Tidarfelagi.com

ላምብ፤ የበግ ለምድ ለብሶ የመጣው ተኩላ ፊልም

ዘ ጋርዲያን <<ያሬድ ዘለቀ የሀገሩን ባህልና ወግ በሚያስደንቅ ሁኔታ አይቶ ያሳየበት ድንቅ ፊልም›› ብሎ ያወደሰው ላምብ ወይም ዳንግሌ በካን ፊልም ፌስቲቫል የ 68 አመት ጉዞ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ተመርጦ የታየ የኢትዮጵያ ፊልም ነው፡፡

ትላንት ፊልሙ በኤድና ሞል ሲኒማ እየታየ መሆኑን ስሰማ ሄጄ እስካየው ቸኮልኩ፡፡

ማታ ሄጄ ከማየቴ በፊት ስለፊልሙ በተለያዩ ድረ ገፆች ላይ በአመዛኙ በፈረንጆች የተፃፉ እጅግ ብዙ ሙገሳዎችን ሳነብ ቆይቼ ጉጉቴ ከፍ ባለበት ሰአት እዚሁ አዲስ አበባ ከእኔ በፊት ያዩት ጓደኞቼ የተሰማቸውን ያሉባቸውን ፅሁፎች ፌስቡክ ላይ አገኘሁ፡፡

የፊልም ባለሙያ የሆነው ዳዊት የተባለ ወዳጄ ፊልሙን <<….ግራ የሚያጋባ፣ አሰልቺ ….. ገፀባህሪያቱ ከአከባቢያቸው ጋር ክፉኛ የተነጠሉ ከመሆናቸው የተነሳ ‹‹ካንጋሮዎችን ሰሜን ተራራ ላይ እንደማየት›› ሆኖብኛል ….›› ብሎ ባነበብኩት ጊዜ ‹‹ምነው ጨከነበት›› ባሰኙኝ ቃላት የታጨቀ አስተያየቱን ፅፏል፡፡

ሌሎች ጓደኞቼ ያሉትን አየሁ፡፡ ሁሉም ‹‹እኔ አልወደድኩትም፣ አንቺ ግን ሂጂና ለራስሽ እይው›› አሉኝ፡፡

እናም ሄድኩ፡፡

ፊልሙን ላላያችሁትና ለምታዩት ሰዎች ክብር ሲባል የታሪክ ዝርዝር ውስጥ አልገባም ግን የተሰማኝ ይሄ ነው፡፡

1. ‹‹በእንግሊዝኛ አምሳል የተፈጠረ አማርኛ››

ከዚህ በፊት እንዳየነው፣ እንደውም ትንሽ ባስ ባለ ሁኔታ- ውጪ ሀገር አድገውና ኖረው በሚመጡ ‹‹ኢትዮጵያውያን›› ፀሃፊዎችና አዘጋጆች እንደተጻፉና እንደተዘጋጁ ፊልሞች ሁሉ ፊልሙ ላይ ያሉ ምልልሶች እጅግ ይቀፋሉ፡፡ አርቴፊሻል ናቸው፡፡ ምክንያቱም ፊልሙ በእንግሊዝኛ ታስቦና ተፅፎ ወደ አማርኛ የተመለሰ ምልልሶችና እና ንግግሮች ድሪቶ ነውና፡፡

በእንግሊዝኛ አምሳል የተፈጠረ አማርኛ የሚያወሩት በገጠር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ልቋቋመው የማልችለው ህመም ፈጥረውብኛል፡፡ እስቲ በፈጠራችሁ የትኛው የገጠር ልጅ ነው በጉን ‹‹አዝናለሁ እዚህ በማደርሽ …›› ብሎ የሚናገር? ‹‹የነጻነት ትኬታችንን ለማግኘት የሚያስፈልገን 120 ብር ብቻ ነው ›› የሚል? ‹‹የትኛዋ የገጠር ልጃገረድ ናት እናቷን ‹<እንዲህ ልትናገሪኝ መብት የለሽም ›› የምትል? የትኛዋስ ገጠር የምትኖር እናት ናት ልጇን ‹‹‹ደሞ ብለሽ ብለሽ እንደ ሴተኛ አዳሪ በዚህ ሰአት ገባሽ!›› የምትል….? ያማል፡፡ እጅግ ያማል፡፡

ይሄ ሁሉ ሲሆን ሃይ ባይ ሲጠፋ ደግሞ የበለጠ ያማል!

