አክራሞታችን ሸጋና ፍሬያማ እንደሆነ ተስፋ አለኝ። ራእይ-2ን ከጻፍኩ ሳይታወቅ አንዱ አልቆ ሁለተኛው ሳምንትም ተገባድዶ አረፈው። እኔ በእኔ ነገሮች ተወጥሬ ጊዜውም ሳያስበው በራሱ ፍጥነት ሄደ ማለት ነው። ከቀረ የዘገየ ይሽላል በማለት … የደመቀ የሞቀ ሳላምታዬን ለሀሳብ ቤተሰብ፣ ጎረቤት ወዳጆቼ በእጅ በእጃችሁ አቀርባለሁ። በየገጸ-ፊታችን መተያየት መቻላችን ደስ ያሰኘኛል። ደግሞ … በሆነ ምክንያት ሳምንቱ የከበዳችሁ … ቆዘም ብላችሁ የከረማችሁም አይዟችሁ — ይህም ያልፋል … እስኪያልፍ ያስተምራል ብላችሁ ለማለፍ ሞክሩ — በርቱ።
ከራእይ-2 ጽሁፌ ግርጌ የተሰጡ አስተያየቶችን ሳይና ሳስብ … በሳጥኔ ውስጥ የመጡ ጥያቄዎችንና አሳቦችንም ስቃኝ ቆይቻለሁ። ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የማስሎውን የፍላጎት መሰላል ከራእይ አንጻር እንዴት ታየዋለህ? ራእይና ምናብ የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ያምታታል፣ እንዴት ሊለይ ይችላል? በዚህ ችግር በቆላው ሀገር ውስጥ … ምርጫችን በሌሎችና በሁኔታዎች አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ሀገር ባለራእይ መሆን የሚመስል ነገር ነው ወይ? የህይወቴን ራእይ እንዴት ላውቅ እችላለሁ? ይገኙበታል። ሌሎቹን ጥያቄዎች በዚህና በቀጣይ ጽሁፍ ላይ ላነሳሳቸው እሞክራለሁ።
በአካላዊ አለም ያለውን ነገር ብርሃንና አይናችን በሚፈጥሩት መዋደድ የምናገኘውን እይታ አይነሥጋ ብለነው ነበር። ምናብ (imagination) ደግሞ ገና በሀሳብ አለም ውስጥ ያሉ ነገሮችን (ለምሳሌ ልንሰራ ያሰብነውን ቤት ወይም ልናገባ የምንመኘውን ሰው) ነገሩ ከመሆኑ በፊት በልቦና አይናችን የምናይበት እይታ ነው። ለምሳሌ ከቤት ስንነሳ በየት በኩልና በምን የመጓጓዣ መንገድ እንደምንሄድ አማራጮቻችንን ባይነ ልቦናችን እናየለን። ከቤት ወጥተን ስንሄድ የሚያጋጥሙን ዝርዝር ጉዳዮች ግን በብዙ የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ፣ የተወሰነ ማስተካከያም ሊያስፈልግ ይችላል። ለምሳሌ መንገዳችንን ከጀመርን በኋላ … በድንገት ሊዘንብ ወይም ከብዙ አመታት በፊት ያየነውን የልጅነት ልናገኝ እንችላለን … ይህ ደግሞ ባይነ ልቦናችን ያላየንው ጉዳይ ሊሆን እንደሚችልና … በጉዟችን ላይ የተወሰነ ለውጥ ሊያስከትል እንደሚችል ይታወቃል።
ለምንኖርበት ከተማ/ሀገር፣ ለምናገባው ሰውና ለምመሰርተው ቤተሰብ፣ ለምንመርጠው የትምህርት ዘርፍና የሥራ አይነት ውሳኔና መመሪያ የምናገኘው ግን ራእይ የሚባለው የህይወት እይታ ነው። የምንመርጣቸውን ጓደኞቻችንና የምንከተለውን እምነት ሁሉ ባንድ ጠቅልሎ የሚይዝና ለህይወታችን ትርጉምና አላማ የሚሰጠው በአይነ ህሊናችን ብቻ የምናየው … የህይወታችን አላማና በውስጣችን ተቀብሮ ያለው የመሆን አቅምና ችሎታ ነው። ይህንን የመሆን እምቅ አቅምና የመኖር አላማ አይቶ መረዳቱን ነው ራእይ የምንለው። ይሄ ደግሞ ከምናብ ይረቃልም ይለያልም።
