Tidarfelagi.com

ሁለቱ ካድሬዎቹ

ሁለቱ ካድሬዎች

የማነ እና ዳንኤል ካድሬዎች ናቸው። ይሁኑዋ ታዲያ! ካድሬ በበዛበትሀገር እነገሌ ካድሬ ናቸው ማለት ምንድነው?

የማነ እና ዳንኤል ጓደኛሞችም ናቸው፤ ውሏቸው አንድ ላይ ነው፣ ወሬያቸውም አንድ ዓይነት። ስለ ልማቱ ያወራሉ፣ ያደጉትም፣ ያላደጉትም ፣የማያድጉትም ከኢትዮጵያ መውሰድ ሰላለባቸው ተሞክሮ ያወራሉ፣ አዲስ ሲገነባ ስላዮት ህንፃ አንስተው የሀገሪቱ ልማት ከሚጠበቀው በላይ እየተጓዘ እንደሆነ… ፈጣሪ በቃህ ብሎ ካላስቆመው ምንም የሚያስቆመው ሃይል እንደሌለ ያወራሉ።

ባንድ ወቅት የማነ ለማግባት ፈለገ። አንዲት ሴት ላይ ቀልቡ አረፈ። ለዳንኤል አማከረው። ዳንኤል ልጅቷን ለሁለት ቀርቦ አያት…
“ትቅርብህ!” አለው ፣
“ለምን? ” የማነ ደነገጠ።
“ለህገ መንግስቱ ጥሩ አመለካከት የላትም! ”
ዝም አለ የማነ። ከአፍታ ቆይታ በኋላ ሂስ ካላወረድኩ አለ።

“ሂሴን ማውረድ አለብኝ፣ ፀረ ልማቶችን ዐይነ ውሃቸውን አይቸውን አይቼ ማወቅ ነበረብኝ። እኔ ግን ጭራሽ አንዷን ከትዳር አሰብኩ። ምኑ የአይምሮዬ ምህዳር የጠበበ ነኝ በል። ድርጅቴን አሳዝኜዋለሁ፣ ሂስ ላውርድ… ” እንባ እንባ እያለው ይሄን አውርቶ በዳንኤል ፊት ሂሱን አወረደ። ዳግም እንዲህ አይነት ነገር እንደማይለምደው በድርጅቱ ስም ማለ።

ስማ ይለዋል ዳንኤል ለየማነህ፣

“ደርግ አውድማው ነው እንጂ እኮ እግዚኣብሔር ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት እንደሚመጣ። አርባ ዓመት በጥጋብ እንደሚገዛ፣ በዛ ዘመን ቡዙዎች ከልክ በላይ ስለሚበሉ በቁንጣን እንደሚሰቃዪ የሚያወራ ጥንታዊ የትንቢት መፅሐፍ ነበር። ”

የማነ ዝም አለ።
“ምነው አላመንከኝም? ”
እንዴ አምንሃለው እንጂ ግን አንድ ነገር አሳዛነኝ ”
“ምን? ”
” ድርጅታችን የሚገዛው አርባ ዓመት ብቻ ነው መባሉ… ”

“እሱስ ልክ ነህ ”
አብረው በጥልክ ተከዙ!!
* * *

የማነ እና ዳንኤል ካድሬ ናቸው።
“ምን ያዝናናችኋል ” ተብለው ቢጠየቁ እንዲህ ይመለሳሉ፣
” ፊልም! ”
“ምን ዓይነት ፊልም? ”
“ዶክመንተሪ፤ የኢቲቪ ዶክመንተሪ!”
***
ማታ ማታ ይፀልያሉ። የዘውትር ማሳረጊያቸው እንዲህ የሚል ነው፣
“ኢህአዴግ ለዘላለም ይኑር! ”
ያ ሸገር የተባለ ሬድዮ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር “ሲል በሰሙት ቁጥር አንጀታቸው ያራል።
ለምን ኢህአዴግ ለዘላለም ይኑር አይልም? ኢትዮጵያ ያለ ኢህአዴግ ተስፋ እንደሌላት ጠፍቶት ነው? ከየትኛው አሸባሪ ድርጅት የሻይ እየተሰጠው ነው እንዲህ የሚለው?
***
አንዱ ከቤት ሲወጣ ሌላው እንዲህ ይለዋል፣
“ቀዪን መስመር እንዳታልፍ እየተጠነቀክ ”

