ከእኔ በፊት ሁለት ሚስት አግብቶ እንደነበር ሳላውቅ አይደለም ያገባሁት። አውቅ ነበር። ለሁለቱም ሚስቶቹ ልክ ከእኔ ጋር እንዳደረገው የሀብት ውርስ ኮንትራት አስፈርሟቸው እንደነበርም አልደበቀኝም ነበር። በፍቅሩ ነሁልዬ ከእኔ በፊት የነበረው ህይወቱ ገሀነም እሳት ጭስ ሳይሸተኝ ቀርቶም አይደለም። ወይም ፍቅሬ አቅሉን አስቶት በአበባና በስጦታ አንቆጥቁጦኝ ሚዛናዊነቴን አስቶኝም በፍፁም አይደለም። ገና ሳልገባበትም ትዳሬ ሲኦል ሊሆን እንደሚችል የሚንቀለቀል ፍም እሳት ነበልባሉ ሽው ብሎኛል።
ገና ሳንጋባ «ሴት ይሰለቸኛል። ለዛ ነው ትዳር በተወሰነ አመት ኮንትራት መሆን አለበት ብዬ የማምነው።»
«ኮንትራት ያበጀኸውኮ ለትዳሩ ሳይሆን ለውርስ ነው ታዲያ!»
«ያው ናቸው። ለሴት ልጅ ትዳር እና ገንዘብ ያው ናቸው። ቤተሰቦቿ ገና ሽማግሌ ስትልኪ የሚጠይቁት ምንድነው? ልጃችንን በምን ያስተዳድራታል? እሷስ ገና ስታውቅሽ የምትጠይቅሽ ምንድነው? ስራህ ምንድነው? ከስንት አንድ ሴት ናት ማነህ? ምን ትወዳለህ? ምን ትጠላለህ? ምን ትፈራለህ? ብላ የምትጠይቅሽ? ቤተሰቦቿ እሷን በምን እንደምታስተዳድሪ ይሰልሉሻል። እሷ ደግሞ ልጇን በምን እንደምታስተዳድሪላት ትሰልልሻለች። ይኸው ነው።»
ወላፈን አንድ ያዙልኝ!
«መመለስ የማትፈልገው ጥያቄ ከሆነ ይቅርታ አድርግልኝና በምን ተጣላችሁ ከበፊት ሚስቶችህ ጋር?»
«ኸረ ደስ ብሎኝ መልስልሻለሁ። የመጀመሪያዋ ልጅ ካልወለድን ብላ ስትነዘንዘኝ ……» ሳይጨርሰው ከአፉ ቀምቼ
«ልጅ አትፈልግም?»
«በፍፁም!»
«እስከመቼውም እስከመቼውም?»
«እስከመቼውም! እዚህ ብስብስ ዓለም ላይ ያለፈቃዱ ለምን አመጣዋለሁ? ለምን ሰው የመሆን አበሳን ያለፈቃዱ አስጨልጠዋለሁ? እስቲ አንድ ሰው randomly ጠይቂ! ሰው ሆነህ አሁን እየኖርክ ያለኸውን ህይወት ከመኖርና ባለቤቷ ጭኗ ላይ አስቀምጣ እያሻሸቻት የምታስተኛት ነገ እና ትላንት ህይወቷን የማያመሳቅሉባት ድመት ሆኖ ከመፈጠር ምርጫ ቢኖርህ የቱን ትመርጥ ነበር በይው!»
ወላፈን ሁለት ያዙልኝ!!
«ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት የህይወት ፈተና እንደማይገጥመው ሁላ ድመትም ሆኖ ባለቤቷ በማማሰያና በፍልጥ የምታራውጣት ድመት መሆን አለኮ!»
«ማን እድሉን ሰጥቶን መረጥን? እናትና አባቶቻችን ወደዝህች ዓለም መከራ ከሚማግዱት ነፍስ ይልቅ ቅንዝራቸው በልጦባቸው ሲላፉ ያረግዙናል። ደህና ስጦታ የሰጡን ይመስል እልልልል ብለው ውልደት ግርዘት ክርስትና ልደት እያሉ ያከብሩልናል። በይፋ welcome to hell !» እጁን በሰፊው ወደፊቱ እያወናጨፈ ዘርግቶ
«ህይወትን እና ተፈጥሮን እንዲህ እንድትጠላ ያደረገህ ምንድነው?»
«ያለውን እውነታ እንጂ ስለግሌ አይደለም ያወራሁት! እና ደግሞ ብዙ personal የሆነ ጥያቄ የምትጠይቀኝ ሴት አትመቸኝም።»
እዚህኛው ላይ ለህይወት ካለው ጨለምተኛ እና መራራ ምልከታ በላይ የጭንቅላቱ ጤንነት ሊያሳስበኝ አይገባም ነበር? መቼም ቢሆን አልፌ እንድረዳው የማይፈቅድልኝ ጥቁር አለት በልቡ ደብቆ እንደሚኖር ሳላገባውም እዚህ ቀን ላይ አውቃለሁ።
ወላፈን ሶስት ቁጠሩ !!
«ፍቅር የሚባል ነገር የለም! ሰዎች ለምግባራቸው የተቀደሰ ስም ሰጥተው ራሳቸውን ሲነሸግሉ ግንኙነታቸውን የሚያሞካሹበት መጠሪያ ነው። በዚህ ዓለም ላይ ያሉ ግንኙነቶች ወይ ሀላፊነነት ናቸው ወይ መጠቃቀም ናቸው። ሀላፊነቴን እየተወጣሁ ነው ላለማለት ወይም ስለሚጠቅመኝ ነው አብሬው ያለሁት ከማለት <ፍቅር> ብለን እንቀባባዋለን።»
«በምንም ጥቅም ላይ ያልተመሰረተ ወይም በሃላፊነት ግዳጅ ያልታጠረ ግንኑነት አለኮ!»
«ምሳሌ ጥቀሺ!»
«ለምሳሌ ጓደኝነት! የቤተሰብ ትስስር፣ እንዴ ሁሉም የተቃራኒ ፆታ ፍቅርም በጥቅም ላይ የተመሰረተ አይደለም። የአምላክ ፍቅርስ?»
«አምላክን ተይው! …… (ቡም! 💣🔥🔥🔥ይሄ ወላፈን ብቻ አልነበረም! ፍንዳታ ነበር! ፍንጥርጣሪው ለዓመታት የሚባጅ መርዝ የነበረው ፍንዳታ!) ፈጣሪን እንኳን ተይው! ጓደኝነት በስሜት መጠቃቀም ላይ ነው መሰረቱ! ጓደኛዬ የምትዪው ሰው ወይ ስሜትሽን የሚረዳ፣ በሃሳብ የምትግባቢው፣ ጥሩ ልብ ያለው፣ ወይም ግማሽ አንቺን ውስጡ ያገኘሽበት name it እንደጓደኛ የሚያቆራኝሽን ነገር? ያን ኳሊቲ ውስጡ ባታገኚ ጓደኛሽ ይሆን ነበር? አንድ በስሜት የምትመጋገቢው ነገር እየፈለግሽ ባትቆራኚ ኖሮ ዓለም በሙሉ ጓደኛሽ ይሆን ነበር። አየሽ የስሜት መጠቃቀም ነው። ቤተሰብ ላልሽው ……. ዌል እናትና አባት ግዴታም ሀላፊነትም ነው። የእናት ፍቅር ብለው እንደተኣምር ይሞዝቁለታል። ግዴታዋን ነው የተወጣችውኮ። እንደውም በጣም abuse ሲያደርጉሽ የራሳቸው ንብረት እንጂ የራስሽ ሀሳብና ፍላጎት ያለሽ ሙሉ ሰው አትመስያቸውም! አድገሽ ራስሽን ችለሽ ሁላ ወይ እነሱን የመደጎም እና የማኖር ግዴታ ያለብሽ ፣ ሳትፈልጊ ወልደው ስላሳደጉሽ ውለታ የዋሉልሽ እና ያን ውለታ የመመለስ ግዴታ ያለብሽ ያስመስሉታል።
(ይሄን ሲያወራ ምን ዓይነት ልጅነት ይሆን የነበረው? እንዴት ያለ ቤተሰብ ነበር ያሳደገው? ራሴን ጠይቃለሁ። ሴት ልጅ ስትጠይቀው ከማይወዳቸው ጥያቄዎች ዋነኛው ስለሆነ አልጠይቅም!) …………..ልጅ (እዚህጋ ቆየት ብሎ ቀጠለ)
እስኪ ልጅሽን ሀላፊነትሽን አትወጪና አስርቢው አስጠሚውና ቀጥቅጪው እና ከዛም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አብሮሽ ይቆይ እንደሆነ እዪ (በፌዝ ፈገግ አለ) ባገኘው የመጀመሪያ አጋጣሚ ካንቺ ለማምለጥ ነው የሚፈረጥጠው (የመጨረሻው ገለፃ የሚያስበው ብቻ ሳይሆን የኖረው ዓይነት ስሜት ነበረው)……… ተቃራኒ ፆታውን እንኳን አንሸነጋገል። እድለኛ ከሆንሽ በጎደኝነት መሃል ያለው የስሜት መጠቃቀም ሲደመር ወሲባዊ ስሜት መጠቃቀም ሲደመር የቁስ መጠቃቀም!! ብቻውን ፍቅር የሚባል ነገር የለም!!»
ሌሎች ብዙ የወደፊቱ የትዳር ህይወቴን ሲኦልነት የሚገልፁ <ማሳያ ትኩሳቶች> እያወቅኩ እና ፍንጣሪውን እየተለማመድኩ ሰንብቼ ነው ያገባሁት። ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች እና ሌሎች ፍርፋሪ አባሪ ምክንያቶች ነበሩኝ። አንዱ ከሌላኛው ጋር በቀጥታም በጓሮም ይጋመዳል። ከዋንኞቹ አንደኛው እንደአብዛኛዋ በማህበረሰቡ <ሳታገባ እድሜዋ አለፈ> የሚባልበትን በህግ ያልተፃፈ የእድሜ ቁጥር እንዳለፈች ሴት ለቤተሰብ እና ለጎረቤት ፣ ለማህበረሰብ፣ ለጓደኛ ……… ወላ ገና ለሚወለደው ልጄ ስል ነው ያገባሁት!
እንደዛ እኮ ነው! ለእነሱ ነው የምናገባላቸው! ከዛ ኑሮውን እኛ እንኖራለን እነሱ ደግሞ ገሚሱ አገባች ብለው ይደሰታሉ። (አንቺ ደስተኛ ሆነሽ ይሁን አይሁን ግድ የማይለው ይበዛል) የተቀረው ገሚሱ ወደሌላኛዋ ተረኛ እጩ ቋሚ ቀር ምላሱንና ፊቱን ያዞራል!! …. እስክታገባላቸው በምላስም በጥያቄም በአሽሙርም ያነፍሯታል። ስታገባላቸው … ይህችኛዋንም አጨብጭበው ይድሩና ደሞ ወደ ቀጣይዋ….. የእኔን ግን ላብራራልሽ …