ሁለቱ ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው
(ክፍል 11 የመጨረሻ ክፍል)
እንደዛ ከደነፋ ከቀናት በኋላ የተመራቂ ተማሪዎች ፓርቲ አዘጋጅተን ዝግጅቱ የነበረው ከተማ ነበር። ልንመረቅ ሁለት ወር ነበር የቀረን። እኔን ብሎ ደግሞኮ ተተራማሽ። መግቢያ ትኬት ምናምን እየሸጥኩ ስተራመስ ከርሜ የፓርቲው ቀን ጠዋት ከጓደኞቼጋ ጫማ ልንገዛ ከተማ ስንወጣ አገኘሁት። ምንም እንዳላደረገ …… እንደዛ እንዳልደነፋ (ማለት ሁኔታውኮ የዛን ቀን ሳይገለው የሚያድር አይመስልም ነበር።)
“እንዴት ነሽ እማ?” አላለም?
“ደህና!” አልኩት ግራ ገብቶኝ። ሁኔታው የሰማሁትን እንድጠራጠር አደረገኝ።
“ዛሬ ፓርቲ አላችሁኣ??”አለኝ ደነገጥኩ። እየተከታተለኝ እንደሆነ ገባኝ ግን ዝግጅቱ የነበረው ማታ ከ2 ሰዓት ጀምሮ ስለነበር ቢያንስ ቺኩን ትቶ አይመጣም ብዬ ተረጋጋሁ።
“ይመችሽ ፈታ በይ!! ይገባሻል!!” ብሎኝ እንደሰላማዊ ሰው ቻው ብሎኝ ሄደ። የምር ግራ ተጋባሁ። ቀልቤ አልተመቸውም። ቢሆንም ሀገር ሰላም ብዬ ቀሽ ቋ ብዬ ፓርቲውጋ ሄድኳ!!
እስከሆነ ሰዓት ድረስ ድንገት ከመጣ ብዬ በር በሩን እያየሁ አልተረጋጋሁም። ልክ ማታ 5 ሰዓት ሲያልፍ ተነፈስኩ። የዳንስ ወለሉ ላይ ከኔ ሌላ ማን አለ አልኳ!! ከአንድ የክፍሌ ልጅ ጋር ቅንጥስ ውልቅ እያልኩ ስደንስ ልጁ ድንገት እንደጅብራ ግትር ቀጥ አለብኝ። ምን ሆኖ ነው ብዬ አይኑን ተከትዬ ያየውን ሳይ ባሌ እየገባ ነበር። (ልጁ ግን ባሌን ያየ ሳይሆን ይሄ ነጩ የበረዶ ድብ ፊቱ ቀጥ ብሎ የቆመበት ነበር የሚመስለው …..እኔ ክው ልበልለት።) እዛ መሃል ግርግር ከተነሳ የተማሪውን ቀልብ እንስብና የተማሪው ምላስ ላይ መክረሜ ነው ብዬ ፈራሁና ቀስ ብዬ እንዳማረብኝ ወደሱ ሶምሶማ (በሂል ሶምሶማ ግን ኢማጅኑልኝማ ) አጠገቡ ስደርስ እጄን ለቀም አድርጎ መራመድ ጀመረ ወደ ውጪ በሩን እስክናልፍ ዝም አልኩት። ምክንያቱም አዳራሽ ውስጥ ኮሽ ካለ ነገር ተበላሽ። ከዛ ልክ ስንወጣ እጄን መንጭቄ ፊን ፊን አልኩ …….. ተረስቶኝ ነበራ!!
“እኔን ለማስቀናት ሆነ ብለሽ ነው እንዲህ የምታደርጊው?” አላለም? የምር የምለው ጠፋኝ?
