«ስድስት ዓመት ሙሉ ምን ዓይነት ቀኖች እንደነበሩህ ለአንባቢ ምንም ፍንጭ ሳትሰጥ 20 ዓመትህ ላይ ወደ ሆነ ታሪክ መሄድ ታሪኩን አያጎድለውም?»
«ምንም የሚፃፍ ታሪክ የለውም። ፊልም ቢሆን (በጭንቅላቱ ምስሉን እየከሰተ) ምን ዓይነት ትራንዚሽን መሰለሽ? ማታ 14 ዓመቱ ላይ ተኝቶ ጠዋት 20 ዓመቱ ላይ ሲነቃ የሚያሳይ ሲን ነው የሚሆነው።»
ላይብረሪው ውስጥ ዊልቸሩ ላይ ለሰአታት ከሚቀመጥ በሚል ባስገባነው ሶፋ ላይ እሱ ጋደም ብሎ። እኔ መሬቱ ላይ ተቀምጬ ሶፋውን ተደግፌ ባዮግራፊውን መፃፋችንን እየቀጠልን ነበር። ከምንፅፈው በየመሃሉ የምናወራው ይበልጣል።
«አባትህ? እንጀራ እናትህ? ወንድምህ? ከነርሱጋር የነበረህ ግንኙነት? ትምህርት ቤት? ጓደኛ ? የሆነ የሚወራ የሚወሳ ይኖረዋል። ለህፃን አይደለም ለአዋቂ የሚከብድ ሰቀቀን ያሳለፈ ህፃን እንደማንኛውም ልጅ የተለመደ ዓይነት ዓመታት ሊኖሩት አይችልም መቼም።»
«እነዛ ዓመታት የ trauma ው አካል እንደነበሩ ትልቅ ሰው ከሆንኩ በኋላ ነው ያወቅኩት። ምንም ስሜት ነበር የማይሰማኝ። በቃ ምንም! አድርግ የምባለውን ከማድረግ ውጪ ፀጥ ያለ ህይወት ነበር። አይከፋኝም! አልናደድም! አላለቅስም! ማውራት ብችልም ከማናቸውምጋ አላወራም ነበር። 2 ዓመት ያቋረጥኩትን ትምህርት ቀጥዬ ነበር ብዙም አይገባኝም እንጂ። ቤተሰቦቼን በነዛ ዓመታት አውቃቸው ነበር ማለት ይቸግረኛል። ለእንጀራ እናቴ በእናቱ ሞት ምክንያት በሽተኛ የሆነ፣ አንድ ክፍል ሶስቴ የሚወድቅ ፣አስተውላ ባየችኝ ቁጥር ከንፈሯን የምትመጥልኝ የሆነ ደደብ ልጅ ነኝ። አባቴ ብዙውን ጊዜ ሊያዋራኝ ሞክሮ ፍላጎት እንደሌለኝ በመረዳቱ ከመተው በተጨማሪ በስራ ምክንያት ከቤት ውጪ የሚያሳልፈው ጊዜ ነው የሚበልጠው። ጓደኛ ቅብጠት ነው። በምማርባቸው ክፍሎች ሁሉ በእድሜም በሰውነትም ትልቅ ልጅ፣ በዛ ላይ እንደበሽተኛ የሚቆጠር ማን ጓደኛ ሊያደርገው ፍላጎት ይኖረዋል? ወንድሜ በሁለት ዓመት ቢበልጠኝም በጊዜው ልጅ ነበር።»
«አልገባኝም አባትህ ከእናትህ በኃላ መስሎኝ………»
«ህም የተጋቡት ከእናቴ ከተለየ በኋላ ነው። እንጀራ እናቴ ከእናቴ በፊት ፍቅረኛው ነበረች። የእነሱ ታሪክ ብቻውን ሌላ መፅሃፍ ይወጣዋል። ወንድሜን ወልዳለትም እናቴን ያፈቅራት ስለነበር ለማግባት እናቴን መረጠ። በኋላ ትቷት ቢሄድም።»
