ይሄ ሁሉ ሲሆን በጌታ ነን በጌታ ፍቅር ጥላ ስር ሆነን ነው የምንፋቀረውም የምንቧቀሰውም። ቸርች እናስመልካለን። የምሬን የምፀልይለትስ “ጌታ ሆይ ቁጣውን እንዲገታ እርዳው” ብዬ እሱ በተቃራኒው “ጌታ ሆይ ዱላዬን የምትችልበት ፀጋ ስጣት!” እያለ እየፀለየ ይሁን እንጃ አይደለም ተመትቼ ጮክ አድርገው ተናግረውኝ ቤት የማምስ ልጅ ዝም አልኩ ……… ውርድ አልኩ…..
“ትቼለትለሁ የእኔን ጉዳይ ትቼለታለሁ የእኔን ታሪክ
መላ አለው እንዴት እንደሚያደርግ ያውቃል
ዘዴ አለው እንዴት እንደሚያደርግ ያውቃል”
የሚለው የሊሊ መዝሙር እየዘመርኩ ስነፋረቅ አመሻለሁ። ዛሬም ድረስ ስሰማት እንባዬ ይመጣልኮ
ጎበዝ ተማሪ ከመሆን ውጪ ለሌላ ምንም ምርጫ ጭንቅላቴ ዝግ ነው። ገና ትምህርት ቤት እንደገባ ህፃን ቦረቅኩ ሰው በማትስ ይወሰወሳል? በቃ በትምህርት ጠፋሁ …… ከሱ ውጪ ጓደኞች ኖሩኝ። Bilen ቢዬ መጣች …… ሳልነግራት ገባኋት። እሱን እንዴት እንደምወደው ማውራት ከጀመርኩ የሚሰማኝ ሁሉ ጤንነት አይመስለውም። ጓደኞቼን አስተዋወቅኩት ወደዱት። እያደር እየዋለ ግን በአጠገቤ ዝንብ ራሱ ብታልፍ ጾታዋን ማጣራት ጀመረ። እንዴት እንደምወደው እንዴት እንደማይገባው ይነደኛል። ወንድ አይደለም እኔ አይቼው እሱ አይቶኝ ነገር አከተመ። ችግሩ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ነጠላ ማገር በህይወቷ ዝንፍ ያለባት የማልመስል ተጫዋች ነኝና ወንዱም ሴቱም ይቀርበኛል። እቤት ስመጣም ቆንጆ ነገር ይቀርብልኛል። “ቅድም አብሮሽ ሲገለፍጥ የነበረው ልጅ አስተያየቱን አልወደድኩትም ሁለተኛ አብረሽው እንዳላይሽ”
ቆዩኝማ መሆን የነበረበትኮ ተቃራኒው ነው። እኔ ነኝ መቅናት የነበረብኝ። ቁመቱ ሜትር ከ83 ሰውነቱ ገራሚ አይኖቹ ጥርሱ ከንፈሩ (ልጆቼን አይታችሁ መስክሩኣ?) የትም ቦታ ሄደን ሲያወራኮ ሴቶቹ አፉ ውስጥ ሊገቡ ትንሽ ነው የሚቀራቸው ሲቀልድ ሲያምርበት ሲኮሳተር ግርማ ሞገሱ ሲደመጥ (እየቀለድኩ አይደለም! አሁን ይሄንኑ ታሪክ እየነገራችሁ ያለው እሱ ቢሆን ተከርብታችሁ እንዲህ እየወደደሽ ቢቀጠቅጥሽ ምናለበት ቻዪው ነበር የምትሉኝ!! ፍቅርንማ እሱ ያውራት) የትም ብወስደውኮ ኩራቴ ነው:: ሁሉም ሰው ይወደዋል። እሺ በዚህ ላይ ፍቅር ችሎበት ….. በዚህ ላይ ስለምንም ርእስ ቢነሳ በሃሳብ መከራከር ችሎበት…. በዛ ላይ ጉዳዩ ላይ ጉድ አርጎኝ (ከዛኛው እሱ ውጪ ሌላው ነገሩ እኮ በምድር የሌለ ሰው ነው።)
የተለወጠው ነገር ልጄን ለማሚ ሰጥቻት ከመጣሁ በኋላ በጣም ተሰብሬ ስለነበር ድጋሚ እንዳይሰብረኝ ራሱን ይፈራው ነበር። ሲናደድ መማታቱን ትቶ ጥሎኝ ይወጣ ጀመር። እንደመፍትሄ የወሰድነው ያንን ነው። ከዛ ግን ትምህርት ቤት መዋሌ ለኔ ሳቅ ሲጨምርልኝ ለሱ ስጋት ሆነበት። አስተማሪዎቼን የክፍል ተማሪዎችን በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ያውቃቸዋል።
አንድ ቀን የሆነ ርእስ ተሰጥቶን በግሩፕ በተማሪ ፊት ከግሩፑ ሁለት ሰው ወጥቶ present ሊያደርግ አሳይመንት ተሰጠን። ከኛ ግሩፕ እኔና ሙሄ የሚባል ጓደኛዬ ተመረጥን። በደስታ ተቀብለን ተዘጋጀን!! የሚቀርብ ቀን 60 የማይሞላ ተማሪ ፊት ወጥቶ ለማቅረብ ፈራሁ። እኔ ሜሪ ሰው ፊት መቆም ፈራሁ ……. በ10 ዓመቴ በሺዎች ፊት ቆሜ ግጥም ያነበብኩ ልጅ …….. ማንንም ፈርቼ የማላውቅ ልጅ እጄን ሲያልበኝ አገኘሁት …….. የምወደው ነገርኮ በሰዎች ፊት ቆሞ ያን ሁሉ ጆሮ መያዝ ነበር …. የዛን ቀን ፍቅሬን ላለማጉደል ራሴ እየጎደልኩ እንደሆነ ገባኝ። “ደህና ነሽኣ?” ይለኛል ሙሄ መቶ ጊዜ ….. ይግባው አይግባው አላውቅም ” ፈሪ ሆኛለሁ ማለት ነው!” አልኩት
“አንቺ? እኮ አንቺ … በይ አትቀልጂ …” ብሎኝ የሱን ፓርት ቀጠለ
የሆነው ሆነና ጨርሰን ስንወጣ አስተማሪያችን ለባሌ “ሚስትህ በራስ መተማመኗ ምናምን ….” ብሎ አዳንቆ ነግሮታል። ያለፉትን ዓመታት ምርጥ ከሚባሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአንደኛው ስለተማርኩ ጥሩ መሰረት ነበረኝ። …… እና ባልዬ ሊኮራብኝ ሲገባ (የትኛው ሰይጣን ሹክ እንዳለው መድሃንያለም ብቻ ነው የሚያውቀው) አቴንሽን ፍለጋ ሆነ ብዬ ሰበብ እየፈለግኩ ተማሪ ፊት እንደምቆም ነገረኝ። ከተፈጠረው ነገር ጋር ተደማምሮልኝ የዛን ቀን ፀቡን እኔው ጀመርኩት። ልክ ከሆነ ነገር እንደነቃ ሰው ሁሉም ነገር ዛሬ እንደተገለጠልኝ ነገር። ….. የተዋበች ቡጢዬን ቀምሼ ባበጠ ፊቴ ትምህርት ቤት ገባሁ። ወድቄ ነው አልኩ። … ለመጀመሪያ ጊዜ ባሌ መታኝ ብዬ ለሰው ተናገርኩ። ለቢዬ !! ምሳ እየበላን ብቻችንን ቁጭ ብለን ነገርኳት። እቤት ስመጣ ግን ከፋኝ!! እሱን ማንም በዛ መንገድ እንዲያውቅብኝ አልፈልግማ!! ማንም እሱን ከዛ ማንም ከሚያውቀው ተወዳጅ ስብዕናው እንዲያወርደው አልፈልግም!!
አንዳንዴ ምልክት ኖሮኝ ትምህርት ቤት እገባለሁ:: ሙሄ “እሺ ዛሬስ ምንላይ ወድቀሽ ነው?” ይለኛል:: ቢዬ ታውቃለች:: …. የልጄ ናፍቆት ሊያስነቅለኝ ይደርሳል:: እንዲያም ሆኖ ዓመቱ አለቀ::
ማትሪክ ሰኞ ልፈተን ቅዳሜ እሱ ታመመ። ቅዳሜ ለሊት ሀኪም ቤት ሄድን። እጄ ላይ ያለው ገንዘብ 1000 ብር አይሞላም። ለሊት 6 ሰዓት ገደማ ነው። አሁኑኑ መተኛት አለበት ሰርጀሪ መደረግ አለበት ተባልኩ። የሆስፒታሉ በረንዳ ላይ በቂጤ ዘጭ ብዬ ተቀመጥኩ።
“ለምን? ምን አድርጊ ነው የምትለኝ? ለምንድነው አንዱን በአንዱ የምትጭንብኝ? እላይ ሆነህ ሙድ ነው የምትይዝብኝኣ? ለመሆኑ ትሰማኛለህ ግን?” ከሰው ጋር እንደሚያወራ ሰው ከእግዜሩ ጋር ጭቅጭቅ ጀመርኩ። ገንዘብ ልጠይቀው የምችለው ብቸኛ ሰው በዛ ሰዓት ቢዬ ብቻ ነበረች። ደወልኩላት!! ከእናቷ ጋር ሲመጡ ሳያቸው ላለማልቀስ ታገልኩ። ተኛ። ሆስፒታል እያደርኩ ፈተናዬን ተፈተንኩ።
ከሆስፒታል ሲወጣ ብር ስላልነበረኝ እናቴ ለሰርጌ የሰጠችኝን ወርቆች ሸጬ የሚደረገውን ሁሉ አደረግኩ። ሳድግ እንዳየሁት ሰው ከታመመ በግ ይታረዳል:: ወግ ነው ብዬ በግ ገዝቼ አሳረድኩ:: (እራሴው እንባባባባ ብል ይሻለኝ ነበር) ሲሻለው በቀረኝ ብር ለልጄ የሆነ የሆነ ነገር ገዝቼ ልጄጋ ሄድኩ። አንዳንዴ ምኑም አይገባኝም። ወርቆቼን እንደሸጥኳቸው ሲያውቅ እኔ ለሱ ብዬ የምሄደው ርቀት ሳይሆን የታየው “ለምን አልነገርሽኝም” ብሎ መቀወጥ ነበር። ደከመኝ። ልቤ ዛለ …… የምር ደከመኝ። ….. ምን ባደርግ ደስተኛ እንደሚሆን አላውቅም:: ያስቆጣዋል ብዬ የማስበው ነገር ምንም ሳይመስለው ያልፋል:: ጭራሽ ያልጠበቅኩት ነገር እብድ ያደርገዋል:: ክረምቱን ልጄጋ ከሱ ተለይቼ አሳለፍኩ። እዛ እያለሁ ውጤት መጣ።
ውጤቴ መጣ። ከትምህርት ቤቱ ከፍተኛውን ውጤት አምጥቼ አለፍኩ። ቅብርር ያለ ውጤት አምጥቼ። ውጤቴን ያየልኝ እሱ ነበር። በስልክ እየነገረኝ አላስጨረስኩትም ሳቅና ለቅሶዬ ተደባለቀብኝ። ነፍስ ዘራሁ ነገር….. አለሁኝ አልኩ…. ለእናቴ ስነግራት እልልልልልልል አለች። አባቴ ውጤቴን ሲሰማ አቀፈኝ። በቃ ዝም ብሎ ለደቂቃዎች አቀፈኝ። ምንም ሳይናገር ሁሉንም አለኝ። …. ልጄ ይህቺ ናት ያለ መሰለኝ…… ኮራሁብሽ ያለ መሰለኝ….. ከዛ በኃላ ምንም ዳገት የሚወጣ አቅም እንዳለኝ አመንኩ:: …. ትችያለሽ አልኳት ራሴን!!!
የዛኔ ልክ ውጤት ሲመጣ ነበር የትምህርት ምርጫችንን የምንሞላው።
“አባ በቃ ሙላልኝ እና አስገባ!” አልኩት ምክንያቱም የትና ምን እንደምፈልግ ያውቀዋል። እኔን የሚያውቀኝ በሙሉ ያውቃል ህግ መማር እንደምፈልግ። ከተማ የመጀመሪያ ምርጫ ሀዋሳ ሁለተኛ አዲስ አበባ
ወደ እሱጋ ተመልሼ መጣሁ:: አቃቤ ህግ ነሽ ወንጀለኛ መቅጫ ብቻ ሊጠቅመኝ ይችላል ብዬ የማስበውን በሙሉ መፅሃፍ ከላይብረሪ እያወጣሁ ማንበብ ሆነ ስራዬ እዚህ ወቅት ላይ ምንም ተጨማሪ ፈጣሪዬን የምጠይቀው ነገር አልነበረኝም።
አዳራሽ ውስጥ ተቀምጠን በፕላዝማ ምድባችን ሲነገር ስሜ ብቅ አለ አርባምንጭ ዩንቨርስቲ FBE Faculty …… ተማሪው አብሮኝ “WHAT?” አለ…. ዓይኔን ማመን አቃተኝ…
እግሬ እንዴት እየረገጠልኝ እቤት እንደደረስኩ አላውቅም። ለመጀመሪያ ጊዜ እሱ ከልቤ ግምስ ሲል ታወቀኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ልለየው እንደምችል አሰብኩ። በቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞልቶ ከጠበበው ልቤ ሲቀነስ ታወቀኝ።
“እንኳን ደስ ያለህ እዚሁ ነው የደረሰኝ” አልኩት ማታ ሲመጣ
“እማ እርቀሽኝ እንድትሄጂ ስላልፈለግኩ ነው። ….ስለማፈቅርሽ አንቺን ላለማጣት …….” እንባው ለመጀመሪያ ጊዜ የማንም ሰው እንባ ዓይነት ሆነብኝ።
“አላሳዝንህም? ቢያንስ ህግ እንደምማር አምኜ ያን ሁላ መፅሃፍ በፍቅር ሳነብ ‘እማ ተይ የሞላሁልሽ ሌላ ነገር ነው እንዲህ አትልፊ አትለኝም?’ ልቤ እንደሚሰበር መገመት ከባድ ነበር? አላሳዝንህም? የ5ተኛ ክፍል አስተማሪዬ እንኳንኮ ህግ መማር እንደምፈልግ ያውቃል። እንዴት አንተ ከአይንህ እንዳታጣኝ ህልሜን ትቀማኛለህ? እስቲ ራስህን ጠይቅ የእውነት ትወደኛለህ? እኔስ ራሴን ነጥቀኸኝ… ህልሜን ነጥቀኸኝ … ከዛም ዝም ብዬ ማፍቀሬን ልቀጥል?”