Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ ሁለት)

«ዝናቡ ፀቡ ከምሽቱ ጋር ይሁን ከእርሱ ጥበቃ ጋር አይገባውም። የጠቆረው ሰማይ እያፏጨ ያለቅሳል። ……… »
«የመብረቁ ብልጭታ ምናምን ምናምን ብለህ አትቀጥልማ?» ከት ብሎ ሳቀ
በድጋሚ ሌላ ቀን ባዮግራፊውን ልንፅፍ ተቀምጠን ነው ከምን እንደምንጀምር ላልቆጠርነው ጊዜ የምንጀምር የምንሰርዘው። ዛሬ ባልተለመደ ሁኔታ ጥሩ ሙድ ላይ ነው።
«why not?» አለው አይደል እየሳቀ የሚያወራበት ድምፁ?
«come on you are better than this! ሰማዩ የአህያ ሆድ ሲመስል፣ ፀሃይዋ ብርቱካንማ ሆና ስትንቀለቀል አይነት ጅማሬ አንተ ብትሆን ይስብሃል? ተረኩን እያስኬድከው ባለታሪኩ ያለበትን ቦታና ሁኔታ ከታሪኩ ስሜት ጋር ተያያዥነት ካለው ሳለው። ካለዚያ ግን ምንድነው ዝናቡ፣ መብረቁ ? ዝናብ ከሆነ ሰማዩ እንደሚጠቁርና መብረቅ እንደሚኖር አንባቢው የሚያውቀውን እውነት እየደጋገሙ ማደናቆር ነው።»
«አንቺ የራስሽን ባዮግራፊ ብትፅፊ ከምን ትጀምሪያለሽ?»
«ህምምም ካንተ በፊት ለመፃፍ የሚበቃ ታሪክ የለኝም! (አይኑን አሸንቁሮ አየኝ) ምናልባት በየመሃሉ አስተዳደጌን እጠቅስ ይሆናል እንጂ …… ስለዚህ በእርግጠንኝነት የምጀምረው ከሆስፒታል በዊልቸር ይዤህ ስገባ ነው።»
በመገረም እያየኝ «ምን ያህል እንደተለወጥሽ ግን ይታወቅሽ ይሆን? ከሰባት ዓመት በፊት ሬስቶራንት ያገኘኋት ለሰው መኖር የደከማት ምስኪን ሴት፣ ምን እንደምትፈልግ ግራ የገባት ሴት ድምጥማጧ ነው የጠፋውኮ!»
«thanks to you! ሰው ካንተ ጋር ኖሮ ካልተቀየረኮ ፍጥረቱ መመርመር አለበት!”
“Is that a good thing or bad?”
“Honestly both. የሚገርመኝ ሰው እንዴት ሁለቱንም perfect ይሆናል? እጅግ በጣም ደግ ደግሞ እጅግ በጣም ጨካኝ! እጅግ በጣም ሚዛናዊ ከዛ ደግሞ በውስን ነገሮች ላይ ሚዛነ ቢስ! ሁለት ተቃራኒ ፅንፍ ድንቅፍ ሳይልህ ትመታለህኮ!! ከሁለት አንዱ ተፅዕኖ ስር አለመውደቅ ከባድ ነው::”
