Tidarfelagi.com

ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው!!

ግርምታችሁን እና እርግማናችሁን ከማዥጎድጎዳችሁ በፊት ትንፋሽ እየሰበሰባችሁ ከመጀመሪያው ልጀምርላችሁና ሁለቱንም ላስተዋውቃችሁ።
የመጀመሪያው ባሌ “ባለቤቴ ነው ተዋወቂው!” ብዬ ያስተዋወቅኳት ጓደኛዬ “ወየው በፈጣሪ ባልሽ ሲያምር አጣብሺኝ!” ያለችለት ውብ ነው።
የገዛ እናቴ ልክ እንደጠበስኩት ስታውቅ “ውይ ልጄ የልጁን ህይወት አታበልሺ አጉል ታደርጊዋለሽ !ይቅርብሽ በሞቴ!!” ብላ የለመነችለት ስነስርዓታም ነው።

የቤተክርስቲያናችን ፓስተር ጠርቶኝ “ሜሪ ሰይጣን አንቺን ተጠቅሞ ልጁን ከጌታ ቤት ሊያስኮበልል እየተጋ ነው።” ያለለት የቸርቻችን ዓይን የሆነ አገልጋይ ነው።
እሱስ ብትሉ? መጀመሪያ እጄን የጨበጠ ቀን “ሜሪ እባላለሁ!” ስለው
“ሜሪ ….ሜሪ ? ” ብሎ ሰይጣንን ራሱን የጨበጠ ይመስል እንዴት እጄን አሽቀንጥሮ እንደጣለው። የጨበጠኝን እጁን ልብሱ ላይ ሁላ ቢጠርገው ደስ የሚለው ይመስለኛል።
እሱ ለከተማውም ለቸርቹም አዲስ ነበር። እኔ ደግሞ ከቸርቹም ከወሬውም ገለል ለማለት ክረምት ስለነበር ሁለት ወር አዲስአበባ ከርሜ መመለሴ ነው። ጫፉን እንኳን ያልነካሁትን ቀድሞ የነበረውን ፓስተር በዝሙት ጣለችው ተብዬ ተወንጅዬ መሆኑ ነው። ቢችሉ እንደጌታ ቢሰቅሉኝ ደስ ይላቸው ነበር። ያው ጫፉን አልነካሁትም አልኳችሁ እንጂ ከንፈሩን ነክቼዋለሁ። ከንፈርና ጫፍ ይለያያል አይደል? እኮ!! 🤷🏽🤷🏽 ነገሩ ውስብስብ ሆኖ አይደለም ሲያወሳስቡት እንጂ። ስለፓስተሩ በኃላ እመለስላችኋለሁ።

ስለዋናዬ ላውጋችሁ። ክረምቱን ጨርሼ እንደተመለስኩ እቤት ከምላሳቸው ላይ የሱን ስም እንዴት ላውርደው? ቸርች ውስጥ የማይገባበት የለውም። ይሰብካል ….. ይዘምራል(ውብ ድምፅ ድክመቴ ነውኮ ደግሞ) …….. ፒያኖ ይጫወታል……. ወላ ኤሌክትሮኒክስ ነገር ሲበላሽ ይጠጋግናል …….. ቸርቹን ያፀዳል የማያደርገው የለውም። በቃ ምንም ይሁን
እነማሚ ….ቸርች አዲስ የመጣው …. ልጅ እንዲህ ብሎ …. እንዲያ ብሎ …. ሳላየው ብዙ ሰማሁ። የተዋወቅን ቀን ደግሞ እሱም ሳያየኝ ብዙ እንደሰማ ገባኝ። ያው ክፉ ክፉውንም ቢሆን……
ወንድሜ አጠገቡ ነበረ “እህቴ ናትኮ!” ይለዋል
“ሜሪ ያንተ እህት ናት?” አባባሉ ይህቺ አጋንንት እንዴት ብላ ከእናንተ ቤተሰብ ተፈጠረች? እንዴት ነው መልዓክና ሰይጣን ተስማምታችሁ አንድ ቤት የምትኖሩት? አይነት ለዛ ነው። የለመድኩት ነገር ስለሆነ ስቄ ለወንድሜ ምግቡን አቀብዬ ተመለስኩ።
ከዛ በኋላ እኔ አልደረስኩበትም። ስለእውነቱ ጭራሽ በሀሳቤም በልቤም የለም። ለራሴ በአንድ ፓስተር ከንፈር ጦስ ሳቢያ መፅሃፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ክፉ ሴቶች መንፈስ ሁላ ስም (የኤልዛቤል መንፈስ የደሊላ መንፈስ ሲወጋ የሚውለው የሴቶች መንፈስ ብዛት ) እየተጠቀሰልኝ እጅ በመጫን ፀሎት ብዛት ሌላ አገልጋይጋ መድረሻ እጅም እግርም ፍላጎትም የለኝም።

ከወንድሜጋ ሁሌ እሁድ ከቸርች በኋላ እቤት ይመጣሉ። እሱ ማውራት ሲጀምር እቤት አፉን የሚከፍት የለም። ፀጥ ብለው ይሰሙታል። ስለምንም ርእስ ይነሳ ይቀዳል የቸርቹ ወሬ ብዙም ስለማይጥመኝ አልሳተፍም። ድንገት በሆነ ሰበብ ወደሳሎን ብቅ ካልኩ በገዛ ቤቴ ይገላምጠኛል። ወይ በነገር ይተናኮሳል። ቤቴ ነው ብዬ አልፈዋለሁ።
“ቸርች ለምንድነው የማትመጪው?” አለኝ የሆነ ቀን ኮስተር ብሎ ውጪ ተቀምጬ የማነብበት መጥቶ
“ለምንድነው የምመጣው?”
“ለመፀለይ ….. ጌታን ለማምለክ ….. ጌታን ለመፈለግ …. ወንድሞች በህብረት ቢቀመጡ መልካም ነው እነሆም ያማረ ነው!!”
“ዌል ወንድም አይደለሁም እንደምታየው!”
“የምሬን ነው!” አለ ፈገግ ብሎ። ‘ጥርስህኮ ሲያምር በየሱስ ስም! ምን ሆነህ ነው ሁሌ የምትኮሳተረው?’ ልለው ነበር። ያው በደህና አያይብኝም ብዬ ዋጥኩት
“ሲገባኝ ቸርች የምትሄደው ሸክምህን ለማራገፍ ነው። ፈራጅ በየመንገዱ ሞልቷል። ለምን ብዬ ቸርች ሄጄ የፈራጆቼን አይን እያየሁ ራሴን እኮንናለሁ? አምላክ ፍቅር ነው እኔ እስከገባኝ። ፍቅርን ፍለጋ የምሄድበት ቸርች ገና እግሬ ሲረግጥ ዘማዊት ናት ትወገር የሚሉ አይኖች እና እኛ ካንቺ የተሻልን ፃድቃን ነን ብለው የሚመፃደቁ ሰዎች ጋር ተቀላቅዬ ራሴን ለምን አሳንሳለሁ? Am ok where I am now. “
ዝም አለኝ። ሁለታችንም ዝም ከምንል ብዬ ቀጠልኩለት
“ታውቃለህ ያቺ ዘማዊት ሴት መፅሃፍ ቅዱስ ላይ ስትዘሙት አጊንተናት ነው ብለው ወደእየሱስ ያመጧት? ህም ሁሌ የሚገርመኝ ነገር ከሆነኛው ሰውዬጋ ነውኣ ስታመነዝር ያዩዋት? እሱን ‘በል ሱሪህን ታጠቅና አምልጥ ብለውት ነው እሷን ብቻ ይዘዋት የመጡት? ለምን እሷን ብቻ ኮነኗት? ምናልባት ሰውየው ወዳጃቸው ነው? አልያም ክብሩ የማይነካ ስም ያለው ሰው ነው? ለሁለት ባጠፉት ጥፉት እሷ ብቻ እንድትወገር ለምን ተፈለገ?”
ብዙ ዝም አለኝኛ “የሚወራው ግን እውነት ነው?” አለኝ
“አይገርምህም ግን ማንም ሰው እውነት ነው ወይ ብሎ ጠይቆኝኮ አያውቅም! ቤተሰቤን ጨምሮ የተፈጠረውን እንኳን ሳያውቁ ነው ሲወጉ የሚውሉት” ድክም ብሎ ሳቀ
“እውነት ነው ግን?”
“ግማሹ እውነት ነው። እውነት የሆነው ክፍል ‘የሆነ ነገር ነበራቸው’ የሚለው ነው። ‘በሷ ምክንያት ነው ከአገልግሎት የታገደው!’ የሚለውም እውነት ነው። እርግጥ ‘አሳሳተችው’ የተባለውም እውነት ነው ያው የተሳሳተው ምን ድረስ ነው የሚለውን ነው ልክ ያልሆኑት።”
እንደሆነ ተዓምር ያየኛል። …… ፈገግ ይላል። እሱ እንደሚለው ይሄን ቀን ነው ነፍሴን የወደዳት ….
“ፓስተር የመጣ ጊዜ እኔ ዼንጤነቱን እርግፍ አድርጌ ትቼው ነበር። … ማሚ በስንት ጉቦ የሆነ ቀን ይዛኝ ስትመጣ … ሸበላ .. ወጣት … ሲናገር የሚጣፍጥ አዲስ ፖስተር እየሰበከ ነው። ከጏደኞቼጋ ነበር የመጣነው። ተያየን … ‘በየሱስ ስም ይሄ ዼንጤ ብሆን ራሱ ሲኦል ደርሶ መልስ ትኬት ያስቆርጠኛል’ አልኳቸው። ‘በፍፁም አይደረስበትም … ፓስተርኮ ነው!’ ተባባልን። ከዛ በብር አስያዝን … እጠብሰዋለሁ ብዬ!! … ያው አባቢ ፓስተር ስለሆነ መግባባት ጊዜ አልፈጀብኝም። … እንዳልኩትም ጠበስኩት። ችግሩ እሱ የምሩን የጌታ ሰው ነው…. ልክ የደፈርኩት አስመስለው የሚያወሩት (ልክ ልፉ ነገር አስመስለው) … እሱ እወድሻለሁ ካለኝ በኃላ ራሱ ንሰሃ የሚገባ ነው የሚመስለኝ።”
ድክም ብሎ እየሳቀ ይሰማኛል። …. ይኼኛው ዼንጤው እሱ አይደለም። ሰው የሆነው እሱ ነው። ከቤት እየወጡ ቼክ እያደረጉ ስላስቸገሩን ወክ እያደረግን ወሬውን ቀጠልኩለት።

