ቀድማው ትነቃለች፡፡
ምርጫ ስለሌላት ሆዷ እየተንቦጫቦጨ ጥላው ትሄዳለች፡፡
ስራ ቦታ ስትሆን ‹‹ልጄ ልጅነቱን ሳላጣጥመው እያደገብኝ ነው›› ብላ ትብሰለሰላለች፡፡
ከዳዴ ወደ እርምጃ በተሸጋገረበት ቀን ለመስክ ስራ አሶሳ ነበረች፡፡
‹‹እሺ›› የምትለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንደበቱ ሲያወጣ በረጅም ስብሰባ ተጠምዳ ነበር፡፡
ሞግዚቱን ‹‹ማማ›› ብሎ የጠራት ቀን ሽንት ቤት ተደብቃ አልቅሳለች፡፡
ሞግዚቱ እረፍት የወጣች እለት ቀኑን ሙሉ ሲነጫነጭ በመዋሉ መጣሁ ብሎ ያስፈራራትን እንባዋን በመከራ ገትታለች፡፡
በእሷ ተከፍቶና አልቅሶ ሞግዚቱ ጉያ ገብቶ ሲጽናና በሃዘን ተኮማትራለች፡፡
ሞልቶላት ቤቷ ስትውል የልጇ ኮልታፋ አንደበት ስለማይገባት አሁንም አሁንም ሞግዚቲቱን ‹‹ምንድነው የሚለኝ?›› ብላ ትጠይቃለች፡፡
ሞግዚቷ ‹‹ቼ ፈረሴ አጫውቺኝ ነው የሚልሽ››
‹‹ምግብ አልፈልግም ነው ያለው›› እያለች ታስተረጉማለች፡፡
ቤት ቤት ስትሆን ኢምፖርትድ አፕልና ብርቱካኑን ቃኘት፣ ውዱን የሳልመን አሳና ብሉ ቤሪ አየት፣ ቦታ ጠቧቸው አንዱ በአንዱ ላይ የተከመሩትን መጫወቻዎቹን፣ ቁምሳጥን ሞልቶ የተዝረከረከውን ልብስና ጫማውን ጎብኘት ስታደርግ ፣
‹‹ጥሩ እናት እኮ ነኝ….ጠንክሬ እየሰራሁ ለልጄ እኔ ያልነበረኝን ነገር ሁሉ እየሰጠሁት ነው›› ብላ ትጽናናለች፡፡
እሷን ተክተው ፍቅር እንዲለግሱት ትመኝ ይመስል ገንዘብ የሚገዛውን ቁሳቁስ ሁሉ ሸምታ ትገባለች፡፡
አብዛኛውን ምሽት ልጇ ከተኛ በኋላ በስራና በመንገድ ደክማ ቤቷ እንደገባች ግን ጉንጩን ደጋግማ ትስምና እንዲህ ብላ ታስባለች፡፡
ልጄ አደግ ሲል የትኛውን ያስታውስ ይሆን?
ለእኔ ማለቴን ትቼ ምንም እንዳይጎድልበት የከፈልኩለትን መስዋእትነት ወይስ ከአጠገቡ በመራቄ ያጎደልኩበትን የእናትነት ፍቅር?