“እሺ ወንድሜ አንተም የፀረ ሀሰላማውያን ሃሳብ ሽው እንዳይልህ እየተጠነቀክ”

“ደህና ዋል ”
“ድርጃትችን እያለ ምን እሆናለሁ ብለህ?! ”
“እሱስ…!! ”

*************************************************  ክፍል ሁለት *************************************************

የማነህና ዳንኤል!
(ካድሬዎቹ እንኳን…)

የማነ እና ዳንኤል በሚኖሩባት ክፍልግድግዳ ላይ፣ አንድ የማርያምና የልጇ ስዕልና ቢቆጠሩ የማያልቁ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፎቶዎች ይታያሉ።
ትክ ብሎ ላስተዋለ የቀድመውን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሂወት ለማሳየት የተዘጋጀ የፎቶ ጋለሪ እንጂ መኖሪያ አይመስሉም።

የማነህና ዳንኤል ካድሬ ናቸው ብለናል፤ አንደግምም (እየደገምን ቢሆንም)
የማነህ ለአንድ ዓመት ያህል መምህር ነበር። አሁን ምስጋና ለድርጅቱ ይግባውና በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ጥሩ ቦታ ይዟል።

መምህር ሳለ ተማሪዎችን
“ለሞዴል ፈተና ተዘጋጁ ” ብሎ ባዘዘበት አንድ ቀን፣ “ሞዴል ” የምትለዋ ቃል ሞዴል አርሶ አደሮችን አስታወሰችው። ከሞዴል አርሶ አደሮችም መካከል በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስ ትር የተሸለሙት ሞዴል አርሶ አደሮች በዐይነ ህሊናው ተሳሉበት።
ስለ bladder እያስተረ የነበረው የማነ ስለሞዴል አርሶ አደሮች በስሜት መናገር ጀመረ።
ተማሪዎቹ ከብላደር ወደ አርሶ አደር የሚያሸጋገር ምን ተዓምር እንደተፈጠረ ግራ ገባቸው። ጥቂት የማይባሉት ድምፃቸውን አፍነው መሳቅ ጀመሩ።
የማነ ግን ስለ አርሶ አደሩ የዘመናት ተጨቋኝነት፣በዘመነ ቅዱሱ መንግስት ነፃ ስለመውጣቱ፣ ለውጥ ስለመምጣቱ፣ ሁሉም አርሶ አደር አይሱዙ ስለመግዛቱ እስኪያልበው አወራ።

ጎበዝ፣ ጎበዛዝት ተማሪዎች፣
“ቲቸር ቀወሰ” አሉ።ሌሎች “መምህርነቱን አቁሞ አርሶ አደር ሊሆን ነው ” ሲሉ አሰቡ።
ተደወለ። ወጣ።
አርሶ አደር የሚል ቅፅል ስም ወጣለት።
******

የማነን ወይም ዳንኤልን ማንም ፣
“እንዴት አድርሃል” ብሎ ቢጠይቀው፣
“ፓርቲያችን እያለ ምን ይኮናል ” ብሎ ይመልሳል።

ለዳንኤልና የማነ መንግስት አለላቸው፤ ወዲህ ደግሞ የፌስ ቡክ አካውንት አላቸው።

በየፌስቡካቸው፣
ስለልማቱ፣ ስለልማታዊ አርቲስቶች በጎ ስራ፣ ስለህንፃው፣ ህገመንግስቱን መናድ ስለማስናዱ፣ አንድም ጋዜጠኛ ፅፎ ሲታሰር አለማየታቸውን… ከዛ ይልቅ በአዲስ አበባ ፎቆች በየቀኑ እንደ እንጉዳይ ሲፈሉ ማየታቸውን ፣ ስለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራቸው (አባታቸው) ፣ ባይሄዱበትም ገና ሲያስቡት ስለሚመቸው ባቡር… ወዘተ ይፅፋሉ። አንዳንዴ እደውም የታክሲ ውስጥ ገጠመኞቻቸውን ባቡር ውስጥ እንደተከናወነ አድርገው ይፅፋሉ።

አንድ ቀን ዳንኤል ፌስ ቡክ ላይ በተተከለበት እንባ ይወርደው ጀመር። የማነ ደንግጦ ምን እንደሆነ ጠየቀው፣
“እንደው እኚ ፀረሰላም ኀይሎችን ምን ብናደርጋቸው ይሻላል? አሁን እነወዴት ሰው እንዲህ ብሎ ይፅፋል? ” በምሬት እየተንገፈገፈ…

“እስቲ አንብብልኝ? ” የማነ ጠየቀ።
” እንደጀመርን እንጨርሰዋለን ያሉት ሕዝቡን ነው ግድቡን ብሎ እኮ ነው የፃፈው በናትህ…
አሁን ይሄ ለጣልያን እንጂ ለኛ ፓርቲ ይፃፋል? ሶስት ቀን ባበላ? በየቀኑ መከራ ለሚያበላው ደርግ እንኳን መች እንዲህ ተባለ? እንደው ግን እግዜር መቼ ነውእንዲህ አይነት የጥፋት ኀይሎችን የሚያጠፋልን እባክህ… ውይይይ… እንዴ፣ ይህን የመሰለ ፓርቲ ሕዝቡን ነው ግድቡን ተብሎ ይዘበትበታል? እንደው ሕገ መንግስቱ ባይኖር ይሄንን ጀርባ ጀርባውን በቆመጥ እየዠበጡ እስከናይጄሪያ ድረስ በእግር ማባረር ነበር” በእልህ እየጦፈ ዓይኑን አባበሰ።
የማነም የሰማውን ባለማመን በንዴት ጥፍሩን ሲበላ ቆይቶ ብስጭታቸውን ለመረሳት ባቅራቢያቸው ወደሚገኝ የካድሬዎች ሆስፒታል (መጠጥ ቤት) ተያይዘው ሄዱ

 

*************************************************  ክፍል ሦስት  *************************************************

(የማነ እና ዳንኤል)
****
የማነ እና ዳንኤል ወደ መጠጥ ቤት ሄዱ ብለን ነበር ያቆምነው። መጠጥ ቤት የሄዱት መጠጥ ልማቱ ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለመወያየት አይደለም፤ ለመጠጣት እንጂ!
ሲጠጡ አመሹ። ሞቅ ብሏቸው፣ ከመሞቅም አልፈው ቅጥል ብለው ሰክረው ወደሚኖሩበት ክፍል ገቡ።

ዳንኤልም አለ (በስካር መንፈስ)
” አንዳንዴ ግን እፈራለሁ…”
“ምን ያስፈራሃል?! ” አለ የማነ በመገረም (እናት ድርጅታቸው እያለ፣ በምድር ላይ የሚያስፈራ ነገር አልከሰትልህ ብሎት!)

” አይ እንደው እንደዚ ግንባታውን በላይ በላዪ ስናጣድፈው ፣ እግዜር እንደ ሰናዖር የስልጣኔ ዘመን፣ የባቢሎን ግንብ ዐይነት ገንብተን እሱ ላይ ልንደርስ መስሎት ተቆጥቶ ቋንቋችንን እንዳይደበላልቀው ፈራሁ ”

የማነ ተከዘ።
” በእርግጥ እውነትህን ነው ያሰጋል፤ ግን ደሞ የፓርቲዎችን ሁሉ ልብ የሚመረምረው ጌታ፣ የድርጅታችንን ሃሳብ ይረዳል ብዬ አምናለሁ። ይልቅ ያቺ ከመጠጥ በኋላ ለድርጅታችን ያለን ፍቅር ልባዊ መሆን አለመሆኑን ለመለየት የምንጠያየቃት ጥያቄ ናፍቃኛለች፤ ብንጠያየቅስ? ”

“እሺ ፣ ጀምር ።”

የማነ ጀመረ፣
“ይህ ቅዱስ ስርዓት ሀገራችን ላይ ከሰፈነ ረጅም ጊዜያት ተቆጥረዋል። በነዚህ ጊዜያት ውስጥ በመፃፉ የታሰረ ጋዜጠኛ ወይ አሸባሪ ዐይተህ ታውቃለህ? ”

“ጋዜጠኞች በሁሉም ያለፉት ስርዓቶች ሲገረፉ፣ ሲታሰሩ፣ የሚፅፉበት እጃቸው በመንግስት ቅጥረኞች ተሰብሮ መፃፍ እንዳይፅፉ ሲደረግ አይቻለሁ፣ ሰምቻለሁ። ጋዜጠኞችእና ጦማርያን በምኒልክም ዘመንም፣ በኃ /ስላሴም፣ በደርግም ፣ ከምኒልክም በፊት ባሉት መንግስታት በሚፅፉት ፅሁፍ ተንገላተዋል። በዚህ መንግስት ግን በፃፈው ፅሁፍ ምክንያት ዝምቡን እሽ የተባለ ጋዜጠኛም፣ ጦማሪም እንደሌለ ማንም ልቡ ቅን የሆነ ሰው መርምሮ ማረጋገጥ ይችላል።

ግን ብዕር ጨብጡ ብለን የፈቀድልናቸው ጋዜጠኞች ቦንብ ጨብጠው እጅ ከፍንጅ ይዘን አስረናል። በጋዜጠኝነት ስም የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች ደሞ ጋዜጠኛ እንዳልሆኑ ሁሉም ያውቃል ” አለ ዳንኤል።

“ብራቮ፣ እንዳንተ የሀገሩን ተጨባጭ ሁኔታ የሚረዳ ሰው እኮ ነው ያነሰን! ” የማነ በማዳነቅ ጮኸ።

“ሌላ ጥያቄ፣ የፀረ ሽብር ህጉ ላይ ምን ጥያቄ አለህ? ”

” እኔ? ጥያቄ? በስመአብ! የፀረ ሽብር ህጉ ደሞ ምን ይጠየቃል? ለብዙ ጥያቄዎቼ መልስ ሆኖልኛል እንጂ!! ”

“ካነበብካቸው መፅሐፎች ውስጥ፣ በቋንቋ አጠቃቀሙ፣ በሳቢነቱ፣ በበሳልነቱ ማራኪ ነው የምትለው የቱ ነው? ”

“ሕገ መንግስቱ! ”

አሁን ደሞ አንተ ጠይቀኝ። ”

እሺ… እእእ… ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ አቃተኝ፣ በዛብኝ ሳይሉ አንዲት ሀገርንና አህጉርን የመሩት መሪየዓለማችን ታላቅ መሪ ማን ይባላሉ? ”

የማነ ፊቱ ተለዋወጠ። ሳግ ተናነቀው። እንባው ወረደ።
” እእ አታስታወስኝ እስቲ… እህህህ… ወይኔ ደሀው አባቴ! ”
ተነስቶ ቤት ውስጥ ያሉትን ፎቶች በእጁ እየዳሰሰ መነፋረቅ ጀመረ። ዳንኤልም ተከተለው።

“በቃ በቃ… የማነ፣ ይቅርታ ስሜትህን የሚጎዳ ነገር ስላነሳሁብህ። በቃ፣ ለዛሬ ጥየቄና መልሱ ይብቃህ ”

“አይ፣ እሳቸው እኮ ብቻቸውን አይደል የሞቱት፣ እኛም እሳቸው ሲሞቱ ነው አብረን የሞትነው…
አለ እንባውን እየጠራረገ። በሀዘን ስሜት ለደቂቃወች ከቆዩ በኋላ ወደ መኝታቸው ሄዱ።
እንቅልፍ ወሰዳቸው ( በነገራችሁ ላይ ካድሬም እንቅልፍ ይወስደዋል)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *