Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ስምንት)

ጥፋቴ ማፍቀሬ ነበር አላልኳችሁም? የትኛው ዓመት ፣ መቼ ላይ እንዳፈቀርኩት እንኳንኮ አላውቅም! ቀስ በቀስ ……. መሰረቱን ሲጥል ….. ግድግዳውን ሲገነባ ….. ጣራውን ሲከድን …… ቀለም ሲቀባባባ ፣ ወለሉን ሲያሳምር …… ገዝፎ ገዝፎ ተሰርቶ አልቆ …… በአራተኛው ዓመት በራሴ ላይ ማዘዝ የማልችል ሆኜ ሽምድምድ ካልኩ በኋላ ነው ከእንቅልፉ እንደባነነ ሰው የማደርገው ጠፍቶኝ ጥፋት እንዳጠፋ ህፃን ባየሁት ቁጥር ልቤ ከአቃፊዋ ካላመለጥኩ ትል የጀመረችው። ሰርቆ መች ከመቼ ተነቃብኝ እንደሚል ሌባ ..

መሰረቱን ሲጥል
በተጋባን በሆኑ ወራቶች ውስጥ የሆነ ቅዳሜ ከሰዓት ሁሌም ላይብረሪ ሲቀመጥ እንደሚያደርገው ስልኩን አጠፋፍቶ እያነበበ ነበር። ሁሌም ማንበብ ሲጀምር በስርዓቱ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ መፅሃፉን ጠረዼዛው ላይ አስቀምጦ ነው።
ከሆነ ሰዓት በኋላ ተነስቶ እየተንጎራደደ ማንበብ ይጀምራል። ይቆይና ደግሞ ምንጣፉ ላይ ቁጭ ብሎ መደርደሪያውን ተደግፎ ያነባል። ቀጥሎ በደረቱ ምንጣፉ ላይ ይተኛል። ወይም በጀርባው። ሁሌም ቅደም ተከተሉ ይለያያል እንጂ እንዲህ ይመሳቀላል። የዛን ቀን ራሴን አሞኛል ብዬው ምንጣፉ ላይ ተቀምጦ እግሮቹ ላይ አስተኝቶኝ እያነበበ ፀሃይ ስትጣደፍ ገባች
«የሆነ ሰውዬ እየፈለገህ ነው! » አለች።
ተከታትለን ወደሳሎን ገባን። ቤታችን እኔን ብሎ የሚንጋጋው የእኔ ዘመድ እንጂ ማንም ሰው እሱን ፈልጎት መጥቶ አያውቅም። ከሰውየው ጋር እንደተያዩ እንደሚግባቡ ያስታውቃሉ።
«ህሊና በጣም ታማለች። ስልክህን ደጋግሜ ብደውል አታነሳም። ይቅርታ የነፍስ ጉዳይ ባይሆንብኝ እቤትህ ድረስ መጥቼ አልደፍርህም!» አለው ሰውየው።

አዲስ ምንም ቃል አልተነፈሰም። ዞር ብሎም አላየኝም። ሊያስረዳኝም አልሞከረም። ከነቱታው በሲሊፐር ዋሌቱንና ጃኬት ብቻ አንስቶ ወጣ! ህሊና ማናት? ስልኩን እንኳን አልያዘም! እንዲህ አለት ልቡን የነቀነቀችው ማናት? እህቱ? ሚስቱ? እናቱ? ልጁ? አላውቅማ!! ስለእርሱ ከግምት ውጪ የማውቀው የለማ!! ብቻ ማንም ትሁን ቀናሁባት! የዛን ቀን ማታ ምንም ቢፈጠር ከቤቱ ውጪ የማያድረው ሰው እቤት አልመጣም አደረ። ምኑ ልትሆን እንደምትችል እያንዳንዱን ምርጫ እያሰላሁ መኝታ ቤቱን በእርምጃዬ ስመትር ነጋ!! ጠዋት የዛለ ሰውነቱን እየጎተተ መጣ!
«ማናት?»
«ህፃን ልጅ ናት! ታማ ነው።»
«እኮ ማን ናት? ምንህ ናት? ከቀድሞ ትዳርህ ልጅ አለህ?»
«ያልነገርኩሽ እንጂ የዋሸሁሽ ነገር የለም! ልጅ ኖሮኝ ለምን ዋሽሻለሁ?»
«አላውቅም አዲስ! አላውቅህምኮ! ምንም ስላንተ የማውቀው ነገርኮ የለም።»
«እኔ ያለፈ ታሪኬ ውስጥ የለሁም! እኔ ይሄ ዛሬ የምታዪው አዲስ ነኝ። ድሮዬ ውስጥ አትፈልጊኝ። ማወቅ ኖሮብሽ ያልነገርኩሽ ምንም የለም! የምዋሽበት ምንም ምክንያት የለም! ራስሽን አታድክሚ! ብሎኝ ልብሱን አወላልቆ አልጋ ውስጥ ገባ! «ይልቅ ነይ ተኚ! በኃላ አስረዳሻለሁ»

