“አገኘሁት! ራሁ አገኘሁት!” ይለኛል የሆስፒታሉ ኮሪደር መሃል እየደነሰ
“ምኑን? እስኪ አንዴ ዳንስህን አቁመህ ንገረኝ!”
“የትዝታን ፍቅረኛ አገኘሁት!”
“በጣም ጥሩ! የሚጠቅም መረጃ አገኘህ?”
“ገና ነው። ደቡብ አፍሪካ ነው ያለው። ከሀገር እንዲወጣ ያደረገው ማን እንደሆን ገምቺ? የትዝታ አጎት! አስፈራርተውት ነው ከሀገር እንዲወጣ ያደረጉት።”
“ለምን?”
“ትዝታን ለሌላ ለተከበረ ሰው ሊድሯት እንደሆነና ከሷ ህይወት እንዲወጣ እንዳስፈራሩት ጓደኛው ነው መረጃ የሰጠኝ። የሚደውልለትን ስልክ ሰጥቶኝ ደውዬለት ነበር።”
“እና?”
” በዚህ ርቀት ሆኖ እንኳን ይፈራቸዋል። ገና ስለትዝታ ሳነሳበት ‘ሰውየው አረመኔ ነው። አታውቁትም። ትንፍሽ ብል ይገድለኛል።’ አለኝ። ትዝታ ያለችበትን ሁኔታ አስረዳሁት። ልጁ ያለእናትና አባት መቅረቷ መሆኑን ስነግረው ስራ ቦታ መሆኑን እና መልሶ እንደሚደውልልኝ ነግሮኝ ስልኩን ዘጋው።”
“በቃ?”
“ለጊዜው አዎን በቃ!”
“እና የሚያስደንስህ ይሄ ነው? ገና የመፅሃፉን ሽፋን እየገለጥክ እንደሆነ አልገባህም ልበል? ገና ገፅ አንድን እንኳን አላነበብክም እኮ!”
“ራሁዬ ገፅ አንድ ላይ ነኝ ማለት ታዲያ ቢያንስ ትክክለኛውን ትራክ አጊንቻለሁ ማለት አይደል? የተሳሳተ መፅሃፍ ካልገለጥኩ am good ማለት ነው። ሌላው የውልሽ ትዝታን አናገርኳት። ‘ተወኝ’ ከሚል ቃል ውጪ ትንፍሽ ብላ የማታውቅ ልጅ። የልጇን አባት እንዳገኘሁት ስነግራት ከመቀመጫዋ ዘላ ተነስታ ‘በህይወት አለ?’ ብላ ነበር የጠየቀችኝ። ደስ ያላት ትመስላለች። ሞቷል ብላ አስባ ነበር ማለት ነው። ከዚህ ተጨማሪ ነገር ልትናገር አልፈለገችም። ይልቅ ያሰብሽውን ንገሪኝ።”
“የማስበውማ እንዴትም ብለህ ድጋሚ ልታናግረው ይገባል! ስለሰውየው የሚያውቀው ነገር የሚያስገድለው ወይም ከሀገር የሚያሰድደው ከሆነ ሰውየው እንዴት ያለ ወንጀል ውስጥ የዘቀጠ ቢሆን ነው? ስለሰውየው ተጨማሪ መረጃዎች መሰብሰብ አለብህ። የማስበው ዜሮ ላይ እንዳለን ነው።”
በእርግጥ ለእርሱ ይሄን ልበለው እንጂ በትዝታ ጉዳይ የሚገኙት መረጃዎች ብጥቅጣቂና ለማስረጃነት የማይበቁ ምስክርነቶች መሆናቸው ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ እንኳን በየቀኑ መረጃ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት እያስገረመኝ ነው። ካሳሁን በሁኔታው መደሰቱን እያመሰገነኝ ነግሮኛል።
