1. ፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ስመ ጥር መኮንን ነበሩ። ከፍተኛ ዲፕሎማት በመሆን ለዓድዋ ጦርነት የሩሲያ መንግስትን የጦር መሳሪያ ድጋፍ እና የህክምና እርዳታ እንድናገኝ ያደረጉ ስኬታማ ሰው ናቸው። እኝህ ሰው ታዲያ ከሩሲያ በዲፕሎማሲያዊ ስኬት ተመልሰው እረፍት እንኳን ሳያደርጉ ዓድዋ ድረስ ተጉዘው በ1888 ዓ.ም የካቲት 23 ቀን ከወራሪው የጣልያን ጦር ጋር ገጥመው የጀግንነት ጀብዱ ፈጽመው በዚያው እለት ህይወታቸው እዚያው ጦር ሜዳ ላይ አልፏል። እኚህ ሰው “የሀገር ጀግና” የሚል ስያሜ መለያቸው ሆኖ እሰከዛሬ ስማቸው ይታወሳል።
2. የእኚህ ታላቅ ሰው የአብራክ ክፋይ የሆኑት [ራስ] ደስታ ዳምጠው እንደ አባታቸው ሁሉ በርካታ መልካም ስራዎችን ለሀገራቸው ፈጽመው ሲያበቁ በ1928 የጣልያን ጦር ሀገራችንን ለሁለተኛ ጊዜ ሲወር በሱማሌ በኩል ይመጣ የነበረውን ጦር በጀግንነትና በወኔ ዶሎ ድረስ ወርደው በመግጠም የጀግንነት ስራ ቢሰሩም ጦሩ በደረሰበት ሽንፈት ሰራዊታቸው ተበተነ። እሳቸው ግን በአርበኝነት ለአንድ አመት ያህል ሲፋለሙ ኑረው ጣልያን እጅ ላይ ወደቁ። ጣልያን እኒህን ታላቅ ጀግና በየካቲት 16ቀን 1929 ዓ.ም በአደባባይ በጥይት ደብድቦ ገደላቸው። ራስ ደስታ በስማቸው መታሰቢያ ሆስፒታል የተገነባላቸው “ጀግና ሰው” በመሆን ዛሬም ድረስ ይታወሳሉ።
3. የእኚህ ታላቅ ሰው ልጅ የነበሩት [ሪር አድሚራል] እስክንድር ደስታ ደግሞ እንደ አባታቸው እና እንደ አያታቸው ስኬታማ የአስተዳደር እና የዲፕሎማሲ ሰው ነበሩ። የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ምክትል አዛዥ በመሆን ስኬታማ የነበሩት እኚህ ሰው እናታቸው የቀ.ኃይለሥላሴ ልጅ [ልዕልት ተናኜወርቅ] በመሆናቸው ብቻ በህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ከ60ዋቹ ከፍተኛ ባለስልጣናት መሀል አንዱ ሆነው በደርግ ጥይት ተደብድበው ተገደሉ።
ሦስተኛው ይባስ እንግዲህ ይህ ነው። እኚህ ሰው
የሞቱት በሀገራቸው ሲሆን ገዳያቸውም የሀገራቸው ሰው ነው። እንደ አያታቸውና አባታቸው በጠላት እጅ ሳይሆን በሀገራቸው በግፍ ተገደሉ። ታሪካቸውን ስናጤነው የሀገሩን ልጅ የገደለው ደርግ እራሱ ጀግና አልተባለም። በሀገራቸውም ሰው የተገደሉትም እስክንድር እንዲሁ። ምክንያቱም “ለሀገሩ ሲል” የሀገሩን ልጅ የገደለ ጀግና አይባልም። “ለሀገሩ ሲል” በሀገሩ ልጅ የተገደለም እንዲሁ።
“ለሀገሬ ስል ነው” የሚል ሰው የሀገሩን ልጅ የሚገድል ከሆነ ጀግና አይባልምና የታሪክ ተወቃሽ መሆኑ አይቀርም። “ለሀገሬ ስል ነው” ብሎ በሀገሩ ልጅ የሚሞትም እንዲሁ። ሦስተኛው ይባስ በሉ። እርስ በርሱ እየተላለቀ “ለሀገሬ ስለ ነው” የሚል ካለ ልቦና ይስጠው።
ታሪክ ማለት ዛሬ አልፎ ሲያረጅ እንጂ የጨበጥነው ዘመን እውነታ አይደለምና፥ ዛሬ በሚሰጠን የጀግንነት ስያሜ አንመርቅን። ታሪክ አድሮ ይወቅሳል።
ፈጣሪያችን ሆይ! ጠላት ሲመጣ ተፋልመን ለሀገራችን በክብር የምንሰዋ እንጂ እርስ በርስ የምንተላለቅ ህዝቦች ከመሆን አድነን!!
ለሀገር ሰላምና ደህንነን ስል ነው የምገድለው የሚለውን ልብ ይስጠው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
2 Comments
የማይሰማ መንግስት ባለበት መሞት ከባድ ጀግንት ነዉ፡፡
መረጃዎችህ ደስ ይላሉ ነገር ግን ምንጭ መጥቀስ ቢቻል አሪፍ ነው