Tidarfelagi.com

ራሴው ማበዴ ነው (ክፍል ስድስት)

እናቴ ከመሞቷ በፊት ልውልላት የምችለው አንድ ውለታ አባቴ እንዲያገኛት ማድረግ ነው። ቢያንስ የዘመናት ፍቅሯን እጁን ዳብሳ ደስተኛ ሆና ትሞታለች። እናቴን ማጣት ማሰብ አልፈልግም። የባሰው ደግሞ ስትለየኝ ማን መሆኔን እንኳን ሳታውቅ እብደቷ ተነስቶባት መሆኑን ማሰብ ያሳብደኛል። ያ እንዲሆን አልፈልግም። የቀራትን ጊዜ ጭንቅላቷ ልክ መሆን አለበት!! ውስጤ እንዲቀር የምፈልገው የእናቴ ምስል የምትፈራኝና የምትሸሸኝ ‘አንቺ ደግሞ ማነሽ?’ የምትለኝ እብዷ እናቴ ምስል አይደለም። ያቺ በለስላሳ እጆቿ ደባብሳኝ የማትረካዋ ፣ እሷ ያልኖረችውን የስነ ምግባር ኑሮ እንድኖር የምትመክረኝ፣ በሌላት ጡት ‘በጡቴ ይዤሻለሁ በቀል ከሀሳብሽ አይኑር።’ ብላ የምትለምነኝ፣ ልጄ ስስቴ የምትለኝ፣ አገላብጣ እየሳመች ‘አሳቃየሁሽ ልጄ’ እያለች የምትለማመጠኝ፣ ለእርሷ ስል መኖሬ የሚገባት(የሚያሳስባት) እናቴ… … እሷን እናቴን ነው በልቤ ይዣት መኖር የምፈልገው።

“እንደምንም ብዬ አባቴን ማናገር አለብኝ።” አልኩት ካሳሁንን ሳለቅስ ቆይቼ። ያልኩት ግርር እንደሚለው ያሰብኩት ባይገባውም የገባው ለመምሰል ሲሞክር ሳየው ነው።

“ግን ልታናግሪው አትፈልጊም?” አለኝ።

“ላገኘውም አልፈልግም። የእሱን እርዳታ መጠየቅ ደግሞ ያሳምመኛል። ለእማዬ ስል ግን አደርግላታለሁ። ለሷ ስል አደርግላታለሁ።” አልገባውም። በጥያቄ ሊያስጨንቀኝም አልፈለገም። ከእቅፉ ወጥቼ ጋደም እንዳልኩ ከየትኛው ሃሳቤ በኋላ እንቅልፍ እንደወሰደኝ አላውቅም።… ……

በሚቀጥሉት ቀናት የካሳሁንን እና የፍትህን እማዬ አጠገብ መሆን፣ ራሴን ካሳሁን እቅፍ ውስጥ ወይም የፍትህ አልጋ ላይ አልያም የፍትህ ቢጃማ ውስጥ ማግኘት፣ የፍትህን በቡናና በቁርስ ሰበብ የቢሮዬን በር መክፈት… የተለመድኳቸው ክስተቶች ሆኑ። የሚፈጥሩብኝን ስሜት ግን በደነዘዘ ልቤ መረዳት አልቻልኩም።

ከሳምንት በኋላ አራታችንም(እኔ እና የስራ አጋሮቼ ፀሃፊያችንን ወይኗን ጨምሮ) ቢሮ ተሰበሰብን እና ለተወሰነ ጊዜ ስራ ላቆም መሆኑን ስነግራቸው በድንጋጤ አፈጠጡብኝ።

“ለምን? ቆይ እስከመቼ? ምን ተፈጥሮ ነው?” ጌትነት ነው የሚጠይቀኝ።

“እስከመቼ እንደሆነ አላውቅም ጌትሽ! ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው። መቼ እንደሆነ ባላውቅም ቃል እገባልሃለሁ ወደ ስራዬ እመለሳለሁ። እስከዛ ድረስ እጄ ላይ ያሉትን እንድትሰራልኝ ፈልጋለሁ።”

“ስራ ማቆሙ አስፈላጊ ነው? ራሁ please ፍቀጂልኝ እኔ ልርዳሽ? በምትፈልጊው ሁሉ እኔና ካስዬ ከጎንሽ ነን።” አለኝ ፍትህ ሌሎቹ ሲወጡ ጠብቆ።

“ፍትህ ልትረዳኝ ትፈልጋለህ?” አልኩት (ቁልምጫው ልቤን ቢሰርቀውም ባልሰማ አለፍኩት)

“Whatever it is.”

“መልካም! ብዙ ትግል እና ትእግስት የሚጠይቅ ስራ እጄ ላይ አለ። ሙሉ ሰዓትና አቅም ይፈልጋል።አሁን በሙሉ አቅሜ ልሰራ አልችልም። አስቸጋሪ ቢሆንም ይሄን ኬዝ አንተ እንድትይዝልኝ እፈልጋለሁ።”

” ራሁ እኔ ያንቺን ያህል ጎበዝ አይደለሁም። ……”

“ሁና! ጎበዝ ሁን! ጉብዝና ተፈጥሮ አይደለም። ጎበዝ ለመሆን ትለፋለህ እንጂ ጉብዝና ድንገት ጉብ የሚልብህ መንፈስ አይደለም። እኔን መርዳት ትፈልጋለህ? ይኸው……(መረጃ የያዘ ፍላሽ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጥኩለት)… አሁን እማዬጋ መሄዴ ነው። እየውና ስትወስን ደውልልኝ… ” ብዬው ወጣሁ።

“እሺ ላድርስሽ?”

“Am ok መንዳት እችላለሁ።”

እማዬጋ ስደርስ ካሳሁን ከእማዬ ክፍል አቅራቢያ ውጪ ተቀምጧል።

“አባትሽ ውስጥ ነው። ብቻቸውን ይሁኑ ብዬ ነው።” አለኝ ቀለል አድርጎ። ለመግባት ስፈጥን እጄን ይዞኝ። “ምንም አትሆንም እንደውም ደስተኛ ናት። ተያቸው።” አለኝ።

“ደስ የማይል ነገር ቢናገራትስ? የሆነ ነገር ብትሆን……” እጄን አስለቅቄው ገባሁ። መግባቴን ያየችው እሷ ብቻ ናት። እሱ (አባቴ) ከግርጌዋ ተንበርክኮ ሁለት እግሮቿን አቅፎ ያለቅሳል። እየሆነ ያለው ሁሉ ግርር አለኝ…… ከተቋሰሉት መቋሰል በላይ እንደምትወደው የሷን አውቃለሁ። የእሱ ግን… …
‘ገዳይሽ እኔ ነኝ ማሪኝ ፤ ያንቺን ስቃይ ለኔ ያድርገው፤ ባንቺ ቦታ ልሰቃይልሽ……’ ይላታል። ያቀፋቸውን እግሮቿን ይስማል። ‘ማሪኝ እማ እኔው ነኝ በሽታሽ። ለምን አልነገርሽኝም? ለምን ሀጢያቴን አበዛሽው?’ እንባው እግሮቿን ያርሳቸዋል። እሷን አየኋት። እንባዋ ወደጆሮዎቿ ሲወርዱ ስትጠርጋቸው አየኋት። የእኔ መኖር ምቾት የሰጣት ስላልመሰለኝ ቀስ ብዬ ወጣሁ። እኚህ ሰዎች ሙድ ነው የሚይዙብኝ? ጭንቅላቴ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች እየተርመሰመሱ ቢሆንም ደምቆ የሚያቃጭልብኝ ‘መታመሟን ማን ነገረው?’ የሚለው ነው።

“እኔ ነኝ የነገርኩት።” አለኝ ካሳሁን ያሰብኩትን ያወቀብኝ መሰለኝ። ቀጠል አድርጎ “እነርሱ እስኪጨርሱ አንድ ቦታ ደርሰን እንምጣ?” ብሎኝ ተንቀሳቀሰ። ተከትዬው መኪናው ውስጥ ገባሁ። ብዙ ከተጓዝን በኋላተጀምሮ ያላለቀ ቤት ያለበት ጊቢ ይዞኝ ገባ። እያየሁት መንፈሱ ሲቀየር አስተዋልኩኝ። ሀዘን የተጫነው ሰውዬ ሆነ። ምንም ምንም ሳይለኝ ግድግዳውን ተደግፎ የተቀመጠ መጥረጊያ አንስቶ በጅምር ከቀረ የከራረመ የሚመስለውን ቤት ግድግዳና መሬት በጥንቃቄ ማፅዳት እና ማውራት ጀመረ።

“አበባ ጎበዝ አርክቴክት ነበረች። የፍትህ እናትን ማለቴ ነው። ለወደፊት ኑሯችን ራሷ ዲዛይን ያደረገችውን ቤት መገንባት ነበር የምትፈልገው። ይሄ ነበር የወደፊት ቤቷ ( መጥረጉን ቆም አድርጎ ቤቱን አመላከተኝ) ቤቷ ተሰርቶ ሳያልቅ እሷ ሞተች። ቤቱን አሰርቶ የመጨረስ ብርታቱ አልነበረኝም። በነበረበት ቆመ። ስትናፍቀኝ ላዋራት ፈልጌ መቃብሯ ጋር ስሄድ ሀዘኔ ይበረታል። ሙት መሆኗ በድን ያደርገኛል። እዚህ ስመጣ ግን እንደዛ አይሰማኝም። እዚህ የኔ አበባ ህይወት አላት። እዚህ ህልውናዋ ይሰማኛል። እና መቃብሯጋ መሄዴን ትቼ እዚህ መምጣት አዘወተርኩ። የሆነ ቀን እንደለመድኩት ስመጣ ፍትህ ቤቱን ሲያፀዳ አገኘሁት። ሁሌ ስመጣ ቦታው ፅዱ እንደነበር አስታወስኩ። ምንም አልተባባልንም። እስከትናንት ድረስም በዚህ ጉዳይ ቃላት ተለዋውጠን አናውቅም። ለ19 ዓመታት ይሄ ቦታ ፅዱ ነበር። እንዲህ ቆሽሾ አያውቅም። ሁሌም እሁድ ጠዋት መጥቶ እንደሚያፀዳው አውቃለሁ። አልመጣበትም። ሁሌም እሁድ ከሰአት እንደምመጣ ያውቃል። አይመጣብኝም። ትናንት ከዚህ በኋላ ወደዚህ ተመልሶ እንደማይመጣ ነገረኝ። በእናቱ ትዝታና ሀዘን መደበቅ እንደሚበቃው ነገረኝ። አየሽ ሁሌም የአዲስ ነገር ጅማሬ የአሮጌው መቋጫ ነው። ከአሮጌው ቅጥያ ከሆነ ምኑን አዲስ ሆነ?”

እየሆነ ያለው፣ የሰማሁት እና የማስበው ተፐውዟል። የካሳሁንና የአበባ ታሪክ ከእናትና አባቴ ታሪክ ጋር ይደባለቅብኛል። አባቴ ለእናቴ የፃፈላት ደብዳቤ ካሳሁን ለሚስቱ የፃፈላት ይመስለኛል። ደግሞ ስለፍትህ አስባለሁ። በፍፁም ለቅፅበት እንኳን ከፍቶት የሚያውቅ የማይመስለኝ ሰው ለነዚህ ሁሉ ዓመታት ይሄን ስቃይ እሹሩሩ ሲል ነበር የኖረው? እርስ በርሱ የተከላለሰ ነገር እያሰብኩ የቤቱ ደፍ ላይ ቁጭ አልኩ። መጥረጉን ሲጨርስ አጠገቤ መጥቶ ተቀመጠ።

“ታውቃለህ ከእናቴ በቀር የሚያውቀኝ ሰው ሳለቅስ አይቶኝ አያውቅም።” ካልኩት በኋላ እሱ ካወራው ልብ የሚቦረቡር ታሪክ ወይም እሱ ካለበት ስሜት ጋር በመልክም በቅርፅም የማይገናኝ ነገር ማውራቴ አሳፈረኝ።

“አየሽ አንዳንዴ ምንም ካልሰራንበት ዘመናችን ስህተት የሰራንበት ዘመን ይሻላል። ምክንያቱም ምንም ውስጥ ምንም የለም። ስህተት ውስጥ ቢያንስ የመሳሳቻ አንዱን መንገድ አውቀሽዋል። ደግመሽ በዚያ መንገድ መንደፋደፍ ወይም መንገድ መቀየር ያንቺ ምርጫ ይሆናል።” አለኝ። ለእኔ ያውራ ለራሱ ወይ ለሚስቱ አልገባኝም። ጭራሽ ያለውም አልገባኝም። ምን እየሆንን ነው? ጭራሽ እኔ የማወራው ነጭ እሱ የሚመልስልኝ ጥቁር!! እያበድን ነው እንዴ?… …ፀጥ ተባብለን ከቆየን በኋላ ተነሳ። ተመልሼ ሆስፒታል ስሄድ አባቴን ባላገኘው ደስ ስለሚለኝ መቆየታችንን ወድጄዋለሁ። ተከተልኩት። …… ቃል ሳንተነፍስ ሆስፒታል ደረስን።

“እኔ በቃ ወደቤት ልሂድ! ከቻልኩ በኋላ ብቅ እላለሁ።” አለኝ ከመኪናው ሳይወርድ። ተሰናብቼው ወደ እማዬ ክፍል እየሄድኩ ካሳሁንን ከጭንቅላቴ ማውጣት አልቻልኩም። መከፋት የተጫነውን ፊቱን ከሀሳቤ ማደብዘዝ አቃተኝ። እማዬና ፍትህ ከክፍሉ ውጪ የሚሰማ ሳቅ እየተሳሳቁ ደረስኩ። ሰላም ብያቸው ሳልጨርስ

“እኔ የምለው ጀብዱ ትወጃለሽኣ?” አለኝ ፍትህ የተጋነነ መገረም ባለው ድምፅ። የሰጠሁትን መረጃ አይቶት እንደሆነ ገብቶኛል።

“ማን ይጠላል?” አልኩት።

“እኔ!” አለኝ ኮስተር ብሎና አስረግጦ።

“ሃሃሃሃ ፈሪ ነህ ማለት ነዋ! ሊያውም የምትጠላው ጀብዱን አይደለም። የሚጠይቀውን ድፍረትና risk ነው። ” እያልኩት ፊቱ ላይ ስስት ያለበት ፈገግታ ተንሰራፋ…… እያወራን ካለበት ስሜት የማይገናኝ ዕይታ እያየኝ ነው። “ምንድነው?” አልኩት ግራ ሲያጋባኝ።

“ሳቅሽ!! ራሁ ድምፅ አውጥተሽ ሳቅሽ እኮ! ራስሽን ሰምተሽዋል?” እየፈነደቀ ነገር ነው ልበል? ድምፁ ውስጥ የምሰማው ነገር ምንድነው? ከመደሰት ያለፈ

“እና?”

“በፍፁም ድምፅ አውጥተሽ ስትስቂ ሰምቼሽ አላውቅማ።”
(ስቄ አላውቅም ይሆን? መቼ ነው ለመጨረሻ ጊዜ የሳቅኩት? መቼስ ይሆን የሚያስቅ ነገር የሰማሁት? ከሁልጊዜው በላይ እንባን በሚያዘንብ ሁኔታ ተከብቤ ዛሬ ምን አሳቀኝ?)
አሳፈረኝ። ያሳፈረኝ ዕይታው ይሁን አነጋገሩ አልገባኝም። ‘ተሽኮረመመች’ ተባብለው ከእማዬ ጋር ተሳሳቁብኝ። አፍንጫዬ አላበኝ። ጉንጬ የቀላም የነደደም መሰለኝ። ምንድነው እየሆንኩ ያለሁት? መቼ ነው እንዲህ የሆንኩት?
ድሮ ድሮ ድሮ ድሮ ድሮ ድሮ… ………

ራሴው ማበዴ ነው (ክፍል ሰባት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *