Tidarfelagi.com

ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው (ክፍል ዘጠኝ)

ከሁሉም ከሁሉም ምኑ ያስጠላል መሰለሽ? ራስሽን ባልሽ ካባለጋት ሴት ጋር ማነፃፀር …… መድቀቅ የምትጀምሪው እዚህጋ ነው …… ራስሽን ከሆነ ሰው ጋር ማነፃፀር ስትጀምሪ በራስ መተማመንሽ እየተምዘገዘገ ይፈጠፈጣል። ከዛ በፊት ከማንም በልጣለሁ ወይም ከማንም አንሳለሁ ብዬ ራሴን ከማንም አወዳድሬ አላውቅም እራሴን እንዳለሁ እንደዛ በብዙ እወደዋለሁ። ደግሞ ምናለ ከሆነች ጥፍጥፍ ጋር እንኳን ቢያደርገው ……… ማለት ምንም ንፅፅር ሳያስፈልገው ቆርጥማ ትበላኛለች።
እንደው ለማረጋገጥ አለ አይደል ከወንዱም ከሴቱም ‘እገሊት ግን ታምራለችኣ?’ ብዬ ጠይቃለሁ? ሴቱ ‘ልቅም ያለች ቆንጆ ናት!’ ይለኛል። ወንዱ ‘ፓ ቂጥዋ ይምጣብኝ!’ ይለኛል። (ይኸው በሷ የለከፈኝ ……. ትልቅ ቂጥ ሳይ አንገቴ እስኪጠማዘዝ እየዞርኩ እሸኛለሁ። ሰርች ሳደርግ ራሱ ቂጥ ለማተለቅ የሚረዱ 10 የምግብ ዓይነቶች የሚል ነገር ዓይኔን ይጠልፈዋል።)
የዛን ቀን ማታ እቤት አላድርም ብዬ 6 ሰዓት ጊቢ በሚሄድ የሰራተኞች ሰርቪስ ዶርም ገባሁ። ደጋግሞ የሆነ ጥፋት ባጠፋ ቁጥር የማለቅሰው መጠን እየቀነሰ የህመሜ መጠን እየቀነሰ መጥቷል። ማሪኝ ባለ ቁጥር ይቅርታ ሳደርግለት እንደመጀመሪያው ሁሉ ነገር ይቀጥል ነበር። ሁለታችንም ያልገባን ቀስ በቀስ ፍቅራችንን እየገዘገዘው እንደሆነ ነው። መጀመሪያ ቢላ አንገቴ ላይ ያደረገ ቀን ለሳምንታት ነው ባሰብኩት ቁጥር ያለቀስኩት የዛን ቀን ማልቀስ ብፈልግ ራሱ አላለቀስኩም። ካደረገኝ ሁሉ የከፋ ነው ያልኩት እኮ ይሄንንን ነው። ግን እንባ እንቢ አለኝ። ይልቅስ ለመጀመሪያ ጊዜ እሱ የሌለበት ህይወቴ ምን ሊሆን እንደሚችል ከአሁኑ ጋር ማነፃፀር ጀመርኩ። እሱን መጥላት የምችልበት ጉልበት አይደለም የነበረኝ ራሴን መውደዴን መጨመር የምችልበት ጉልበት አገኝሁ። ….. ዳዴ ማለት …… ያቺ እሱ ቢሆን የሚወዳት ሴት ብዬ የሆንኳትን ሜሪ አውጥቼ ጣልኳት። እሱ ስለሚሰማው ሳይሆን እኔ ስለምፈልገው ነገር መጨነቅ ጀመርኩ። የዛን ቀን እንቅልፍ በአይኔ ሳይዞር አደረ። ጠዋት ክላስ ቀርቼ ተኛሁ። ስነሳ መከፋቴ ልቤን ቢጫነውም ከሌላው ጊዜ በተለየ በማንም ላይ ያልተደገፈ መነቃቃት ውስጤ ነበር።
“ባልሽኮ ውጪ ተቀምጧል!” አለችኝ ጓደኛዬ ወደዶርም እየገባች
“ተይው ባክሽ ይቀመጥ!” ስል ራሴን ሰማሁት።
ለሳምንታት እንደዛ አደረገ። ሊያዋራኝ አይሞክርም። አይቶኝ ብቻ ይሄዳል። ሲበርድልኝ የሆነ ቀን ‘እናውራ’ ብዬ ጠራሁት እና ካፌ ተገናኝኝ። (እቤት ከሄድኩ እንደምቀልጥ አውቀዋለሁ።) አንድ ጥያቄ ብቻ ነው የነበረኝ።
“ለማያቅህ ሰው ሁሉ የሜሪ ባል ነኝ ብለህ ሳትጠየቅ የምታወራ ሰው ያውም እንደምታውቀኝ እያወቅክ ለሷ መንገሩ እንዴት አልመጣልህም?”
“አላውቅም እማ! ሁሉም ነገር በአጋጣሚ የተከሰተ ነው። የአንድ ቀን ስህተት ነው። እባክሽ ዲቴሉን እንዳወራ አታድርጊኝ። ላንቺ ማውራቱ ከሰራሁት በላይ ያማል።” አለኝ።
“እንለያይ?” አልኩት። የሰማውን ማመን አቃተው።
“እንለያይ! አባ እንዲህ እንዳፈቀርኩህ እንለያይ! አልጥላህ …. እውነቱን ልንገርህ በፊት እንደምወድህ አሁን አልወድህም! በዚህ ከቀጠልን ግን ጭራሽ ላልወድህ ነው። እኔ መኖር የምፈልገው ካሉን ጥሩ ትዝታዎች ጋር ነው። አንተን ሳስብ ካፈቀርከኝ ፍቅር በልጦ የጎዳኸኝ እንዲያመኝ አልፈልግም። ሳስብህ ፈገግ ማለት ነው የምፈልገው።” አልኩት
“አልችልም። እኔ አንቺን አጥቼ መኖር አልችልም። ቤተሰቤ እኮ አንቺ ነሽ! ማን አለኝ? እንለያይ? ከዛስ? ሰው አልሆንብሽምኮ! እማ እታመምብሻለሁ ተይ!” አለኝ (እሱ እውነት ነው ከኔ ውጪ ቤተሰቤ ብሎ የሚጠያየቀው የለም። ቤተሰቦቹም ከሁለቴ በላይ ደውለውልን አያውቁም። ዛሬም ድረስ የማይገባኝ የተወሳሰበ ግንኙነት ነው ያለው ከቤተሰቡ ጋር። ብቻ እንዲህ ሆንኩ የሚባባለው ቤተሰብ የለውም። ይሄም ሌላኛው ለራሴ ከምሰጣቸው ምክንያቶች አንዱ ነበር። ቤተሰቤ ለእኔ ምን ማለት እንደሆነ አውቃለሁና ‘ከኔ ሌላ ማንም የለውም’
“እኔ ደግሞ እንዲህ መኖር አልችልም።”
“ልጃችንስ?”
“እኔ እየሞትኩ ለልጄ እንዴት ነው እናት የምሆናት?” (በዚህ ጉዳይ ያለኝን አቋም ያውቃል። እውነቱን ነው ልጄን ሳላስባት ቀርቼ አይደለም። ባሌ ለልጆቼ ጥሩ አባት ከሆነ መቻል አይከብደኝም ብዬ የማምን ዱዝ እንደሆንኩ ያውቃል።)
“እማ በፍፁም አይሆንም! እኔና አንቺ ገና ነጭ ፁጉር እስክናበቅል አብረን እንሆናለን። ፍቅርን እንወልዳለን (ፍቅር የሁለተኛ ልጃችን ስም ነው።) የፈለግሽውን ጊዜ ውሰጂ ብቻ ተመለሺልኝ …. አትተይኝ” አለኝ
ብዙ ነገር አውርተን። ‘እንለያይ’ ያልኩት ልጅ ከንፈሩን ስሜው የምለየውስ ነገር? ሸኝቶኝ ልንለያይ ስንል
“ካንተ ውጪ ከሌላ ወንድ ልጅ አልወልድም። ምናልባት ወደፊት ፍቅርን የመውለድ ሃሳብ ከመጣልኝ ትቸገርልኛለህ።” ብዬው ተሳስቀን ተለያየን። የእውነቴን ነበር ከሁለት አባት ልጅ አልወልድም።( እሱ ሌላ ታሪክ ነው ግን የራሴ ምክንያት አለኝ።) በዛ ላይ come on እሱኮ ጣኦቴ ነበር።
ወደ ዶርሜ ተመለስኩ። ከትምህርቴ በተጨማሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የማልገባበት መድረክ ነገር የለም። እሱን የማስብበት ጊዜ እንዲኖረኝ አልፈልግም በተጨማሪ እሱ ደስ ስለማይለው ተውኩ እንጂ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ እወድ ነበር። ብሄር ብሄረሰቦች ቀን ….የሴቶች ቀን ….ኪነጥበብ ምሽት ….ብቻ ምንም ይሁን …… እንደቀይ ወጥ መሃል ላይ ዱቅ ….. ግጥም ….አጭር ልብወለድ …. ዘፈን መዝፈን ….. መድረክ መምራት …. ብቻ ምንም አልኩ እኮ Douglas ዋሸሁ? የአባቶች ቀንም መድረክ አስመሩኝ ብዬ ከልክለውኝ ነው።
“ትቼለታለሁ የኔን ጉዳይ …” ያልኩትን ጌታ ራሴ ትቼ
“ይማርሽ ይሉኛል አሜን ይማረኝ
አንተ ልጅ ፍቅርህ እንዳልሄድ ይዞኝ ” ማቀንቀኑን ያዝኩት (የምሬን ነውኮ ይሄንኑ ዘፈን ጊቢ ዝግጅት ላይ ዘፍኜዋለሁ)
እኔ መድረክ ዝግጅት ሲኖርብኝ ወፎቹ ይነግሩታል። ይመጣል። ያየኛል። “ዛሬ ታምሪ ነበር” ብሎኝ ይሄዳል። እርግጥ አንዳንዴ “ይሄ ነገር ትንሽ አላጠረም?” ይላል። በሱ እልህ የሃመሮቹን ቆዳ ብለብስ ራሱ ውስጤ ነበር። ወደቤቴ ሳልሄድ ወራት አለፈ። መጥቶ ያላየኝ አንድም ቀን የለም። እንለያይ ካልኩት በኋላ ግን ቢያንስ ሰላም እንባባላለን። ‘ምንድነው አንተ እህል አትበላም እንዴ? ከሳህኮ?’ ‘ምንድነው ሸሚዝህን አትተኩሰውም እንዴ?’ ዓይነት ንግግሮች አሉበት። በጠዋት አንድ ቀን አይኔን ስገልጥ ጊቢ ሳየው ‘ለመሆኑ ቁርስህን በልተሃል?’ነው መጀመሪያ ከአፌ የወጣው።
ሀቁንኣ የምናወራው? በጣም ከመናፈቄ የተነሳ ብዙ ቀን “በቃ አባ ይቅር ብዬሃለሁ ወደ ቤት እንሂድ” ልለው አስቤ አውቃለሁ። ሰላም ስንባባል አለው አስተቃቀፍ ውስጡ ክትት የሚያደርገኝ ለቅጽበት የሆነውን ሁላ እርስት የሚያስደርገኝ። እልሄ ያንን ያልፍ ነበር።
የሆነ ቀን አስተማሪያችን ቢሮ አስጠራችኝ። ምንም የሚያገናኘን ኮርስ ስላልነበረ እየገረመኝ ሄድኩ። ገና እንደገባሁ ቀለበቴን እጄ ላይ ቼክ ስታደርግ አየኋት።
“አላወለቅኩትም” አልኳት
“እባክሽ አታውልቂው በናትሽ። የልጅሽ አባት ነው። ይቅርታ ልጠይቅሽ ነው የጠራሁሽ። በጉዳዩ መጠየቅ ካለብኝ እኔም ነኝ ጥፋተኛ! እኔም እሱም አስበን ያደረግነው ነገር አይደለም። እናቴ ትሙት ባለትዳር መሆኑን ግን አላውቅም ነበር።” እያለች ነገሩን ስታብራራልኝ እኔ ያደረጉት ነገር በስዕል መልክ እየተከሰተብኝ ደሜ መንተክተኩን አልክድም። ብዙ መጠየቅ የምፈልገው ነገር ነበር ዲቴሉን ማወቅ ህመም እንጂ የሚሰጠኝ መልስ እንደሌለ ሳውቅ ተውኩት። ከእርሷ ጋር ያወራሁ ቀን ድብዝዝ ብሎ የነበረው ቁጣዬ ፈላ!! ማታ ላይ ሳየው ሀገር ሰላም ብሎ ሲያቅፈኝ። ለነገር ሲሊፐሬን አቀብሉኝ አልኩ። … ሌላ የማላውቃት ሴትዮ ከውስጤ ወጣች …. እያለቀስኩም እየተሳደብኩም… እየተራገምኩም….. የሆነ የማልወዳት የመንደር ነገረኛ ሴት ነገር ሆንኩ። …….. … ዝም አለኝ። በሚቀጥለው ቀን አልመጣም። ………. ማለት ሲቀርብኝ ጠበቅኩትኮ። ‘እንለያይ’ ብዬው ነበርኮኣ? ምን ሆኖ ይሁን ብዬ ስጨነቅ አደርኩ። በሚቀጥለውም ቀን አልመጣም። ማታ ላይ ማሚ ደወለችልኝ።
“በይ ነይ እቤት እየጠበቅኩሽ ነው!”
“የት ቤት ነው?”
“እቤትሽ!”
“አርባምንጭ ነው?”
“አዎ!” ማሚ ከሀዋሳ ልትመጣ የምትችልበትን ምክንያት ማሰብ ቸገረኝ። …. የሆነ ነገር ሆኖ ቢሆን ግን ድምፅዋ እንዲህ አይረጋጋም።

One Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *