ይቅርታ! ፓለቲከኛ ያልኩት ተሳስቼ ነው። የአሁኗ ሚስቴ ሃይማኖተኛ ናት።ፓለቲካኛ ያልኩት በቀደመው ትዳሬ ተፅዕኖ ነውና ይቅር በሉኝ።
የአሁኗ ሚስቴ ጴንጤ ናት።
አንድ ሰው ታሞ እያጣጠረ ብታገኝ፣ ራበኝ እያለ አጠገቧ ቢያጣጥር አንድ ጉርሻ በመስጠት ፈንታ«ቆይ አንዴ ልፀልይለት ብላ እጇን በላዩ ላይ» የምትጭን ናት።
ገላዋ ናፍቆኝ ፍቅር ልንሰራ ፈልጌ ብጣደፍ፣
«ኸረ ማሬ»
«እ»
«በስም አብ በል እንጂ» ትለኛለች።
ሁለ ነገሯ እየሱስ ነው። እንቅፋት ቢመታት እየሱስ፣ ቢያስነጥሳት እየሱስ፣ ዐይኗ ትንሽ ቢገባ እየሱስ ይጠራል።
ቢዘገይም፣ ሃይማኖት መንፈሳዊ ፓለቲካ መሆኑ ገባኝ።
ቤቴ ስገባ፣ ተሰብስበው፣ዐይናቸውን ጨፍነው የሚፀለዩ ብዙ ሰዎች አገኛለሁ።ሴቶቹን ከሷ መለየት ያቅተኛል።አሁን ያቺ ጓደኛዋን በሷ ቦታ ባገባ፣ እሷን ደግሞ ከማግባት በምን ይለያል እላለሁ።አስር ቢሆኑም አንድ ሆነዋል። በእየሱስ አንድ ሆነናል ትለኝ የለ እሷስ።
ነገሯ ሁሉ፣ ፓስተር እንትና እዚህ ያስተምራል።እዛ ቸርች እንሄዳለን፣ ጆሽዋ ሊመጣ ነው… በሚል የታጠረ።
ሰዎች፣ «ትዳራችሁን እየሱስ ይግባበት» ብለው ሲመራረቁ እሰማለሁ። በእኔ እና እሷ ትዳር ግን እየሱስ ቤተኛ ሆነ።
ቤታችንም የእየሱስ ነው።
«ማሬ፣ እየሱስ ማመን ጥሩ ነገር ነው። ግን የሰጠንንም አቅም መጠቀም ያለብን አይመስልሽም? »
«ምን ማለትህ ነው። ያለ እየሱስ የሰው ልጅ ምን አቅም አለው። ሰው እኮ ያለ እየሱስ ትል ነው፤ገባህ? … ደሞ እርግጠኛ ነኝ እንዲህ የሚያናግርህ መንፈስ ነው! ፕሮግራም ይዘን እንፀልይልሃለን»
«ፍቅር ምን ሆነሻል፣ የምን መንፈስ ነው።»
«ተወኝ ባክህ እኔ ዐይቼ ነው የማውቀው። መንፈስ እንዳለብህማ ዐይንህ ውስጥ ያስታውቃል። እየሱስ መንፈሳዊ ፀጋ ሰጥቶናል»
ቤቴ መጥተው ሲፀልዩ በይሉኝታ መሃላቸው ቆሜ ተሳትፊያለሁ። በመሃል ሚስቴ በልሳን ስታወራ ደጋግሜ ሰምቻለሁ።
ይሁን፣ ይሄስ መንፈሳዊ ህይወት ነው። ታዲያ ለምንድነው በትዳራችን ውስጥም ልሳን የምትናገረው? ለምንድነው የምትለው የማይገባኝ? የምላትስ የማይገባት?
ቤታችን ውስጥ ሁሉ ነገር የእየሱስ ነው።ቴሌቭዥኑ የእየሱስ ነው።ሪሞቱ የእየሱስ ነው።ቴሌቪዥኑ ስለ እየሱስ የሚያወራ ጣቢያ ላይ ካልሆነ ትነጫነጫለች።ዜና ላይ ስላት ትቆጣለች።
«ጠቢቡ ሰለሞን ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም ያለውን አልሰማህም?! ምን ለማግኘት ነው ዜና የምታየው? ከእየሱስ ክርስቶስ ውጪ አንዳች አዲስ ነገር የለም»
ትዳር መቻቻል ነው ብዬ ዝም እላለሁ።ለሁለተኛ ጊዜ ላለመፍታት ራሴን አስገድጄው ተቀመጥኩ።
ሰው ተቸግሮ ስትሰጥ አላይም፣መንግስት ቢከፋ ቅር አይላትም(መንግስትን የሚያወጣም የሚያወርድ እሱ ክርቶስ ነው። የኛ ስራ የሱን ፍቃድ መፈፀም ነው ትላለች። የፍቃዱን ጊዜ አልጠይቃትም። እሷም አትነግረኝም)
… መርፌ ለጠፋበትም፣ የህይወት መንገድ ለጠፋበትም መፍትሔዋ ፀሎት ነው።
«ማሬ»
«ወዬ»
«ገላሽ ናፍቆኛል»
«ገላ በናፈቀን ጊዜ የምንጫወትበት ተራ ነገር አይደለም። የእየሱስ ቤተ መቅደስ ነው። አርፈህ ተኛ»
ኩም!
«እሺ»
ቢሆንም ላልፈታት እየታገልኩ ነው።
እየሱስ ያድናል ብላኛለች። ይሁን፣ ትዳራችንንም ያድነው።