Tidarfelagi.com

ትውስታ ስለ ጀግናው አበበ ቢቂላ

የታሪካዊዎቹ ጥቅምት 10 እና ጥቅምት 11
52ኛ ዓመት እና 56ኛ ዓመት

‹‹ማሞ››
‹‹አቤት አበበ››
‹‹እኔ ሩጫውን አልጨርሰም ላቋርጥ ነው››
‹‹ምን! አዝናለሁ››
‹‹ማሞ አደራህን እንድታሸንፍ፣ ከኛ ማለፍ የለበትም››
‹‹እሺ አቤ››
‹‹አደራ››
ዕለቱ እሑድ ጥቅምት 10 ቀን 1961 ዓ.ም. ከሃምሳ ሁለት ዓመት በፊት ነበር። የሜክሲኮ ኦሊምፒክ የማራቶን ሩጫ የተካሄደበት ቀን። የሮምና የቶኪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን ባለድሉ አበበ ቢቂላ ሦስተኛውን ወርቅ ለማሸነፍ ሲሰለፍ አብረውት ማሞ ወልዴና መርዓዊ ገብሩም ነበሩበት። በውድድሩ ሒደት 17 ኪሎ ሜትርን እንዳለፉ ነበር፣ አበበ ቢቂላ ድንገት ወደ ማሞ ወልዴ ቀርቦ ከላይ የተጠቀሰው ምልልስ ያደረጉት።

ከ41 አገሮች 75 ተወዳዳሪዎች በተሳተፉበት የሜክሲኮ ማራቶን አበበ ቢቂላ ጨምሮ ዐሥራ ስምንቱ ውድድሩን አቋርጠዋል። በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር በ9 ሰዓት፣ የሙቀት መጠኑ 23 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሆነበትና በ2,500 ሜትር ከፍታ በተካሄደው የሜክሲኮ ማራቶን ተመሳሳይ ከፍታ ካላት አዲስ አበባ የተጓዘውን ማሞ ወልዴ ሥፍራው አላስቸገረውም። በ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ26 ሰኮንድ በቀዳሚነት በማጠናቀቅ አገሩን ለተከታታይ ሦስት ኦሊምፒኮች የማራቶን ባለድል መሆኗን አብስሯል። መርዓዊ ገብሬም በ6ኛነት አጠናቋል።
‹‹ማራቶን ማራቶን ማራቶን ልዕልቷ
አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ›› ተብሎም ተዘፍኖለታል።

ማሞ ከማራቶን ወርቃዊ ድሉ አንድ ሳምንት አስቀድሞ ጥቅምት 3 ቀን 1961 ዓ.ም. በ10 ሺሕ ሜትር ለጥቂት በኬንያዊው ናፍታሊ ቲሙ ተቀድሞ በሁለተኛነት የብር ሜዳሊያን አጥልቋል። በአንድ ኦሊምፒክ አንድ ኢትዮጵያዊ ወርቅና ብር ሜዳሊያ በማግኘት ማሞ ወልዴ ቀዳሚ ባለታሪክ ሆኗል። በዚሁ 19ኛው ኦሊምፒያድ በ400 ሜትር ሦስት ማጣሪያዎችን በ3ኛና በ4ኛነት ያለፈው ተገኝ በዛብህ በፍጻሜው በ45.4 ሰከንድ 6ኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ባለዲፕሎም ሆኗል። በኦሊምፒክ ታሪክ በአጭር ርቀት የተሸለ ውጤት ያመጣ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ሆኗል።

ጥቅምት 11

ከሃምሳ ስድስት ዓመት በፊት ረቡዕ ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. በተከናወነው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር፣ አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ የማራቶን ድሉን ያጣጣመበትና ወርቅ ያጠለቀበት ነበር። ማራቶኑን በ2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11.2 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመፈጸም የኦሊምፒኩን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ክብረ ወሰን ሰብሯል።
በዚህን ጊዜ ነበር ታላቁ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ስፖርት እንዲሁም የኦሊምፒክ መሪ ይድነቃቸው ተሰማ፣
‹‹እንደ በረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ
ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ›› ብለው የተቀኙለት።
የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሙዚቀኞች እነ ጥላሁን ገሠሠም፡
‹‹በጣም ደስ ብሎናል ምኞታችን ሞላ
አሸንፎ መጣ አበበ ቢቂላ፣
በጥቅምት 11 በሩጫው ገበያ
አቤ ይዞት መጣ የወርቁን ሜዳሊያ›› የሚለውን ለአበበ ቢቂላ ከዘፈኑለት 56 ዓመት ሞላው።
💚💛❤

ምንጭ:- ሪፖርተር ጋዜጣ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *