መልካም ጋብቻ

(ከማታ ማታ መጽሐፌ (2012 ዓ.ም.)

ከጓደኞቼ ማኅደርና እስከዳር ጋር፣ ዘናጭ ካፌ ቁጭ ብለን ውድ ማኪያቶ እየጠጣን ነበር፡፡ ማኪያቶው አሪፍ፣ ጨዋታው ደማቅ ነበር፡፡ መርዶዬን እስኪነግሩኝ… “ናሆምና ማርታ ሊጋቡ ነው” እስኪሉኝ፡፡

እንደሰማሁ በድንጋጤ ምራቄ ከአፌ አለቀ፡፡ በማኪያቶ የሞቀ ሰውነቴ በአንድ ጊዜ ቀዘቀዘ፡፡ ሰበባ’ ሰበብ ድርድሬ፣ራሴን አመመኝ ራይድ ጥሩልኝ ብዬ ካሰብኩት በጣም ቀድሜ ተለየኋቸውና ቤቴ ገባሁ፡፡

ናሆም ሊያገባ ነው?

የኔ ናሆም ሊያገባ ነው?

ያውም ያቺን አብረን እንፎግራት የነበረች ዝንጅብል ቅርጽ ማርታ?

ሶፋዬ ላይ ቁጭ ብዬ ጥፍሬንም ነገርም ሳኝክ፤ ቅናት ሳመነዥክ፣ ልጆቼ ከባለቤቴ ጋር ከትምህርት ቤት መጡ፡፡

“እንዴት ዋልሽ…? ፊትሽ ጠቋቆረ ምነው?” አለኝ ባሌ፡፡ ጉንጮቼን በእጆቹ እየዳበሰ፡፡ መልካሙ የአሥር ዓመት ባሌ፣ እንኳን ፊቴ በሐዘን ሲከስል፣ ለአፍታ ከፈገግታ ሲለይ ይጨንቀዋል፡፡

“ደህና ነኝ… ትንሽ ደክሞኝ ነው… ራስ ምታት ነገር አለኝ…”. ቶሎ መለስኩለት፡፡

ላግኘው?

አላገኘውም፡፡

ስለምን ላወራው አገኘዋለሁ? ምንስ እለዋለሁ? ብቻውን ሊያገኘኝ ፈርቶ እየተንቦቀቦቀ ያቺን ማማሰያ እግር ይዞብኝ ቢመጣስ?

አላገኘውም፡፡

ደብዳቤ እጽፍለታለሁ፡፡

ምን ብዬ? ማግባትንህን ሰማሁ… ምነው ደውለህ ሳትነግረኝ… ቢሆንም እንኳን ደስ ያለህ… መልካም ትዳር… ማርታንም እንዴት ነሽ? እንኳን ደስ አለሽ በልልኝ… እኔና ሶል ከልጆቹ ጋር ዱባይ ለእረፍት ልንሄድ ነው… ለሁለት ሳምንት…. ኀምሳ አራት ኪሎ ገባሁ እኮ… በጣም ተሸናቅጬያለሁ ብታይ… አምሮብኛል… መልካም ትዳር ምናምን ብዬ… ?

ሳሎን ወርጄ ሽንጠ ረጅም ወረቀትና እስኪብርቶ ይዤ ወደ መኝታ ቤቴ ተመልሼ ደብዳቤዬን ጀመርኩ፡፡

ወደ ፊት እንጂ ወደኋላ የማላውቅ ጠንካራ ሴት መሆኔን አሳየዋለሁ፡፡

በትዳሬ ፍፁም የረጋሁ፣ መልካም እናትና ፍጹም ደስተኛ ቀጭን ሴት መሆኔን የሚያመላክት ደብዳቤ መጻፍ ጀመርኩ፡፡

“ሰላም ናሆም… እንዴት ነህ? መቼም በዚህ ዘመን በእጄ ደብዳቤ ስጽፍልህ ግር ሳይልህ አልቀረም፡፡ ልታገባ እንደሆነ ስሰማ ደውዬ ከምረብሽህ (መቼም ያው ደስታ ላይ ስለሆንክ) በደብዳቤ ይሻላል ብዬ ነው፡፡ በጣም ደስ ይላል፡፡ ደግሞ ከማርታ ጋር መሆኑ በጣም አሪፍ ነው፡፡ ገና ከድሮ ጀምሮ ትወድህ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ደስ ይላል….

ለምን ደውለህ እንዳልነገርከኝ ሳስብ ግምቴ አንድ ብቻ ሆነ፡፡ ምናልባት ስሜቷ ይጎዳል ብለህ ይሆናል፡፡ ያው ያኔ የነበረኝን ፍቅር አስበህ ምናልባት የኔ ማግባት ሊያማት ስለሚችል አልንገራት ብለህ ነው አይደል?

እንደዚያ ከሆነ በጣም ተሳስተሃል፡፡ ትንሽም አዝኜብሃለሁ፡፡ ትንሽ ክሬዲት ልትሰጠኝ ይገባ ነበር፡፡ የተፈጠረው ሁሉ ከሆነ በኋላ ቢሆንም ይህን ነገር እናቁም ብዬ የወሰንኩት፣ የተለየሁህ እኔ መሆኔን ትረሳለህ መሰለኝ… ወይ ደግሞ በ’ኔ ሕይወት ውስጥ ያለህን ቦታ አጋንነህ ትገምት ይሆናል… ባለትዳር …የልጆች እናት ሆኜ ካንተ ስለተኛሁ… በስሜት ማእበል ተውጬ እወድሃለሁ ብዬ ለሁለት ዓመታት አብሬህ ላይ ታች ስላልኩ፣ በልቤ ውስጥ የተለየ ቦታ እንዳለህ ተሰምቶህ አዝነህልኝ ይሆናል ግን ይሄ ስህተት ነው፡፡

በተደጋጋሚ ነግሬህ ነበር… ቦታህን አመላክቼህ ነበር… አሁን ግን ማግባቴ ልቧን ይሰባብረዋል ብለህ ማሰብህን ስገምት ላስታውስህ ፈለግኩ፡፡

ኖሆም፣ አንተ እኮ ደካማ በነበርኩ ቀናት የሠራሁህ ስሕተት ነህ፡፡ በረጅም የሕይወቴ መጽሐፍ ውስጥ ቢበዛ አንዲት የማትረባ ገጽ ነህ፡፡ ብፈልግ ቡጭቅ

አድርጌ ልጥልህ የምችል፤ ስፈልግ ገንጠጥዬ ላወጣህ የምችል፤ የማትረባ አንዲት መናኛ ገጽ ነህ፡፡ መጽሐፎቹ ባሌና ልጆቼ፣ አብረን የገነባነው ቤትና ሕይወቴ ናቸው፡፡

አሁንም መሽቶ በነጋ፣ ነግቶ በመሸ ቁጥር፣ ስላንተ የማስብ፤ የምቆዝም መስሎ ከተሰማህ በጣም ተሳስተሃል፡፡

ልጆቼን ከትምህርት ቤት ሳመጣ በ’የ ትራፊክ መብራቱ ላይ የመኪና መሪ ይዤ የማይረሳ አሳሳምህን እያሰብኩ የምብሰለሰል፤ ስንቃበጥ የነበረኝን የኀጢአት ደስታ መልሼ መላልሼ እያሰብኩ፣ እምባ ባይኔ ሞልቶ ከኋላዬ የቆሙት መኪኖች በጥሩምባ ሂጂ ብለው እስኪያምባርቁብኝ ድረስ የት እንዳለሁ የምረሳ ከመሰለህ፤ እጅግ ተሳስተሃል፡፡

ዛሬ ድረስ ከባሌ ጋር ፍቅር ስሠራ፣ ስምህ ከአፌ እንዳያመልጠኝ የምታገል፤ ፀሐይ እንዳትወጣ የተመኘሁባቸውን እነዚያ ካንተ ጋር ያደርኩባቸው፣ አ ጭርና ስኳር ስኳር የሚሉ ሌሊቶች እያሰብኩ እንባዬን የማብስ መስሎህ ከሆነ… ናሆም በጣም ተሳስተሃል፡፡

አንተ እኮ ደካማ በነበርኩ ቀናት የሠራሁህ ስሕተት ነህ፡፡ በረጅም የሕይወቴ መጸሐፍ ውስጥ ቢበዛ አንዲት የማትረባ ገጽ ነህ፡፡ ብፈልግ ቡጭቅ አድርጌ ልጥልህ የምችል፣ ስፈልግ ገንጠጥዬ ላወጣህ የምችል የማትረባ አ ንዲት መናኛ ገጽ ነህ፡፡

ጌትነትን አልችል ብሎ የጠገበ ባለትዳር ልቤ ሲዋልል የተራመድኩብህ ሰወርዋራ መንገድ እንጂ፣ አውራ ጎዳናዬ አልነበርክም፡፡ ዋና መንገዴ ሆነህ አታውቅም፡፡

አሁንም አልጋ ውስጥ ገብተን ትንሽዬ የአንሶላ ድንኳን ቀልሰን ብርሃንም ንፋስም ሳናስገባ የምናወራው፣ የምንሳሳመው፣ የምንደባበሰውን ነገር ሁሌ እያሰብኩ ከእንባዬ የምታገል ይመስልህ ይሆናል፡፡

ለልጆቼ በሶ ሳበሰብስ፣ እዚያች ሚጢጢ ግን የምትሞቅ ቤትህ መጥቼ በሶ በቅቤ ስሠራልህ፤ ሁለመናችን በሶ በሶ እየሸተተ የምንተቃቀፈው፣ ሰውነቴ ከሰውነትህ የሚቆላለፈውን እያስታወስኩ የምርበተበትልህ ይመስልህ ይሆናል፡፡ ግን ተሳስተሃል፡፡

አንተ እኮ ድንገተኛ እንቅፋት፣… ጊዜያዊ ፈርማታ እንጂ፤ ዘላቂ ማረፊያዬ

አልነበርክም፡፡ አንተ እኮ ደካማ በነበርኩ ቀናት የሠራሁህ ስሕተት ነህ፡፡ በሙሉ ጊዜ ሕይወቴ ውስጥ የነበርክ የትርፍ ጊዜ ሥራ ነህ፡፡ መሪ ሳይሆን አጃቢ… ዋና ሳይሆን አስተኔ ገጸ ባሕርይ፡፡

በዛሬው ሕይወቴ፣ ስንዝር ቦታ የሌለህ፤ የሕይወት ታሪኬ ውስጥ በእልባት የገባህ፤ በስርዝ ድልዝ ያስወጣሁህ፣ ምራቂ ሰው ነህ፡፡ እስከዛሬ በፌስቡክ፣ በቫይበርና በዋትስ አ ፕ የምንላላካቸውን “ቴክስቶች” እያነበብኩ የምታመም፤ ፎቶህን ከባሌና ልጆቼ በሚስጥር ቆልፌ መታጠቢያ ቤት ገብቼ እያየሁት የማለቅስ፤ በፈገግታህ የምታመም፤ በናፍቆትህ የምፈረካከስ ይመስልህ ከሆነ ተሳስተሃል፡፡

የሁለት ዓመት ወጣ – ገባ ፍቅራችን፣ የድብቅ ስሜት ጡዘታችን፣ የአሥር ዓመት ትዳሬን አፈር ድሜ አስግጦት፤ የሕይወት ትርጉም፣ ጭራና ቀንዱ ጨርሶ እንደጠፋብኝ፣ በየቀኑ ሐዘን እንደ ቱባ ክር እንደሚተረትረኝ የምታስብ ከሆነ በጣም ተሳስተሃል፡፡

አንተ እኮ ስምህ በእርሳስ የተጻፈ የማፍርብህ ትላንቴ እንጂ፣ ዛሬዬ ወይ ነገዬ

አይደለህም፡፡ በአሸዋ ላይ አንጼ ወዲያው ያፈረስኩህ ዛኒጋባ ቤት እንጂ፣ ቋሚ መኖሪያ አይደለህም፡፡ አሻራ አልባ ዱካ እንጂ፣ የማትረሳ ሰው አይደለህም፡፡

ስለዚህ ማርታን ለማግባት ስትወስን በመደወል ፈንታ፣ ብነግራት ትናዳለች፤ ብነግራት ትሰባበራለች፤ ሰርጌ መርዶ ይሆንባታል፤ በሚል ታብየህ ከሆነ ተሳስተሃል፡፡

በልቤ ያለህን ቦታ በድፍረት አጋንነሃል፣ በድፍረት አስፍተሃልና ትንሽም ታሳዝናለህ፡፡ ለማንኛውም ልክ እንደኔ የራሴ የምትለው ሰው ስላገኘህ ደስ ብሎኛል… ናሆም….. እህህ….መልካም ጋብቻ ናሆሜ… እህህ….መልካም ጋብቻ….

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *