የሆነ ሰበብ ፍጠርና ጥላችሁኝ ሂዱ…ከሚስትህና ልጆችህ ጋር ምሳ መብላት አልፈልግም
(ይቀጥላል)