Tidarfelagi.com

Finite and Infinite games

አንድ “James Carse” የሚባል ሼባ “Finite and Infinite games” በሚል ርዕስ የፃፈውን ፀዴ መፅሃፍ ሰሞኑን እያነበብኩ ነው። የሚያነሳቸው ሃሳቦች እና ዓለምን የሚያይበት መነፅር ደስ ይላል!
ገና መፅህፉን ስትጀምረው ምን ይላል መሰለህ?
እዚህች ዓለም ላይ ጦርነትም በለው፣ ስፖርትም በለው፣ ህይወትም በለው፣ የፍቅር ግንኙነትም በለው፣ ቢዝነስም በለው፣ ፖለቲካም በለው፣ ስራም በለው በሁለት ጨዋታዎች ላይ የተመሰረተ ነው።
አንደኛው “Finite games” ወይም “ማብቂያ ያለው ጨዋታ” ሲሆን ሰዎች፣ ቡድኖች ወይም ሃገራት ይሄንን ጨዋታ የሚጫወቱት ለማሸነፍ ነው። በዚህ ጨዋታ፣ ውድድር፣ ፍልሚያ ወይም ጦርነት ውስጥ የተገደበ የመጋጠሚያ ሜዳ እና የተወሰነ ግዜ አለ። ለምሳሌ የእግር ጓስ ጨዋታ ውስጥ አንዱ ቡድን 11 ሆኖ ሌላውን “X” የሚባል ቡድንን ይገጥማል። ጨዋታው የሚታወቁ ህጎች አሉት፣ መደበኛ የመጫወቻ ሰዓታቸው ተወስኖለታል፣ አሸናፊውም መጨረሻ ላይ ይታወቃል።
በዚህ ጨዋታ ውስጥ ለምሳሌ ጦርነት ከሆነ ሁለቱ ተጋጣሚዎች በውስጠ ታዋቂነት የሚያከብሯቸው ህጎች ይኖሯቸዋል። ጦርነቱ ከየት ተጀምሮ የት እንደሚያልቅ ይታወቃል፣ ሁለቱም ተጋጣሚዎች የታወቀ ድንበር/ወሰን አላቸው።

በድሮ ጦርነቶች ወቅት ሁለት ሃገራት/ቡድኖች ሲፋለሙ “…አንተም አለኝ የምትለውን ትጥቅ እና ወታደሮች ይዘህ ና፣ እኔም የራሴን ይዤ እመጣለሁ! ከዛም ሚያዝያ 26 ከሰዓት በኃላ ጦርነቱን እንጀምራለን! ከተሸነፍን እንገዛለን፣ እንገብራለን! ካሸነፍናችሁ ደግሞ እንደዛው! ታድያ በጦርነቱ ወቅት ህፃናትን መግደል ወይም የተማረከን ማሰቃየት የተከለከለ ነው!…” ተባብለው ይስማማሉ! በዚህ ጨዋታ ውስጥ ግዜ፣ ድንበር እና የመጨረሻ ግብ(ዓላማ) አሉ!
ጨዋታውን የሚጫወቱት ወይም የሚዋጉት ሁለቱ ቡድኖች የተፃፈ ባይሆንም የሚስማሙበት እና ሁለቱም የሚያከብሯቸው ህጎች አሏቸው!
ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ “Infinite games” ወይም “ማለቂያ የሌለው ጨዋታ” ይባላል! በዚህ ጨዋታ ውስጥ ሁለቱም ቡድኖች ጦርነቱ/ጨዋታው እንዲያበቃ ወይም እንዲገደብ አይፈልጉም። ልክ ጨዋታው ወደ መገባደድ ሲደርስ ከሁለት አንዱ ግዜ ገዝቶ ጨዋታውን/ጦርነቱን ያራዝመዋል!
ይሄኛው ጨዋታ ውስብስብ ነው፣ አሸናፊ እና ተሸናፊ የለውም፣ መቼ እንደሚያልቅ አይታወቅም፣ ሁለቱም ተፋላሚዎች ወይ ደግሞ ከሁለቱ አንዱ ጦርነቱ/ጨዋታው ማለቂያ እንዲኖረው አይፈልግም። ህግ የሚባል ነገር አይሰራም! በዚህ ጨዋታ ውስጥ ሁለቱ ተፋላሚ ቡድኖች ከራሳቸው በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችን/ቡድኖችን ወይም ሃገራትን ስበው ያስገባሉ። አንደኛው ተፋላሚ እንዳበቃለት ወይም ዋጋ እንደሌለው እየተረዳ በመጣ ቁጥር ጦርነቱን/ጨዋታውን ወጥሮ መጫወት ይጀምራል! የሱ ህልውና በጨዋታው መቀጠል ላይ የተመሰረተ ነውና!
ማሳያ አንድ!
በአሜሪካ እና በራሽያ መካከል የነበረው “Cold war” ወይም “ቀዝቃዛው ጦርነት” እንደ “infinite games” ሊወሰድ ይችላል። አሸናፊም ተሸናፊም የለውም! አበቃ ስትል ቀጥሏል! የትኛው ቡድን ምን እንደሚፈልግ በግልፅ አይታወቅም። ጨዋታው በቀጠለ ቁጥር ሁለቱም ተፋላሚዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ይመጣሉ፣ የማን ጡንቻ ትልቅ እንደሆነ ለሌሎች ለማሳየት ይጋጋጣሉ። አሁን ላይ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ፍልሚያ “Cold war” የሚል ስያሜ አይሰጠው እንጂ ሽኩቻው፣ ጡንቻ ማሳየቱ እና እርስ በእርስ ጣልቃ መገባባቱ እንደቀጠለ ነው፣ ለወደፊትም ይቀጥላል! ምክንያቱም “infinite game” ውስጥ ናቸው።
ማሳያ ሁለት!
ብዙ ግዜ ችግር የሚፈጠረው አንዱ ተፋላሚ “Finite games”ን ሲጫወት ሌላኛው ተፋላሚ ደግሞ “infinite games” መጫወት ከመረጠ ነው። ምክንያቱም “finite games”ን የሚጫወተው ተፋላሚ የሚጫወተው ለማሸነፍ (winner) ለመሆን ሲሆን “infinite games” የሚጫወተው ተፋላሚ ደግሞ ለመኖር እና ለህልውናው ሲል ነው። ለሱ ጨዋታው የ “survival” ጉዳይ ነው!
እ.ኤ.አ 1978 ላይ የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት (የአሁኗ ራሽያ) በወቅቱ የሚችላት የለምና አፍጋኒስታን ውስጥ የተጠነሰሰን መፈንቅለ መንግስት “sponsor” አድርጋ የፈቀደችውን መሪ እና መንግስት ታስቀምጣለች። ነገር ግን ህዝቡ የተቀመጠውን መንግስት አልቀበልም ብሎ በከባዱ አመፀ! ግማሹ ይሄንን መንግስት ለመጣል ተደራጅቶ አማፂ በመሆን እራሱን “Mujahideen” ብሎ ሰይሞ ጫካ ገባ! እነዚህ አማፅያን ሃገራቸው ነው! መውጫ መግቢያውን፣ ጋራ ሸንተረሩን… ብቻ ምን አለፋህ ሁሉንም በደንብ አብጠርጥረው ያውቁታል። የአማፅያኑ ፀብ ከራሽያ ጋር ስለሆነ አሜሪካ ሳትቀር አስታጥቃቸዋለች። እነዚህን አማፅያን ለማሸነፍ ቀናት አይፈጅብኝም በማለት ራሽያ ጦሯን ወደ አፍጋኒስታን አዘመተች። ጦርነቱ በ “finite” እና በ “infinite” ተፋላሚዎች መካከል ይደረግ ጀመር! ሶቭየት ህብረት(ራሽያ) ለማሸነፍ፣ አማፅያኖቹ ደግሞ ለህልውናቸው!
ጌታዬ! በቀናት ውስጥ ጦርነቱን አገባድዳለሁ ብላ ያሰበችው ሶቭየት ህብረት ጦርነቱ የተጀመረ ሰሞን ማሸነፍ ብትችልም አማፅያኑ ቀስ በቀስ እየተጠናከሩባት መጡ!
ብታምንም ባታምን እነዚህ አማፅያን 451 የጦር ጀቶቿን ከአየር ላይ ከሰከሱባት ፣147 ታንኮቿን ከጥቅም ውጪ አደረጉባት፣ 15 ሺህ ወታደሮቿም ሞቱ! ይህ ብቻ ሳይሆን ከ 35 ሺህ በላይ ወታደሮቿ ክፉኛ ቆሰሉ!
በዚህ ውጥንቅጡ በወጣ ጦርነት ወቅት በአፍጋኒስታን በኩል ደግሞ 1 ሚልዮን ሰዎች ሞቱ(አብዛኛዎቹ ንፁሃን ናቸው) ፣ 5 ሚልዮን አፍጋኒስታናዊያን ለስደት ተዳረጉ፣ 3 ሚልዮን የሚሆኑ ደግሞ ቆሰሉ! ከአማፅያኑ ወደ 56 ሺህ ሰዎች ረገፉ! ህፃናት ተራቡ፣ ሴቶች ተደፈሩ፣ መሰረተ ልማት ወደመ! በመጨረሻም ከአስር አመታት እልቂት በኃላ ጦርነቱ አሽናፊም ተሸናፊም ሳይኖረው የሶቭየት ጦር ከአቅሙ በላይ ሆኖበት አፍጋኒስታንን ጥሎ ወጣ! ጦርነቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሶቭየት ህብረት መዳከም እና ኃላም ላይ መበተን አስተዋፅኦን አበረከተ! ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ለአፍጋኒስታን የእርስ በእርስ ጦርነት ቡርቅቅ ያለ በርን ከፈተ።

