የአንድ ወዳጄ የ”እንኳን ለፀሎተ ሃሙስ አደረሳችሁ” መልዕክት Leonardo Da Vinci የተባለው ስነ ጥበበኛ ‘The Last Supper’ ብሎ ለዓለም ባበረከተው ዝነኛ የጥበብ ስራው ዙሪያ ይችን አጭር መጣጥፍ እንድፅፍ ገፋፍቶኛል።
ዳ ቬንቺ ይህንን ኢየሱስ እና ደቀ መዛሙርቱ በአንድነት ማዕድ ላይ የታዩባት የመጨረሻዋን ዕለት የሚያሳየውን የጥበብ ስራውን ሲጀምረው የ 43 ዓመት ጎልማሳ ነበር።
ስዕሉን ለመጨረስ ከሁለት ዓመት በላይ ፈጅቶበታል።
ይህ ስዕል ተወዳጅ ያደረገው በሚያስተላልፈው መልዕክት እና ቁም ነገሩ ነው። ብዙ ሰው ይህ ስዕል ሸራ ላይ የተሳለ ይመስለዋል። ዳሩ ግን ይህ ስዕል የተሳለው ግድግዳ ላይ ነው። የስዕሉ መጠን 460 ሳ.ሜ. በ 880 ሳ.ሜ .ላይ ያረፈ ሆኖ ጣሊያን ሚላን ውስጥ በሚገኘው ቅድስት ማሪያም (Santa Maria) ካቴድራል ውስጥ በአንደኛው ከፍል ግድግዳ ላይ ይገኛል።
ስዕሉ በዮሓንስ ወንጌል 13 ፡ 21 ላይ በተፃፈው ዕውነታ ላይ ተመስርቶ የተሰራ እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማማሉ።
ኢየሱስ “ከእናንተ መካከል አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ በተናገረ ጊዜ በወቅቱ የደቀ መዛሙርቱን ስሜት ለማሳየት ሊዮናርዶ የተጠበበትን ይህንን ስዕል ለመረዳት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የመፅሐፍ ቅዱስን ዕውቀት ይጠይቃል
***ስዕሉ ከሚያስተላልፋቸው ቁምነገሮች መካከል ተከታዮቹን እናገኛለን—-
ደቀ መዛሙርቱ ሦስት ሦስት ሆነው 4 ቡድኖችን መስርተዋል።
ከአራቱ ቡድኖች መካከል የሁለቱን ቡድኖች ስዕላዊ መልዕክት ስንመለከት …
👉–የጴጥሮስ የዮሓንስ እና የአስቆረቱ ይሁዳ ቡድን
ኢየሱስ ‘ ከመካከላችሁ አንዱ ይክደኛል’ ሲል
ይሁዳ ዐቅዱ የተነቃበት ስለመሰለው ደንግጦ ወደ ሗላ ተለጥጦ ተቀምጧል። በእጁ ቦርሳ ይዟል ። ምናልባት የተቀበለውን ዲናሮች ለማሳየት ተፈልጎ ሊሆን ይችላል። ወይ ደግሞ ይሁዳ የደቀ መዛሙርቱ ገንዘብ ያዥ (Treasurer) ስለነበር ያንን ለማሳየትም ይሆናል።
ይሁዳ ክንዱን የተደገፈ ብቸኛ ሰው ሆኖ የጨው መያዣውን (Salt cellar),የነካ ይመስላል። ጭንቅላቱም ከሌሎቹ ዝቅ ብሎ ይታያል።መልዕክቱም ብዙ ጊዜ ያዘነ ወይ ያፈረ ሰው አጠገቡ በተገኘ ቁስ ላይ ሙሉ ክብደቱን በክንዱ አማካኝነት ያሳርፋል። በቅርብ ምስራቅ አገሮች የስነ ቃል አባባል ‘To betray the salt’ (ጨውን መክዳት) ማለት መሪህን መክዳት ማለት ነው።
ጴጥሮስ ተናዷል በእጁም ቢላዋ ይዟል። ኢየሱስ በጌተ ሰማኒ እያለ ጴጥሮስ የቆረጠውን ጆሮ ያስታውሰናል። ወደ ዮሓንስም ተጠግቷል ። ከሁሉም ደቀ መዛሙርት መካከል በኢየሱስ ዘንድ የሚወደድ ተብሎ የተጠቀሰው ዮሓንስ በመሆኑ ጴጥሮስ የካሃዲውን ማንነት ከኢየሱስ ጠይቆ እንዲነግረው የፈለገ ይመስላል።
👉—ሌላኛው ቡድን የቶማስ የፊሊፖስ እና የጄምስ ቡድን ነው።
ቶማስ አዝኗል ጣቱንም ወደ ላይ ቀስሯል። የጌታን ትንሳኤ ለማብሰር ይመስላል።
ጄምስ ግራ ተጋብቷል ። ማብራሪያ የፈለገ ይመስላል።
— ምስሉ ላይ ዝቅ ብላችሁ ከጠረጴዛው ስር ስታዩ የእየሱስ ክርስቶስ እግሮች ተነባብረዋል ። ልክ ሲሰቀል እንደሆኑት ማለት ነው
ወዘቸ
የስዕሉ አስደማሚ መልዕክት
1—እያንዳንዱ ቡድን ሦስት አባላት አሉት
2— አየሱስን ስታስተውሉ ራሱን ችሎ በ Triangle (ሦስት መዓዘን ) ቅርፅ ተቀምጧል።
3—–ከኢየሱስ ጀርባ የሚታዩት የክፍሉ መስኮቶች ብዛታቸው
ሶስት ነው።
ሁሉም ስላሴን ይገልፃሉ።
መልካም በዓል
(በ2011ዓ.ም ልክ በዛሬዋ ቀን የተፃፈ ነው)