ራእይ ራስን ማወቅ ነው። ደግሞም የመኖርን ትርጉም ማግኘት ነው። እኔ ማነኝ? ለምን ምክንያት ነው የምኖረው? ደግሞስ መኖር ብቻ ሳይሆን ልሞትለትስ ፈቃደኛ የምሆንለት ጉዳይ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችለን ራእይ ነው። ራእይ መጨረሻውን መጀመሪያ ላይ ማየትና መረዳት ነው።
የማስሎው የፍላጎት መሰላል (Abrham Maslow’s hierarchy of needs) – መሰረታዊ ፍላጎት (ምግብ መጠጥና አካላዊ የመኖር ፍላጎቶች) -> ደህንነትና ከስጋት ነጻ የሆነ ኑሮ መኖር -> መውደድና መወደድ/መወዳጀት -> በሌሎች መከበርና ለራስ ጤነኛ ክብርና ግምት መስጠት -> ራስን በጥልቀት ማወቅና ሙሉ ለሙሉ መሆን … ናቸው። ሰዎች በባህርያችን መጀመሪያ ያለው ሳይሟላልን ለቀጣዩ ፍላጎት አንማስንም። የታችኛው ረሀባችን እንዲሞላላን የላይኛውን ፍላጎት መስዋእት ማድረጋችን አይቀርም ይላል የማስሎው ቲዎሪ። ሆኖም ግን እንዱን ሙሉ ለሙሉ ጨርሰን ወደ ሌላው እንደማንወጣ፣ ደግሞም የላይኛው ላይ የደረሰ ሰውም ቢሆን የታችኛውን ለማሟላት ጥረቱ እንደሚቀጥል ያስረዳል መሰላሉን የፈጠረውየስነ ልቦና ሊቁ ማስሎው።
የማስሎው መሰላል የሰው ልጅ የፍላጎት ደረጃ መሰላል ነው። ራእይ ደግሞ የሕይወት ግብንና የመሆን ጉዳይን ነው የሚመለከተው። ራእይን መረዳትም ሆነ መኖር በአንዴ የሚፈጠር ሳይሆን የእድሜ ልክ ሥራ ነው። ራእይን አጥርቶ ከማየትና ከመሆን አንጻር የእድሜ ልክ ሂደትና ስራ ነው። ሰው የህይወቱን ራእይ በእስር ቤትም ሆነ በጎዳና ላይ ሊያገኘው ይችላል። በቤተመንግስት ተሹማም ይሁን ቤተመቅደስ ውስጥ በተመስጥኦ በጸሎት ሆና ልትረዳው ትችላለች።ማየት ከመሆን ይቀድማል።
ዛሬ ጠዋት አንዲት ጓደኛዬ በቅርቡ በሚት-ኢቲቭ (ተፈራ ገዳሙ) ላይ ቀርባ የነበረች ወጣትን ታሪክ እንዳይ የዩቲዩብ ማጣቀሻውን ላከችልኝ። ባለታሪኳ ወጣት ሀበሻ ስትሆን በአሜሪካ ሀገር ያደገች ናት። ከታዋቂው የሀርቫርድ የህግ ትምህርት ቤት ተመርቃለች።እድሜዋ ገና አምስት አመት ሊሆን ግድም ነው የማየትና የመስማት ችሎታዋን ያጣችው። አሁን ግን የመጀመሪያዋ አይነ ስውርና መስማት የተሳናት ከሀርቫርድ ዩሂቨርስቲ የተመረቀች ጠበቃ ለመሆን በቅታለች። ዛሬ በየስፍራው ሰለ አካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብት ተሟጋች ሆና የምትሰራ የልጅነት ህልሟን የምትኖር ባለስኬት ሰው ሆናለች።
‘መስናክሎቼ፣ ተግዳሮቶቼና አካላዊ ውሱንነቴ … መሆን ከምፈልገውና ውስጤ ከተቀበረው ህልሜ ሊያግዱኝና ሊያስቀሩኝ አልቻሉም’ በማለት በአጽንኦት ትናገራለች። ‘የሆንኩትን ሁሉ የሆንኩት መሆን የምፈልገውና የተፈጠርኩለት ስለሆነ ነው እንጂ የሌሎችን ነቀፋ ለማሸነፍ ወይም ካጋጠመኝ አካላዊና ማህበራዊ ፈተናና ጋሬጣ በመነሳት አይደለም’ ስትል ጣፋጭ አንደበቷ ተሰምቶ አይጠገብም።
(ይሄው ማጣቀሻው የቀረውን እናንተው ተከታተሉት)
https://www.youtube.com/watch?v=13puGDZtr5E
ታዲያ በመጀመሪያው ጽሁፌ ላይ ባነሳሁዋት ትንሽ ልጅና በዚህች በስኬት የተንቆጠቆጠች ወጣት መሀል ያለውን ልዩነት ምንድነው? የእድሜ ልዩነታቸውን ለማጥፋት ሁለቱንም የአምስት አመት እድሜያቸው ላይ ውሰዱና አስቧቸው። በጎዳና ላይ ያገኘኋት ትንሿ ሚሚ — ሙሉ አካል፣ ብሩህ አይኖችና ስል ጆሮዎች ያላት ናት።ግን በልጅነቷ በጎዳና ላይ ተጥላ በመለመን የሆዷን ጩኸት አልፋ ማለም አልቻለችም። የአካባቢዋ ታጋች … የእድሏ እስረኛ ያደረጋት ምንድነው? በሌላ በኩል ደግሞ የዛሬዋን ጠበቃ የያኔዋን ሌላዋ ሚጡም … እይታዋንና መስማቷን በጨቅላ እድሜዋ በመንጠቅ እድል ፊቷን ብታዞርባትም የአካል ጉድለቷ እስረኛ ሳትሆን ወደ ግብና የልጅነት ህልሟ እንዴት ደረሰች?
አይነ ሥጋና ጆሮ ቢታጡም አይነልቦናና አይነ ህሊና እስካልታወሩ ህልማችንን ከመሆን የሚያግደን ኃይል የለም። የጠነከረ የመሆን ህልም ከኖረን … ያንን መሆን የፈለግነውን ነገር በውስጥ አይናችን ለማየት ከቻልን … ወደ መሆን የሚደረገው ጉዞ ቀና ጅማሬ አገኘ ማለት ነው። ለጎዳናይቱ ሚሚ ዋና ችግሯ … ጎዳናው ወይም የተፈጠረችበት ቤተሰብ ወይም ያላት አካላዊና ኑሯዊ ውሱንነትና ድህነት ብቻ ነው ወይ? የጎዳናይቱ ሚሚን የልቦናና የህሊና እይታዋን ማንቃት ቢቻል … የሰው ቤት ሰራተኛ መሆንን ህልሟ አድርጋ በማሰብ እንዳትታሰር ማድረግ አይችልም ወይ? በርግጥ የቤት ስራተኛ መሆን እንደስራ ምንም ችግር የለውም — ችግሩ ህልማችን እሱ ሲሆን ነው። መጀመሪያ መለወጥ ያለበት ህልሟ ነው ኑሮዋ?
ነገሩ እንዳይበዛና እንዳይንዛዛ እስኪ ለህልመ-ስንኩልነትና ምናበ ስውርነት ሊዳርጉ ይችላሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ጥቂት ነጥቦች ልዘርዝርና እስከ ሳምንት እነርሱን እያመነዠክን እንቆይ።
1. ስንኩል ሰበብና ርካሽ ምክንያቶች (lame excuses and cheap reasons)
2. የሀሳብና የሞራል ጠኔ (idea starvation and moral depravity)
3. የመሪና የተምሳሊት እጦት (Lack of leadership and role models)
4. ጨለምተኛ አመለካከትና የሞተ ወኔ (Pessimistic Attitude & demotivation)
5. ባዶ ኩራትና ከንቱ ጉራ (empty pride and vain glory)
6. ልክ የለሽ ግፍና የተንዛዛ እንግልት (Abuse and neglect)
7. ጭፍን ልማድና ትብታብ ባህል (blinding superstition and enslaving culture)
8. የእጦት አስተሳሰብና የዘቀጠ ቅንጦት (scarcity mentality and spoiled luxury)
9. ማን አለብኝነትና አለማወቅን አለማወቅ (Arrogance and Ignorance)
የኛስ ራእይ እንቅፋትና ተግዳሮት ምን ይሆን?
One Comment
ዶ ርየ ነፍሰን ነዉ የምታለመልመዉ።