Tidarfelagi.com

ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው!! (ክፍል ሶስት)

 ሁለተኛውን ባሌን እስክተዋወቀው ሰዓት ድረስ ዓለሜ ሁሉ እሱ ነበር (የመጀመሪያው ባሌ) ትምህርቴ …. ትዳሬ …. ፍቅሬ …. ቤተሰቤ … ጓደኛዬ …. ወንድሜ ……. ይሄን ሁሉ ከኋላዬ ትቼ እርሱን መርጫለሁኛ!!
እንዲህ ነበር የሆነው
«ይዘኸኝ ጥፋ!» ያልኩት ቀን ከተማ ይዞኝ ሄዶ ቀለበት ገዛን። ማንም በሌለበት ቸርች ሄድን። ልክ እኔና እሱ ሙሽራ እንደሆንን … የቸርቻችን ፓስተር እያጋቡን እንደሆነ አስመስለን መድረኩ ፊት ቆምን።
“ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን በወደደበት መውደድ በፍፁም ልቤ ልወድሽ በህመምሽ በጤናሽ በማግኘት በማጣት…..” ብሎ ቃል ገባልኝ! በእንባው ቃሉን አተመልኝ።
“ሚስት ለባሏ እንደምትገዛው ልገዛልህ! በጤናም በህመምህ በማግኘት በማጣትህ ልኖርልህ …..” ብዬ ቃል ገባሁለት። የደስታ እንባዬን እያነባሁ ቃሌን አተምኩለት።
‘Now you can kiss the bride’ የሚለውን ክፍል የኛ ቸርች ፓስተሮች የማይሉት ቢሆንም እኛ ለራሳችን ብለን ተሳሳምን።
‘just married’ ብለን መኪና ጀርባ ላይ ባንለጥፍም ወደ እሱ ቤት እንዲያደርሰን ለያዝነው ባለላዳ ሹፌር ‘ተጋብተን መምጣታችን ነው!’ ብለን ነግረነዋል። እንደሙሽሪት ወግ ከነዩኒፎርሜ ወደላይ ተሸክሞ አቅፎኝ ወደተከራየባት አንድ ክፍል ቤት (አንድ ክፍል ቤት ለማለት እንኳ ይከብዳል። አንድ አልጋ ቢባል ይቀላል። ክፍሏ ከመጥበቧ የተነሳ ያለማጋነን በሩን ከፍተን አልጋው ጋር ላይ ነው ያረፍነው። ላለመሳሳት ሀሳብ ኖሮን ቢሆን እንኳን ክፉኛ ፈታኝ ነበር።) ልብሶቻችንን ምኑጋ እንዳወለቅነው ሳናውቅ ተጣመድን!! (ብዙም አታስቡት የመጀመሪያዬ አይደለም። የመጀመሪያው አይደለም። ሁለታችንም አሳምረን ያወራነው ጉዳይ ስለሆነ ቀጥታ ወደስራ) ካላብን በኋላ የምንጠፋበትን ቀን እስክንቆርጥ ደብዳቤ እየተፃጻፍን ትምህርት ቤት ደጅ ያለ ሱቅ ልናስቀምጥ ተነጋግረን ወደቤት ሄድኩኝ። አባቢ ትምህርት ቤት ሊያመጣኝ ሄዶ ገና በጠዋቱ ‘አመመኝ’ ብዬ መውጣቴ ተነግሮት ስለነበር እሳት ለብሰው ነገር ጎርሰው ሲንጎራደዱ ጠበቁኝ። ልቤ አብጧል:: ፍቅር ጠግቤ ነዋ የመጣሁት
“አዎ እሱጋ ነበርኩ” አልኩ
“ምን ልሁን ነው የምትዪው?” ማሚ ቀወጠችው።
“ማግባት ነው የምፈልገው። ላገባው ነው የምፈልገው። አስገድዳችሁ ከሱ ልትለዩኝ አትችሉም!” ደሞኮ እያለቀስኩ ነው ምኑ እንደሚያስለቅሰኝ ባላውቅም
“እንዴት እንደማልችልማ አሳይሻለሁ። ትዳር? አንቺኮ ህፃን ነሽ? ጌታ ሆይ ልጄን ምንድነው ያስነካብኝ?”
“18 ዓመት ሞላሁ::” አልኩ ፍርጥም ብዬ። ይሄኔ በምንም የማልሸነፍበት ግትርናዬ ላይ መድረሴን ስታውቅ መውረግረጓን ትታ ተቀመጠች። እስከዛ ምንም ያላለው አባቴ
“ህልምሽስ? ትምህርትሽስ?” ሲለኝ ሃሳቤ ሊከፈል ምንም አልቀረውም። አባቴ ኩራቱ እንደሆንኩ አውቃለሁ። ልጄ ህግ ተምራ ወነጀል ነክ መፅሃፍ መጻፍ ነው የምትፈልገው ብሎ ሲጎርርብኝ በእርግጠኝነት ነው። ትምህርት ቤት በየተርሙ ውጤት ሊያይልኝ ይሄድ የነበረው እሱ ነው። ‘ሜሪ በትምህርቷ ጎበዝ ናት!’ ብለው ውጤቴን ይዘረዝሩለትና በመደዳ ያጠፋሁት ጥፋት ሲነገረው ‘እኔ እቆጣታለሁ ትታረማለች!’ ይልልኛል። ስንወጣ ግን ለጥሩ ውጤቴ እጋበዛለሁ እንጂ ለጥፋቴ ቁጣም ሆነ ተግሳፅ አያዘንብብኝም። ልጁ ከነረባሽነቴ ኩራቱ ነኝ!! በፊት ወንድሜ በህይወት እያለ ወደቤት ሲገባ የሚጠራው የሱን ስም ነበር። ከሱ ሞት በኋላ ‘ሜሪ’ እያለ ነው ወደቤት የሚገባው
“እማራለሁ። እሱ እንዳልማር አይከለክለኝምኮ!” ድምፄ ወደማባበል ሄደ። “እማራለሁ። ተመርቄ አኮራሃለሁ። እሱን አጥቼ ግን መማር አልችልም።” በቃ አባቴ ከዚህ በኋላ አልተናገረም። ማሚ ቀጠለች።
“ትዳር እንደምታስቢው ቀላል አይደለም ልጄ!” ልምምጥ ….. ከዛ ደግሞ ቁጣም ታደርገዋለች።
“አይሆኑ ሆነን ያን ሁሉ ብር እየከፈልን ያስተማርንሽ ለከንቱ ነው? ሽሮ እየበላሁ ስጋ የቋጠርኩልሽ ሰው እንድትሆኚልኝ እንጂ ማንንም አግብተሽ የትም እንድትቀሪ ነው?” ደግሞ ድምፅ አውጥታ ታለቅሳለች:: ሆዴ ቡጭቡጭ ከማለቱ ደግሞ እልህ ይይዛታል መሰለኝ(የእኔ እናት አይደለች)
“እስኪ ልብ እዚህ ቤት አስተዳዳሪው ይለያል። እኔ በህይወት እያለሁማ እንዲህ አይደፍረኝም። “
በተዘባረቀ ስሜት ከረምኩ። ከሱጋር በደብዳቤ መገናኘታችንን ቀጠልን። እሱም የቢሮ ፕሮሰሱን እየጨራረሰ ሳለ የሆነ ቀን እቤት ጠዋት ማሚ ከእንቅልፌ ቀስቅሳ
“እውነቱን ንገሪኝ እርጉዝ ነሽ?” አለችኝ። አበድኩባት::
“ምንድነውሱ? ከየት ያመጣሽው ነው?” ብዬ እየቀወጥኩት ፔሬዴ መምጫውን ቀን እቆጥራለሁ።
“ማታ በህልሜ አይቻለሁ::” ብላ ገገመች። በፍፁም ብዬ ገገምኩ። እንደለመድኩት ከትምህርት ቤት ጠፍቼ ልመረመር ከሱጋ ሄድን። አርግዣለሁ!!
ደስታም ድንጋጤም ብቻ መላው ያለየለት ስሜት ተተራመሰብን። እዛው የሆስፒታሉ አግዳሚ ላይ እንደህፃን ልጅ ውስጡ ጥቅልል አድርጎ አቅፎኝ ለአንድ ሰዓት ተቀመጥን። ብቻ እየደጋገመ
“እኔ አለሁልሽ አይደል?” ይለኛል። ምንም ቃል ከአፌ ባያወጣም ግራ የገባው ስሜት ነበር የሚሰማኝ።
ከዚህ ብዙም ባልራቀ ቀን ጨርቄን ማቄን ብዬ ሁለታችንም ከዛ በፊት ረግጠነው ወደማናውቀው ከተማ ሄድን። እንደማንኛውም መደበኛ የዘመናችን ትዳር አንድ ፍራሽ … ሁለት ብርጭቆ … አንድ ድስት …. አንድ መጥበሻ … አንድ ጭልፋ ….. ቢላ …… ብለን ቤት ተከራይተን መኖር ጀመርን። በእርግጥ አንዳንዴ እቤት ውልብ ይሉብኝና ከሆርሞኑ ጋር ተደርቦ እነፋረቃለሁ።
እናቴ መጥፋቴን ስታውቅ የምትለውን አስባለሁ አባቴ እንዴት አዝኖብኝ ይሆን እላለሁ። ባሌ ግን እናቴም አባቴም ወንድሜም ፍቅረኛዬም ጓደኛዬም ሆነ።
የአራት ወር እርጉዝ ሆኜ ነው አዲሱ ባሌ የመጣው። በዓል ሆኖ እሱ ዶሮ እያረደልኝ። አጠገቡ ቆሜ እያየሁት ነው። ከጎናችን ያለው ተከራይ አሁን በውል የማላስታውሰውን ነገር ያወራኛል። እመልስለታለሁ። ባሌ ሲናደድ አየሁት ምክንያቱ ስላልገባኝ ወሬዬን አላቆምኩም:: ደግሞ መገልፈጤስ? ጨርሰን ስንገባ ደም የነካካውን ቢላ እና ሞረድ እያጣጠብኩ
“አባ ምን ሆንክ?” አልኩት
“ባለትዳር አይደለሽ እንዴ? ከላጤ ጋር ምንድነው እንዲያ መሆን?” ሲለኝ ሳቄን ለቀቅኩት እሱ መሳቄ ይባስ አናደደው
“አባ አንደኛ ባለትዳር እንደሆንኩ ያውቃል። እርጉዝም እንደሆንኩ። በዛ ላይ አንተን ከመውደድ የሚተርፍ ልብ ኖሮኝ ነው ሌላ ሰው ታስብበታለች ብለህ የምትቀናው?”
አንድ ሁለት አንድ ሁለት መመላለስ ጀመረ። እኔም በፍቅር ማባበሌን ትቼ በቁጣ መመላለስ ጀመርኩ።
ይሄኔ የሆነ ሌላ የማላውቀው ሰው ሆነ። ሌላ ፈጡር !!! ድምፁ ሻከረ። ደምስሩ ተገታተረ። ከመቼው ዘሎ አጠገቤ እንደደረሰ ሳላውቅ አጥቤ ያሰቀመጥኩትን ቢላ አንስቶ አንገቴ ላይ አደረሰው። ሰውነቴ በደነ። እንባዬ እጁና ቢላው ላይ ተንጠባጠበ። አሰፈሪ ህልም አይቶ እንደባነነ ህፃን ሰውነቴ ተርበተበተ። በዛች ደቂቃ ሁሉ ነገር ፀጥ አለብኝ:: ‘አባ’ ብዬ የምጠራው ባሌ ውስጥ ሌላ የማላውቀው ሰው አለ:: …..

One Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *