አብዬ መንግስቱ ለማ እጅግ ሲበዛ አስተዋይ ነበሩ።
አማሪካን ሀገር ሄደው ተምረው ሲመለሱ ከሀሳብ ሁሉ ገዝፎ ሀሳብ የሆነባቸው ከአንድ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ጋር ድንገት ቢገናኙ ሊጠይቃቸው የሚችለው ጥያቄ ነበር። ውጪ ተምረው እንደመጡ ሲያወሩ ድንገት የሰማ ገበሬ ጠጋ ብሎ “መርፌ ትሠራለህ? ” ብሎ ቢጠይቃቸው የሚመልሱት ጠፍቷቸው በዝምታ ተውጠው ድርቅ ብለው ሲቀሩ መልስ ያላገኘው ገብሬ ጥሏቸው ወደሚነዳቸው አህዮች እየሮጠ ሲሄድ ያስተውሉታል። በሀሳባቸው!!
በመርፌ አሮጌ ጨርቁን ሠፍቶ ያሠነብታል። በመርፌ በእግሮቹ መሃል ሠርሥሮ በመግባት ደሙን የሚመጠውን ሙጀሌ መንግሎ ያወጣበታል። በእሳት አግሎ እባጩን ይበጣበታል።
አዎ! ለዛሬ ምሁራንና እንዳሸን በፈሉት ዩኒቨርሲቲዎች ስለት ሲማዘዝ ለሚውለው ተማሪ የገበሬው ጥያቄ ዛሬም ” መርፌ ትሠራለህ!? ነው። የምትመረቁበት ዲግሪ መርፌ ለገበሬው አባታችሁ ከምትሠጠው ጥቅም በላይ ፋይዳ እንዳለው ማረጋገጥ ይቅደም። ነጋሪት ይመስል በዱላ ስትናረቱ ገበሬው ቢያያችሁ ጥያቄው ” መርፌን ትበልጣለህ!”?ሳይሆን ይቀራል?
በሀገራችን ከያንዳንዱ መቶ ሰው ሰማንያ አምስቱ በገጠር ይኖራል። ሥራውም አፈር እየገፋ እኛን ከተሜ ሳንሆን በከተማ የምንኖረውን መቀለብ ነው።
” መ ር ፌ እ ን ሠ ራ ለ ን!!!?”
©Alemayehu Areda