«ለአንባቢ ሙሉ ስሜት እንዲሰጥ መካተት አለበት እንደእኔ።» አልኩኝ። ትከሻውን ሰብቆ ዝም አለ። የነገረኝን አሳምሬ ለመፃፍ ሞከርኩ እና ጮክ ብዬ አነበብኩለት። ማስረዳት በማልችለው ምክንያት ያለፈበትን እኔ እንዳውቀው እንጂ መጽሃፍ ሆኖ ስለመታተሙ ብዙም ግድ የሰጠው አልመስልሽ አለኝ። ምንም ከማለት ተቆጥቤ የሚቀጥለውን እሱ እየነገረኝ መፃፍ ጀመርኩ።
«መጀመሪያ እቤት የመጣች ቀን ነው ከማውቃቸው ሰዎች ለስሜቴ የቀረበች እንደሆነች የገባኝ። ቀጥታ መኝታ ቤቴ ገብታ የለበስኩትን ብርድ ልብስ ከላዬ እየገፈፈች።
<ያንተ አቻ ፈረንጅ ስንት ቴክኖሎጂ ለሀገሩ አበርክቷል አጅሬው በ20 ዓመትህ ዘጠነኛ ክፍል እየተማርክም እስከ ጠዋቱ 4 ሰዓት እንቅልፍህን ታገነፋለህ?> አለችኝ።
ማንም ሰው እድሜዬንና የትምህርት ቤት ደረጃዬን ከንፈሩን ሊመጥልኝ እንጂ እንደሷ ያውም ለራሴው ተናግሮ ሰምቼ አላውቅም። አባቴ ዘጠነኛ ክፍል ስገባ በግል እንድታስጠናኝ ብሎ የቀጠረልኝ በእድሜ እኩያዬ የሆነች የዩንቨርስቲ ተማሪ ናት። የዛን ቀን ብርድልብሱን ከላዬ ስትገፍ የዓመታት ሰቀቀኔንም ነበር አብራ የገፈፈችው።
<ማዕረግ እባላለሁ። አስጠኚህ ነኝ I think አባትህ ነግሮሃል። ጊዜዬን አትብላብኝ ሳሎን እየጠበቅኩህ ነው።> ብላ ትታኝ ሄደች።’”
እያወራልኝ የፊቱ ፀዳል ያቺ ሴት ማን እንደነበረች ሳይነግረኝ በፊት አወቅኩ። ዞር ብሎ ሳያየኝ ወቅቱን ከነስሜቱ ወደአሁን ጎትቶ ማውራቱን ቀጠለ።
«ለሳምንታት እሰማታለሁ እንጂ ብዙም አላወራም። በሷ ጣፋጭ ቃላት እና ለዛ ስታወራው ትምህርትም ህይወትም ቀላል ነው። የፊደል እና የቁጥር ሰልፍ ከመሆናቸው ውጪ እምብዛም የማይገቡኝ ፅሁፎች እሷ ስትፈተፍታቸው ትርጉም ነበራቸው። አንድ ቀን ሳሎን እያስጠናችኝ እንደምትፈልገው አልመልስ ስላት <አንተ ግን በዚህ ዓይነት እንዴት ነው ከሰው ጋር ተግባብተህ የኖርከው በአባቢ ሞት? ከአፍህ በሚወጡት ፊደላት ልክ አትከፍልም እኮ ወይም እዳ አይሆኑብህም! ምንድነው? My God! > ብላ ስትጮህ እየሰማች መሆኑን ያላወቅኳት የእንጀራ እናቴ በጣም ሳቀች። አስከትላም። < እንደውም አንቺ ከመጣሽ ጀምሮ እየተሻሻለ ነው። እናቱ ከሞተች በኋላ ጭራሽ ………> ብላ የሆነውን ትነግራት ጀመር። ማዕረግ ያለፈ ህይወቴን መስማቷ መጥፎ ስሜት እንዲሰማኝ አደረገኝ። ተነስቼ ወደ መኝታ ቤት ገባሁ። ከደቂቃዎች በኋላ ወደክፍሌ ስትመጣ ብዙ ለሊት ተኝቼ አልጋ ላይ ሽንቴን መሽናቴን ጨምሮ ምንም ያላወቀችው ገበናዬ እንደሌለ እርግጠኛ ነበርኩ። የተለመደ ነው። ስለእኔ ለጠየቀ ሰው በሙሉ ይነገረዋል። እናቴ መቃብር ላይ ካለቀስኩኝ ቀን በኋላ ግን ምንም ስሜት ሰጥቶኝ አያውቅም ነበር። ሰሚዋ ማዕረግ እስከሆነችበት ቀን ድረስ
<you are brave> አለችኝ መጥታ አልጋዬ ላይ እየተቀመጠች። <ምፅ! ምስኪን> የሚል ሀዘኔታ ነበር የለመድኩት እና ጆሮዬ ደነገጠ።
<ታውቃለህ ? ያልገባህ ነገር ያንተ ጥፋት አልነበረም! ማድረግ የምትችለው ነገር አልነበረም። ራሷን አይደለም ያጠፋችው ያን ታውቃለህ አይደል? አንተ ጥለሃት ስለሄድክ አይደለም የሞተችው! ድራጉን ኦቨርዶዝ ወስዳ ነው።> ልዩነቱን ማወቅ አለማወቄን ለማረጋገጥ አይኔን እያየች <ታውቃለህ እሱንኣ?> ዝም አልኳት <God damit መልስልኝ!> ብላ ስትጮህ ጥያቄዋ ሁሉ ጠፋብኝ እና ዘልዬ ቁጭ አልኩ። የእኔ መደንገጥ አላስደነገጣትም። ጭራሽ ተመቻችታ እየተቀመጠች። ትጮህብኝ ጀመረ።
<ስማኝ? ምናልባት አንተ እዛ ያለመኖርህም ትዝ አላላት ይሆናል። ከለመደችው መጠን ሞቅ ያለ እብደት ፈልጋ ጨምራ የወሰደችው ድራግ ነው የገደላት። አጠገቧ ሆነህም ቢሆን አታድናትም ነበር። ለሷ ሞት ያበረከትከው ምናምኒት አስተዋፅኦ የለም።>
<አጠገቧ ብኖር ተጨማሪ ላትወስድ ትችላለች፣ አጠገቧ ብኖር ስትወድቅ ሀኪም ቤት እወስዳት ነበር፣ አጠገቧ ብኖር ሞታ እንኳን ሳትሸት ትቀበር ነበር። ……….. > መቃብሯ ላይ ካለቀስኩ በኋላ ያላለቀስኩት እንባዬ በዓረፍተ ነገር ታጅቦ እናጠው ጀመር። ጭንቅላቴ ውስጥ ያለውን <ባልተዋት ኖሮ > በሙሉ ነገርኳት። አቅፋ እያባበለችኝ ግን ደግሞ ትቆጣኛለች።
<ቢሆን ኖሮ እያልክ በመላ ምት ስትጃጃል መኖር ነው የምትፈልገው? እኩዮችህ እንደ ዝግምተኛ ሲያዩህ መኖር ነው የምትፈልገው? እስከመቼ ነው ራስህን ስትቀጣ ለመኖር ያሰብከው? ምንም ጥቅም የሌለው ልጅ ሆነህ እዚሁ አልጋ ላይ ማርጀት ነው የምትፈልገው? ያን መከራ በ12 ዓመቱ ተቋቁሞ ያለፈ ልጅ በ20 ዓመቱ እንዲህ ጂል ይሆናል?>
እብድም ግልብም ናት ስታወራ። ከዛ በኋላ ብዙ ነገር ስሜት ይሰጠኝ ጀመር። ቢነኩት ይፈርጥ ይመስል የተድቦለቦለ ሰውነቴ አስጠላኝ። እስፖርት መስራት ጀመርኩ። ትምህርት ቤት ልጆቼ ከሚመስሉ ተማሪዎች ጋር መማሬ ያሳፍረኝ ጀመር። ወንድሜ ዩንቨርስቲ ተማሪ ቢሆንም ሴት በማሳደድ እና ጭፈራ ቤት ለጭፈራ ቤት እንደሚያድር ማወቅ ያሳዝነኝ ጀመር። አባቴ በእኔ ዝምታ ውስጥ ፀፀት እንደሚያንገበግበው አስተውልለት ጀመር። የእንጀራ እናቴ ድንገት እንደባነነ ሰው የመንቃቴ ነገር ደስታ እንዳልሰጣት ማገናዘብ ቻልኩ። የማነባቸው መፅሃፍት እያመጣች ትሰጠኛለች። ለሷ ስል ራሴን ልቀይር በረታሁ። እሷ ማለት ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ዋሻ ውስጥ በርቀት የታየችኝ የብርሃን ፍንጣቂ አይነት ነገር ናት። የድሮው አዲስ የሞተ ይሄኛው አዲስ ማዕረግ ከሞቱ ቀስቅሳው ለማዕረግ የሚኖርላት ነበር። ድጋሚ የመኖር እድሌ ነበረች።
አንደኛ ሴሚስተር ሲያልቅ በትምህርቴም በአካሌም በውስጤም ሌላ ሰው ነበርኩ። ማዕረግ የሞላችበት ሰውነት ያለው ሰው። የአንደኛ ሴሚስተር ውጤቴን አያለሁ ያልኳት ቀን በጠዋት መኝታ ክፍሌ <የታል?> እያለች ገባች። ስታየው ቦረቀችልኝ። ካርዱን ወርውራው ከንፈሬን ለደቂቃ ሳመችኝ። <ወይኔ ጉዴ ለካ ምንም አታውቅም!> ብላ ምንም እንዳልሰራች ነገር <ና እኛ ቤት እንሂድ የማሳይህ ነገር አለ> ብላ እጄን እየጎተተች ወጣች። ታክሲ ተሳፍረን እቤታቸው እስክደርስ ድረስ እኔ የማስበው ቅድም የሳመችኝን ነበር። እሷ የተለየ ነገር እንዳላደረገች ሌላ ወሬ ታወራለች። እቤታቸው ማንም የለም። በሩን ቆላልፋ <የምከፍትልህ ፖርን ነው። ተሽኮርምመህ አማትበህ ምናምን እንዳታፀፅተኝ> ብላኝ ትንፉሽ እንኳን ሰብስቤ ሳልዘጋጅ ከፈተችው። አጉል አጉል የሆነ እያሳየችኝ አጓጉል አደረገችኝ።» እኔ ራሴ ሊከሰት የሚችለውን አስቤ መፃፌን መቀጠል አቃተኝና ሳቅኩ። በሳቁ አጀበኝ።
«እብድ ናት!» አለኝ እየሳቀ።
«መድሃኒት የሆነህ እብደቷ አይደል?»
«exactly!!» (ካለ በኋላ መጥፎውን ትዝታ እንደጫረው እስከአሁን የነበረውን የክፍሉን ድባብ የቀየረ የፊቱን ፀዳል አደበዘዘው)
«እንቀጥል ወይስ ማረፍ ትፈልጋለህ?»
«am good እየፃፍሽ ያለሽውኮ አንቺ ነሽ! ማረፍ ከፈለግሽ የተወሰነኮ መፃፉንም ጣቴን ሳላደክም ላግዝሽ እችላለሁ!»
«እንቢየው! መጻፉንማ ራሴ ነኝ የምፅፈው!»
«<አፈቅርሃለሁ እኮ አንተ ዱዝ!> አለችኝ አጓጉል ባደረገችኝ ማግስት
<አውቃለሁ!> ብዬ መለስኩላት
<ወይኔ ጉዴ! ስንቱን ነው አስተምሬህ የምዘልቀው? ሴት ነኝ! ሴት ልጅ መፈቀሯን በጆሮዋ መስማት ትፈልጋለች።>
<ምርጫኮ አልሰጠሽኝም ነበር። አንቺን አለማፍቀር አልችልም ነበር።>
<ጎበዝ ሆነህ አኩራኝ> አለችኝ ያን ቀልብ የሚነሳ መሳሟን እየሳመችኝ። እብደቷን አበድኩት። ፍቅሯን ለነፍሴ ደርቤ ሞቀኝ። በሷ ውስጥ ነፍስ ዘርቼ ደስታን ቃረምኩ። አልፈልግም ብላ አውጥታ ብትጥለው ይጎዳብኛል ሳልል ስጋዬንም ነፍሴንም ልቤንም ያልሰጠኋት አልነበረም። እሷው እንደአዲስ ያበጃጀችው እኔነቴ ነበር እና ልሰስትባት አልችልም ነበር።
ዘጠነኛን ክፍል እንደጨረስኩ እሷ እናቷ ስለታመመችባት ትምህርቷን ልታቋርጥ ሆነ። አባቴን እሱጋ ስራ እንዲያስገባኝ ለምኜው እኔ ትምህርቴን ተውኩት እና እሷን ማስተማር ጀመርኩ። ለእርሷ መኖር የህይወት ግቤ ስለነበር እሷ የምታገኘው እንጂ እኔ የማጣውን የምቆጥርበት ልብ አልነበረኝም። አባቴ ትምህርቴን መተዌ ባያስደስተውም እንደጤነኛ ልጅ ዳግም ሰው መሆኔ ስላስደሰተው አልተጫነኝም። አኖረችኝ። ኖርኩላት። በአመቱ እናቷም ወደጤንነታቸው ተመለሱ። አባቴ በወቅቱ መጠነኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ ነበረው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ስራዎቹን ለምጄ ማሻሻያ ሀሳቦች ማቅረብ ስጀምር አባቴ በደስታ ሲቅበጠበጥ እንጀራ እናቴ በግልፅ በእኔ ስራ ብቃት እምነት እንደሌላት ያለፉትን ዓመታት እና ያለመማሬን እያጣቀሰች መናገር ጀመረች። ማዕረግ ያጎበዘችው ልቤ ለሷ ኩራት ለመሆን የማይረግጠው ቦታ የለም።
<አንተ ዱዝ አፈቅርሃለሁኮ! አንተ ባትኖርልኝ ምን ይውጠኝ ነበር? > እያለችኝ ተመረቀችልኝ። በዛው ዓመት እንደማዕረግ በማዕረግ ባይመረቅም ወንድሜም ተመርቆ ነበር። የሱ ምርቃት ድግስ ቀን የኔ ማዕረግ ውብ ሆና መጥታ ነበር። እንደሁሌውም በህይወት ውስጥ ከሷ ውጪ ዓይኔን የሚስበው ነገር እንዳለመኖሩ አጠገቤ አስቀምጬ አይን አይኖቿን ሳይ መሸ። ለአፍታ ዘወር ብዬ ስመጣ ሳሎን የለችም። ምናልባት ወደ መታጠቢያ ቤት ሄዳ ይሆናል ብዬ ልፈልጋት ስሄድ ሳቋን ሰማሁት። ከወንድሜ መኝታ ቤት ነው። ምን አስቤ ይሁን ሳላስብ አላውቅም እግሬ ወደዛ ተራመደ። ጆሮዬ የገባው
«አንተ እረፍ ልመለስ! ያወቀ እንደሆነ ደግሞ ዲዳ ሆኖ ሀሁ ሳስቆጥረው ልክረም?» የሚለውን ሳቃቸው ያጀበውን ድምፅዋን ነው። ሳቃቸውን ሳይጨርሱ ብቅ ሲሉ መንቀሳቀስ አቅቶኝ እንደቆምኩ ነበር።
አልጨረስንምኮ ይሄን ነገር የሱን ክፍል ሲዝን ሁለት ብለን ሌላ ጊዜ እንቀጥለው እንዴ?