አምላክ ሆይ! ይህንን የምፅፍልህ፣ ከአመት ለማታልፍ ፍቅረኛ በውሸት በኮሹ፤ በቆሸሹ ቃላት ከምቸከችከው ውዳሴ ከንቱ የተሸለ መሆኑን አምኜ ነው፡፡ የእውነት አምላክ ነህና የምትወደው እውነትን ነው፡፡ ስለዚህ እቅጭ እቅጯን እናወጋለን፡፡
ሃሳቤን ለሰዎች ባወጋቸው በአንተ ያምኑ ይመስል፣ ደም ስራቸውን ገትረው፣ ዐይናቸውን አፍጠው ይከራከሩኛል፡፡አንተ ግን እንደነሱ አይደለህም፡፡ ዝም ብለህ ታደምጠኛለህ፡፡ ብዙ ስናገር ሳትሰለች ትሰማኛለህ…. ነው እየሰማኸኝ አይደለም? አትፍረድብኝ፤ አንዳንዴ ልቅ ቁመት ያለው ዝምታ ካለማድመጥም እንደሚመጣ ስለምጠረጥር ነው፡፡ እንዲያ እንዳላስብ ደግሞ፣ ያንተ ፈጥኖ መልስ መስጠትን የመሰለ መልስ የለም፡፡
የትም ቦታ አለህ አይደል? …ያ ማለት በሃሳቤ፣ በእንቅልፌ፣ በንቃቴ፣ በእንቅስቃሴዬ፣ በትንፋሼ፣ በደሜ…. ወዘተ ውስጥ አለህ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጥሩ ባስብ ያ ጥሩ ሃሳብ ውስጥ አለህ ወይም ያ ሀሳብ አንተ ነህ ማለት ነው፡፡መጥፎ ባስብ እዛ መጥፎ ሀሳብ ውስጥ አንተ አለህ- መጥፈውን ሃሳብም ነህ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አንተ የትም ነህ! ሁሉም ነህ! የፈጠርከውን ሁሉ መሆን ትችላለህ፡፡ በደግነትም ሆነ በክፋት ውስጥ አለህ፡፡ በዓለም ላይ ያላንተ ፍቃድና እውቅና ውጪ የሚሆን አለን? … ሁሉም ባንተ ፍቃድ ነው ካልን፣ ደግን እንደምትፈቅድ ሁሉ፣ መጥፎ ነገሮች እንዲሆኑ የምትፈቅደው አንተ ነህ ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል መጥፎ ነገሮችን ታደርጋለህ፡፡ …ለመጀመሪያ ጊዜ መጥፎ የሰራኸው፣ መጥፎ ነገሮችን የፈጠርክ ጊዜ እንደሆነ ማስታወስ አይገባኝም መቼም፡፡ መጥፎን ከሚያደርግ የበለጠ፣ መጥፎን የፈጠረ ጥ/ክፋቱ አይበልጥም ትላለህ? …ብቻ እኛም በአምሳልህ ስለተፈጠርን መጥፎ ነገሮችን እንፈፅማለን፡፡ ልዩነቱ እኛ ሀጢያተኛ ስንባል፣ አንተን የሚልህ የለም፡፡ አንዳንዶች ይህን ሀሳብ ሳዋራቸው፤
“ መጥፎ በሌለበት ጥሩን እንዴት ማወቅ ይቻላል” ይሉኛል፡፡ እኔም “ አምላክ የሚሳነው የለም አላላችሁም ወይ?” እላለሁ፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
… ብዙ ጊዜ ሳስብ የሳጥናኤል ነገር ግርም ይለኛል፡፡ አንተ እጅግ ብዙ ሰራተኞች፣ ብዙ ስራ አስፈፃሚዎች አሉህ፡፡ ሴጣን ግን ብቻዋን ናት ማለት ይቻላል- ብቻዋን ባትሆንም ያንተን ያህል ባልደረባ እንደሌላት ግልፅ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ ዓለምን ስታንጰረጵረው የሚያህላት የለም፡፡ ይህ ሁሉ አማኝ፣ ይህ ሁሉ ላንተ ሰጋጅ፣ ወዳንተ የመጣው በጉያህ ከሳጥናኤል ሊሸሸግ እንደሆነ አታጣውም መቼም፡፡ አንዳንዴ አስባለሁ፤ ይህ ሁላ ሰው ላንተ ነው ለሳጥናኤል እየሰገደ ያለው? እርግጥ የሚሰገደው አንተ “ጉልበት” ስር ነው፡፡ ግን ለማን ነው የሚሰገደው? ገነት ለመግባት ነው፣ ሲኦል ላለመግባት?( ገነትን ሲሹ አገኙህ ወይስ ሲኦልን ሲሸሹ?) የሴጣን የተደረገውን ሞት ለማምለጥ ወይስ አንተ የምትለውን ህይወት ለማግኘት? …. መልሱ ጥያቄ ውስጥ አለ፡፡
እንደው ስለሴጣን ካነሳን አይቀር፣ እስቲ ስለ አፈጣጠሩ እናውራ፡፡ እንዳአባባልህ ሴጣን ሲፈጠር ሴጣን አልነበረም፤ አንተ “ሰይጣንን” አልፈጠርክም፡፡ የፈጠርከው መላዕክ ነው፡፡ የሰጠኸውም የመላዕክትን ባህሪ ነው፡፡ እሱ ግን እንደፈጠርከው አልሆነም፣ አሊያም አንተ እንደፈለከው አልፈጠርከውም፡፡ እንዴት ነው መላዕክ ፈጥረህ፣ ሴጣን ሊሆንብህ የቻለው? የሆነ ነገሩ ተበላሽቶብሃል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሴጣን መላዕክ ልትሰራ አስበህ `ሴጣን` የሆነብህ ፍጥረት ነው፡፡ በአጭሩ ሴጣን የአንተ የእጅ ስራ ክሽፈት ነው፡፡ ከተሳሳትኩ አርመኝ፤ ሕዝቦችህ ባለመረዳት መንገድ እስከ መቼ ሲወለካከፉ ዝም ትላለህ?
…. እንደ መፅሐፉ እውርም ዲዳም የምታደርግ አንተ ነህ፡፡እንዲህ የሚያደርገው “ክብሩን ሊገልፅ ሲፈልግ ነው” ይባላል፡፡ ቆይ ያንተ ክብር አካል ካልጎደለ አይገለፅም? ለናተ የክብር መግለጫነት ሲባልስ፣ የገዛ ፍጡራንህን ማሰቃየት አለብህ? እንደምን ሆኖስ፣ “ ሁሉ በእጅህ፣ ሁሉ በደጅህ” እየተባለ የክብር መሻት ደጅህ ተገኘ? ክብር እኮ የኛ የተራዎቹ ጥያቄ ነው፤ አንተን እንደምን ያሳስብ፣ ያስጨንቅሀል?
ዳንኤል በአንበሳ ጉድጓድ በወደቀ ጊዜ፣ ሕይወቱን ያዳንክ አንተ፤ ዛሬ አንዲት ሕፃን በሕይወት እያለች በእሳት ስትቃጠል፣ የሁለት ዓመት ህፃን፣ በ40 ዓመት ወፈፌ ስትደፈር መመልከት እንደምን አስቻለህ? በቃ ጥቅም ካልሰጡህ ታደርግላቸው የለህም? ብቻ ይሄም ክብርህን ለመግለፅ እንዳይሆን፡፡
…እንደነዲሞክራተስ አገላለፅ፣ አቶም የማይከፈል፣ የማይፈጠርና የማይጠፋ ነው፡፡ ይሄን የሰሙ አንዳንዶችም፣ “እግዚኣብሔር አቶም ነው” ይላሉ፡፡አንተ እራስህን ማን ትላለህ? …. መቼም ፈጣሪ ነህና ጥያቄን የፈጠርከው አንተ ነህ፡፡ እኔም በጠየቁህ ቁጥር የፈጠርከውን መልሼ ወዳንተ እየላኩ እንጂ፣ በራሴ ጥያቄ እየተፈታተንኩህ እንዳልሆነ ስለማውቅ አልፈራም፡፡እዚህ ጋር አንድ ጥያቄ ልጨምር፤ … “በሰው ዘንድ 1000 ቀን፣ በአንተ ዘንድ አንድ ቀን ነው ይባላል፡፡ እኔ ግን እጠይቃለሁ፣ “ገደብ የለሽ” ሆነህ ሳለ፣ እንደምን በዚህ አንድ ሺ ቀን ውስጥ ተቀነበብክ? ምን ማለት ነው ይሄ?! አንድ ቀን የሆነው ባንተ ዘንድ፣አንድ ሺ አንድ ቀን መሆን አይችልም ማለት ነው? ገደብ የለሽ ከሆንክ እኮ፣ የኛ አንድ ቀን፣ ላንተ 1 ሚሊዮን…. ኸረ የምን አንድ፣ 2 ሚሊዮን እንጂ … 2 ሚሊዮንም ገደብ ነው ….. ዝምብለው አይነካም፣ አይለካም! ብለው ቢያልፉህ ምን ነበረበት? በቁጥር የሚቀመጥ ነገር ሁሉ ገደብ አለው፤ ልኬቱ ተደርሶበታል ማለት ነው፡፡ የኛ አንድ ቀን፣ አንተ ጋር 1000 ቀን ከአንድ ደቂቃ መሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ እና ይሄ ከባህሪህ አይጣላም? ገደብ ያለው አያደርግህም? … ጥያቄን ጥያቄ ያነሳዋል መቼም፣ ሌላ ጥያቄ ላንሳ እስቲ፡፡ … እኔ የምለው ቆይ? የድሮ እንስሳት ማውራት ይችሉ ነበር እንዴ? ታዲያ እንዴት ነው ሄዋንን እባብ ያናገራት? … ይህን ጥያቄ፣ ለቅርቦችህ ሳቀርብላቸው፣ “ ሴጣን በውስጡ አድሮ ነው” የሚል ተመሳሳይ መልስ ይሰጡኛል፡፡ እኔም ሌላ ጥያቄ ጠየኩ፣ “ሄዋን ይሄን ማወቅ የሚያስችል ንቃተ ህሊና የላትም ነበር?” ታዲያ እሷ እራሷስ ከእንሰሳ በምን ትለያለች? እባቡስ ቢሆን፣ ከሴጣን አቅም በታች ሆኖ ሳለ፣ ሴጣን ስለተገለገለበት ብቻ መረገም አለበት? መፅሐፉን ወደ ተረትነት አያወርደውም? እውንቱን ንገረኝ ካልክ፣ ባንተ ዘንድ ያለው አመክንዮ ምንም ጭራው ሊያዝልኝ አልቻለም፡፡ ….. አፍቃሪህ ነን ባዮቹን እንኳን፣ በጠየኳቸው ጊዜ፣ የሚያውቁትን ከማስረዳት ይልክ፣ ጅብ እንዳየ ውሻ አከታትለው ይጮሃሉ፡፡ እኔ ትቻቸው ከሄድኩ በኋላ እንኳን አያቋርጡም- “ጅብ ከሄደ….”
እመንም አትመን ግን ከነርሱ እኔ እሻልሀለው፡፡ እኔ የልቤን እነግርሃለው፡፡ስቀየምህ ቅያሜዬን ገልፅልሃለው፡፡ መንገድህን ካልወደድኩ፣ መንገዴን እመርጣለሁ፡፡ እነሱን ግን እያቸው እስቲ፤ ሞባይላቸውን ክፈት ለምሳሌ! …መቼም ሁሉን ታያለህ አይደል? ‘format’ … ‘ delete’ ‘empty’ …. ምንምን የሚሉ ፎልደሮችን ከፋፍተህ ተመልከት፣ የተከፋፈቱ ወንድና ሴት ታገኛለህ፡፡ “Pornography” ይለዋል የኛ ዓለም፤ “ማመንዘር” ይለዋል ያንተ ቀለም፡፡ እኚህ ናቸው እንግዲህ ላንተ ጠበቃ ለመሆን የሚሹት፡፡ አንተን ለመከላከል መነሳታቸው በራሱ፣ እራስህን መከላከል እንደማትችል አቅመ ቢስ መመልታቸውን አያሳይም ጌታዬ? ታዲያ ከዚህ በላይ ምን አለ? አምላክ ለሚያህል አካል፣ “እኔ አውቅለታለሁ” ከማለት ወዲያ ወንጀል የት ይገኛል ?
በሰዎችና በአንተ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲህ ባይሆን እወድ ነበር፡፡ አንተ ግን አቋም ከወሰድክ ወሰድክ ነው፡፡ ፍንክች አትልም፡፡እኔም ይህን ሁሉ ለፈለፍኩ -ምንም ላላመጣ፡፡ ይህን ሁሉ ግን ከመፃፌም በፊት ታውቀው ነበር- ሁሉን አዋቂ ነሃ! ከዚህም በላይ ብፅፍ ምንም አዲስ ስለማልነግርህ ይብቃኝ፡፡