/መጋቢ ሀዲስ እሸቱ እንዳወሩት ያሬድ ሹመቴ እንደፃፈው/
እንደምን አመሻችሁ? በባከነ ሰዓት ነው (የመጣሁት) የዓድዋ ጦርነት እንኳን የዚህን ያህል ግዜ አልወሰደም። (ሳቅ) ጦርነቱ በአጭሩ ተጠናቀቀ። ስለጦርነቱ ለማውራት ግን አራት ሰዓት አስፈልጎናል። እንግዲህ መናገር እና መዋጋት የተለያየ ነው። መናገር ውጊያ የለውም። ፍልሚያ የለውም። መሞት የለበትም። ሁላችንም ብዙ እንናገራለን እግዚአብሔር ይመስገን። (ረዥም ሳቅ)
ቅድም ከነበሩ ተናጋሪዎች ከዲያቆን ዳንኤል ክብረትና ከወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ ንግግሮች ወስጄ (አጋጥሜ) አንድ ነገር ልስፋ።
ዳንኤል ከነገረን ቁምነገር አንዱ “በሁሉም ነገር መግባባት አለብን ወይ?”
ወ/ሮ ሰሎሜ ደግሞ የነገሩን “ነገሮችን በሙሉ በፖለቲካ መግባባት አለብን ወይ?”
ሁለት አይነት ናቸው የተነገሩን። ከስድስት ወር በፊት አንድ ቃለ መጠይቅ ላይ እንደ አጋጣሚ የተናገርኩት ነገር አለ። ‘ጣሊያንን ከሀገር ለማስወጣት አባቶቻችን ደማቸውን አፈሰሱ። በግልባጩ ደግሞ ጣሊያን ለመግባት ዛሬ ሜዲትራሊያን ባህር ደማችን እየፈሰሰ ነው” ብዬ ተናግሬ ነበር። (ሳቅ)…
….እንደውም እኔ ጣሊያንን ከምናሸንፍ ምን አልባት ጁቬንቱስ (የእግር ኳስ ቡድንን) አሸንፈን ቢሆን ብዬ አሰብኩ። (ሳቅ)..ወይም ኢንተር ሚላንን አሸንፈን ቢሆን ኖሮ የበለጠ ይወራልን ነበር!? ብዬ አሰብኩ!
ቅድም ዳንኤል እንዳለው እኔም ባለፈው እንግሊዝ ሀገር ሔጄ ስሰማ፥ ማንቺስተር ሊቨር ፑል ምናምን የሚባሉት የእግር ኳስ ቡድኖች በሙሉ ለካስ ከተሞች ናቸው። አሁን አንድ ወጣት አግኝታችሁ ‘ሊቨር ፖል ምንድነው? ብትሉት ‘የእግር ኳስ ቡድን ነው። ነው የሚላችሁ’። ፈረንጆቹ ሳናውቀው የቀበሌዎቻቸውን ስም ያሸመድዱናል። (ረዥም ሳቅ) እነ ሲ ኤም ሲ እነ ኮልፌ እነ መርካቶ ማንም አያውቃቸውም (ምክንያቱም) የኳስ ቡድን የላቸውም።(ረዥም ሳቅ) እናም ዓድዋን ለማስጠራት ዓድዋ የሚባል የኳስ ቡድን ማቋቋም አለብን ወይ? የሚል ሌላ ሀሳብ አለኝ።
ሌላው ደግሞ ጀግንነት አሁንም መሰበክ አለበት። በአለም ላይ ጦርነት እንዲጠፋ መፀለይ፥ ፀሎቱን የመሰማት እድሜ ማራዘም ይመስለኛል። ጦርነት ምክንያታዊ እንዲሆን መፀለይ ነው እንጂ ጦርነት እንዲጠፋ መፀለይ ጅልነት ነው የሚመስለኝ። እንኳን ስንት ቢሊየን ህዝብ ባለበት ዓለም፥ አዳምና ሔዋን ሁለት ሆነው በገነት መስማማት ያልቻሉበትን ህይወት፥ እኛ ከየት አግኝተን ነው በድርድር የምንግባባው…(ሳቅ) ውሸት ነው። ስለዚህ ጀግንነት መሰበክ አለበት።