“ከዛማ በቃ … የሆነ ቀን ስሞኝ …. በፀፀት አለንጋ ሲዠለጥ ከረመ። … እኔ ብሬን በላሁ። እሱ አመረረ … ጭራሽ በቅድስና ፍቅራችንን እንድንኖር እንጋባ አለ። … ከዛ እውነቱን ነገርኩት። … መልቀቂያ አስገብቶ ወደአዲስ አበባ መሄዱን ሰማሁ…. ከዛ እዛም እንዳያገለግል መታገዱን ሰማሁ !! ከዛ የማውቀው ታሪክ የለም። … ምን እንዳላቸውም አላውቅም። ብቻ በኔ ምክንያት መሆኑን ነግሯቸዋል!! …. ”

ሳናውቀው ብዙ መንገድ ተጏዝን!! …. ስንመለስ እጁን ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጎ …. እብድ እንደሆንኩ እየነገረኝ ነበር።
“ይቅርታ በጣም! በሰማሁት ልዳኝሽ አይገባም ነበር።” አለኝ እቤት ልንደርስ አካባቢ
“እሺ ይኸው እኔ እውነቱን ነግሬህ የለ? ምንድነው የሰማኸው?”
“ካንቺ በጣም መጠንቀቅ እንዳለብኝ። ካለበለዚያ እንደምታባልጊኝ ” እየሳቀ ነው…
ማሚ በሩጋ ቆማ እየጠበቀችኝ ነው። ….. አስተያየቷ ‘ደሞ በምን አገኘሽው?” አይነት ነው።

ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው!! (ክፍል ሁለት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *