የኛ ሕዝብ ሲከፋውም ሆነ ሲደሰት ሥነ-ቃሎችን ተጠቅሞ ብሶቱን፣ ችግሩንና ደስታውን ይገልፃል። ጉልበት ኖሮት በትር ባይወዘውዝም፣ ዘገር ባይነቀንቅምና ጠመንጃ ባይወድርም፣ ተንኳሹን፣ በዳዩን ወይም አጥቂውን ወገን በሥነ-ቃል ያለፍራቻ ያወግዛል። ይሄን ሲያደርግ እታሰራለሁ፣ እገረፋለሁ ወይም እሰቀላለሁ የሚል የፍራቻ ስሜት ልቡ ውስጥ ሽው የሚልበትም አይመስል። ይህ ዓይነቱ የሕዝብ እንደፈለገ ወይም እንዳሻው የመናገር ድፈረት በእጅጉ ያስደንቃል፤ ያስቀናልም። አንደው በሞቴ፣ በገና ጨዋታ ጊዜ አጤ ምኒሊክ በግላጭ የተተረቡባቸው (የተሸነቆጡባቸው) የተባሉት የሚከተሉት ዓይነት ሥነ-ቃሎች በአድናቆት አያስደምሙም?
ቅማል ምን ታሳዝን ዳርዳሩን ስትባዝን፣
ራቷን ለቃቅማ እምን ስርፋ ትኛ (ትተኛ)! (አጤ ምኒሊክ መላጣ ነበሩ አሉ።)
ታሪክ እንደሚነግረን ታዲያ የሄንን የገና ላይ ጨዋታ የሰሙት ነጉስ ምኒሊክ፣ “ተጫወቱ… ተጫወቱ…” በሚል ያበረታቷቸው ነበር ይባላል።
ጽድቅና ኩነኔ እንዲህ ያስታውቃል፣
ከከንፈሮ ተርፎ ጥርሶ ጣይ ይሞቃል። (አጤ ምኒሊክ የፊት ጥርሳቸው ወጣ ወጣ ያለ ነበር ይባላል።)
የነዚህ ዓይነቶቹን የሕዝብ ሥነ-ቃላዊ ውርጅብኞች በባህላዊው የገና ጨዋታው ላይ ተገኝተው ያደምጡ የነበሩት እምዬ ምኒሊክ፣ በተለይ የመጨረሻዋ ሥንኝ በተወረወረችባቸው ጊዜ፣ ‹‹በቃኝ!…በቃኝ!›› ብለው ከመሄድ በዘለለ በ‹እንዴት ተደፈርኩኝ› ቁጣ ያዙኝ ልቀቁኝ አለማለታቸው ይነገርላቸዋል። በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ!
ከዚህም አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ በተከሰተ ጊዜ ለሰፈራ ይሰደድ የነበረው የሃገራችን ሰው ቅሬታውን ለፈጣሪም ጭምር በሥነ-ቃል ይገልፅ ነበር።
ቀና ብዬ ሳየው ሰማዩ ቀለለኝ፣
አንተንም ሰፈራ ወሰዱህ መሰለኝ።
እንዲህ እንዲህ እያልኩ መሰል አንዳንድ ሥነ-ቃሎችን በመምዘዝ ላጫውታችሁ ከጀልኩ። ለዛሬው በዓፄ ቴዎድሮስና በዓፄ ዮሐንስ ዘመነ-መንግስት የተባሉትን በጨረፍታ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። በምንጭነት የተጠቀምኩባቸው መጽሐፍት የአለቃ ተክለ-ኢየሱስ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ› እና የጳውሎስ ኞኞ ‹አጤ ቴዎድሮስ› መሆናቸውን ከወዲሁ አሳውቃለሁ።
ደጃች ብሩ፣ የጎጃሙ ገዢ የነበሩት፣ የደጃች ጎሹ ልጅ ናቸው። ደጃች ጎሹ ደምቢያ፣ ጉራምባ ላይ ከዓፄ ቴዎድሮስ ጋር በተደረገ ጦርነት ተገለዋል። ዓፄ ቴዎድሮስ አልበገር ብለው ያስቸገሯቸውን እኚሁን የጎጃሙን ደጃች ብሩን ከያዙ በኋላ ጭልጋ ውስጥ ካለው አርባ ከሚባለው ቦታ በእስር አስቀመጧቸው። እዚያ ታስረው በቆዩ ጊዜም ሚስታቸው ወ/ሮ የውብዳር ከእልፍኝ አሽከሮች አንዱን መርጠው ውሽምነት ያዙ። ይሄንን ጉድ ደጃች ብሩ እስር ላይ እያሉ በሰሙ ጊዜ፣ በገና እየደረደሩ እንዲህ በማለት አንጎራጎሩ።
“መከራን በሰው ላይ እንዲያ ሳቀለው፣
ምንኛ ከበደኝ እኔ ብይዘው።
መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ፣
ሲገሰግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጂ።
ዘሃው ለሰለሰ ሸማኔው ተቆጣ፣
እስተወዲያው ድረስ መጠቅለያው ታጣ።
የኔታም አይምጡ እኔም አልመለስ፣
ዋ ቢቸና ቀረ እስተወዲያው ድረስ።
ከእልፍኝ ሰው አይግባ፣ ሚስቴን ሰው አይያት አይሉም አይሉም፣
ፈረሴን ሰው አይጫን፣ በቅሎዬን ሰው አይጫን አይሉም አይሉም፣
ጠጁ ቀጠነብኝ፣ ሥጋው ጎፈየብኝ አይሉም አይሉም፣
ቀን የጣለ ለታ፣ የጨከነ ለታ ይደረጋል ሁሉም።
አጤ ቴዎድሮስ የደጃች ብሩን ማዘን በመገንዘብ፣ ፈታችሁ አምጡልኝ ብለው አዘዙ። ብሩም ከታሰሩበት ተፈትተው መጥተው ቴዎድሮስ ፊት ቀረቡ። ያን ጊዜ ራሳቸውን ተከናንበው ነበር። በዘመኑ ይደረግ እንደነበረውም፣ ‹ይማሩኝ› ለማለት ሎሚ የምታህል ድንጋይ በትከሻቸው ላይ ይዘዋል። አጤ ቴዎድሮስ ይህን ባዩ ጊዜ ተቆጡና፣ ‹‹አሁንም ትዕቢት አለቀቀዎትም?›› አሉ፣ ገረሜታን በተላበሰ ድምጽ።
‹‹ክንብንቡ እንደሁ የጭልጋ በረሃ ጠጉሬን ጨርሶት ባፍር ነው፣›› ሲሉ ደጃች ብሩ መለሱ።
ቴዎድሮስም፣ ‹‹(እንግዲያው) ከበራዳው ስፍራ ከመቅደላ ይቆዩ። እኔማ ልፈታዎ ነበረ። ነገር ግን ክርስቶስ ማቆያ የትዕቢት ምክንያት አመጣብዎ። ፈቃዱ ሲሆን ይፈታሉ፣›› ብለው በ1846 ዓ.ም ወደ መቅደላ ሰደዷቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግሊዞች ለአጤ ቴዎድሮስ ሱላድ የሚባል ጠመንጃ በስጦታ ይልኩላቸዋል። ቴዎድሮስ የተሰጣቸውን ጠመንጃ ተኩሰው ለመፈተሸ ፈለጉ። ጠመንጃው ባሩድ ያለመጠን በዝቶበት መጉረሱን የተመለከቱት ጳጳሱ፣ አቡነ ሰላማ፣ ‹‹አይሆንም፤ እንዳትተኩስ፣›› ሲሉ ይከለክሏቸዋል። ቴዎድሮስ እተኩሳለሁ ብለው ቢያንገራግሩ፣ ጳጳሱ በቁጣ ገዘቷቸው።
ይኸው አዲሱ ጠመንጃ በአንዱ የቴዎድሮስ ጋሻ ጃግሬ ቢሞከር፣ ከባሩዱ ብዛት የተነሳ የኋልዮሽ ተራግጦ ተኳሹን ገደለው። አጤ ቴዎድሮስ በደረሰው አደጋ በጣም ያዝኑና ለደጃች ብሩ፣ ‹‹የምወደው አሽከሬ ሞቶብኛልና የለቅሶ ግጥም ያበርክቱልኝ፣›› ሲሉ ላኩባቸው።
ደጃች ብሩ፣ ቅን የማይናገሩ ትዕቢተኛ ነበሩና ለተላከባቸው መልዕክት እንዲህ ሲሉ በግጥም መልስ ሰጡ፤
‹‹አቡን ባይገዝቱ ያ ባሪያ ባይኖር፣
ያበሻ መከራ ያልቅለት ነበር።››
ቴዎድሮስም፣ ‹‹ዕድሜ ይፍታዎ። ራስዎን ጎዱ እንጂ እኔን አልጎዱኝም፣›› ብለው እስሩን አጠበቁባቸው።
ደጃች ብሩ በስልጣን ዘመናቸው ይሰሩት በነበረው ግፍ ሕዝቡ አይወዳቸውም ነበር ይባላል። አለቃ ተክለ-ኢየሱስ እንደጻፉት ብዙ ግፍ የሰሩ ሰው ናቸው። አንድ ጊዜ መሽገውበት በነበረው በሶማ አምባ ላይ ምስጥ አስቸገረ። ‹‹ጉንዳን ቢኖር ኖሮ ምስጥ አይኖርም ነበር፣›› የሚል ወሬ የሰሙት ደጃች ብሩ በደረቤ ሕዝብ ላይ የጉንዳን ግብር ጣሉበት። በየወረዳው ያለ የደረቤ ሕዝብ አስር እንስራ ጉንዳን እንዲያዋጣ ብለው አዋጅ አስነገሩ።
የህ አዋጅ የተነገረበት የደረቤ ሕዝብ በሥጋ ላይ ጉንዳን እየሰበሰበ በእንሥራ ሲከት ከረመ። እንስራው ሲሞላም በቅጠል እየወተፈና በትከሻው እየተሸከመ ወደ ሶማ ይጓዝ ገባ። ጉንዳኑም ከእንሥራው ውስጥ እያፈተለከ እየወጣ ተሸካሚውን ቢነክስ፣ የባሰ ቅጣት የተጣለበት ባላገር እንደምንም እያለ ሶማ ደረሰ። ያን ጊዜ ታዲያ ባላገር ብሶቱን እንዲህ ሲል በስንኝ ተነፈሰ።
‹‹ከመከራው ሁሉ የጉንዳኑ ባሰ፣
የተሸካሚውን ጆሮ እየነከሰ።››
ዓፄ ቴዎድሮስ ጎጃምን ካስገበሩ በኋላ ወደሸዋ ለመሻገር ሲገሰግሱ፣ የወሎ ዘራፊ (ሽፍታ) አላሳልፍ ብሎ አስቸገራቸው። ከብዙ ውጊያ በኋላ፣ ሰራዊታቸው በርትቶ እየተዋጋ ምርኮ ማምጣት ጀመረ። ቶዎድሮስም በመጀመሪያ የመጡትን 47 ምርኮኞች አስቀርበው ሁለት ሁለት እጆቻቸውን እያስቆረጡ በገመድ አንገቶቻቸው ላይ አንጠልጥለው ወደመጡበት ሰደዷቸው። ከዛ በኋላ ይሄን ያየ ወሎዬ በሙሉ ሸሽቶ መንገዱን ከፈተላቸው። የወሎዎችን እጅ መቆረጥ ያየ ቀልደኛም፣
‹‹እራቱንስ ሚስቱ ታጉርሰው፣
ኧረ ቂጡን በምን ያብሰው!›› ብሎ ተናገረ ይባላል።
ባላምባራስ ገልሞ (የዓፄ ቴዎድሮስ የጦር መኮንን) ከደጃዝማች ጎሹ ጋር በተደረገው ጦርነት ላይ ሸሽተዋል ተብሎ ተወርቶባቸው ነበር። አንዲት አዝማሪ ካሣ ፊት ቀርባ፣
‹‹አይሸሽም ያልከው ገልሞ እንኳን ሸሸ፣
የደምቢያን ግራር እያበላሸ፣›› ብላ ገጠመች።
ካሣም ወዳጃቸውን ባላምባራስ ገልሞን የሚያንኳስሰውን የአዝማሪዋን ግጥም እንደሰሙ፣
‹‹አብለሻል እንጂ እውነቱን አላልሺም፣
በዙበት እንጂ ገልሞ አይሸሽም፣›› ብለው በግጥም መለሱላት።
የትግሬው ገዥ ደጃች ውቤ በአጤ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ታስረው ቆይተው በ1859 ዓ.ም ሞቱ። ውቤ ለቴዎድሮስ አማች ናቸው። ደጃች ውቤ ትግራይን ለ24 ዓመታት ገዝተዋል። እሳቸው ከመሞታቸው በፊት በዓፄ ቴዎድሮስ ግዛት ማንም ዘመድ የሞተበት ሰው እንዳያለቅስ በአዋጅ ተከልክሎ ነበር። ይሁን እንጂ፣ የሟች ልጅና የዓፄ ቴዎድሮስ ሚስት፣ ጥሩወርቅ፣ ያባታቸውን ሞት ሲረዱ፣ ተከልክሎ የነበረው ለቅሶ እንደገና በአዋጅ ተፈቀደ። ሕዝቡም ለደጃች ውቤ በማስመሰል ቀድሞ ለሞተበት ዘመዱ ሁሉ አለቀሰ ይባላል። ይህን ያጤነች አንዲት አልቃሽ እንዲህ በማለት የለቅሶ ሙሾዋን አወረደች፤
‹‹የኔታ ደጃዝማች ሁልጊዜ ደግነት፣
ዛሬ እንኳን ለደሃው እንባ አተረፉለት።››
ዓፄ ቴዎድሮስ ከራስ ዓሊ ጋር (የሚስታቸው የእቴጌ ተዋበች አባት) አይሻል በሚባል ቦታ ላይ ያደረጉትን ጦርነት በአሸናፊነት ደምድመው ሲመለሱ፣ የደጋ ዳሞት ሕዝብ ወጥቶ ከደከመው የካሣ ሰራዊት ፈረስና በቅሎ ይማርክ ጀመር። በየጥሻው እየተደበቀና አፋፍ ላይ እየሆነ፣ ‹‹የጎሹን ደመኛ፣ የዓሊን ወደረኛ ትለቀዋለህን!›› እያለ ብዙ አስቸገረ። ያላሰቡት ችግር ያጋጠማቸው ደጃች ካሣ፣ ሰገድ ከሚባለው ቦታ ሲደርሱ ሠራዊታቸውን፣ ‹‹በለው!›› ብለው አዘዙ። ትእዛዝ በማግኘቱ የተደሰተው ሠራዊት ብዙውን ዘራፊ ባላገር ፈጀው። አንዲት የደጋ ዳሞት ሴት ባልዋ ለዘረፋ ወጥቶ በመገደሉ እንዲህ ስትል አለቀሰችለት ይባላል፤
‹‹አመጣለሁ ብሎ የካሣን ፈረስ፣
ሳያርመው ሞተ የዘራውን ገብስ።››
ራስ ዓሊ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የእናታቸው ስም ሐሊማ መባሉ ቀርቶ መነን እንዲባል በአዋጅ አስነገሩ። ሐሊማ ሲል የተገኘም ሰው ብርቱ ቅጣት እንደሚጠብቀው ተለፈፈ። አንድ ቀን ታዲያ ራስ ዓሊ ግብር አስገብተው ሲበላና ሲጠጣ፣ በመሃል ላይ ቆሞ ታዳሚውን ሲያዝናና የነበረ አንድ አዝማሪ እንዲህ የሚል ስንኝ ይቋጥራል፤
‹‹ዓሊ ማን ይላታል እናቱን?
እኛስ የምንላት እቴገ መነን።››
ይሄ አዝማሪ፣ ትርጉሙ ለጊዜው ባልተገለጠላቸው ራስ ዓሊ የ‹አበጀህ› ሽልማት እንደተበረከተለት ይነገራል።
ዓፄ ቴዎድሮስ ሸዋን አስገብረው የጎጃሙን ተድላ ጓሉን ለመውጋት በመጡ ጊዜ፣ እሳቸውን በመቃወም የሸፈተውን ሁሉ እየማረኩ ይሰቅሉ ነበር። ብዙ ሰው መሰቀሉን ያየች የጎጃም አልቃሽ ታዲያ እንዲህ ስትል በሙሾ ተቀኘች፤
‹‹ወይ አልተባረከ ይሄ ሁሉ ሰው፣
ንጉሥ መስቀልዎን ቢተውት ምነው?››
የማሳለሚያ መስቀልን አስመስላ መናገሯ ነው።
አንድ ቀን አንዲት ሴት ቴዎድሮስ ዘንድ ቀርባ እጅ ነሳች። ቴዎድሮስም፣ ‹‹ሞያሽ ምንድን ነው?›› ሲሉ ጠየቋት። ሴትየዋም፣ ‹‹የከተማ ቅሬ (ሴትኛ አዳሪ) ነኝ እንጂ፣ ሥራ የለኝም፣›› ብላ መለሰች። ቴዎድሮስም፣ ‹‹እግዚአብሔር ሁለት እጆች የፈጠረልሽ እንድትሰሪባቸው ነበር። ለመብል ብቻ ከሆነ ግን፣ አንድ እጅ ይበቃሻል፣›› ብለው አንድ እጇን አስቆረጧት። ያን ግዜ ታዲያ እንዲህ ተብሎ ተገጠመ፤
‹‹ማረስ ይሻላል፣ መገበር፣
እጅ እግርን ይዞ ለመኖር፤
አላርስም ያሉ አልነግድ፣
ተመለመሉ እንደግንድ።››
የጎጃሙ ተክለ-ሐይማኖት ለዓፄ ዮሐንስ አልገብርም ቢሉ፣ ዮሐንስ በ1880 ጎጃምን ሊመቱ ጦራቸውን ዝመት አሉት። ከብትና ንብረት ተዘረፈ፤ ቤት ተቃጠለ፤ ሰው አለቀ። ያን ጊዜ ታዲያ ከብቷን የተዘረፈች፣ ልብሷን የተገፈፈች የጎጃም አልቃሽ እንዲህ አለች፤
በላይኛው ጌታ በባልንጀራዎ፣
በቅዱስ ሚካኤል በጋሻ ጃግሬዎ፣
በፅላተ ሙሴ በነጭ አበዛዎ፣
ጎጃምን ይማሩት ፈሪም አንልዎ።
ዓፄ ዮሐንስ ደርቡሽን ሊወጉ ወደ መተማ በዘመቱ ጊዜ፣ ከብቷን የተዘረፈች፣ ልብሷን የተገፈፈች ሌላዋ የጎጃም ሴት እንዲህ ብላለች፤
ዘንድሮ ንጉሡ ደህና ቢመለሱ፣
ምንኛ ጎልድፏል ጎጃሜ ምላሱ።
ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ህብረተ-ሰቡ ሥነ-ቃልን ተጠቅሞ ሃሳቡን የሚገልፀው በችግር ጊዜ ብቻም አልነበር። በጥጋብም ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ሥነ-ቃል ግልጋሎት ላይ ስለማዋሉ የሚከተለው ማስረጃ ያሳየናል። አለቃ ተክለ-ኢየሱስ፣ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ› በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፤ ‹‹ጥጋብ በሆነ በዓመቱ የስናን ኢየሱስ ደገኛ፣ ድንች ያወፈራት፣ እንኳን ባመቱ በኑህ ዘመን እማይረሳውን ዘመነ-ረሃቡን ድሮ ረስታው ጠገበችና እንዲህ አለች፣
ጉንጨም ቅጥ አጣ፣ ቂጤም ቅጥ አጣ፣
እባክህ ጌታዬ የአምናውን ቀን አምጣ።››
-የጽሁፉ መጨረሻ-