“እጅ እድፉን ያየበትን አይን ጉድፍ ያፀዳል”
ተቆራኝተው የኖሩት የአካል ክፍሎቻችን በእድሜ ብዛት ሲወራረሱ “እጅ አይንን ተክቶ፥ አይን ግን እጅን ይተካ ዘንድ አይቻለውም” ስል ያሰብኩት ዛሬ በምተርክላችሁ ገጠመኜ ነው።
ለፊልም ስራ ባህርዳር ከተማ ዙሪያ በነበርኩበት ወቅት እንዲህም ሆነ።
ፊልሙ – የገጠር ያውም የሽፍታ ታሪክ ነበረና “አብራራው” የተባለው የድሮ ጠመንጃ አስፈለገ። “አብራራው” ስሙን ያገኘው ለማቀባበል ከሚወስደው ጊዜ ተነስቶ ይመስላል። አንድ ሰው ነገር ስያረዝም “አብራራው” እንደሚባለው ማለት ነው።
ይህን ጠመንጃ ፈልጎ ማግኘት ቀላል ቢሆንም ፈቃጅ ማግኘቱ ግን እጅጉን ያለፋል። ምክንያቱም የጦር መሣሪያ ነዋ። ከፖሊስ ሊገኙ የሚችሉት መሣሪያዎች ዘመናዊ በመሆናቸው አንዱን የየአካባቢው ሠው ማሳመን ግድ ሆነ።
“አብራራው”ን አስፈቅደን ቀረጻ ላይ ለማዋል “አብራራው” ከሆኑ አቶ አዝመራው ከተባሉ ሰው ጋር ስንለማመጥ ስንነታረክ አረፈድን። በኋላ በቀን 50 ብር ክፍያ ተስማምተን ያለ ጥይት አብራራውን ተከራየነው።
“አብራራው” በጠዋት ስራ ጀምሮ ፀሀይ ስትጠልቅ “በሞክሼው” (የጠመንጃው ባለቤት) ወደ ቤቱ ይወሰዳል። እንዲህ እንዲህ እያለ ጥይት አልባው ጠመንጃ የፊልም ባለሙያ ሆነ።
ብዙውን ጊዜ በቀረጻ ወቅት ደጋግሞ ማቀባበልና ቃታ መሳብ የተለመደ ስለሆነ ከዚህ ቀደም ሰርቶ የማያውቀውን ከባድ እንቅስቃሴ ለመደ። ለካንስ ይህ አሮጌ መሳሪያ እለት በዕለት በሚገጥመው ከባድ ስራ የቃታው ማስፈንጠሪያ እየላሸቀ ሄዷል። ከተቀባበለ በኋለ ቃታውን ለመሳብ በማሰብ ብቻ ተወንጭፎ መርፌውን ይመታል።
ጠመንጃ በባህሪው ልክ እንደ ውሀ እያሳሳቀ ነው የሚወስደው። “ወይ ወደ መሬት፥ አልያም ወደ ሰማይ ተደርጎ ነው የሚነጣጠረውም፥ የሚተኮሰውም።” የሚለውን መርህ ለመሻር ጥይት አልባውን አብራራው ለሁለት ቀናት ብቻ ሲያቀባብሉ እና ቃታ ሲስቡ መዋል በቂ ነው። ከዛ በኋላ ማቀባበሉም ሆነ መተኮሱ በወዳጅ ላይ ልክ እንደ ቀልድ ነው የሚቆጠረው። ጥይት የጎረሰለት መጉረሱ ይዘነጋና የዕለት ቀልድ ሊቀጥል ይችላል።
አንድ ቀን ታዲያ ጠመንጃው ጥይት ሲጎርስ መቀረጽ ስለነበረበት ባለ ንብረቱ ጥይቶች ይዞልን መጣ። ጥይቱን ተከትሎ ዝናብ መጣ። ቀረጻው ተስተጓጎለ። ጠበቅን ጠበቅን አያባራም። “ለበጎ ነው” የሚለውን ጥቅስ ያስታወሰ ማንም አልነበረም። ተበሳጭተን ተስፋ ቆርጠን እቃችንን ጠቅለን የገጠሩን መንደር ለቀን ወደ ባህር ዳር ተመለስን።
የአብራራው ባለቤት እዛችው መንደር ባለች “አንጓች አረቄ ቤት” ውስጥ የላሸቀውን ጠመንጃ ጥይቱን አጉርሶ፥ እንደነገሩ ነቅነቅ ሲያደርገው ተፈትልኮ መርፌና እርሳስ ተገናኝተው ባረቀ። በተአምር ማለት ይቻላል አንድም ሰው ሳይጎዳ አካባቢውን አሸብሮ የተደረደሩ 6 ትላልቅ ጋኖችን በታትኖ ቤቱን በ ጠላ ጎርፍ ሞላው።
የተፈጠረውን ድንጋጤና ከባድ የቁጭት ስሜት ለመረዳት ቦታው ላይ መድረስ አላስፈለገንም ወሬው 42 ኪ.ሜትሮችን አቆራርጦ ባህርዳር ሳለን ሰማን። የነበረን ምርጫ ከቦታው መሰወር ብቻ እስኪመስለን ድረስ ተደናገጥን። የአብራራው ባለቤት አቶ አዝመራው ግን “የምወዳትን ጠመንጃዬን አሰሩልኝ እንጂ እግዜብሔር ባዘዘው ገብቼ እናንተን አልወቅስም” አለ።
ያስጠነቀቀው ግን ታዲያ “ጠመንጃዬ ያልተሰራች እንደው ይቅርታም አላደርግ” ብሎ ነው። በአካባቢው አሉ የተባሉ የመሳሪያ አዋቂዎች ዘንድ ተንከራተትን። የመሳሪያው አሮጌነትና በአይን ለማየት አስቸጋሪ የሆነውን የውስጡን ክፍል ለይቶ ማን ይወቀው። እንግዲህ ፀባችን እርግጥ ሆነ ስንልም ሁላችንም ሰጋን።
በዚህ ግዜ ነበር አንድ ወዳጄ ባህር ዳር ሆስፒታል አካባቢ አንድ ባለሙያ መኖራቸውን የጠቆመኝ። ወደተባሉት ሰው የመጨረሻ እድል ለመሞከር ሄድኩ።
እኚህ ሰው ጋሽ ጥላሁን ይባላሉ። በአካባቢው ስመጥር ናቸው። ግን ሸምግለዋል። ሽማግሌ መሆናቸውን ስሰማ አይሳካም ስልም አመነታው። ነገር ግን “የባሰ ለካንስ አለ” አልኩ ቤታቸው ደርሼ ሳያቸው። በእርጅና ምክንያትም አንድ አይናቸው ከናካቴው ሲጠፋ ሌላው ደግሞ ጭል ጭል ከሚል ብርሀን ውጪ ማየት አይችሉም።
“አሰላሳይ አገናዛቢ” ነኝ ብሎ ለሚታበይ ሰው በሙሉ የሚመጣለት፥ “ጊዜ መግደል ጥሩ አይደለም” የሚል ሀሳብ ነው። እኔም ቢሆን እንዲያ ማለቴ አልቀረም።
ነገር ግን ሰውየው። አብራራውን ተቀበሉኝና ከመቅስበት በእጃቸው ዳብሰው በስሙ ጠሩት። “አብራራው” አሉ። ትንሽም ቢሆን ላምናቸው ሞከርኩ። እሳቸው ለዘመናት የሚያውቁትን መሳሪያ እኔ ያን ሰሞን ስላወኩት የምበልጣቸው መስሎኝ ነበር። የሥህተቴ ብዛት።
እኚህ ሰው ፊታቸውን ወደ ጣራው መልሰው ጥቂት ዳብሰውት “ሰው አገኘባችሁ ታዲያ?” አሉ። “ሰምተው ነበር እንዴ?” አልኳቸው። “ምንም አልሰማሁም። ምላጭ ማስወንጨፊያው ከጥቅም ውጪ መሆኑን እያየሁት!” አሉኝ ቆጣ ብለው። ዋጋ ነግረውኝ በኋላ ተመለስ ብለው ቀጠሩኝ።
በቀጠሩኝ ሰዓት ስደርስ ልቅም አድርገው ስራቸውን አጠናቀው ነገረኛውን አብራራው ጤነኛ አድርገው ጠበቁኝ። በጣም ገረመኝ። ለሙከራም አንገላታሁት። ወይ ፍንክች።
እንደ ጠላት የታየንበት መንደር በኩራት ተመልሰን የፊልማችንም ቀረጻ ቀጠለ። አብራራውም አደብ ገዛ( ከነ ሞክሼው) ጤነኛውን ጠመንጃም ለባለንብረቱ አቶ አዝመራው ሳስረክበውም አንድ ጥያቄ ግን ደጋግሞ ጠየቀኝ። “ማነው የሰራው?” የሰውየውን ማንነት “አብራራሁለት”። አይናቸው እንብዛም እንደማያይላቸው ስነግረው ትልቅ ቁም ተናገረ። “እጃቸው ላይ ሸምግለው ነዋ” አለኝ።
በአንድ ሙያ ውስጥ ማርጀት፥ አይን እንኳ ጠፍቶ ጠቢብነትን አይነጥቅም”
ይህ በሆነ በ3 አመቱ በጓደኛዬ ስነ-ጥበብ ታደሰ አማካኝነት ጋሽ ጥላሁንን በስልክ አገኘኋቸው። በጣም ማረጀታቸው በድምጻቸው ቢያስታውቅም አሁንም ጥንካሬ እንዳላቸው ያስታውቃሉ። ለልጃቸው ሙያቸውን እንዳወረሱትም ነገሩኝ።
“የሙያ ውርስ ከንብረት ውርስ ይበልጣል”
ቀሪ እድሜያቸውን እግዚአብሔር የደስታ ያድርግላቸው።
አይን እና መዳፍን እንዲህ ስታዘባቸው ታላቁን ጥቅስ እንዳልረሳው “ነገር ሁሉ ለበጎ ነው”።
(Photo by Sinetibeb Tadesse)