እንዴት በፊልሙ ላይ የተሳተፉ አንጋፋ የሚባሉ እዚሁ ተወልደው፣ እዚሁ አድገው ፣እዚሁ ሲተውኑ የኖሩ ተዋንያን ‹‹የለም የእኛ ሰው እንዲህ አያወራም›› ብለው ለመናገር አይዳዳቸውም! እንዴትስ ፀኃፊ እና አዘጋጁ ከአስር አመት እድሜው ጀምሮ በባእድ ሀገር እንደመኖሩ ‹‹እንዴት ነው…ይሄ ነገር ልክ ነው…?ይሄ አባባል በአማርኛ ስሜት ይሰጣል…?››ብሎ ደህና ሰው ሊያማክር፣ ብሎም ቀጥሮ ሊያሳይ አያስብም?

ያሬድ ከካን ፊልም ፌስቲቫል ይልቅ ፊልሙን አዲስ አበባ ማሳየቱ ፍርሃት እንዳሳደረበት ተናግሯል ሲባል አንብቤያለሁ፡፡ ልክ ነው፡፡ እዚህ ያለነው ቋንቋውን እና ባህሉን የምንረዳ ሰዎች ስለሆንን ሊፈራ ይገባ ነበር!

ከቋንቋው አኞነት በተጨማሪ ሲያሳቅቀኝ ያመሸው በፊልሙ ላይ የገቡ ፍፁም ስሜት የማይሰጡና እጅግ ግራ የሚያጋቡ አንዳንድ ንግግሮች ናቸው፡፡ ከብዙ ነገር አንድ ምሳሌ ብቻ ላምጣ፡፤ የፊልሙ ዋና ገፀ ባህሪ የሆነው ትንሹ ልጅ ኤፍሬም ከዘመዶቹ ጋር ለመኖር አዲስ ቤት ሲመጣ ያገኛትን የስጋ ዘመዱን ሴት ልጅ ‹‹መቀነትሽ ያምራል›› ሲላት መስማት እጅግ ይረብሻል፡፡ ከዚያ በላይ የሚረብሸው ግን ኤፍሬምና ይህች ዘመዱ ሲለያዩ በመኪና መስኮት መቀነቷን ፈትታ መስጠቷ ነው፡፡ በሀገራችን ‹‹መቀነት መፍታት›› ምን ማለት እንደሆን ያሬድ ያውቅ ይሆን!

2. ህዘቡ ተኩላ ሆኖ ተስሏል

በትንሹ ኤፍሬምና በሚወዳት በጉ ጩኒ ዙሪያ በሚያጠነጥነው ፊልም ላይ ከ ጅማሬ እስከ ፍፃሜ ኤፍሬም በጉ እንዳትታረድበት መላ ሲቀይስና ‹‹መከራውን ሲያይ›› የፊልሙ ፀሃፊና አዘጋጅ በኤፍሬም ዙሪያ ያለውን ማህበረሰብ፣ በተለይም ቤተሰቡን የኤፍሬምን በግ ለመብላት ያሰፈሰፈ ተኩላ ብቻ አድርጎ ስሎታል፡፡

ቤተሰቡ ፍቅር የሌለው፣ ለሆዱ ብቻ የሚያስብ፣ እንግዳን የሚንቅና ለጥቅም ብቻ የቆመ አድርጎ ያሳየናል፡፡ በተለይም በረሃብ የሞተች እናቱን ትዝታ ተሸክሞ ለመጣ ምስኪን የአደራ ዘመድ ልጅ አንድ የገጠር ቤተሰብ ሊሰጥ የሚችለው ነገር ይሄ ብቻ ነው ተብሎ መሳሉ የደራሲና አዘጋጁን ጠባብ እይታ የሚሳይ እና የሚያሸማቅቅ ነው፡፡

በድህነት ውስጥ ፍቅር የሚመግበውን፣ በረሃብ ውስጥ ፍቅርና ለልጅ መሳሳትን የሚያሳየንን፣ በከፋ ረሃብ ጊዜ እንኳን ‹‹ከብቶቼን አላርድም›› ብሎ ከእንሳሶቹ በፊት የሚረግፈውን ማህበረሰብ በእንዲህ ያለው ‹‹ለፊልሙ ሲባል በግድ በተፈጠረ›› ቤተሰብ መወከል ወንጀል ሆኖ ታይቶኛል፡፡

3. በመጨረሻም….ፊልሙ በፈረንጆች የተወደደበት ምክንያት ገብቶኛል!

ሆሊውድ ኬንያዊቷ ሉፒታ ኒዮንጎን ኦስካር የሸለማት የሚፈልጋት ቦታ ስላገኛት ነው፡፡ ባሪያ ሆና ስለሰራች፡፡

ሆሊውድ ዴንዘል ዋሽንትተንን በሙስና የተዘፈቀ ጥቁር ፖሊስ ሆኖ ሲሰራ ኦስካር የሸለመው የሚፈልገው ቦታ ስላገኘው ነው፡፡

ሆሊውድ ሆቴል ርዋንዳን መታየት ያለባቸው የምንጊዜም 250 ምርጥ ፊልሞች መካከል ያስቀመጠው የሚፈልገው ቦታ ስላገኘው ነው፡፡ የአፍሪካን ሰቆቃ የሚተርክ ስለሆነ፡፡
ቋንቋውን እና ባህሉን ለማያውቅ ሰው ላምብ ግሩም ፊልም ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ በተለይም አፍሪካን እና ኢትዮጵያን አንድ ሳጥን ውስጥ አስቀምጦ ከዚያ የወጣ ነገር ለማየት ፈቃደኛ ባልሆነ ምእራባዊ አይን ላምብ ግሩም ፊልም ነው፡፡ የሚፈለገውን ሁሉ ያሟላል፡፡

ከምእራቡ አለም በዘመናት ወደ ኋላ ቀርተው ሳሎናቸው ውስጥ በእንጨት ማገዶ የሚያበስሉ ሰዎችን ያሳያል፡፡ የአፈር ወለል ያለው ደሳሳ ጎጆ ውስጥ የሚኖሩ ችጋራም ኢትዮጵያውያንን ያሳያል፡፡ በረሃብ የሞተች እናትን ታሪክ ይናገራል፡፡ በግ አርደው ለመብላት ያሰፈሰፉ ረሃብተኛ ኢትዮጵያውያንን አጉልቶ እንካችሁ ይላል፡፡ ይሄ ለእነሱ አውነት ነው፡፡ ይህ ለእነሱ ልክ ነው፡፡ ስለዚህም ወደውታል፡፡

ምእራባውያን ስለ እኛ የሚሰሩትን ፊልም መቆጣጠር አንችል ይሆናል፡፡ ‹‹የእናንተ ነኝ›› የሚል ሰው ግን እነሱን ሆኖ ፣በእነሱ አይን አይቶን፣ እንደነሱ ሲፅፈን እና ሲያበጀን ማየት ያሸማቅቃል፡፡ ያሳቅቃል፡፡

እናውቃለን- ደሃ ነን፡፡ እናውቃለን – ረሃብተኞች ነን፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ደሃ እና ረሃብተኞች ብቻ አይደለንም፡፡ በድህነታችን እና ረሃባችን ውስጥ እሴት ያለን ሰዎች ነን፡፡ ራበን ብለን አደራ የምንሰለቅጥ ህዝቦች አይደለንም፡፡

ስለ ረሃብና ድህነት በሚተርክ ፊልም ውሰጥ ስብእናችን፣መተሳሰብና እንደ ህዝብ ያለንን ማንንት ለማሳየት የሚያስፈልገው ችሎታ ብቻ ነው፡፡

ያሬድ እና አጃቢዎች ያንን ለማድረግ የሚያስችል የፊልም ጥበብን እንደ ተካኑ ማየት አይከብድም፡፡ ግን አያውቁትም ወይም የሚያውቁን አልጠየቁም፡፡

እናም፤ ዘ ጋርዲያን <<ያሬድ ዘለቀ የሀገሩን ባህልና ወግ በሚያስደንቅ ሁኔታ አይቶ ያሳየበት ድንቅ ፊልም›› ብሎ ያወደሰው ላምብ ወይም ዳንግሌ ፊልም በካን ፊልም ፌስቲቫል ታይቶ የተወደደው ለእነሱ የሚፈልጉትን ኢትዮጵያ ስላቀረበ ይሆናል፡፡ እኔ እና መሰሎቼ ግን ታመንበታል፡፡

ያሬድ ዘለቀ ተወድሶበታል፡፡ እኛ ግን አፍረንበታል፡፡

2 Comments

  • ወዳጅሽ commented on November 18, 2016 Reply

    ህይወትዬ በጣም እንደምወድሽ እና እንደማከብርሽ ከመንገር ልጀምር!
    ፊልሙ ትላንትና ወደምኖርበት ከተማ ዘለቀና ለማየት ቻልኩ። ያልሽው ሁሉ በመጀመሪያ የተሰማኝ ስሜት ነበረ። እንደው በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር እንዲህ ይቀለዳል? ብዬ ታዝቤ ሳላበቃ ከአንድ ወዳጄ ጋር የጠለቀ ውይይት አደረግንበት። የታሪክ ፍሰት፣ የቋንቋ ቀናነት በሌለውና ታማኝነት በጎደለው ስራ ውስጥ በግልፅ ያላየሁትን አንድ ነገር ይሄ ወዳጄ አሳየኝ። ከለመድነው አካሄድ ወጣ ብሎ፣ ምቾት እያሳጣ ከምናየው ነገር ይልቅ ጠለቅ ያለ እውነት እንድንፈልግ ፊልመኛው መትጋቱን ተረዳሁ።
    በጊቱ ነፃነቱ ናት። በጊቱ በምንም ዋጋ ሊያገኛት የተመኛት እውነቱ ናት። የታመመች ህፃን ልጅ ቤት ውስጥ እያለች እንኳን እሷን አስረስቶ ወደሀገሩ ሊመለስ ሲተጋ ስናየው፣ ውጣ ውረዱ ብዙ ነው። ምን ልልሽ መሰለሽ?
    የለመድነውን አካሄድ ስላልተከተለ እንጂ ዝግ ብለው ካሰቡት እና ሌላ አይን ካገኙ ፊልሙ ብዙ ሊያወያዩ የሚችሉ ነጥቦች አሉት!
    የእንጀራ እናቲቱና የልጅቱ የአነጋገር ዘይቤ የአዲስአበቤ እንዲሆን ያደረገበት የራሱ ምህኛት እንዳለው ሁሉ ሰማሁ። ምን አለፋሽ! ወዳጄ! የማይሆኑ ያልኳቸው ነገሮች ሁሉ በምህኛት መግባታቸውን ስሰማ ይሄ ልጅ አንድ ለየት ያለ የጥበብ ዘውግ ለሀገራችን እንዳበረከተ ተሰማኝ። ነመስቴ! ብዬ አለፍኩለት!

  • Tegegn commented on February 8, 2022 Reply

    I need to be a memeber of this page

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *