ሐዲስ አለማየሁ የበዛብህ እና የጉዱ ካሳ ቅልቅል ናቸው። በዛብህ የተማሪነታቸው ጉዱ ካሳ የአዋቂነታቸው። በሚቀጥሉት ሁለት ታሪኮች በሐዲስ አለማየሁ ነፍስ ውስጥ ስናጮልቅ ጉዱ ካሳንና በዛብህን እናገኛለን!
፨፨፨
ያንድ ሃገር ሕዝቦቹ በሙሉ ያብዱና ንጉሡ ብቻ ጤነኛ ነበር። ህዝቡ ግን ወጥቶ ንጉሡ አበዱ እያሉ ይጮሁ ነበር። ንጉሱ ግራ ገባው፤ ልብሱን አውልቆ ተመሳሰላቸው። አውቆ የአበደ መሰለ️።
ካሳ ዳምጤ አይመሳሰልም። አለም ሁሉ ቢያብድ ብቻውን ጤነኛ ሆኖ የመኖር ብቃት አለው። ትንሹ የዲማ አለም ለፊታውራሪ መሸሻ ቢሰግድ አብሮ አያጎነብስም። በአማርኛ ስነፅሁፍ ውስጥ እንደ ካሳ ዳምጤ አብረቅራቂ ገፀባህሪ የለም።
ታድያ ካሳ ዳምጤ ሙሉ ለሙሉ ፈጠራ አይደለም። ካሳ ዳምጤ ሃዲስ አለማየሁ ናቸው። በራሳቸው ላይ ተመስርተው ነው የፃፉት። ሃዲስ አለማየሁ ድንቅ ደራሲ ብቻ ሳይሆኑ ድንቅ ሰው ናቸው።
ሃዲስ አለማየሁ ኃይለሥላሴ ከሚያከብሯቸው ጥቂት ባለሥልጣኖቻቸው አንዱ ናቸው።መንጌም ካልገደላቸው ጥቂት የሃይለስላሴ ባለሥልጣናት አንዱ ናቸው።
ሲበዛ ብልህ ናቸው። ኃይለሥላሴ አስተዳደራቸውን ካላስተካከሉ አብዮት መምጣቱ እንደማይቀር ቀድመው ተንብየዋል። መተንበይ ብቻ ሳይሆን “ኢትዮጵያ ምን አይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?” የሚል ረቂቅ አዘጋጅተው ነበር። ሰሚ ጆሮ አላገኙም በአፄው ዘመን።ደርግ እራሱ የተጠቀመው የሳቸውን ሃሳብ ነው።
ለሃገር በጣም ያስባሉ። የሥልጣን ፍላጎት የላቸውም። ለዝና ለሃብት አይጎመዡም። ለማንም አያጎነብሱም፤ አያጎበድዱም። ወገንተኝነታቸው ለእውነት ብቻ ነው። What a personality!!! ሐዲስ አለማየሁ የእውኑ አለም ግዙፍ ስብእና!!
፨፨፨
ፍቅር እስከ መቃብር
ሁለት ወጣት ኢትዮጵያውያን ከሃገራቸው ብዙ ርቀት እየሩሳሌም ላይ ተገናኙ። ወጣቱ ሃገራቸውን በዲፕሎማትነት ሊያገለግሉ በ1937 በእየሩሳሌም ከትመው ነበር። በግዜው እየሩሳሌም በእንግሊዝ ግዛት አስተዳደር ስር ነበረች። ወጣቱም በዛ የኢትዮጵያ ቆንሲል ሆኑ። በቆይታቸው አንዲት ውብ ኢትዮጵያዊት ተዋወቁ።
ኢትዮጵያዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዳ በሁለት አመቷ ወደ እየሩሳሌም መጣች። አያቷ ለመመንኮስ ወደ እየሩሳሌም ሲመጡ ነበር ህፃኗን ይዘው የመጡት። ህፃኗ በእየሩሳሌም በአያቷ መልካም አስተዳደግ ውብ ወጣት ሆነች።
ሁለቱ ወጣቶች ወዲያውኑ ተጋቡ። ምንም እንኳን ፍሬ ለማየት ባይታደሉም ደስተኛ እና የሚያስቀኑ ጥንዶች ነበሩ።
ሁለቱ ባለትዳሮች በባልየው ስራ ምክንያት አውሮፓ እና አሜሪካ በሚዘዋወሩበት ወቅት እንኳን ተለያይተው አያውቁም። በ1954 ግን ኃያሉ ሞት ለያቸው። ወይዘሮዋ በህመም አረፉ። አርፈው አስከሬናቸው አያታቸው ወደ አሉበት ቅድስት እየሩሳሌም ባለቤታቸው ወስደው በጌቴሰማኒ የመጨረሻው እንዲሆን አደረጉ፡፡
ጎልማሳው ብርቱ ሃዘን ገባቸው። በአዲስአበባ የሚገኘውን መኖሪያ ቤታቸውን በባለቤታቸው ስም ለተሰየመ በአዲስአበባ ከተማ ምክር ቤት ለሚተዳደር የልጆች ማሳደጊያ በስጦታ ሰጡ።
ጎልማሳው ዳግመኛ አላገቡም። አርባ አመት በብቸኝነት ኖረው በ1995 አረፉ።
ባለታሪኮቹ ሃዲስ አለማየሁ እና ክበበ―ጸሐይ በላይ ነበሩ። ፍቅራቸውም እስከ መቃብር ነበር!