የ “Vietnam” ጦርነት ወቅት የተፈጠረውም ተመሳሳይ ታሪክ የ “infinite games” እና የ “finite games” ገፅታ ያለው ነው!
እዚህ መፅሃፍ ላይ ከተቀመጡት ታሪኮች በጣም የመሰጠኝን አንድ ሌላ ነገር ላንሳልህ!
በ “finite games” ውስጥ ጦርነት ላይ ሳይቀር ህግ ይሰራል!
ወቅቱ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሚካሄድበት ግዜ ነው! አንደኛው ጎራ ጃፓን፣ ጀርመን እና ጣልያንን አሰባጥሯል! ሁለተኛው ጎራ ደግሞ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ራሽያ እና አሜሪካን ይዟል! ጌታዬ! ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማለት ከ 100 ሚልዮን በላይ ወታደሮች የተሳተፉበት፣ የሰው ልጅ ኒዩክለርን የሚያክል ነገር ታጥቆ ወደ ጦርነት የገሰገሰበት፣ በሰው ልጅ ታሪክ እጅግ አደገኛው እና ከፍተኛ እልቂት የደረሰበት ጦርነት ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን ፋሺስት ጣልያን፣ ናዚ ጀርመን እና የጃፓን ዘውዳዊ አገዛዝ የወደቀበት እና ከ 50 ሚልዮን በላይ ንፁሃን ዜጎች ያለቁበት እጅግ ቀፋፊ ጦርነት ነው።
በዚህ መሃል ጀርመን ውስጥ “Heidelberg” በምትባል ከተማ ውስጥ ከ 600 ዓመታት በላይ የቆየ ዩኒቨርሲቲ አለ። “Heidelberg university” ይባላል! ይቺህ ጥንታዊት ከተማ እና ታሪካዊ ዩኒቨርስቲ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በቦንብ እንዳትደበደብ ተፋላሚዎቹ ተስማምተው እውነትም ሳትደበደብ መትረፍ ችላለች! አሁን ላይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቦንብ ያልነካት ከተማ በመባል እንደጉድ ቱሪስቶች እየጎረፉ ይጎበኟታል።
እንግሊዝ የሚገኘው “Oxford” ከተማ እና ከ 900 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው “Oxford University”ም እንደዚሁ ከ “Hitler” ቦንብ ድብደባ በስምምነት መትረፍ ችሏል!
በተመሳሳይ የፈረንሳይዋ ጥንታዊት ከተማ “Paris” በውስጧ ብዙ ታሪኮችን እና የሚደንቁ ሙዝየሞች ያሉባት በመሆኗ እና በወቅቱ ጦርነቱን ሸሽተው ብዙ ስደተኞች የተጠለሉባት ከተማ ስለነበረች “Hitler” እንደሌሎቹ ከተሞች የቦንብ ናዳን ሳያወርድባት አልፏል!
ምክንያት?
“The game was finite! It had certain rules! It was time bound! It had goals!”
ማጠቃለያ!
በነገራችን ላይ “James Carse” ይህንን መፅሃፍ የፃፈው የዛሬ 35 ዓመት ነው! በወቅቱ መፅሃፉን እምብዛም ትኩረት የሚሰጠው ጠፍቶ በደንብ አልተነበበለትም ነበር! ነገር ግን ከቅርብ ግዜ ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች እንደ አዲስ እየተነበበ ነው።
ጌታዬ! ፀሃፊው “Finite” እና “infinite” ጨዋታዎችን ከህይወት፣ ስራ፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር እያዛመደ አሪፍ እይታን ይሰጥሃልና ብታነበው አትጎዳም! እረፍትህን በሱ አሳልፍ!😀
መልካም ምሽት!🙏 ፅድት ያለች ቅዳሜ ትሁንላችሁ!😀

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *