የቡሄ ጭፈራ እጅግ በጣም ‹‹አስገራሚ ››ከሚሆንባቸው ቦታወች አንዱ ኮንዶሚኒየም ህንፃወች ላይ ይመስለኛል !! ህፃናቱ በዱላወቻቸው አራተኛ ፎቅ ላይ ወለሉን እየደቁ ሲጨፍሩ ..ጠቅላላ ብሎኩ ይነቃነቃል ይንጋጋል …ህንፃው ከቆርቆሮ የተሰራ ነው የሚመስላችሁ ! በዛ ላይ ሰወች ኮንዶሚኒየም ቤት ሲኖሩ ከኢትዮጲያ ውጭ (ኧረ ከአለም ውጭ ) የሚኖሩ ይመስል ህፃናቶቹ ላይ ሲሞላቀቁባቸው ማየት የተለመደ ነው ! ….ጎረቤቴ ምስክር ነች …. ሙሉ ቀን በሯን ዘግታ የሚያናግራት ሰው እንዲመጣ ስትፀልይ የምትውል ሴትዮ ህፃናቱን ‹‹ ሄይ የሰው ፕራይቬሲ ምናምን ›› ብላ ቀልባቸውን በጩኸት ትገፈዋለች …አይ ፕራይቬሲ ‹‹ ብሎኩ እስኪነቃነቅ መዝሙር ከፍታ እንቅልፍ የምታሳጣኝ ጎረቤቴ እኮ ነች !
‹‹እዛ ማዶ ጠብደል ዲሞክራሲ
እዚህ ማዶ ሚስኪን ዲሞክራሲ
የኔ እትየዋ ባለ ፕራይቬሲ ›› እላለሁ በውስጤ …ሂሂሂሂ
ሌላው ጎረቤት ጋ ይጨፍራሉ
‹‹ መጥተናል ቤታችን በቀጠሯችን ›› ሌላኛው ሞልቃቃ ቱታውን እንደለበሰ እየተንጎማለለ ወጥቶ ‹‹ ዌል ይህ የቡሄ ባአል አገራችንን የቱሪስት መናሃሪያ ትሆን ዘንድ የራሱን አስቷፅኦ ያበረክታል … በቅርቡ ሲ ኤን ኤን እንደዘገበው ከሆነ ቅድስት አገራችን በአለም ላይ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑ ሰላሳ ሶስት አገራት የሃያ ሰባተኝነቱን ደረጃ ይዛለች …. እያስመዘገብን ያለነው እድገት …..›› ልጆቹ ስልችት እስኪላቸው አውርቶ …. ሊቀጥል ሲል
‹‹ እሽ ጋሸ ሙልሙሉ ወይም ሳንቲሙ የት አለ ›› ቢሉት
‹‹ ዌል እድገት ማለት ‹ኦቨር ኦል ዚ ካንትሪ › የሚከሰትና ቀስ በቀስ በእያንዳንዱ ሰው ቤት የሚገባ ለውጥ ነው …እ በአንድ ጀምበር ሁሉም ባለሙልሙል ሊሆን አይችልም …..እ በዚህም መሰረት እኔ ቤት ሙልሙል የለም በቀጣይ አስራ አምስት አመታት …..›› ልጆቹ ጣጥለውት ሄዱ እየተነጫነጩ
ልጆቹ ግን ሚስኪን ናቸው …. ቀጥሎ ያለው የጎረቤቴ ደምሳቸው ቤት ጋ ይጨፍራሉ … በቡሄው ቀን ሳይቀር ‹‹ የማያልፉት የለም ›› የሚለውን ዘፈን ከፍቶ እየተዝናና ነበር ! ድንገት ልጆቹ በሩን እየደቁ ይስማማዋል ብለው ያሰቡትን ጭፈራ አወረዱት
እዛ ማዶ አንድ ክክ
እዚህ ማዶ አንድ ክክ
የኔ ጋሽየዋ ባለ ታንክ !
‹‹ባለታንኩ›› በብስጭት በሩን ከፍቶ ልጆቹን እያመናጨቀ ‹‹ የምን ታንክ ነው…. አሁን የዲሞክራሲ የልማት ዘመን ነው ትራክተር ምናምን አትሉም ….. ምንድን ነው ሙሉ አካል አላችሁ ሰርታችሁ አትበሉም ….መንግስት ባመቻቸላችሁ እድል ተደራጅታችሁ በጥቃቅንና አነስተኛ …. ›› አሁን እስቲ እነዚህ አንድ ፍሬ ልጆች አንዲት ዘና የሚሉባት በአል ብትኖር ይችኑ ይነጅስባቸዋል ….
ልጆቹ በሰውየው ስድብ ተበሳጭተው ራቅ ካሉ በኋላ በሚገባው ቋንቋ ልኩን !
እዛ ማዶ አንድ ጋቢ
እዚህ ማዶ አንድ ጋቢ
ጋሽ ደምሳቸው ኪራይ ሰብሳቢ ! (ኮንዶሚኒየሙን አጭበርብሮ ነው ያገኘው እየተባለ ይታማል )
‹‹ ቆይ ላግኛችሁ …እናተ እንደውም ኮንዶሚኒየሙን በሃይል ለመናድ ቡሄን ሽፋን በማድረግ ተልእኮ እንዳላችሁ የማናውቅ መስሏችኋል ….ቆ…..ይ ! ››
ልጆቹ ዛቻውን ከቁብ ሳይቆጥሩት ወደሌላኛው ቤት …….
እዛ ማዶ አንድ ድንጋይ
እዚህ ማዶ አንድ ድንጋይ
የዚህ ቤት ባለቤት
የነፃነት ታጋይ
ልጆቹ በቂ መረጃ ይዘው ነው የመጡት… የሚጨፍሩበት ቤት ባሏ ጋዜጠኛ ነው ታስሯል ! በልጆቹ ጭፈራ ልቧ ተነክቶ ድፍን አስር ብር ከሙልሙል ጋር ….ስታሽራቸው ደምሰው ፎቁ ላይ ቁሞ ‹‹…ይች አገር አስራ አንድ በመቶ ኢኮኖሚዋ ባያድግ ምድረ ማቲ ሙልሙል እንዳማረሽ ነበር የምትቀሪው ›› እያለ ያጉረመርማል ! ልጆቹ ባሏ የታሰረባትን ባለሙልሙል ይመርቃሉ ….
ክበር በስንዴ ክበር በጤፍ
መከራው ይርገፍ
ካቴናው ይንጠፍ
የወፍ ፋፋ የወፍ ፋፋ
ማስረጃቸው ይጥፋ
እውነትም ይፋፋ !
ህፃናቱ አለፍ ብለው የክፍለከተማው ሴቶች ጉዳይ ሃላፊ የሆነች ሴት ቤት መጨፈር ጀመሩ …ሴትዮዋም በሯን ከፈት አድርጋ ስድስቱን ልጆች አንድ በአንድ ተመለከተችና …‹‹ሁላችሁም ወንዶች ናችሁሳ …ሴቶች ለምን በእኩልነት ጭፈራው ላይ አልተካተቱም …ባደጉት አገራት ሴቶች ከወንዶች ጋር በሁሉም ነገር በእኩልነት ነው የሚሳተፉት ለምሳሌ በቻይና …. ›› ስትል ቆጣ ብላ ጠየቀች … ከዛም ስለሴቶች እኩልነት ሰፋ ያለ ዲስኩር አሰምታ ሰባራ ሳንቲም ሳታቀምሳቸው በሯን ጠረቀመችባቸው ! ድሮስ የቡሄ ጭፈራ ላይ ከመቸ ወዲህ ነው ሴትና ወንድ አንድ ላይ የሚጨፍረው … እስቲ አሁን ማን ይሙት ቻይና ቡሄ ይጨፈራል …
እንግዲህ ኮንዶሚኒየም የሁሉ መኖሪያ አይደል ….ከታሳሪው ጋዜጠኛ ቤት ፊት ለፊት ደግሞ የመንግስት ቀንደኛ ደጋፊ ሰውየ አለ … ሁልጊዜ ‹‹ሰላም ዋልክ ›› ሲባል
‹‹ ከጭቃ አንስቶ ፎቅ ላይ ያስቀመጠን ፀሃዩ መንግስታችን ይባረክ ›› የሚል …ይሄ ሰውየ አንዴ የኮንዶሚኒየሙን ሰው ለምርጫ ሲቀሰቅስ ‹‹ መንግስታችን የህዝብ ድምፅ እህ ምን ጎደለ ብሎ በማድመጥ ተወዳዳሪ የለውም ….ለምሳሌ ባለፉት መንግስታት የዚህ ክፍለ ከተማ ህዝብ የመቃብር ቦታ አልነበረውም አሁን ግን መንግስት ምቹ የሆነ የመቃብር ቦታ ሰጥቷል ሟቾች አፍ ቢኖራቸው መንግስታችንን ባመሰገኑ ነበር ›› አለ አሉ
አንድ ሰው ታዲያ ነገሩታ … ‹‹ጌታው በቀደሙት መንግስታት መቃብር ቦታ የለም ያሉት ዘመዶቻችን ሲሞቱ ስጋቸውንም ነፍሳቸውንም ነበር እንዴ ይዘው የሚሄዱት ….ደግሞስ የሞቱት ያመሰግኑናል የሚሉት ያለነው መቸ ነገረ ስራችሁ ጣመንና ነው ….ተው እንጅ ምርጫ እንቀስስቅስ ብላችሁ ብሶታችንን አትቀስቅሱ!››
እናም ቡሄ ጨፋሪወቹ ህፃናት ወደሱ ቤት ጎራ ብለው …..
‹‹መጥተናል መጥተናል
ቀጠሮ አክብረናል ››
ሰውየው ጋዜጠኛውን መመረቃቸው አበሳጭቶት ሲጠብቃቸው ነበር …! ከመንግስት እና መንግስትን ከሚደግፉ ሰዎች በስተቀር ሌላ ሰው ሲመሰገን አይወድም ደሙ ነው የሚፈላው!
መምጣቱን መጥተሃል
ማን አባክ ቀጥሮሃል !! አላቸው …ከትልቅ ካድሬ በማይጠበቅ ሁኔታ!
ልጆቹ ምላሳም ናቸው … ‹‹ ፍርድ ቤት በየአስራ አራት ቀኑ ካልቀጠረ ቀጠሮ አይመስለዎትም ጋሸ ›› ብለውት እብስ …. ስድስት ማቲወች የያዟትን አንዲት ሙልሙል እየተመለከቱ ….ሁለቱ ካድሬዎች ታዲያ እርስ በእርስ ማውራት ጀመሩ ‹‹መንግስታችን ገና ብዙ ያሳየናል …እስቲ ቡሄ ፎቅ ላይ ይጨፈራል ብሎ ማን አስቦ ያውቅ ነበር … ›› እየተባባሉ
ህፃናቱ ጭፈራው ሲደክማቸው ቁመው ያወራሉ … ‹‹ ስነዜጋ ቲቸራችን ባለፉት ስርዓቶች ከተከበሩት ቡሄዎች ጋር ሲነፃፀር በዘንድሮው ቡሄ የሰው ኑሮ በአስራአንድ በመቶ ተሸሻለ ብለውን አልነበር እንዴ ….ታዲያ የታለ ሙልሙሉ…. ›› ሲሉ ተከዙ ! ታዲያ እነዚህ ልጆች ለጭፈራ የያዙትን ብትር ተደግፈው ሲተክዙ ስመለከት ህዝብ መሰሉኝ … መቸስ ጨፍሮውም መርቆም መጨረሻ ላይ ይቀምሰው ሙልሙል እጁ ላይ ያጣ ህዝብ ለመጨፈሪያ ያነሳውን ዱላ … የተነጠቀውን ሙልሙል ለማስመለስ እንዳይጠቀምበት ….ከመፍራት ጋር !
ዋናው ጥያቄ ፎቅ ላይ መጨፈሩ አይደለም … ሙልሙሉ የታለ ??