እሱን ዞሬ አየሁት! መልሼ እነሱን አየሁ! እግሬ መቆም አቃተው! ዘሎ እጆቹን ከስሬ ሲያነጥፋቸው፣ እጁ ላይ ራሴን ስጥል፣ አይኔ ከመከደኑ በፊት ከጉሮሮው የማይወጣ ጩኸት እያማጠ ሊጮህ ሲታገል አየዋለሁ። ስቃይ ያለበት ፊት……….
ሰከንዶች ወይ ደቂቃ አላውቅም እጁ ላይ ምንያህል እንደቆየሁ ግን እንደነበርኩ መሬቱ ላይ ስለሆነ የነቃሁት ብዙም ጊዜ እንዳልሄደ ገምቻለሁ። የረጠበ ፎጣ ደረቴና ግንባሬ ላይ አድርጎልኝ እሱ ቁና ቁና እየተነፈሰ ነቃሁ። ተጠርቶ ይሁን ማወቅ ያልቻልኩት ጎረቤት ያለው ሰውዬ ተሸክመው ወደ መኪናው እንዲወስዱኝ ይወተውታል። መርዶ ሊያረዱኝ የመጡት ሰዎች ይተረማመሳሉ። ፀሃይ ፀሎት ይሁን ወቀሳ ያልለየለት ማልጎምጎም ለአምላክም ለእኛም ታሰማለች። መተንፈስ አቅቶት ሲጨነቅ እሱን ያየው የለም። የተንተራስኳቸው እግሮቹ ይንቀጠቀጣሉ፣ ፎጣ የያዙት እጆቹ ይንቀጠቀጣሉ። ግንባሩ ላይ ላቡ ኩልል እያለ ነው። ማንም አላስተዋለም! የሚያወራው አይሰማኝም ግን አፉ ይንቀሳቀሳል። እኔን አፋፍሰው መኪና ውስጥ ካስገቡኝ በኋላ እሱ እላዩ ላይ አስተኝቶኝ ከጎረቤት የመጣው ሰውዬ እየነዳ ወደሆስፒታል ሄድን። መርዶ ነጋሪዎቹ ወደቤት ተመለሱ።
«እኔኮ ደህና ነኝ! ነቅቻለሁኮ!» እለዋለሁ እየደጋገምኩ ባለኝ አቅም የእሱ ሁኔታ ጨንቆኝ። አፉ ይንቀሳቀሳልኮ ግን ቃል አይዋጣውም። ሆስፒታል እንደደረስን ያስመልሰው ጀመር። የታመመው ማን እንደሆነ ግራ እስኪገባ እርሱ ብሶ ቁጭ አለ። በላይ በላዩ እየተነፈሰ ማስመለስ ቀጠለ። ነፍሱ ካልወጣው ብላ እየታገለችው ነው የሚመስለው። ፊቱ ላይ የተገታተሩት ደምስሮቹ ካጠመቀው ላብ ጋር ሲኦልን ያየ ነው የሚመስለው። እኔ ተወስጄ ጉሉኮስ እየተሰጠኝ ዶክተሩ ስለራሴ እየጠየቀኝ ሁላ እሱ ምን ሆኖ እንደሆነ ነው የምጠይቀው።
«panic አድርጎ ነው።» ይሉኛል። እንዲህ የሚባል ነገር ስለመኖሩ ራሱ ዛሬ ነው የምሰማው። ሰዎች ሲደነግጡ በተለይም በህይወታቸው ከዚህ በፊት ገጥሟቸው የነበረ አስፈሪ ወይም አስደንጋጭ አጋጣሚ ከነበር ተመሳሳይ ነገር ሲገጥማቸው ሊፈጠር ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ለምሳሌ መድረክ ላይ ሲወጡ ፓኒክ የሚያደርጉ አሉ ……………. በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸው ሰዎችም አሉ። ………… ያለማቋረጥ እየጠየቅኩ ስላስቸገርኩ አብራራልኝ። ከሰዓታት በኋላ የራሱን ህክምና ጨርሶ እኔ ወደተኛሁበት ክፍል መጣ………… ፊቱ ጥላሸት መስሎ፣ ከጣረሞትጋ ሲታገል የቆየ አይነት መስሎ ፣ ከፍ ያለው ትከሻው ወርዶ ፣ ቀና ያለው አንገቱ አቀርቅሮ ………… የእርሱ ባልሆነ አረማመድ የእርሱ ያልሆነ አመጣጥ መጥቶ አልጋው ጫፍ ላይ ተቀመጠ። የሆነ ነገር እንደተፈጠረ ቢገባኝም ምን ብዬ እንደምጠይቅ ግራ ገባኝ!
«ምግብ ስለማትበዪ አቅም ጨርሰሽ ነው አሉኝ!» አለኝ ሞገስ በራቀው ቀሰስተኛ ድምፅ ቀና ብሎ ሊያልቅ የደረሰውን ጎሉኮስ እያየው።
«አዎ እኔ ደህና ነኝ! አንተ ደህና ሆንክ?»
«ደህና እሆናለሁ! ትንሽ ማረፍ አለብኝ። ወንድምሽ እየመጣ ነው! ትንሽ እረፍት ካደረግሽ በኋላ ወደ ቤት ይወስድሻል።» አለኝ
«አንተስ?»
«ወደቤት ልሂድ!» በሚያቃጥል እጁ ፊቴን ነካካኝ። መልሶ ጉሉኮስ ያልተደረገበትን እጄን አንስቶ በመዳፉም በአይበሉባውም እያገላበጠ ሳመው። ዓይኖቼን ተራ በተራ ሳማቸው፣ በሹክሹክታ ነገር «ምንም አትሁኚ!» አለኝ። መርበትበቱ በፍፁም የእርሱ አይደለም። «ምንም አልሆንኩምኮ ደህና ነኝ!» አልኩት!!…………………የስንብት እንደሆነ ልቤ ነግሮኛልኮ ላለማመን ታገልኩ እንጂ …………………. ለደቂቃ ከንፈሬን ከሳመኝ በኋላ። ተነስቶ አሁንም ድጋሚ «ምንም እንዳትሆኚ!» ብሎኝ ወጣ!! ልቤ ተከትሎት ሄደ……. ስንብት እንደሆነ ነፍሴ አውቃለች። ሆድ ባሰኝ!! ተከትዬው ሄጄ አትሂድብኝ ማለት አማረኝ። ……
የአባቴን ለቅሶ እንኳን አልመጣም! ቀብር የለ፣ ሳልስት የለ፣ ……. «አዲስ የት ነው? እንዴት ቀብር እንኳን ይቀራል? ምን አይነት ሰው ነው?» ሲሉኝ መልስ አጣሁ። ሀዘኔን አከበደብኝ። የአባቴን ለቅሶ እንኳን በነፃነት እርሜን እንዳላወጣ አሳቀቁኝ። <እንዴት የሚስቱን አባት ለቅሶ አይመጣም?> አይነት አስተያየታቸው አንገበገበኝ። አዲስ የለም! እንኳን ለቅሶ እቤትም የለም! ከአስራ ሁለተኛው ቀን በኋላ ወደ ቤት ልሂድ ብዬ ስነሳ እናቴ ተከትላኝ ከቤት ወጥታ
«ምንድነው ጉዱ? ከባልሽ ጋር ሰላም አይደላችሁም እንዴ? ደግሞስ ምንም ቢሆን ሀዘን ሀዘን አይደል እንዴ? እንዴት ይቀራል?» ስትለኝ መከፋት፣ ንዴት፣ የአባዬ ሀዘን፣ የአዲስ ህመም……… ሁሉም የእስከዛሬ ጥርቅም ግንፍል ብሎ ተዘረገፈ።
«ዛሬ ለቅሶ ቀረ ብላችሁ ለመውቀስ ጊዜ ነው ሰላም መሆናችን የሚያስጨንቃችሁ? ትዳርሽ እንዴት ነው ብለሽ ጠይቀሽኝ ታውቂያለሽ? ደስተኛ ነሽ ወይ ብለሽ ጠይቀሽኝ ታውቂያለሽ? ንገሪኝ እስኪ እናቴ ደህና መሆኔን ለመጠየቅ ወይም ናፍቀሽኝኮ ብለሽ የደወልሽልኝ መቼ ነው? ብር ያለው ሰው ስላገባሁ የናንተ ፍቅርና መጠየቅ የማያስፈልገኝ፣ የሆነ ነገር ስትፈልጉ ብቻ የምትደውሉልኝ፣ ደበረኝ ስላችሁ ምን ጎድሎሽ ነው የሚደብርሽ አትቅበጪ የምትሉኝ፣ እናቱ የሞተችበት እና እናቱ ገበያ የሄደችበት እኩል ያለቅሳሉ እያላችሁ መከፋቴን ቅንጦት የምታደርጉብኝ። ለወቀሳ ሲሆን እና መሃን ነው ያገባችው ባል እያላችሁ ከእህቶችሽ ጋር ለማማት ጊዜ ግን ትዝ እላችኋለሁ።»
ደነገጠች። እንዲህ ተናግሬም ስለማላውቅ ዝም አለች። እንደልጅነቴ ውስጧ ክትት አድርጋ አቀፈችኝ እና «ወይኔ ልጄን!» አለች በቁጭት! «እኔ ልብሰልሰልልሽ!» በቁጭት ማልቀስ ስትጀምር እኔ ብሼ ተገኘሁ። አይኔ ሊፈርጥ እስኪደርስ ተነፋርቄ ወደቤቴ ተመለስኩ። አዲስ አልመጣም!! አሁን ሀሳብ ያዘኝ! ምን ሆኖ ነው? የት ብዬ ልፈልገው? የዛን ቀን የሆነውን እያሰብኩ የሆነ ነገር ሆኖ ቢሆንስ ብዬ ተጨነቅኩ። ስልኩ ዝግ ነው። ቢያንስ እንዴት ስልኩን ለስራ ሲል ክፍት አያደርግም? ስራ ቦታዎቹ በሙሉ ዞርኩ። ሁሉምጋ ለተወሰነ ጊዜ እንደማይመጣ ነግሯቸው ሀላፊነት እና ስራ አከፋፍሎ እንደሄደ ሰማሁ። ቢጨንቀኝ ፀዲጋ ተመልሼ ሄድኩ። ሰብለምጋ ደወልን! በፍፁም እንዲህ አይነት ባህሪ እንደማያውቁበት ቤቱን እንደቤተክርስቲያን የሚሳለም ሰውዬ ለሁለት ሳምንት ከቤቱ የሚጠፋበት ምክንያት ማሰብ አቃታቸው።
ቤተሰቦቼጋ እየተመላለስኩ ብጠይቃቸውም ባሌ ቤቱን ለቆ ከጠፋ ሰነባበተ ብዬ የምናገርበት አቅም አጣሁ። በአባዬ ሞት እማዬ ተሰብራ ስለነበር ቤቷ አይኗ እያየ በጥጋበኛ ቁማርተኛ ሲወሰድባት ዝም ብዬ ማየት ስላቃተኝ ብሩን በጊዜ ገደብ እንድንከፍላቸው ወንድሜ ተስማምቶ መጣ። በ18 ወር ቀስ እያልኩኝ ልከፍላቸው። አዲስ ይመለስልኛል ብዬ አስቤ ከመጣ እና ከጠየቀኝ አስረዳዋለሁ። ካልጠየቀኝ እሰየው ብዬ ወስኜ ነው።
ከአንድ ወር ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደቤት ተመለሰ። ሌላ ሰው ሆኖ መጣ! ያ ሆስፒታል የተሰናበተኝ ሰውዬ አይደለም። ያ በፍቅሩ እየጨስኩ ሳልነግረው ሳለ በልዝቡ የሚወደኝ ሰውዬም አይደለም። ያ መጀመሪያ ሳቀው ጤንነት እንደጎደለው ሰው እንጋባ ያለኝ ሰውዬም አይደለም። ያ በመሃል እያለሁ እንደሌለሁ የሚቆጥረኝም ሰውዬ አይደለም። ሌላ ሰውዬ! አዲስ ሰውዬ ሆኖ ተመለሰ።
ሳየው በደስታ ጦዤ ስጠመጠምበት ልክ ምንም እንዳልተፈጠረ፣ ትናንት እዚሁ እንደነበረ ሁሉ፣ ጭራሽ <ምን ሆነሻል?> በሚል ግራ መጋባት እንደዝምብሎ አስተቃቀፍ ለእቅፌ ምላሽ ሰጥቶ ከቅድም የቀጠለው ውሎ እንደሆነ ነገር ቤት ውስጥ ይንቀሳቀስ ጀመር። ስር ስሩ እየተከተልኩ።
«ምን ሆነህ ነው? እሺ ቆይ በደህናህ ነው ይሄን ያህል ቀን? የት እንደነበርክ አትንገረኝ ቢያንስ ደህና ሆነህ መሆኑን አትነግረኝም?» እለዋለሁ።
«ደህና ነኝ አልኩሽ አይደል? ከራሴ ጋር ጊዜ መውሰድ ፈልጌ ነው!!»
«እና እንደዛ ብለህ አትናገርም? ትጨነቃለች ብለህ አታስብም?»
እያፏጨ እቤት ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ይላል። ስለምንም ስለማንም ግድ እንደማይሰጠው። የማላውቀው ሰውዬ ነው። ንዴትም፣ መከፋትም ከዛ ደግሞ ያልገባኝ መዋረድም አይነት ስሜት ተሰማኝ። ትንሽዬ እልህም ነገር። ትቼው ወደመኝታ ቤት ገባሁ። ምን ማሰብ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። በምንም መንገድ ይሄን ሰው ማወቅ እንደማልችል ተረድቻለሁ። <አወቅኩት ብለሽ ስታስቢ ተቀይሬ ብታገኚኝ> ያለኝ ይሄንን መሆኑ ነው? እኔ ግን መንቀሳቀስ ቸገረኝ፣ ወዴት ልንቀሳቀስ? በቃ አዲስ ከህይወቴ ወጥቷል ብዬ ልንቀሳቀስ? ይሂድ? ይቁም የማውቀው እንኳን የለኝምኮ። ልሂድስ ብል ወዴት ነው የምሄደው? እናቴጋ? ግራ ገባኝ! ያለኝ አማራጭ የሚሆነውን ዝም ብሎ ማየት ነበር። የሚሆነው ግን ለመረዳት የቸገረ ነበር።ሌላኛውን መኝታ ቤት በቋሚነት እንድታሰናዳለት ለፀሃይ ትዕዛዝ ሰጠ። ጠዋት ከእንቅልፉ ይነሳል ልክ ምንም ዓይነት ነገር በመሃከላችን እንደሌለ የአዘቦት ቃለምልልስ እናደርጋለን። ጓደኛውን ቻው እንደሚል አይነት <ደህና ዋዪ> ብሎኝ ይወጣል። ምሳ ይመጣል። ስራ ቦታ ስለዋለው ውሎ ያወራል። ተመልሶ ይሄዳል። ማታ ይመጣል። አሁንም ልክ እንደ ትክክለኛ ነገር የቀን ውሎውን ወይም የሆኑ ፍልስፍናዎቹን፣ ወይም ስለገጠመው አዲስ ነገር ሲያወራ ይቆያል። እራቱን በልቶ ላይብረሪ ይሄዳል። ከዛ ወደራሱ መኝታ ቤት!!
እሺ ምን ላስብ? አብረን ነን? ወይስ አብረን አይደለንም? ተጣልተናል ወይስ ሰላም ነን? ልክ ያልሆነ ነገር እየሰራ ያለው እሱ ሆኖ ለማውራት እና ለመጠየቅ የምፈራው እኔ መሆኔስ ምን ይሉታል? ከብዙ እንዲህ ዓይነት ልክ የሚመስሉ ልክ ያልሆኑ ቀናት በኋላ ላይብረሪ ተቀምጦ ላወራው ሄድኩኝ።
«እስከመቼ ነው እንዲህ እንድንሆን ያሰብከው? ምነድነው? ምንድነን እኔና አንተ?»
«ምን ሆንን? ምን መሆን ነበረብን? የአኗኗር ዘይቤዬ ላይ አንዳንድ ለውጦች አድርጊያለሁ። አንዳንዱ ካንቺ ያኗኗር ሁኔታጋ ላይሄድ ይችላል። ያው እንደምታውቂው እኔ ማንንም በማስገደድ አላምንም! የግድ መስማማት የለብሽም!» በአዲስ ሰውነት ውስጥ የሆነ ጋጠወጥ ባለጌ ሰውዬ እያናገረኝ መሰለኝ።
«ምን ማለት ነው? »
«ማለትማ ራሴ ላይ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገኝ ነበር። ያንን ነው ያደረግኩት! የሰው ልጅ በየሆነ ጊዜው ራሱን upgrade ማድረግ ያለበት አይመስልሽም?»
«upgrade እስከገባኝ ድረስ ወደመሻሻል ነው። ወደመዝቀጥ አይደለም።»
«ኑሮውን የሚኖረው ባለቤቱ አይደል? እየተሻለው ይሆን እየባሰበት የሚያውቀውም ባለቤቱ ነው። እንደቁስ ተጠቃሚው ቼክ አድርጎ በልፅጓል ወይም ቆርቁዟል የሚል ሰርተፊኬት የምንጠብቀውኮ ኑሯችን ሁሉ ለራሳችን ሳይሆን ለሰው ስለሆነ ነው። እኛ ለራሳችን የሚመቸንን ሳይሆን ሰዎች የሚመቻቸውን እኛን ነው የምንኖረው።»
«ፍልስፍናህን ተወው እና ማወቅ ያለብኝን ንገረኝ! ምንህ ነኝ? ምንስ ሆነን ነው እንድንኖር የምትፈልገው?»
«ምርጫውን ላንቺ ሰጥሻለሁ! ምንድነው ሆነሽ መኖር የምትፈልጊው? የራሴን ፍላጎት ደግሞ እነግርሻለሁ። አንድ መኝታ ቤት መተኛትም ምንም አይነት ስሜታዊ መነካካት አልፈልግም። ከዛ በተረፈ አብሮ መውጣት መግባቱ አይጎረብጠኝም። የግድ ካልተዋሰብን አብሬህ መኖር አልፈልግም ካልሽ እሱም ምርጫው ያንቺ ነው።» የሆነ ጋጠወጥ ሰውዬማ የአዲስን ሰውነት ተውሶ ነው እንጂ አዲስ እንዲህ ባለጌ አይደለም።