” ተፅዕኖ አንድ ነገር ነው:: ለውጥ ግን ምርጫ ነው:: በየቀን ተቀን ውሎሽ ውስጥ ጫና በሚያሳድርብሽ ብዙ አይነት ግለሰብ እና መረጃ ተከበሽ ነው የምትውዪው … ለየትኛው እንደምትሳቢ የምትመርጪው አንቺ ነሽ!! ለምሳሌ በፈጣሪ ላይ ባለሽ እምነት የእኔ አለማመን ያመጣብሽ ለውጥ የለም:: እምነትሽን መለወጥ ምርጫ ውስጥ የሚገባ መሰረትሽ ስላልነበረ:: … .. አየሽ ለውጥሽ በምርጫሽ ነበር:: ይህችን ምድር ከተቀላቀልን ጀምሮ በህይወታችን በሚያልፉ ሰዎች እና በምናገኛቸው መረጃዎች እና በሚያጋጥሙን ክስተቶች ተፅዕኖ ስር ነን። ምን ያህሉ ናቸው ለለውጥ የተጠቀምንባቸው? ያገኘናቸው መረጃዎች በሙሉ እውቀት ቢሆኑን፣ ያወቅናቸው እውቀቶች በሙሉ ደግሞ ቢለውጡን አስበሽዋል? እንዲለውጡን የፈቀድንላቸው ብቻ ናቸው የሚለውጡን።»
« 100% ለውጥ በእጃችን ነው ማለት የማያስችሉን አጋጣሚዎች የሉም?። ለምሳሌ በህይወታችን የሚገጥሙን አንዳንድ መጥፎ ክስተቶች ባላሰብነው አቅጣጫ ይቀይሩናል። ፈሪ ወይም ደፋር፣ ደካማ ወይም ጠንካራ ያደርግሃል።»
«አየሽ እራስሽ አመጣሽው! ተመሳሳይ የህይወት መሰናክል አንዱን ሰው ትሁት ሲያደርገው ሌላውን ክፉ ያደርገዋል። ተመሳሳይ ገጠመኝ አንዱን ሰው ሲያስተምረው አንዱን ሰው ይገድለዋል። ሰካራም አባት ኖሯቸው አንዱ ልጅ እንደአባቱ ሰካራም ሌላኛው በተቃራኒው መጠጥ የማይደርስበት ዋለ። ሰካራሙ <ከአባቴ ምን ልማር? የማውቀው ስካሩን ነው። የተማርኩት ያንን ነው> ሲል ያኛው <ከአባቴ የተማርኩት ሰካራምነት ምን አይነት ከንቱ አባት እና ባል እንደሚያደርግ ስለሆነ ከመጠጥ በብዙ ራቅኩኝ> እንዳለው ነው። ምርጫ አይደለም?»
ፈዝዤ እያየሁት በጭንቅላቴ ንቅናቄ ልክ ነህ ካልኩት በኋላ እኔ የራሴን ምርጫ እያሰላሰልኩ ነበር። ለምን በእርሱ ክፋት መንገድ መጓዝ መረጥኩ? እርሱን ከነጭካኔው ትቼው ያልተበረዘ ልቤን ይዤ መውጣት አልችልም ነበር?
«እንሞክር ደግሞ?» አለኝ ጥዬው በሃሳብ መንጎዴን ሲያስተውል።
«እሺ ግን ያልገባኝ ያንተ ታሪክ ሆኖ ለምንድነው በአንደኛ መደብ መፃፍ ያልፈለግከው? <እርሱ> እያልክ ስትፅፈው እሩቅ ነው! ውስጥህ ያለ ሰው አይመስልም!»
«አንቺ እንድትፅፊው የምፈልገው ክፍል ስላለ!» ልፅፍ እየነካካሁ የነበረውን ኮንፒውተር አቁሜ አየሁት። ቀጠል አድርጎ «ስንደርስበት እነግርሻለሁ።»
«እንደዛም ቢሆን በተለያየ ምእራፍ ያንተን ባንተ አፍ እኔ እንድሞላው ያሰብከውን ታሪክ ደግሞ በእኔ አፍ መፃፍኮ ይቻላል። ምቾት እንደሰጠህ እሺ!» ብዬ ለመፃፍ አጎነበስኩ።
«እኩዮቼ የትምህርት ቤት የቤት ስራቸውን ወላጆቻቸው እያገዟቸው በሚሰሩበት ሰዓት እኔ እሷን ፍለጋ ከአንዱ መጠጥ ቤት ወደሌላ መጠጥ ቤት እዳክራለሁ። እኩዮቼ በሞቀ አልጋ ውስጥ በዳበሳና በተረት ሲተኙ እኔ እናቴ የምትጠጣበት መጠጥ ቤት ደጅ ላይ ተቀምጬ ዝናቡ ያረጠበው ልብሴ እላዬ ላይ ተጣብቆ እጠብቃታለሁ። ትልቅ መሆንን የምመኘው እንዲህ ባሉ አመሻሾች ላይ ነው። ሁሌም መጠጥ ቤቱ እና ሰዎቹ ይለያያሉ እንጂ ሂደቱ ተመሳሳይ ነው። አቅሏን አጥታ ሰክራ መረበሽ ስትጀምር እየጎተቱ ያስወጧታል። እንደዘመናይ እመቤት አጊጣ ከቤትዋ ስትወጣ ላያት የምሽቷ መጨረሻ ከመጠጥ ቤቱ ተጎትቶ መባረር አይመስልም። <የፈረደበት ልጅ! ና በል ውሰዳት! ምስኪን! ምፅ!> ይሉኛል ሲያዩኝ። ይሄኔ በጣም ትልቅ ብሆን ከመጠጥ ቤቱ አፋፍሼ ራሴ ይዣት ብወጣ ነውኮ ምኞቴ ………… ማንም ባይጎትትብኝ!! ማንም ባያዋርድብኝ! እንደ እኩዮቼ እናቶች <የእገሌ እናት> ብለው ቢጠሩልኝ፣ ደግሞ መጣች ባይሉብኝ። ያ ነበር ምኞቴ ……….
ማታ ስተኛ ተንበርክኬ <ትልቅ ሰው አድርገኝ> ብዬ የህፃን ፀሎት እፀልያለሁ። ትልቅ ብሆን መጠጡን እቤቷ እገዛላታለሁ። ትልቅ ብሆን መጠጥ ቤት መጠጣት ስትፈልግ እስክትጠጣ ጠብቄ ማንም ጫፏን ሳይነካት በፊት ይዣት እገባለሁ። በትንሽዬ ሀሳቤ ከምንም እንደማልጠብቃት አውቃለሁኮ ግን እቤት ተኝቼ ብጠብቃት የምትመጣ አይመስለኝም። አንድ ምሽት እንቅልፍ ጥሎኝ ባልመጣላት መንገድ ላይ ወድቃ የምትቀር ይመስለኛል። ለራሴ ይሁን ለራሷ የምጠብቃት አላውቀውም!! አባቴ እሱ በብዙ እድሜው፣ በትልቅ አካሉ፣ በተከማቸ ልምዱ እና በዳበረ እውቀቱ ሊጠብቃት ያልቻለውን ሚስቱን <እናትህን አደራ> ብሎኝ ሌላ ሚስት አግብቶ መኖር ከጀመረ ሶስት ዓመት አለፈው።
የተለመደ ቀኗ እንዲህ ነው። ጠዋት ስትነሳ ከእንባዋ ጋር ትምህርት ቤት ትሸኘኛለች። <ልጄን ልጠብቅህ ሲገባ ጠበቅከኝ! ይሄ የተረገመ አባትህ ትቶን ባይሄድ !> እያለች ትንሰቀሰቃለች። ከትምህርት ቤት ስመለስ ጭሰቶቿን አንዱን ከአንዱ አምታታ ስባ ራሷን አታውቅም። የምበላው አይኖርም። አንዳንዴ እንግዳ ይኖራታል። እንዲህ ባለ ቀን መኝታ ቤቴ ውስጥ ትዘጋብኝና ትረሳኛለች። የሚርበው ልጅ እንዳላት ትረሳኛለች። በሩን እየቀጠቀጥኩ ካስቸገርኳት ከቤት አስወጥታ ውጪ ትጥለኛለች። የመጠጥ ሰዓቷ እስኪደርስ እጠብቃትና እከተላታለሁ። የባሰባት ቀን «ሂድ አባትህጋ! ምን አድርጊ ነው የምትለኝ? ለምን በፀፀት ታበስለኛለህ? የአባትህ አይበቃኝም? ሂድ ጥሎ መሄድ ከዘርህ ነው ሂድ አንተም!» ትለኛለች።
አባቴ ምን እንደበደላት አላውቅም! በምን ምክንያት እንደተለያዩ እንኳን በዛን የልጅነት ጭንቅላቴ ማገናዘብ አልችልም ነበር። የአባቴን በደል እኔ እየከፈልኩ እንደሆነ ነበር የሚሰማኝ። የሱ ልጅ ስለሆንኩ ብቻ ለሱ በደል መቀጣጫ እንዳደረገችኝ። በልጅነት ትንሽዬ ልቤ የሱን በደል ልክሳት ታገልኩላት። እንደሱ ጥያት አልሄድም ብዬ ልጅነቴን ጣልኩ። የእሷን በደል ትቼ የአባቴ ዘር እንዳልሆንኩ ፣ ትቶ መሄድ በደሜ እንደሌለ ላሳያት በጥንጥዬ አቅሜ ባዘንኩላት። አልቆጠረችልኝም።
የሆነኛው ቀን በቃኝ! ደከመኝ! እናቱን የሚጠብቅ ልጅ ሳይሆን እናቱ የምትጠብቀው ልጅ መሆን አማረኝ!! ልጅ መሆን አማረኝ። እንደልጅ መባባል፣ እንደእኩዮቼ ትምህርት እንዴት ነበር መባል፣ እንደእኩዮቼ ምሳ ምን ይታሰርልህ መባል ……. እኩዮቼን መሆን አማረኝ!! ጠዋት እንደተለመደው አገላብጣ እየሳመችኝ ከእንባዋ ጋር ፀፀቷን ስታጥብ ቆይታ
«ልጄ እወድሀለሁኮ! ጠልቼህኮ አይደለም! ወድጄ አይደለም!» እያለች አገላብጣ ስማ ላከችኝ። የማላስታውሰውን ያህል ሰዓት ተጉዤ አባቴ ቤት ሄድኩ።
ከሶስት ቀን በኋላ ግን ከጭንቅላቴ አውጥቼ ልረሳት አቃተኝ። ጥፋት ያጠፋሁ መሰለኝ። የአባቴ ዘር መሆኔን ያረጋገጥኩላት መሰለኝ። እንቅልፍ አልተኛ ምግብ አልበላ አለኝ። የሆነኛው መጠጥ ቤት ደጅ ጎትተው ሲጥሏት፣ እቤት መድረስ አቅተት መንገድ ላይ ስትወድቅ፣ ስትንገዳገድ አንድ መኪና ሲድጣት፣ ደሞ እኔ ልጠብቃት እንዳልመጣሁ ስታውቅ አባቴ ጥሏት ሲሄድ እየተንከባለለች እንዳለቀሰችው ስታለቅስ………. የማስበው ሁሉ የከፋ የከፋውን ሆነ። በነገታው ለአባቴም ለእንጀራ እናቴም ሳልናገር ተመልሼ ወደ ቤት መጣሁ። በሩን ባንኳኳ አልመልስ ስትልኝ በጓዳ መስኮት ዘልዬ ገባሁ። ሳሎን ተዘርራለች። እናቴ ተስፋ እንደቆረጥኩባት ስታውቅ በራሷ ተስፋ ቆርጣ ሄዳለች። አምላክን ለመንኩት! <አንዴ መልስልኝና እስከሁሌው እጠብቃታለሁ! አንዴ ብቻ መልስልኝ!> አልኩት አልሰማኝም! » ጣቶቼ ኪቦርዱ ላይ እየተንቀለቀሉ እንባዬ ታፋዬ ላይ ይንዥቀዥቃል። ዝም አለ። ዝም አልኩ። ለደቂቃዎች ምንም አላወራንም……… የምፈልገውኮ አቅፌው እሪሪሪ ብዬ ማልቀስ ነው። ግን ከተቀመጥኩበት አልነሳም።

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ ሶስት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *