ዝምታ ጥሩ የሚሆንበት ጊዜ አለ፤ ክፉም የሚሆንበት ጊዜ አለ። ዝምታን እንደየሁኔታው ማከናወን ከብልህ ሰው ይጠበቃል። ዝምታህ ለከት ይኖረው ዘንድ ማስተዋል ይፈልጋል። በሆነ ባልሆነው ከመዘባረቅ፣ በማይመለከትህ በሌሎች ሰዎች ግላዊ ጉዳይ ከመቀባጠር ዝም ማለት የተሻለ ነው። ዝምታን ወርቅ ማድረግ የሚችሉት የዝምታ ቅኔነትን በአግባቡ የፈቱና የተረዱ ብቻ ናቸው። ሆኖም ግን ሌሎችንም አንተንም እየገደሉ ዝም ማለት፣ ነፃነትን እየደፈሩ ዝም ማለት፣ የመኖር መብትህን ሲደፈጥጡ ዝም ማለት፣ ያለጥፋትህ ሲያስሩህ ዝም ማለት ወገኖቸህንም ራስህንም ለግፈኞች አሳልፈህ መስጠት ነው።
በአንዲት ሐገር ፍርድ ሲጓደል፣ ሕገወጥነት ሲፋፋም፣ አድሏዊነት ሲከር፣ አምባገነንነት ሲነግስ፣ እኩልነት ቦታ ሲያጣ፣ ፍትሐዊነት ተሽቀንጥሮ ሲጣል ዝም ማለት ከጨቋኞች ጋር አብሮ መቆም ነው። የሌሎችን እንግልትና ስቃይ፤ ጭቆና እና እስር እኔ ጋር አልደረሰም ብለህ እጅህን አፍህ ላይ ከጫንክ ዝምታህ ሌሎችንም ያጠፋል፤ አንተንም ይደመስስሃል። ነግ በእኔ አለማለት ነገ ጥቃቱ አንተ ራስህ ላይ እንዲደርስ ከአጥቂዎች ጋር መተባበር ነው። የጎረቤትህ ቤት ሲቃጠል ቆሞ ማየት አንተን ከመቃጠል አያድንህም። ቃጠሎው አንድ ቀን ጊዜውን ጠብቆ አንተም ጋር መድረሱ አይቀርምና።
ማርቲን ሉተር ኪንግ በነበረበት ዘመን በታላቋ አሜሪካ እኩልነት ይሰፍን ዘንድ ታላቅ ትግል አድርጓል። የነጮች የበላይነትና የጥቁሮች የበታችነት ያከትም ዘንድ በቀርጠኝነት በሃሳቡ ተፋልሟል። ኢፍትሐዊነትን በመቃወም፣ ሕገወጥ ስራዎችን በማውገዝ የፊት ለፊት የሃሳብ ተቃውሞውን በተለያየ ጊዜ አንስቷል። ከነዚህም ውስጥ ተጠቃሽ ከሆኑት አባባሎቹ መካከል በፈረንጆቹ አቆጣጠር መጋቢት 1965 ዓ.ም ላይ ለደጋፊዎቹ የተናገረው ነው። አባባሉም፡-
‹‹ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ዝምታን የመረጥን ቀን ሕይወታችን ያበቃል። (‘our lives begin to end the day we become silent about things that matter.’)››
ሲል አጉል ዝምታችን አጉል እንዳያደርገን አስጠንቅቋል።
አዎ! ለሌሎች መጮህ ለራስም መጮህ ነው። ስለሠላም መናገር፣ ስለፍትህ መጮህ፣ በህገ አምላክ ማለት ታላቅ ነገር ነው። አንደኛው ገፊ ሌላኛው ተገፊ ሲሆን ዝም ማለት ከሰውነት መውጣት ነው። ጨቋኞችን የሚፈጥር ስርዓት ሲዘረጋ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ መሆን ለጨቋኙ የልብ ልብ መስጠት ነው። ሰውነቱን ያስቀደመ ሰው የየትም ዓለም ይሁን ብሄር፤ ጎጥ ይሁን መንደር ለማንም ሰው ይቆማል። በሰውነቱ ብቻ ለተገፋ ሰው፣ ለተጨቆነ ሰው፣ ለተፈናቀለና ለተሰደደ ሰው፣ ያለአግባብ በእስር ቤት ለሚማቅቅ ሰው መወገንና ጥብቅና መቆም ታላቅነት ነው። ነግ በእኔ በሚል ግፈኞች በርትተው መላውን የሰው ልጅ አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ሰውነቱን ያስቀደመ ሰው ዝም አይልም።
በብሽሽቅ ፖለቲካ ናላው የዞረ ሰው በሌሎች ስቃይ ይደሰታል። በብሔር ፖለቲካ ልቦናው የተጠናገረ ሰው በተረኝነቱ ይፎክራል። በጎጥና መንደር የጠበበ ሰው አስፍቶ ማሰብ ይሳነዋል። በሌሎች መጎሳቆልና መጨቆን፤ መገደልና መሰደድ ደስ የሚለው ሰው ካለ ሰውነቱን ያልተረዳና ከሰብዓዊነት ነፍሱ ያፈነገጠ ነው። በሌሎች ቁስል ላይ እንጨት ለመስደድ የሚጣደፍ ሰው ሰውነቱን የዘነጋ ነው።
ወዳጄ ሆይ… እኔም አንተም ሰው እንሁን! በሰውነታችን ለሰው ሁሉ ጥብቅና እንቁም። ድምጽ ላጡ ድምጽ እንሁንላቸው። ለመናገር ጊዜ ላጡት እንጩህላቸው። ለጭቁኖቹ ዝምታችንን ሰብረን አለንላችሁ እንበላቸው። ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለሰላም፣ ለነፃነት እንወግን የዕለቱ መልዕክት ነው!
ሰው መሆን ከሁሉ ይልቃል!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ይባርክ!
ቸር ሰውነት!
___________________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ማግሠኞ ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.
2 Comments
በጣም ጥሩ ትምህርት ነው በርታ የስነልቦና ጥንካሬ ይሰጠናል!
ምርጥ ሰው፡፡ ሰው አያሳጣን!!!!