አንተ ማነኝ ብለህ ነው የምታስበው? ምን ልሁን ነው? አታፍርም ሴት እቤትህ አስተኝተህ ልታስቀኚኝ ስትል? እኔና አንተ ተለያይተኛል። ረስተህ ከሆነ ራስህን አስታውሰው? የትም ከመሄድ ምንም ከማድረግ አትከለክለኝም” እሪሪሪሪ አልኩ (ቆይ ለምስሉ በደንብ እንዲገለፅላችሁ ድመት ዝሆን ፊት ስትውረገረግ ማለት ነው ላየኝ )
አንዴ በቦክስ ሲጠጣኝ ብዙ እስካሁን ስያሜ ያላገኙ ሁላ ከለሮች ታዩኝ። በቃ የሆኑ የቀለሞች ድብልቅ …. ሀምራያዊ ….. ብርቱጓዴ …. ምናምን በስንት እጅ መጫን ቢባል በዘይት በፀሎት ያላወራሁትን ልሳን ሁላ ሳልናገር አልቀረሁም። ጥምልምል ብዬ መሬቱ ላይ ከመውደቄ በፊት ቀለበኝ። የመታኝ አይኔጋ ነበር!! ከዓይኔ ስር የቀለበቱ ፈርጥ ቀዶኝ ስለነበር ደሙ ወደላይ ተፈነጠቀ። አቅፎ ይዞኝ እሪሪሪሪ የፈራሁት አልቀረም አንዳንድ እያለ የተወሰነ ተማሪ ተሰበሰበ። ደግነቱ ያው ውስጥ ሙዚቃ ስለነበረ ሊያጨስ … ሊሳሳም … አየር ሊወስድ … ዜድ ሪፖርት ሊያወጣ …. ምናምን ከወጣው ተማሪ ውጪ ውስጥ አይሰማም። የለበሰው ነጭ ቲሸርት ቀይ ጠቃጠቆ ሰራ ‘እሺ ልቀቃት?’ ‘አልለቅም።’ ዝም ሲሉት ‘እርዱኝ እንጂ እየደማችኮ ነው።!’ አልኮል ሲሰጡት በሁለቱም እጆቹ ወደላይ ተሸክሞኛል እንዴት ያድርግልኝ? ሊያደርጉልኝ ሲሉ ‘አትንኳት እኔ ነኝ ያደማኋት ራሴ ነኝ የማደርግላት!’ የሚያየው ሰው ግራ ገባው።
በልብሱ ደሜን ከፊቴ ላይ ይሞዥቀዋል። በዛ ላይ እንባው ደግሞ እኔን መልሶ ያወራኛል። “እማ እኔኮ እንዲህ ላደርግ አይደለም የመጣሁት የነበረው ምዬ ነበርኮ አልነካትም ብዬ ምዬ ነበርኮ !” ደግሞ በዚህ ሁሉ መሃል መሳምም አለው። ጉንጬን ከነደሜ አንገቴን ይስመዋል። ከሰከንድ በፊት ‘ምንዓይነቱ ነው?’ ሲሉ የነበሩት ‘ምፅ ምፅ ሲያሳዝን’ አላሉም? በዚህ መሃል ማን መጣ ያ ያባለገኝ ልጅ ባልየው ልክ ሲያየው አወቀው መሰለኝ እኔን እንዳይለቅ እኔ ሆንኩበት ዝም እንዳይል እሱ ሆነበት። በቃ ቆንጆ ቲያትር ተፈጠረ።
“አንተ እናትህ ….. አገኝሃለሁ!!” ያኛው ለራሱ አንድ ሁለት ብሏል መደንፋት።
“ማነኝ ነው የምትለው?” የነበረው ተማሪ የተፈጠረው ሳይገባው ያኛውን ይይዛል ይመስለኛል። እኔ ለራሴ ምንም እንዳልል ልሳን ላይ ነኝ የባሌንና የልጁን ድምፅም መለየት እራሱ እየቸገረኝ ነበር። ፖሊስ መጥቶ እኔ ወደሆስፒታል እሱ ወደፖሊስ ጣቢያ ሄድን። አይኔ ስር ስቲች ተደረግኩ። (ይሄ ምልክት አሁንም ድረስ አይኔ ስር አለ። አዳሜ እየገባሽ ፎቶዬን ዙም አድርጊ አሉሽ!)
እና ከዚህ በኋላ ፍቅር ተወለደ ነው የምትዪው? አላችሁኣ? ግድ የላችሁም እንቀጥል። እኔኮ የብዙ ሰው ህይወት የኖርኩ ነው የሚመስለኝ የምላችሁ ለዚህ ነው።
በነገታው ማሚ እኔጋ ስትደውል ስልኬን አላነሳሁላትም አንድ ጓደኛዬጋ ስትደውል የተፈጠረውን ነገረቻት። እኔ መስማቷን እንኳን ከማወቄ ማሚ መጥታለች። ማታ አሳድረውት ፖሊሶቹ ለቀውት ነበር እሱን። ማሚ ቀወጠችው። ሴቶች ጉዳይም አይደለች? ደዋወለች። አሳሰረችው። እኔጋ ስትመጣ ግን ከፍቷት ነው የደረሰችው።
“ምነው?” ስላት
“ባልሽ ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ? “
“ምን አለሽ?” (ምንም ቢል የምገረም ይመስል)
ልጄን ይገድላታል ብላ ስትቀውጠው። “ሞታም ቢሆን ዘግይተሽ ነው የደረስሽውኮ ታዲያ አንቺ አታስጥያትም ማሚ በሷና በኔ መሃከል አትግቢ!” ብሏት ነው የምትብሰከሰከው። ትምህርት ቤት በዶርሜም አካባቢ ሆነ በክላሴ አካባቢ ብቻ እኔ ባለሁበት አቅራቢያ እንዳይገኝ ታገደ እና ከቀንት በኋላ ተለቀቀ። ሁሉም እንደነበረ ቀጠለ። ማሚም ተመለሰች። እኔም ትምህርቴን ቀጠልኩ። ከዛ ልጅጋም እንደነበረ (ምን እንደነበረ መድሃንያለም ይወቀው ) የነበረውን ቀጠልን። የሆነ ቀን ስልክ ደወልኩለት ለልጁ
“ና በናትህ ወክ እናድርግ!” አልኩት ስልኩን እንዳነሳ
“ገምቺ የት እንደሆንኩ?”
“እኔንጃ የት ትሆናለህ? መሽቷልኮ!”
“እቤትሽ ከባልሽ ጋር !” ቀልድም መሰለኝ።
“አንተ በማይቀለድ ነገር አትቀልድ!”
“እግዚአብሄርን የምሬን ነው።” ጠላታችሁ ክው ይበል። (አሁንም እማጅኑልኝ ያባለግኩት ልጅና ባሌን አንድ ቤት።)
“ይገድልሃል!! እየቀለድኩ አይደለም ይገድልሃል!” አልኩት
“እየጠበቅኩት ነው!…. ተፋጠን ነው ዛሬ የምናድረው!! ነገ ጊቢ ስመጣ ደውልልሻለሁ።” ይለኛል እየሳቀ
“እኔ አንተን ብሆን እዛች ቤት አላድርም።”
ስልኩን ዘግቼው ምን ማሰብ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። ምንድነው ሁለቱን አንድ ቤት የሚያሳድራቸው? ወይ አንደኛው አጋች አንደኛው ታጋች ሆነው ካልሆነ በቀደም እኔ እየደማው እናቶቻቸውን በብልግና ሲቀባበሉ የነበሩ ሰዎች አንድ ቤት ማደር? ይሄ በዓለምም የትኛው ልብ ወለድ ውስጥም የለም። ይሄ የተከሰተው እኔ ቤት ብቻ ነው። እንደ ቅዠትም እንደዱካክም እንደመባነንም እንልክፍትም ሲያደርገኝ አደርኩ።
በነገታው እንዳለውም ደወለልኝ። የምናወራው ጉዳይ አለ ብሎኝ ተያይዘን ፀጥ ያለቦታ ሄድን። ከትናንት ወዲያ ነገር ይኸው ራሱ ጉድ ወድጄሻለሁ ብሎኝ ነበርኮ ዛሬ መጥቶ “ከባልሽ ጋር ታረቂ!” ብሎኝ እርፍ!! ለልብወለድነት ሁላ አይሆንም አላልኳችሁም? የእውነት ዞረብኝ! ተጋድለው እሁድ ፖሊስ ፕሮግራም ላይ ቀርቤ “ሁለቱንምኮ እወዳቸው ነበር …. ጌታ ለእኔ ባይላቸው ነው ….. ፎሊስ ምን ታደርገዋለህ? ” ምናምን ብዬ ቃሌን ሰጠሁ ስል አጅሬዎቹ ፍቅር በፍቅር ሆነው አይዞህ ሲባባሉብኝ ነው ያደሩት!
“ማንም ሰው እንዲህ አይወድም ሜሪዬ ግፍ ነው። በስመአብ እኔ እንዲህ ዓይነት ፍቅር አይቼ አላውቅም!! የትኛውም ወንድ ወንድነቱን ውጦ ከሚስቱጋ ያለ ወንድ አስታርቀኝ አይልም። የመጨረሻ ይወድሻል።”
“ሚስቱ አይደለሁም! ሚስትህ አይደለችም ስትለው የነበርከው አንተ አይደለህ እንዴ?”
“ለሱ አሁንም የሚወዳት ሚስቱ ነሽ!! ሜዬ አሁን አንቺን አጥቶ መኖር ምን ማለት እንደሆነ በጣም ተምሯልኮ አንድ እድል ስጪው!” በአንድ ለሊት ሚኒ ባሌን ሆኖ ብቅ አለልኝ። ስለሌላ ሰውም እያወራ ወይም እሱም ሌላ ሰው ነው የመሰለኝ ሳቅኩኝ
“በቀደም መስሎኝ በቦክስ ያነጠፈኝ …..ይታይሃል ? ፊቴ ገና አልጎደለም። ተለውጧል? ቆይ ምን ቢልህ ነው?”
“እንዴ እሱማ በቃ ቀንቶ ነው። ደግሞ የዛን ቀን የመጣው እኔን ሊጣላ እንጂ ካንቺጋ ሊጣላ አልነበረም። ከወንድ ጋር ሲያይሽ ደሙ ፈልቶ ነው በዛ ላይ አንቺ አጋጋልሽ! ” (ወንዶችኮ ግን አትስማሙ።)
“እ……..ሺ?” ደንቆኝ ነው የማየው። “የምልህ ቆይ አንተ በቀደም ወድጄሻለሁ ስትለኝ አልነበር? “
“እግዚአብሄርን ነው የምልሽ እሱ የሚወድሽን እሩቡን አልወድሽም። ደሞ ሀጥያት ነው እንደዛ እየሆነልሽ እያወቅኩ ለራሴ አላዳላም።”
ነግሬአችኋለሁኮ ከኔጋ አብረው ሲያለቅሱ የቆዩ ጓደኞቼ እሱ መጥቶ “እሷ ማለት ለእኔ የህይወቴ ካስማ ብሎ …” እትት ብትት ሲል በግልምጫ የሚያፈርጡኝ ሰው ነኝ። የሚገርመኝ ያጠፋው እሱ ከሆነ ጥፋቱን አያስተባብልም። የሚናገርበት መንገድ ግን በቃ ለመኮነን አይመችም። የተፈጠረውም እንደዛ ነው። በጉልበት የሚሆን ነገር እንደሌለ ሲገባው ቢያንስ የተሻለ ብሎ ያሰበው መንገድ ይመስለኛል ልጁን ጠርቶ ማናገር ነው። ከዛ ያው ጠርቶ አጥምቆ ላከልኝ። ከቺኩጋ ተጣልቶ ትታው ሄዳለች።
ብቻ ለሌቱን ሙሉ ሲባባሉ ያደሩትን ሲነግረኝ እኛም ልናድር ሆነ። የታሸገ ነገር ሰጥቶኝ ተለያየን። ገብቼ ስከፍተው ቀለበቴ ነበር።
እዚህጋ የተሰማኝን ወይም የሚቀጥለውን እርምጃ እንዴት እንደተራመድኩ ምክንያቴን ልፅፍላችሁ የምሬን አሰብኩትኮ። አላውቅም! ምናልባት እዚህኛው ጊዜ ላይ ቡረቃም ህመምም ስለሌለው ይሆናል ትዝ አይለኝም ምን አስቤ እንደነበር። ኤጭ በሉና ተዘጋጁ አንዴ …….
የሆነ ቀን ልንመረቅ አንድ ወር ሲቀረን ይመስለኛል። እሱም የተወሰነ ኮርስ እየቀረው አብሮኝ ተመራቂ ነበር። ብድግ ብዬ ብቻ ቀለበቴን አደረግኩት። ተነስቼ እቤት ሄድኩ። በቃ ሄድኩ አልኩኮ …….
ምንም እንዳልተፈጠረ…… ይቅርታ የለ …… መወቃቀስ የለ ……. ልክ ትናንት ተገናኝተን እንደነበር ሁላ ጨዋታ ጀመርን:: ስገባ ሲያየኝ የነበረው ፈንጠዝያ እንዳለ ሆኖ …… ወላ
“ቺኳ ጎበዝ ናት አንተ ቤቴን አሪፍ አድርጋ ነው የያዘችው!” ሁላ አይነት ወሬ ነበረው። የገዛነውን መሬት እንደሸጠው ነገረኝ ሚስት ሚስት አልሰራራኝም። ይመችህ አልኩት።
“አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው እሱን የወደድሽው ሎቲ የሚያደርግ ወንድ አትወጂም አልነበር?”
(ሲቆይ ጆሮዬን ልበሳልሽ ከወደድሽ ብሎኛልኮ)
“አንተ ግን በጣም ከሳህኮ እህል አታበላህም ነበር እንዴ?” (እኔምኮ ከስቻለሁ ከዛ በላይ የሚከሳ ቀሪ ስጋ ስላልነበረኝ እንጂ)
“በቃ እስክንመረቅ ለምን አብረን አንሆንም?”
“እንዲህኮ ደስ ስንል” ምናምን ተባብለን ወደ ዶርም ተመለስኩ።
ምንም ሳይጨመር ሳይቀነስ በቃ እንዲህ ነው የሆነው። ዶርም ስመለስ ሁሉም ሊበላኝ በጣም የገረመኝ ማሚ ታብዳለች ብዬ ስጠብቃት።
“እንኳን ነገር አበረድሽ ቢያንስ ተረጋግተሽ ተመረቂ! እኔማ በእልህ ከአሁን አሁን የሆነ ነገር አደረጋት ብዬ ሌት ተቀን አምላኬን ስወተውት ነው የማድረው!” አለችኝ። እንደባልና ሚስት ሳይሆን እንደ ፍቅረኞች ነገር ሆንን ….. ያለፀብ አለቀ እና ልንመረቅ አንድ ቀን ሲቀረን አብረን አደርን!!
በነገታው እነማሚ መጡ ልጃችን ልታስመርቀን መጣች። ተመረቅን!! እንደማንኛውም ተመራቂ ተማሪ ፊታችን እስኪገረጣ ፎቶ ስንነሳ ዋልን!! እንዳሰብኩት በማእረግ ባልመረቅም በሚያኮራ ውጤት ተመረቅኩ። በምወዳቸው ሁሉ ተከብቤ ያ የናፈቅኩት ቀን ሆነ!! በሚቀጥለው ቀን ቤተሰቦቼን ሸኝቼ ዶርም ተመለስኩ። ለማንም ምንም ሳልል እቃዬን ሸካክፌ ወደአዲስ አበባ ……… ለማሚ ያለሁበትን ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቅኩ። ብዙም ሳልቆይ የግል ዩንቨርስቲ ማስተማር ስራ ጀመርኩ።
በወሩ ደወልኩለት።
“ማወቅ ስላለብህ ልንገርህ ብዬ ነው። ፍቅርን አርግዣለሁ!” አልኩት። ደስ አለው። እብድ ናት በሉኝ በማርገዜ ደስታዬን ብታዩት። ከእርሱ ውጪ ከሌላ ወንድ ልጅ መውለድ አልፈልግማ!!
“የት ነሽ?” ቦረቀ። “ላግኝሽ? We can fix this eko ልጆቻችንን አብረን እናሳድጋለን አይደል? “
“ልጆቻችንን እናሳድጋለን። እኔና አንተ ግን አንድ ላይ ሆነን አይደለም። ልጅህን መጥተህ እንድታይ ስወልድ አሳውቅሃለሁ። በልጆችህ ህይወት ውስጥ እንደፈለግክ ሁን አባታቸው ነህ። በእኔ ህይወት ውስጥ ግን አይደለም።” አልኩት።
(ከዛስ እንዳትሉ ደግሞ? ከዚህ በኃላ ያለው ልጆቻችንን ያካተተ ነውና ይለፋችሁ:: እኛ ግንhappily divorced ብለን (ብዬ) ዛሬ ላይ ሁለታችንም የራሳችንን ህይወት እየኖርን ነው። ዛሬ ላይ በህይወቴ እጅግ ደስተኛዋ ሴት ነኝ። ፈጣሪ በብዙ ክሶኛል። ስግጥናዬ እንዳለ ነው ዘንድሮም ስወድ ስግጥ እላለሁ )
እና ዛሬ ላይ ለልጆቼ ሳወራላቸው እንዲህ ነው የምላቸው
“እንዳባታችሁ ያፈቀረኝ ወንድ የለም! ወደፊትም አይኖርም። እንዳባታችሁም ደግሞ የጎዳኝ ወንድም የለም። ……. አባታችሁ ጣኦቴ ነበር። በምድር ላይ ትልቁን ስጦታዎቼን እናንተን ሰጥቶኛል። በእናንተ ደግሞ ደስተኛ ሴት አድርጎኛል። መልካም ነገር ብቻ ይግጠመው።”
One Comment
Betam yewededkut ye hiwet tarik…ejishin…lijochishn amlak yibarik