Tidarfelagi.com

መፋቀር አጋባን፣ መፋቀር አኖረን

ሰሞኑን ‹‹ከእገሌ ዘር አትግቡ…የተጋባችሁም ተፋቱ›› መባሉን ስሰማ ይህችን ላካፍላችሁ መጣሁ።
የእኔ እና የባለቤቴ ሰርግ ብዙዎቹን አግልሎ ያስቀየመ፣ በሃያ ሁለት ሰዎች እንግድነት (ሁለቱ በወሬ ወሬ ሰምተው ራሳቸውን ጋብዘው ነው) ብቻ የተፈፀመ ነበር። ደህና ቤት በደህና ዋጋ ለመከራየት ከሰፈር ሰፈር እየተንከራተትን መቶዎችን ለመመገብ የሚሆን ገንዘብ ማውጣት ስሜት እንደማይሰጥ ተስማምተን ነው እንዲህ ያደረግነው። ከሰርግ ትዳር ይበልጣል ብለን።

እንዳልኳችሁ ወጪ ቆጣቢ ግብዣ ስለነበረች ቤተሰቦቻችን ( እናት አባት፣ እህትና ወንድም ብቻ ነው የተጋበዘው) እዚያው እንዲቀላቀሉ ጠየቅን። ያን ጊዜ የባሌ አባት ብድግ ብለው ስማቸውን እስከ አባታቸው ሲጠሩ ወደ ትኩሱ ባሌ ዞር አልኩና፣ በሹክሹክታ፣ ‹‹እንዴ….አባባ ኦሮሞ ናቸው ለካ!›› አልኩት።

ለአራት አመታት ፍቅረኛዬ የነበረው፣ አዲሳባ ተወልዶ ያደገው ባለቤቴ አያቱ ስላሳደጉትና በእርሳቸው ስለሚጠራ ኦሮሞ እንደሆነ ያወቅኩት በሰርጌ ቀን ፣ በዚህች ሸራፊ አጋጣሚ ነው። ‹‹አዎ የአምቦ ሰው ነው….›› ብሎ በቀላሉ ሲመልስልኝ መልሼ ምን አልኩት?…‹‹እማዬ እኮ የወለጋ ኦሮሞ ናት…በኋላ ይሄንን ጨዋታ በኦሮምኛ አቀላጠፉት በለኛ….!››
ቆይቶ የባሌ እማማ እና አባባ እንዴት እንደተገናኙ ሰማሁ። አባባ ከአምቦ አዲስ አበባ መጥተው ቤት ይከራያሉ። ቤቱን ከመከራየታቸው ከአዲሱ ቤታቸው በላይ ቀልባቸው በማን ይሰረቃል? በአከራያቸው ሴት ልጅ፣ የዛሬዋ እማማ። ተፋቀሩ። ተጋቡ። የእኔን ባል ጨምሮ አምስት ወለዱ። ከበዱ።

የእኔ እማማ እና አባባ ደግሞ እንዴት ተናኙ? እሷ ከደምቢዶሎ ፣ እሱ ደግሞ ከመንዝ ለትምህርት ደብረብርሃን ኮሌጅ ሲሄዱ። ተፋቀሩ። ተጋቡ። እኔን ጨምሮ ስድስት ወለዱ። ከበዱ።
በቃ። የእኛ እና የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ታሪክ እና ኑሮ ይሄው ነው። በትእዛዝ አልተጣመርንም፣ በትእዛዝ አንለያይም።

የተጋባነው ስለተፋቀርን ነው። ዛሬም አብረን የምንኖረውም እስካሁን ስለምንፋቀር ነው። የመጋባታችን እና አብሮ የመኖራችን ምክንያት ፍቅር ብቻ ስለሆነ በመንገዳችን ሁሉ አዛዣችን ፍቅር ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *