በኢትዮጵያ ታሪክ ለረጅም ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት አቶ መለስ ዜናዊ የተወለዱት ግንቦት 1/1947 በትግራይ ክልል በአድዋ ከተማ ነው። የልደት ስማቸው “ለገሠ ዜናዊ” ነበር። “መለስ” በሚለው ስም መጠራት የጀመሩት በሚያዚያ ወር 1967 ገደማ ለትግል ወደ ደደቢት በረሃ ከወጡ በኋላ ነው። በወቅቱ እርሳቸው በተቀላቀሉት ተሓሕት (ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ) ደንብ መሰረት ለቤተሰብ ደህንነት ሲባል ስምን መቀየር የተለመደ ስለነበረ ነው መለስም ስማቸውን የቀየሩት። “መለስ” የሚለው ስም በ1967 መጋቢት ወር “ከጀብሃ ሃይሎች ጋር ተባብረህ የአዲስ አበባን ማዘጋጃ ቤት በፈንጂ አጋይተሃል” ተብሎ ከተረሸነው “መለስ ተኽለ” ከተባለው ወጣት ስም የተወሰደ ነው። እዚህ ገደማ ግን አንድ ነገር ልብ ሊባል ይገባል።
እነ መለስ ዜናዊ የመሰረቱት “ተሓሕት” ለትግራይ ህዝብ በመፋለም ረገድ የመጀመሪያው ድርጅት አይደለም። ከዚህ ድርጅት በፊት በ1966 መገባደጃ ላይ “ግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ” (ግገሓት) የተባለ ድርጅት በትግራይ ተራማጅ ወጣቶች ተመስርቶ ነበር። ይህ ድርጅት በአብዛኛው በኤርትራው “ጀብሃ” የሚደገፍ ሲሆን እስከ የካቲት 1967 ድረስ በትግራይ ገጠር አካባቢዎች አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን አካሂዶ ነበር። እንደዚሁም ጀብሃ በአዲስ አበባ ባካሄዳቸው የቦምብ ፍንዳታዎች ተሳትፎ እንደነበረው ይነገራል።
በየካቲት 11/1967 የተመሰረተው ተሓሕት ከግገሓት ጋር ለመዋሀድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር ይባላል። ይሁንና ሁለቱ ድርጅቶች ሊስማሙ አልቻሉም። በሁለቱ መካከል ለተከሰተው ፍጥጫ ትክክለኛው ምክንያት ምን እንደነበረ መገመት ያስቸግራል። የተሓሕት አባላት የነበሩት ግገሓት ገበሬውን በማስጨነቅና የሀገሬውን ህዝብ አስገድዶ በመዝረፍ የሽፍታ እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆኑ ተሓሕት እርምጃ ለመውሰድ እንደተገደደ ይናገራሉ። ከግገሓት ጋር ቅርበት የነበራቸው ምንጮች ግን ተሓሕት የትግራይ መሬት ከአንድ ድርጅት በላይ የመሸከም አቅም የለውም በሚል መሰሪ ዓላማ ተነሳስቶ ድርጅታቸውን እንዳጠፋው ነው የሚገልጹት። ከሁለቱም ወገን ያልነበሩ ታዛቢዎች ደግሞ ድርጅቶቹ እስከ መጠፋፋት የደረሱት ሻዕቢያ እና ጀብሃ ከጀርባቸው ስለነበሩ ነው ይላሉ።
ያም ሆነ ይህ ግገሓት በትግራይ ምድር ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ መቆየት አልቻለም። እርሱ ሲጠፋ የትግል ሜዳው ለተሓሕት አመቺ ሆኖለት ነበር ለማለት ይቻላል።
——
መለስ ዜናዊ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በድርጅቱ አመራር ውስጥ አልነበረም። ከርሱ ይልቅ ድርጅቱን ይመሩ የነበሩት እነ አረጋዊ በርሀ (በሪሁ)፣ ግደይ ዘርዓ ጽዮን (ፋንታሁን)፣ መሓሪ ተኽለ (ሙሴ )፣ ዘርዑ ገሠሠ (አግዓዚ)፣ ኣባይ ጸሐየ (አታኽልቲ)፣ ስዩም መስፍን (እምባዬ) እና ስብሐት ነጋ (አግዓዚ) ነበሩ። የመለስ ዜናዊ ፖለቲካዊ ስብዕና ጎላ ብሎ መታየት የጀመረው በ1969 በድርጅቱ ላይ የመበተን አደጋ በተጋረጠበት (በድርጅቱ ታሪክ “ሕንፍሽፍሽ” ተብሎ በሚጠራው) አስቸጋሪ ወቅት በተለይም የገለልተኝነት ስሜት ከነበራቸው ወጣቶች ጋር በማበር ድርጅቱን ለማትረፍ ብዙ በመልፋታቸው ነው ይባላል። በወቅቱ መለስ በፖለቲካ ስራዎች ላይ የተመደቡ ኮሚሳር ነው የነበሩት። አንዳንድ የሕንፍሽፍሽ ንቅናቄ መሪዎች “መለስ ዜናዊ አንድ ውጊያ በማበላሸቱ የሞት ፍርድ ሊፈረድበት ይገባል” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ቢጽፉም ይህንን ጉዳይ ከነጻ ወገን ለማረጋገጥ አልተቻለም። ሆኖም ብዙሃኑ ጸሐፊያን መለስ በወቅቱ ገለልተኛ ነበረ በሚለው ይስማማሉ።
—-
በ1971 ድርጅቱ ስያሜውን “ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ” (ሕወሓት) ብሎ ሲቀይር መለስ ዜናዊ የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኑ። በዚህ ወቅት መለስ የድርጅቱ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ኃላፊ በመሆን የካድሬዎችና የፖለቲካ ኮሚሳሮችን ስልጠና በበላይነት ይመሩ ነበር። ለአቶ መለስ ዜናዊ ይህ ጊዜያቸው ወርቃማ ዘመናቸው ነበረ ለማለት ይቻላል። ምክንያቱም ይህ ወቅት ለስልጠና የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎችን ለማዘጋጀት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከፕራግማቲክ ታጋይነት ወደ ጥልቅ አንባቢነት የተለወጡበት ጊዜ ስለሆነ ነው። ይህ ከንባብ ጋር ያዳበሩት ቁርኝታቸው ውጤቱ በ1977 በተካሄደው የድርጅቱ ጉባኤ እና የማሌሊት ንቅናቄ ወቅት በግልጽ ወጥቷል። በነገራችን ላይ መለስ ዜናዊ ከባለቤታቸው ከአዜብ መስፍን ጋር በፍቅር የወደቁት በዚህ ወቅት ነበር። ሆኖም በድርጅቱ ደንብ መሰረት በወቅቱ ጋብቻ ቀርቶ የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ እንኳ ለከባድ ቅጣት የሚዳርግ በመሆኑ መለስ አዜብን ለማግባት ስድስት ዓመታትን መጠበቅ ነበረባቸው።
—-
እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1977
መለስ ዜናዊ እጅግ ከፍተኛ እመርታ በማሳየት የድርጅቱ የወደፊት ዓይን መሆናቸውን ያስመሰከሩበት ዓመት ነበር። በዚህ ወቅት በድርጅቱ ውስጥ ኮሚኒዝምን በሰፊው ማስረጽ ይገባል በሚል እሳቤ አንድ የፓርቲ አስኳል ተመስርቶ ነበር። ይህም “ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ” (ማሌሊት) የሚባለው ሲሆን የዚህ እንቅስቃሴ መሪዎች ዓባይ ጸሐየ እና መለስ ዜናዊ ነበሩ። ይህ ፓርቲ “ኮሚኒስታዊ ርዕዮት በትክክለኛ መልኩ ወደ ታጋዩ እና ወደ ህዝቡ ካልሰረጸ ትግላችን ውጤታማ አይሆንም፤ ውጤታማ ቢሆን እንኳ አብዮታችን ሊቀለበስ ይችላል የሚል” እይታ ነበረው። ድርጅቱ በወቅቱ ኮሚኒስታዊ በመሆኑ እነ መለስ ታጋዩን ለማሳመን ብዙም አልቸገራቸውም። ነገር ግን “እነ መለስ የሚሉት ነገር ጽንሰ ሃሳባዊ እንጂ ፕራግማቲክ አይደለም፤ በተጨባጭ ለመተግበር የማይቻል ጽንሰ- ሃሳብ እያመጣን ታጋዩን ማወዛገቡ ይቅርብን” የሚል ተቃውሞም ተነስቶ ነበር። የዚህ ተቃውሞ መሪዎችም አረጋዊ በርሀ እና ግደይ ዘርዓ ጽዮን ነበሩ።
ሁለቱ እይታዎች በየፊናቸው ድጋፍ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ በወቅቱ የገለልተኝነት አቋም ያሳዩ የድርጅቱ አመራሮች “ነገሩ ሌላ ውዝግብ ከማምጣቱ በፊት በጉባኤ ይለይለት” የሚል የመፍትሔ ሃሳብ አቀረቡ። በዚህ መሰረት መለስ ዜናዊ የማሌሊትን አቋም፣ በመወከል ግደይ ዘርዓ ጽዮን ደግሞ የአፍቃሬ-ፕራግማቲክ ጎራውን በመወከል በ600 ጉባኤተኞች ፊት እንዲከራከሩ ተጋበዙ። (በወቅቱ ክርክሩን በዳኝነት የመሩት አርከበ ዕቁባይ ነበሩ)።
መለስ ዜናዊ እና ግደይ ዘርዓ ጽዮን ለሁለት ሰዓታት ያህል የጦፈ ክርክር አደረጉ። በመጨረሻ ግን አንደበተ ርቱእ የሆኑት መለስ ዜናዊ ጉባኤተኛውን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ቻሉ። በተለይም ግደይ ዘርዓ ጽዮን “በቀኝ በኩል ካፒታሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን፤ በግራ በኩል የሶቪየት ከላሽነትን የምትዋጋና የራሷን ሉዓላዊነት በማስከበር ሶሻሊዝምን መገንባት የቻለች አንዲት ሀገር በምሳሌነት ማቅረብ ትችላለህ?” በማለት ላቀረቡት ጥያቄ አቶ መለስ ዜናዊ “እንዴታ! አልባኒያ ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች” የሚል ቅጽበታዊ መልስ መስጠታቸው ጉባኤተኛውን በረጅሙ አስጨብጭቦት እንደነበረ ታሪኩን የሚያውቁ ሰዎች በተደጋጋሚ የጻፉት ጉዳይ ነው።
ከዚህ ጉባኤ በኋላ ግደይ ዘርዓ ጽዮን እና አረጋዊ በርሀ በድርጅቱ ውስጥ ብዙም አልቆዩም። መለስ ዜናዊ ግን የድርጅቱ የፖሊት ቢሮ አባል ሆኖ የተመረጠው በዚህ ጊዜ ነው።
—-
እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1981
መለስ ዜናዊ ከፖሊት ቢሮ አባልነት ወደ ድርጅቱ ሊቀመንበርነት ያደጉበት ዓመት ነው። በዚህም ወቅት ነው ሕወሓት እና ኢህዲን በጥምረት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የሚባለውን ድርጅት የመሰረቱት። አቶ መለስ ዜናዊ ከህወሓት ሊቀመንበርነታቸው በተጨማሪ የኢህአዴግ ሊቀመንበርም ሆኑ። በሚቀጥሉት 23 ዓመታትም በዚሁ ስልጣናቸው ላይ ቆይተዋል።
አቶ መለስ ዜናዊ ከግንቦት 28/1983 ጀምሮ ኢትዮጵያን በመሪነት አስተዳድረዋል። ምዕራባዊያን በስልጣን ዘመናቸው ኢትዮጵያን አሳድገዋል እያሉ ያሞካሹአቸዋል። እነ ኢሰመጉ፣ ሂዩማን ራይትስ ዋች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግን በስልጣን ዘመናቸው ለተፈጸሙት ህገ-ወጥ ግድያዎች፣ አፈናዎች፣ እስራቶችና የአካላት መጉደል ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሚያደርጉት እርሳቸውንና ድርጅታቸውን ነው። እነ ሲፒጄ እና Reporters without borders ደግሞ በየጊዜው የፕሬስ ጠላት ሲሉዋቸው ነበር።
አቶ መለስ ዜናዊ በአንባቢነታቸው፣ ነገሮችን ቶሎ በመገንዘብ ብቃታቸው፣ ቅጽበታዊ ዘዴ በመፍጠር ችሎታቸው፣ ከጠላቶቻቸው ፈጥነው እርምጃ በመውሰዳቸው ብዙ ተብሎላቸዋል። ታዛቢዎች ግን ራሳቸውን ብቻ እየካቡ ድርጅቱን ገድለውታል በማለት ይወቅሷቸዋል። በእርግጥም በኢህአዴግ ውስጥ የመለስ ዜናዊን የፖለቲካ ክህሎት፣ አንደበተ ርቱዕነትና ዘዴ የመፍጠር ችሎታን የተካነ ሌላ ሰው አለ ለማለት አይቻልም። አሁን ካሉት የኢህአዴግ መሪዎች አንዱም እንኳ የመለስ ዜናዊን ያህል ወዝ ያለው ፖለቲከኛ ሆኖ አይታይም። ይሁንና ለዚህ ክፍተት መፈጠር መለስ ዜናዊን ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ማድረግ ይከብዳል። ምናልባት ድርጅቱን ለዚህ የዳረገው ከኮሚኒስቶች የተወረሰው “ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” የሚባለው አሰራር ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ምክንያቱም ይህ አሰራር ብዙ ጊዜ የፓርቲ መሪዎችን ስብዕና እያጎላ ከነርሱ ህልፈት በኋላ መሪዎቹ የነቢይን ያህል እየገዘፉ የሌሎቹ አስተዋጽኦ ሙሉ በሙሉ እንዲዘነጋ የሚያደርግበት የታሪክ ክስተት ታይቷይልና። ለምሳሌ የሩሲያው “የሶቪየት ህብረት ኮሚኒስት ፓርቲ” (ቦልሼቪክ) በስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን የሁሉም ሶሻሊስት ሀገራት ካድሬዎችና ኮሚሳሮች “ሌኒን እንዳለው” የሚል አባባል ሲደጋግሙ የነበሩበትን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል።
——
ኢትዮጵያዊያን መለስ ዜናዊን በልዩ ልዩ መልኩ ነው የሚያዩዋቸው። ተቃዋሚዎቻቸው “ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተላከ የሰይጣን መልዕክተኛ ነው” ይሏቸዋል። ደጋፊዎቻቸው ግን “ለመበታተን የቀረበውን የኢትዮጵያን አንድነት የታደጉና ኢትዮጵያን ያሳደጉ ታላቅ ነቢይ ናቸው” ይላሉ። ሁለቱም አባባሎች ከእውነታው ዓለም ያፈነገጡ ናቸው። መለስ ዜናዊ ሰይጣንም ነቢይም አልነበሩም። እርሳቸው እንደ ሁላችንም ግለሰብ ነበሩ። ለመሪነት ያበቃቸው ያለፉበት የትግል ሂደት እና የወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ነበር።
መለስ በርግጥ ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት በመሰላቸው መንገድ መድከማቸው በትክክል ይታወቃል። በዚህም ልዩ ልዩ ውጤቶችን ማስመዝገባቸው ተመስክሯል። በተለይም ኋላቀር የሚባሉት ክልሎች ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የተወጠነላቸው በርሳቸው ጊዜ ነበር። መለስ በዲፕሎማሲው መስክም የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ሚና ለማጉላት ብዙ ሰርተዋል። የህዳሴ ግድብ የተባለውን ፕሮጀክት በመወጠን ረገድም ከማንም በላይ ሚና የነበራቸው እርሳቸው ናቸው። በነገራችን ላይ “ይህ ግድብ የዐረብ አብዮት ስለተቀጣጠለ በሀገር ቤት ተመሳሳይ አብዮት እንዳይቀሰቀስ ለመከላከል ሲባል የተፈጠረ የአትኩሮት ማስቀየሻ ነው” የሚባለው አነጋገር ትክክል አይደለም። መለስ የግድቡን ግንባታ በይፋ ከማሳወቃቸው ትንሽ ቀደም ብሎ “ግብጽ ጫካ ሳይኖራት፣ ለጫካ ውጊያ የሰለጠነ ሠራዊት አላት፣ እኛ ያሻቸውን ቢያደርጉ እንኳ በውሃው የመጠቀም መብታችንን እናስከብራለን” በማለት የሰጡት መግለጫ ግንባታው አይቀሬ እንደነበረ የሚያሳውቅ ነው።
ይሁንና መለስ ዜናዊ ለህዝባቸውና ለወገናቸው ዲሞክራሲና ፍትሕን በማምጣት ረገድ ያን ያህል አልተጓዙም። ለምሳሌ መለስ በ1997 ጥሩ የተባለ ምርጫ አካሂደው ነበር። በምርጫው ዙሪያ የተፈጠሩ ውዝግቦችን በሽምግልናና በግልግል መፍታት እየቻሉ የንጹሐንን ደም ያፈሰሰ እርምጃ መውሰዳቸው የታገሉለትን ዓላማ ወደ ኋላ የቀለበሰ ጥቁር ነጥብ ተደርጎ ተቆጥሮባቸዋል። እንደዚሁም በርሳቸው ዘመን በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች የኦነግ አባል ነህ በሚል ጥርጣሬ ብቻ ታፍሰው ያለ አንዳች ፍርድ በእስር ቤት መማቀቃቸው መንግስታቸው ከብዙ ኦሮሞዎች ጋር ሆድና ጀርባ እንዲሆን አድርጎታል።
አንድ የማይታበል ሐቅ ግን አለ። ሰውዬው ችሎታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጎለበቱ መምጣታቸውን መካድ አይቻልም። ለምሳሌ መለስ ዜናዊ ስልጣን በተቆጣጠሩበት ዘመን ስለሚናገሩት ነገር ብዙም አይጨነቁም። ወደ ኋላ ላይ ግን ይህ አመላቸው በብዙ መልኩ ተቀይሯል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ጣሊያን ላይ በጠፉበት ጊዜ “ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ከምናወጣው ብር ይልቅ ለገበሬዎቻችን የምናደርገው ድጎማ ይበልጥብናል” ያሉት መሪ ወደ መጨረሻው አካባቢ የስፖርት ተቆርቋሪ ሆነው መገኘታቸው የዚሁ ምስክር ነው።
መለስ ዜናዊ የአፍሪቃ ህብረት ጽ/ቤት ከአዲስ አበባ እንዲወጣ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት እርምጃውን ለማስቀልበስ ያደረጉት ጥረትና የወሰዷቸው እንቅስቃሴዎች ከተቃዋሚዎቻቸው ጭምር ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል። ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ያለ አንዳች ልዩነት መለስ ዜናዊን ያደነቁበት ንግግር ቢኖር የአዲስ አበባን የአፍሪቃ ህብረት መቀመጫነት ለማረጋገጥ እልህ በተሞላው ስሜት የተናገሩት ያ የደርባኑ ታሪካዊ ንግግር ነው። ኢትዮጵያ ደሃ ሆና ሳለ በየጊዜው በጂ-8 ስብሰባ ላይ እየተጋበዙ መገኘታቸውም ከድርጅታቸው ይልቅ የርሳቸውን ፖለቲካዊ ብቃት የሚያሳይ ምልክት ተደርጎ ነው የተወሰደው።
ሆኖም መለስ ዜናዊ አንዳንድ ጊዜ የሰሩትን ነገር መልሰው ሲያበላሹት ታይተዋል። ለምሳሌ “በአፍሪቃ ህብረት ግቢ ውስጥ የክዋሜ ንክሩማህ ሃውልት ተተክሎ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ መረሳታቸው ተገቢ አልነበረም” የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ትክክለኛ ሆኖ ሳለ አቶ መለስ ጥያቄውን ከድሮ ስርዓት ናፋቂነት ጋር ማያያዛቸው ከትዝብት ላይ ጥሎአቸዋል። በርግጥም የአፍሪቃ ህብረት ጉዳይ ሲነሳ ከማንም በላይ ለተግባራዊነቱ በእጅጉ የደከሙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ነበሩ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤን በሌሎች ብዙ ነገሮች ብንወቅሳቸውም በዚህ በኩል የሚስተካከላቸው አንድም የአፍሪቃ መሪ የለም።
በሌላ በኩል መለስ አላግባብ የሚከሰሱበት ሁኔታም አለ። የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በተነሳበት ወቅት መለስ ዜናዊ “ጦርነት መዋጋት ሀገራችንን ይጎዳል፤ እኛ ደሃ ነን፤ ካለፈው ጦርነት ለማገገም ብዙ መስራት ይጠበቅብናል” በማለት የሰነዘሩት ሀሳብ በተቃዋሚዎቻቸው ዘንድ “ተንበርካኪነት” ተብሎ ተተርጉሞባቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ የእናታቸውን ትውልደ-ኤርትራዊ መሆን በመጥቀስ “ኤርትራዊ ደም ስላለው ነው እንዲህ የሚለው” በማለት የዘረኝነት ቅስቀሳ አካሂደውባቸዋል።
ያም ሆነ ይህ የኢኮኖሚው ነገር ሲነሳ መለስ ዜናዊ ጥሩ አስተዋጽኦ ኖሮአቸው ይሆናል። የዲሞክራሲውና የመልካም አስተዳደር ነገር ሲነሳ ግን ድሮ ያሳዩት ጭላንጭል ሁሉ በመጨረሻ የህይወት ዘመናቸው እየከሰመ ነው የመጣው። መለስ በ1984 እና በ1997 በተካሄዱት ምርጫዎች ወቅት ለተቃዋሚዎቻቸው ያሳዩትን ሆደ ሰፊነት በህይወታቸው መጨረሻ ገደማ ጠቅልለው ወስደውታል። የጸረ-ሽብር ህግ እየተጠቀሰ ጋዜጠኞችን ማሰር፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ማንገላታት፣ በእምነቶች አካባቢ በመግባት አንዱን ቡድን ደግፎ ሌላውን በአጥፊነት መፈረጅ ወዘተ… በህይወታቸው መጨረሻ ገደማ ገሃድ ሆነው የወጡ የመንግሥታቸው ህጸጾች ነበሩ።
እንዲያም ሆኖ ግን መለስ ዜናዊ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደነበራቸው መካድ አይቻልም።
—–
መለስ ዜናዊ በቀልደኝነታቸውና ተረት በመተረት ችሎታቸውም ይታወቃሉ። ይህ ቀልደኝነታቸው በርሳቸው ስም የተለያዩ ፈጠራዎች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኖኣል። እኛም ጽሑፋችንን የምናገባድደው በመለስ ስም የተፈጠሩትን ሁለት ቀልዶች በመጋበዝ ይሆናል።
—
ምርጫ-97 ከተካሄደ ከጥቂት ወራት በኋላ አንዱ ጋዜጠኛ ለአቶ መለስ ዜናዊ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረበላቸው።
ጋዜጠኛ፡ “ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር፤ ምርጫው ቲያትር ነበር ይባላል። በርግጥ ምርጫው ቲያትር ነበር እንዴ?”
መለስ ዜናዊ፡- “ቲያትር አልነበረም። ደበበ እሸቱ በምርጫው በመሳተፉ ቲያትር የመሰላቸው ካሉ ተሳስተዋል”።
—-
መለስ ዜናዊ ወደ ቤልጅየም ለጉብኝት ሄደው ነበር። እዚያ ባደረጉት ስብሰባ ከተጋበዙት ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዷ ሃሳብ ለመስጠት ተነሳች።
ወጣቷ፡- “የርስዎ መንግሥት በጣም አስጠሊታ ነው፤ ስርዓታችሁ አስጠሊታ፤ አካሄዳችሁ አስጠሊታ፤ ባለስልጣኖቻችሁ አስጠሊታ፤ ሁለመናችሁ አስጠሊታ ነው”::
መለስ ዜናዊ፡ -“ጥሩ ነው፤ አስጠሊታ ልንሆን እንችላለን፤ አሁን እዚህ የመጣነው ግን ለቁንጅና ውድድር አይደለም”።
——
ግንቦት 1/2007
አዳማ- መሃል ኢትዮጵያ
One Comment
asteyayet yalemestet ngr nw enji nazret lay berkata anbabi alachu. bertulen ye websitu structurem mirt nw. pls bezu entebekalen.
*** THANKS***