የዛሬ መቶ ምናምን አመት ጣልያኖችን አሸነፍን። ነገር ግን ጠላቶቻችን ተቀይረው ሊሆን ይችላል እንጂ አሁንም ፈጽሞ ሊጠፉ አይችሉም። ስለዚህ ጀግንነት መሰበክ መነገር አለበት።
በሌላ በኩል ደግሞ የጦሩ መሪዎች ፖለቲከኞቻችን፥ በጥንት ግዜ የነበሩት፥ አፄ ምኒልክ በሉ፥ አፄ ኃይለ ሥላሴ ብንል መንግስቱ ኃይለማሪያም፥ መለስ ዜናዊ በሉ፥ አቶ ኃይለማሪያም፥ እነዚህ ሁሉ መልዓክም ሰይጣንም አይደሉም። ሰዎች ናቸው። ምን ለማለት ነው የፈለግኩት?…. ምክንያቱም ሰይጣን ቢሆን ለምስጋና አይመችም። መልዓክ ቢሆንም ለትችት አይመችም። ሰው ከሆነ ግን ለትችትም ለምስጋናም ይመቻል። (ረዥም ጭብጨባ)
የዛሬ 6 ዓመት አካባቢ ኔልሰን ማንዴላ በሞቱበት ወቅት ሰሞን አንድ የግዕዝ ቅኔ አቅርቤ ነበር። ምኒልክን እና ማንዴላን አነፃጽሬ። እና አማርኛውን ልንገራችሁ።
ምዕራባውያኑን እኩል አሸነፉ
ምኒልክ በሰይፉ ወ-ማንዴላ ባፉ።
ነበር ያልኩት (ሳቅ) እና ምን ነበር ለማለት የፈለግኩት፥ ምኒልክና ማንዴላ ሁለቱም ጀግኖች ናቸው። ልዩነቱ፥ ማንዴላ በትህትና ደም ሳያፈስ ይቅር በሉን፥ ይቅር ብለናችኋል ብላ!… (ረዥም ሳቅ) በለስላሳ ዲፕሎማሲ፥ አሁን ዜና ስንሰማ ደቡብ አፍሪካ ነፃ ከወጣች 23 ዓመት ሆናት፥ አሁንም ግን ነፃ ወጥተናል ወይ? እያሉ እየጠየቁ ነዎ ሰዎቹ። ድርድሩ ነጮቹ የያዙትን እንደያዙ እንዲቀጥሉ፥ ጥቁሮቹ ግን ባርያ የሚባል ቆሞላቸው በተዘዋዋሪ ባሮች ናቸው። (ሳቅ)
እዚህ አገር ባለሀብቶቻችን በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ተክለብርሐን አምባዬ የሚባሉ ባለሀብት አውቃለሁ። ሳሙኤል ታፈሰ የሚባል ሰው አውቃለው። ፀጋዩ የሚባል ሰው አውቃለሁ። ባለሀብቶቻችን በሙሉ ገንዘባቸውን ይስጡም አይስጡ አበሾች ናቸው። እንዴት ደስ ይላል። (ረዥም ጭብጨባ) ደቡብ አፍሪካ ብትሔዱ ግን እያንዳዱ ሪል ስቴት እያንዳዱ ባንክ እያንዳንዱ ኢንሹራንስ በጆንሰን እና በፒተር የተያዘ ነው። (ሳቅ) ጥቁሩ ምን አልባት ባንክ ቤት ብር ያስቀምን እንደሆነ እንጂ፥ ባንክ ቤት የለውም። በግልባጩ እውነቱን ለመናገር ይሔ የዓድዋ ድል ውጤት ነው! እውነቱን ለመናገር አፄ ምኒልክ የከፈሉት ዋጋ ነው። (ከፍተኛ ጭብጨባ)
አንድ ሰው ጋር በስልክ ሳወራ እንዲህ አለኝ “እንዴት ማንዴላን እና ምኒልክን ታነፃጽራለህ?”
‘እንደውም ልንገርህ ይቅርታ አድርግልኝና ምኒልክ ይገዝፉብኛል!! አሁን እንግሊዛውያን ለማንዴላ ለንደን ላይ ዋሽንግተን ላይ ሀውልት እንዲቆምለት እየተደራደሩ ነው። እውነት (ማንዴላ) ጥቁሩን አክብረውት ነው ወይ? አይደለም! ነጮቹ ንብረታቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ። ለዚያ የሚከፈል ዋጋ ነው። (ሳቅና ጭብጨባ) ሌላ ምንም ተዓምር የለውም።
አፄ ምኒልክ ግን አዋርደው፥ ማቅ አልብሰው ስለላኳቸው እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንድትኖር የሚፈልጉ አይመስለኝም።
እንደተባለው በሁሉም ነገር መግባባት የለብንም። በወረደ አስተሳሰብ፥ በቋንቋ መጠለፍ የለብንም። መንግስት ክልልን ሲያቋቁም ለአስተዳደር እንዲመች እንጂ ለአስተሳሰብ ክልል አልተመደበም። (ጭብጨባ) አሁን ብዙዎቹ አስተሳሰባቸው ክልላዊ ሆኖባቸው ሲንገላቱ እንመለከታለን።
ሌላው ደግሞ ለአክሱም ሐውልት የሰጠነውን ክብር ቀነስ አድርገን፥ አክሱም ከተማ ላሉት ለነ ጎይቶም ለነ ሐጎስ፥ በዓድዋ ድል እንደተመካነው ሐዳስን አብርሐትን አስገዶምን እናውቃቸዋለን ወይ? የወንዶ ገነትን አቡካዶና ፓፓዬ እየበላን የወንዶ ገነትን ገበሬ ንቆ የት ሊገባ ነው? የጎጃምን ማርና ቅቤ እየበሉ ጎጃምን ቆምጬ ማለት ያዋጣል ወይ? (ረዥም ሳቅ)… ይሔ እየመረረን የምንጠጣው ሀቅ ነው። እኔ አሁን የሚጠቅመንን ነው የምነግራችሁ። የወለጋን ወርቅና ቡናን እየፈለግን እነቶሎሳን ንቆ የት ይገባል?
መግባባት ያስፈልጋል። የአሁኑ ጦርነት የአስተሳሰብ ጦርነት ነው። የአመለካከት ጦርነት ነው። ጽዳት ማለት በህሊና ነው። እኔ በቀደም ሰዎቹ ቆሻሻ ተጭኗቸው አለቁ ሲባል፥ ‘ኣረ በየቢሮው ስንት ቆሻሻ የተጫነው ጭንቅላት አለ አልኩኝ’ እኔማ። እንደው እስካቫተር የማያነሳው ስንት ቆሻሻ አለ እውነት ለመናገር። እዚያው ከቆሻሻው ቦታ አንድ ሰው ላዳ ተከራይቶ ዘርፎ ሊወጣ ሲል ተያዘ አሉ። እኛ አላየነውም እንጂ ይሔ ሰውዬ ጭንቅላቱ ላይ ቆሻሻ ተንዶበታል። (ሳቅ)
ስለዚህ የሚዲያ ሰዎች፥ የፖለቲካ ሰዎች፥ የሥነጽሁፍ ሰዎች፥ የኪነ-ጠበብ ሰዎች፥ ልዩነቶቻችንን ለጥጦ ከማስፋት ይልቅ ልዩነቶቻችን ውበቶቻችን ብለን የሚያግባቡን ነገሮች ላይ እንግባባ።
ለምሳሌ አሉላ አባ ነጋን ለማድነቅ በግድ ትግርኛ መናገር አይጠበቅብንም። (ጭብጨባ)… በላይ ዘለቀን ለማድነቅ አልበልቶም ማለት አይጠበቅብንም። (ረዥም ሳቅ)… ንጉስ ሚካኤልን ለማድነቅ ደሴ መወለድ የለብንም። ይሔንን አስፍተን ልናይ ይገባል። ዓድዋ የመላው ጥቁሮች መመኪያ ነው። የመላው ጥቁር ህዝቦች መኩሪያ ነው። ይህንን አጉልተን ልናሳይ ይገባል።
እንደው አሜሪካ ውስጥ የምሰማው ዝቅጠት ሁሉ። እንደው ወርደን ወርደን… ስለ ዓድዋ ሲወራ ስለተወሰነ ክልል የሚወራ የሚመስላቸው፥ አሜሪካ ገብተው አሜሪካ ያልገባቻቸው ሰዎች ገጥመውኛል – በእውነቱ። (ጭብጨባ) እነዚህን አስተሳሰቦች ማጽዳት አለብን።
አቶ ዳዊት ዓድዋ ስለተወለድኩ ሲሉ ቅድም… እኔ ደግሞ እንዲያውም ዓድዋን ከሀረር መጥቶ እንዲያለማው እፈልጋለሁ። ከወለጋ ሒዶ ዓድዋ ህንጻ እንዲሰራ እፈልጋለሁ። ዓድዋ ላይ የቶሎሳ ሆቴል የሚል እጠብቃለሁ እኔ።… ይሔን ማስፋት ካልቻልን፥ ይሔን ማከም ካልቻልን፥ የዛሬ መቶ ሀያ አመት የምንተርክለት ዓድዋ አየር ላይ ተንሳፍፎ ይቀራል።
ጀግኖቹ ግንባራቸውን ተመትተው፥ ነደው፥ ከስለው፥ ተርበው፥ ተጠምተው፥ ደምተው ስራ ሰርተዋል፥ እኛ ደግሞ አሁን ያለውን የአስተሳሰቡን ጫና እንናደው። አንድነታችንን እንስበክ። (ጭብጨባ)… እዚህች ሀገር ላይ ገበሬ ችግር ሆኖ አያውቅም። ሀገር ውስጥ የሚፈጠሩት ችግሮች በሙሉ አሜሪካም እንግሊዝም አዲሳባም ሁሉም ቦታ የሚራገቡት ችግሮች በሙሉ በዩኒቨርሲቲ ምሁራን ነው፥ ወይ በፖለቲከኞች ነው። (ጭብጨባ) ገበሬ ጤፍና ስንዴ ያመጣል ወንጀል የለበትም። ገበሬ ተሳፋሪ ነው።
እንደምታውቁት 62ቱን ሰው የሚይዘው አውቶቢስ አንድ ሰው ነው የሚሾፍረው። …ለህዝቡ ጥላቻን ከመስበክ፥ መከፋፈልን፥ መነጣጠልን ከመስበክ ይልቅ የሚያዋጣን እዚህ ሐገር ላይ አንድነት ነው በቃ!! ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ በዚህ ሰዓት መገንጠል መከፋፈል ምንም አትራፊ አይደለም። ይሔ የጅል ነጋዴ ፖለቲካ ነው የሚባለው። ዘይት በተወደደበት ጊዜ ቅቤ ከነገደ ይሔ ሰውዬ ጤነኛ አይደለም ጭንቅላቱ። (ረዥም ሳቅ)
አንድነታችን ይሰበክ! ህብረታችን ይሰበክ! ዓድዋ ለትስስራችን የብረት ገመድ ነው ብዬ አምናለሁ!! (ረዥም ጭብጨባ)
ስለ ዓድዋ መስኪድ ሼሁ፥ ፓስተሩ ፀሎት ቤት፥ እኔ ቤተክርስቲያን ልሰብከው ይገባኛል። እኔ በቀደም መስኪድ ሔጄ አስተምሬያለሁ። የሞተው መሐመድ ይሁን እንጂ የሞተው ኢትዮጵያዊ ነው!! ወገኔ ነው አካሌ ነው!! (ረዥም ጭብጨባ) …ኢትዮጵያችን፥ በመስኪድ ከቁርዓን ቀጥሎ፥ በቤተክርስቲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ፥ በሰርግ ቤት ከሙሽራው ቀጥሎ፥ በለቅሶው ቤት ከሬሳው በላይ መሰበክ መቻል አለባት!!
እንኳን ጤነኛ ሆኖ ለመኖር እብድ ሆኖ ለመኖር እንኳን ኢትዮጵያ ታስፈልጋለች። ሰዎች ከአሜሪካ አእምሮዋቸው ሲነካ ይባረራሉ። ኢትዮጵያ ነች የምትረከባቸው። (ረዥም ሳቅ)…እውነቱን ነው የምላችሁ። አሁን ባለፈው ከስድስር ወር በፊት አሜሪካ እያለሁ፥ አንዱን በመርፌ ወግተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲሔድ አደረጉት አሉ። እኔ የሀገሬ ጥቅም ገባኝ ያኔ። ለካ እኔን ጤነኛ ስለሆንኩኝ ነው የተቀበሉኝ እነዚህ ሰዎች። ዲቪ እንኳን ለመሙላት 12ኛ ክፍል መጨረስ ይጠይቃሉ። እዚህ ሀገር ግን መኃይሙም ይኖርበታል እብዱም ይኖርበታል። አብዶ ጨርቅን ለመጣልም ሀገር ያስፈልጋል!! (ረዥም ጥብጨባ) ለምኖ ለመብላትም ሀገር ያስፈልጋል።
ሀገር ለመደገፍ ከፖለቲካ ጋር ማገናኘት የለብንም። ሀገር ለመደገፍ የኢሀዲግ ደጋፊ የቅንጅት ደጋፊ መሆን የለብንም። ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ብቻ ዓድዋ ያኮራናል ዓድዋ ያስመካናል። (ጭብጨባ) ዓድዋን ነገም እሰብከዋለሁ፥ አመሰጥረዋለሁ፥ እተነትነዋለሁ። ለምን? የሀገራችን መመኪያ መኩሪያ ነው።..(ያልተቋረጠ ጭብጨባ)…
…. አሜሪካን ሀገር እኮ የትግሬ ቤተክርስቲያን የአማራ ቤተክርስቲያ ተመድቧል። የትግሬ ሚካኤል የአማራ ሚካኤል የሚባል አለ። እነ ሚካኤል ያልሰሙት ጉድ። (ረዥም ሳቅ)…አንዷ ከዛ ደውላ ትነግረኛለች እዚህ ቤተክርስቲያን የትግርኛ ተናጋሪዎች በዝተውበታልና ጭቆና ተደርጎብናል አለችኝ። ተመልከቱ እንግዲህ ሎሳንጀለስ ተቀምጣ (ረዥም ሳቅ) ወዴት እየተሔደ ነው? ምንስ እየተሆነ ነው? አብደን እስከምናልቅ መጠበቅ አለበት ወይ? ሀይ ማለት የምንችለው እኛ ነን። ለዚህ ዋጋ መክፈል አለብን። ከኮሶና ከስኳር ማን ይጣፍጣል? ስኳር፥ ግን ወስፋት ነው ትርፉ። ኮሶ ለግዜው ይመራል ሲገባ ግን ያፀዳል። አሁን የምናገረው ኮሶ ነው ሲነገር ይመረና ሲገባ ግን ያኖረናል፥ ያሽረናል፥ ተስፋ ይሰጠናል።
ሀገር ላይ ጥቂት ሾፌሮች ነው ያሉት። ሶስት መቶ ሚልየን የአሜሪካ ህዝብ ግማሹ ከአትላንቲክ የተሻገረ አስተሳሰብ የለውም። እዚያው ማክዶናልዱን በላ ስታር ባክሱን ጠጣ በቃ መተኛት ነው። ጥቂቶቹ ግን አለምን በተሻገረ አስተሳሰባቸው… እነ አብርሐም ሊንከን፥ እነ ጆርጅ ዋሽንግተን አለምን የተሻገረ አመለካከት ስለነበራቸው ዛሬ አሜሪካ ከአለም የበላይ ናት።
ሶስት መቶ ሚሊየን አሜሪካውያንን የሚሾፍሩት ሀምሳ ሺህ የማይሞሉ አሜሪካውያን ናቸው። እዚህም ሀገር ዘጠና ምናምን ሚልየን ህዝብ ጥሩ ተሳፋሪ ከሆነ ምን አነሰው። ጥቂት ጥሩ ሾፌሮች ብቻ ይበቁናል። የታሪክ ሾፌሮች፥ የፖለቲካ ሾፌሮች፥ የፍቅር ሾፌሮች፥ የሰላም ሾፌሮች፥ ጥላቻን የሚያነውሩ፥ ጥላቻን የሚንቁ፥ ጥላቻን የሚፀየፉ፥ አንድነት የጠማቸው፥ ፍቅር የራባቸው፥ ሰላም የጠማቸው ሰዎች ካሉን ዓድዋን ለሚቀጥለው አመት… እኔ እንደው ለዘንድሮውም ማመስገን አለብን።
እንደው ያቺ ዘፋኝ ማናት? ምን አገባህ እንዳትሉኝ። በማሪያም? (ሳቅ) … ያቺ ጂጂ የምትባለው። ግጥሟን ሸምድጄው ነበር በቃሌ። አቶ ዳዊት ወደፊት ዓድዋ በምትሰሩት ላይ በትልቁ ተራራው ላይ እንድትጽፉት።
የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት
እንደው ቃለ ህይወት ያሰማሽ ባለሽበት!! (እልልታ እና ረዥም ጭብጨባ) እንደዚህ አይነት ግጥም ነው የሚያስፈልገን።
‘የፍቅር ቀን’ ብለው ቀይ ልብስ ለብሰው አከበሩ፥ በጣም በእርግጠኝነት በ7 ያንን አክብረው በ8 የተለያዩ ሰዎች ሞልተዋል። ውሸት ነው። ዓድዋ ግን እውነት ነው።
ጣሊያኖች አሁን መጥተው ዓድዋን ሲጎበኙ የሚመኩ ይመስለኛል። ‘ያቺ ዓድዋ ነች ከመቶ ሀያ አመት በኋላም ዛሬም ኋላ ቀር ናት?’ ብለው የሚያፌዙብን ይመስለኛል። መንገዱን መቀየር፥ ህንጻውን መቀየር፥ ሀውልቶችን መቀየር አለብን።
ዓድዋ ላይ የአፄ ምኒልክን ሀውልት፥ አንጎለላ መንዝ ሰሜን ሸዋ ላይ የአፄ ዮሐንስን፥ የአሉላ አባ ነጋን ሐውልት መስራት አለብን። ድብልቅልቅ ብለን ለጠላት የማንመች መሆን አለብን። (እልልታና ከፍተኛ ጭብጨባ)
ለሚቀጥለው አመት የምመኘው ዓድዋ ላይ የአፄ ምኒልክን ሐውልት፥ እዚህ አዲስ አበባ ላይ የአፄ ዮሐንስን ሐውልት፥ ወለጋ ላይ የራስ አሉላን ሀውልት መስራት አለብን። ቅድም ዳንኤል እንደነገረን ስማቸው የማይታወቁ ጀግኖችን ፈልፍለን እያወጣን ከሾፌሩ ጋር አብረው ታሪክ የሰሩትን አደባባይ ማውጣት አለብን።
ቋንቋ ፀጋ ነው። ኦሮምኛ ፀጋ ነው። አማርኛ ፀጋ ነው። ትግርኛ ፀጋ ነው። ጉራግኛ ፀጋ ነው። ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የነዚህ ሁሉ ማስተሳሰሪያ ገመድ፥ የፀጋዎች ፀጋ ነው። ደህና እደሩ!! (ረዥም ያልተቋረጠ ጭብጨባ)
ለመምህራችን ቃለ ህይወት ያሰማልን።
ቸር አምላክ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ይጠብቅልን!!
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!