“እሺ እማዬን ተሰናብቻት ልውጣ!” ብሎኝ አልፎኝ ወደ ውስጥ ገባ። እማዬ ዛሬ ጠዋት እንዲህ ብላኝ ነበር።
“ሚሚሾ ወጣትነትሽን ለእኔ ብለሽ ገብረሻል። ለራስሽ መኖር ያለብሽ ጊዜ የደረሰ ይመስለኛል። ፍትህ መልካም ሰው ነው። ይወድሻል። አትግፊው።”
“በምን አወቅሽ?” ስላት ሳቀችብኝ። …… ፍትህን እንደወደደችው አውቃለሁ። ከእርሱም ጋር ሆነ ከካሳሁን ጋር ስትጫወት ያለስስት ነው። እነሱ አጠገቧ ሲኖሩ ደስተኛ ናት።…… ካሳሁን ሲኖር ፍትህን ያበሽቀዋል። እኔና እማዬ እንስቅበታለን። እሱ ሳይኖር እማዬና ፍትህ በእኔ ሙድ እየያዙ ይስቃሉ። …… ሆስፒታል ያለን አይመስልም… …… ወደሞት እየተንደረደረች ያለች እማዬን የከበብን አንመስልም። አዲስ ህፃን ወደቤተሰቡ የቀላቀለች እናት ከበን የምንደሰት ነው የምንመስለው። አባቴም በየቀኑ መምጣቱን አላቆመም። እሱ ሲመጣ እኔ እወጣለሁ። ላናግረው እንደማልፈልግ እርሱም ያውቃል። አይሞክርም። ከእኔ ይልቅ ከፍትህ ጋር ያወራሉ። እንዲህ እየሆነ እማዬ ሆስፒታል ከገባች አንድ ወር አልፏታል።
” ፍቅር ብርሃን ነው ሚሚሾ አይደበቅም። በምንም ልትከልዪው ብትሞክሪ የብርሃን ፍንጣቂዎቹ ቀዳዳ እየፈለጉ ያበራሉ። እንደሚወድሽ ትጠራጠሪያለሽ?” አለችኝ።
“አላውቅም እማ! ገና አጭር ጊዜ ነው ካወቅኩት እንኳን። አላውቀውም!” ከማለት ውጪ ግራ ስለሚያጋባኝ ድርጊቱ ለሷ ማውራት አልችልም። አንዴ በፍቅር አክናፍ አፈናጦኝ አርያም የደረስኩ እንዲሰማኝ ያደርገኝና መልሶ ለቀናት በመሃከላችን ከጓደኝነት የዘለለ ነገር እንደሌለ ያስመስላል። ባለፈው ለት አቅፎኝ አድሮ ጠዋት ስነቃ አጠገቤ ካለመኖሩ በላይ ሳገኘው ማታ እቅፉ ውስጥ እንዳልነበርኩ ያስመስላል። አላውቅም! እንዴትስ ማወቅ እችላለሁ? አዝኖልኝ ይሆን ወዶኝ ራሱ ካልነገረኝ በምን አውቃለሁ?
“ሚሚሾዬ የምትፈልጊውን ነገር ለማግኘት ምቹ ጊዜ እስኪመጣ ወይም ጊዜው የምትፈልጊውን ይዞ እስኪመጣ ቁጭ ብለሽ ለመጠበቅ ህይወት በጣም አጭር ናት። በእጅሽ ያለውን ጊዜ ምቹ አድርጊው።” አለችኝ የተዘጋጀ ምግብ እንደመጉረስ ቀላል ነገር የተናገረች ይመስል ልዝብ ብላ።
በቆምኩበት ሀሳብ ሳመነዥክ ፍትህ ተመልሶ መጣ።
“ባለፈው እማዬ ራሷን የጎዳች ቀን ስናወራ የእህቴን ሰርግ ላለመሄድ እና ለአባቴ ጥብቅና ላለመቆም በምላሹ አንድ ነገር እንዳደርግልህ ጠይቀኸኝ ነበር። ታስታውሳለህ? ምን ነበር?” አልኩት ለመሄድ እየተጣደፈ ስለነበረ ላቆየው ፈልግያለሁ።
“እኔ እንጃ! ብዬሽ ነበር? ትዝ አይለኝም።” አለኝ ጥድፈቱን ሳያቆም ትከሻዬን ጨበጥ አድርጎኝ በቆምኩበት ትቶኝ ሄደ። ከፋኝ። የሚናገረውንና የሚያደርገውን ነገር በፍቅር የምተረጉመው ብቻዬን እንደሆነ ተሰማኝ።ለእርሱ ከቀን ተቀን የተለመደ ድርጊትና ንግግር በላይ ዋጋ ያለው ነገር አልነበረም ማለት ነው። እግሬን እየጎተትኩ እማዬጋ ተመለስኩ። እማዬ እየደጋገመች ምን እንደሆንኩ ትጠይቀኛለች። እየደጋገምኩ የሆንኩት ያለመኖሩን እመልስላታለሁ። ሲመሻሽ ካሳሁን ቢመጣም እንደሌላው ቀን መደሰት አልቻልኩም። አንድ የሰውነቴ አካል የከዳኝ መሰለኝ። በሩ በተከፈተ ቁጥር እሱ እየመሰለኝ አፈጣለሁ። አባቴ ሊያድር ስለመጣ እኔና ካሳሁን ወደየቤታችን ሄድን። ጭራሽ ያለወትሮው ስልክም ሳይደውልልኝ አደረ። በሚቀጥለው ቀን ምሽት ሆስፒታል እማዬጋ ቁጭ ብዬ ደውሎልኝ ሊያገኘኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ።
“ታዲዎስ ተገድሏል!” አለኝ የተቀጣጠርንበት ካፌ ደርሼ ገና ሳልቀመጥ። ያለኝ ገብቶኝ ሳያልቅ ቀጠለ “ያልታወቁ ሰዎች በጩቤ ወግተውት መንገድ ላይ ወድቆ ነው የተገኘው።” ተስፋ የቆረጠ፣ የተናደደ፣ ያዘነ… … ብዙ ዓይነት ስሜት ነው የሚፈራረቅበት። “…… ጓደኛው ነው ደውሎ የነገረኝ። ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ? ‘በሰላም ይኖር የነበረውን ልጅ አስገደልከው። አንተ ነህ ያስገደልከው።’ አለኝ።” የተፈጠረው ነገር በጣም ስሜታዊ ስላደረገው ቅደም ተከተሉን ያልጠበቀ ወሬ ነው የሚያወራኝ።
የትዝታ ፍቅረኛ ታዲዎስ ባልታወቁ ሰዎች ተገድሎ ለቤተሰቡ መርዶ ተረድቷቸው አስክሬን እየጠበቁ ነው። ፍትህ በተደጋጋሚ ደውሎለት ስልኩ እንቢ ብሎት ነበር። የትዝታ አባት ትንፍሽ ቢል እንደሚገድለው ለፍትህ በተናገረ ማግስት ሞቶ መገኘቱ አጋጣሚ ሊሆን አይችልም። ግን ማስረጃ የለም። አጋጣሚ ግጥምጥሞሽም ሊሆን ይችላል። የሟች ጓደኛ ሞቱ ከፍትህ ጋር ከማውራቱ ጋር የተያያዘ መሆኑን በምን እርግጠኛ ሊሆን ቻለ?
“ትዝታ አንቺን ማግኘት ትፈልጋለች።” አለኝ በጎርናና ድምፅ “ምናልባት የምትነግርሽ ነገር ሳይኖር አይቀርም። የታዲዎስን አሟሟት ስነግራት ኩርምት ብላ ነበር የተንሰቀሰቀችው። እሷም ‘አስገደልከው’ አለችኝ። ማን? ለምን? ለሚለው ጥያቄዬ ግን መልሷ ዝምታ ነበር።” ሀዘናቸው ተጋብቶበታል። እሱም አስክሬን የሚጠብቅ ለቀስተኛ መስሏል።
“እሺ! አንተ ተረጋጋ እና ወዴት እንደሚወስደን እናስብ።”
“አይታይሽም? ወዴትም መሄጃ የለም።”
“ገና ከአሁኑ ተስፋ ቆርጫለሁ እንዳትለኝ? ገና ሳትጀምረው ይሄ ጉዳይ የተወሳሰበ ሊሆን እንደሚችል ነግሬህ ነበር። ገና ከመጀመርህ እጅ መስጠትህ ነው?” ስለው በቃል አልመለሰልኝም። ሁኔታው ግን የመሸነፍ ነው። ላፅናናው አልሞከርኩም። ምን እያሰበ እንደሆነ አላውቅም። እኔም በሀሳብ ተጠምጃለሁ። …… ሆስፒታል ማደር የእርሱ ተራ ነበረ።
“ወደቤት ሄደህ እረፍ! እማዬጋ እኔ እሆናለሁ።” አልኩት። ሄደ። እስከ ሶስት ቀን አልተመለሰም። ስልኩም ዝግ ነበር።
“ምን ሆኖ ነው? አስቀየምሽው እንዴ? ንገሪኝ ምን ተፈጥሮ ነው?” እማዬ ሶስት ቀን ስላላያት በጥያቄ ልትደፋኝ ነው። በስራ ምክንያት መሆኑን ብነግራትም አላመነችኝም። ካሳሁን ሲመጣም ተመሳሳይ መልስ ቢሰጣትም አላመነችም። አባቴ እንኳን ‘ምነው ጠፋ?’ ብሎ ጠየቀኝ።
ትዝታን ላገኛት ቀጠሮ አስይዤ አገኘኋት። አልቅሳ የሷን ጉዳይ እንድንተወው ለመነችኝ።
“ነገር መቆፈራችሁን ካልተዋችሁ ሌላ ተጨማሪ ሰው ይጎዳል።” አለችኝ ቃል በቃል።
“ተጨማሪ ማለት ከታዲዎስ ሌላ ማለትሽ ነው? ማነው የሚጎዳው? ልጅሽ? አጎትሽ? ሌላ ማን?” ከዚህ በኋላ ለጠየቅኳት ብዙ ጥያቄ መልስ አልሰጠችኝም።
“የልጅሽ አባት በሰው ነው የተገደለው። በእርግጠኝነት የምታውቂው ነገር አለ። መናገር ግን አትፈልጊም። ማንን ነው እየተከላከልሽ ያለሽው? ለልጅሽ ስታድግ ምን ምላሽ ይኖርሻል? አባቴስ ስትልሽ ምንድነው የምትያት? የአባቷን ገዳይ በነፃነት እንዲኖር የፈቀድሽበትን ምክንያት ታስረጃታለሽ? አባቷን በግፍ ላጣች ልጅ በቂ ምክንያትስ ይመስልሻል? ወይስ የአባቷን አሟሟት ትዋሻታለሽ? እስከመቼ? እውነት ቢረፍድም አንድ ቀን መውጣቷኮ አይቀርም።……… ” ምንም ቢሆን እናት ናትና ደካማ ጎኗ ልጇ ናት። ትዝታ ግን አልተሸነፈችም። ልወጣ ቦርሳዬን ሳነሳ
“የሱ ልጅ አይደለችም። አባቷ አይደለም።” አለችኝ። ከዛ በላይ ግን ልትነግረኝ አልፈለገችም። እየወጣሁ ለፍትህ ደወልኩለት እና ተገናኘን። ከትዝታ ጋር ያወራሁትን ነገርኩት። ሞቶ የነበረው መነቃቃቱ አንሰራርቶ መላምቶቹን ይነግረኝ ጀመር።
“የልጇ አባት እሱ ያለመሆኑን የተናገረችው እውነት ከሆነ ትዝታ ከሌላ ሰው ጋር ግንኙነት ነበራት። ምናልባትም አጎቷ ልድራት ነው ካለው ሰውጋ… … አንዱ ባለስልጣን ወይም አንዱ ሀብታም ይሆናል። ምናልባት ሟች በሆነ መንገድ ከዚህ ሰው ጋር ተያያዥነት ሊኖራት ይችላል። …… ምናልባት…… በስመአብ ወ ወልድ… … እኔ ያሰብኩትን አስበሃል?”
“በትክክል!!…… እያሰብኩ ያለሁት እንደሱ ነው!” አለኝ