ከእንቅልፉ ሲነሳ ህሊና የተኛችበት ሆስፒታል ወሰደኝ። የ12 ዓመት ህፃን ናት። ማታ እቤት የመጣው ሰውዬ አጠገቧ ነበረ። ከህፃኗ ጋር ሲጫወት ሳየው የሆነ የማላውቀው ሰው ነው። ግራ መጋባቴ ገብቶት ይሆን ሰውየው አዲስን በፈገግታ እያየ ። «መቼም እሱ ባይኖር እነዚህ ህፃናት ምን ይውጣቸው እንደነበር? ቅድም ስታቃስት ሁሉ ነበር አሁን እሱን ስታይ ዳነች።» አለኝ።
«ልጅ መውለድ አልፈልግም ማለት ልጅ አልወድም ማለት አይደለም። እነዚህ ወላጆቻቸው ያለሃላፊነት ወልደው ለቁር እና ለጠኔ የዳረጓቸው፣ ያለጥፋታቸው የተቀጡ ህፃናት ናቸው።» አለኝ እየወጣን። የመገረም አስተያየቴ ምን ማለት እንደሆነ ገብቶት።
«ለምን አልነገርከኝም?»
«ምን ብዬ? ደግሞስ ምን ይጠቅምሽ ነበር? ወላጅ የሌላቸውን ልጆች የሚረዳ መልካም ሰው ነው የሚለውን ካባ እንድትደርቢልኝ? ነውር አይደል? ምርጫ ባጡ ህፃናት ሆድ ውዳሴ መሰብሰብ ነውር አይደል?»
ዝም አልኩ!! በምቾት የተቀመጠበት ልቤ ውስጥ መሰረቱን አስፍቶ ቁልል አለ። ደሞ የሆነኛው ቀን ከስራ ደወለልኝና
«ፀዲ ታማ ብር ፈልጋ ጠይቃኝ ነበር። በዚህ ጉዳይ አውርተን ባናውቅም ሳልነግርሽ መስጠቱ ምቾት ስላልሰጠኝ ልንገርሽ ብዬ ነው። ይደብርሻል?» አለኝ
ፀዲ የመጀመሪያ ሚስቱ ናት። አሁን እሷ አግብታ ወልዳለች። የሆነ ቀን ሞል እቃ እየገዛን ልጇን በእጇ ይዛ ተገናኝተን አስተዋውቆኛል። የዛን ቀን
«ይገርማልኮ መቼም የሰው ልጅ ይቀየራል። አዲስ የሰርግ ግርግር ተመችቶት ደግሶ አገባ? ማመንኮ ነው የሚያቅተው? » እያለች ስታበሽቀው፣ እየሞላበት ያለበት ልቤ ውስጥ ገዘፈ። <ለእኔ ብሎ ነው ያደረገው!> ብዬ ማመን ፈለግኩ።
«አትስጣት ይደብረኛል ብልህ አትሰጣትም?» አልኩት።
«እሰጣታለሁ። አትስጣት የምትዪበት በቂ ምክንያት ካለሽ እናውራበት!» ሁሌም ይኸው ነው ፊት ይሰጠኝና ደግሞ ይኮሳተርብኛል። ያቀብጠኝና ደግሞ ይገፋኛል።
«አይ ዝም ብዬ ነው። ታገኛታለህ?» ድምፄ እሱ ላይ ስልጣን ስለሌለኝ ከመቅዘዝ ውጪ ምርጫ እንዳልነበረኝ አሳበቀብኝ።
«አዎ ሄጄ ነው ብሩን የማቀብላት። ታማለችኮ! (ትዝብት ያለበት አይነት ለዛ) መጥቼ ልውሰድሽ አብረን እንሂድ?» ይኸው ደግሞ ሲያቀብጠኝ። መጥቶ ይዞኝ እየሄደ
«ለምንድነው ያላመንሽኝ? ከፀዲጋኮ ተበቃቅተን ነው በምርጫችን የተለያየነው። ለምን የምመለስ መሰለሽ?»
«እኔ እንጃ! ዛሬም ላይ ግን ሲቸግራት የምትጠራህ ሰው ነህ! ምንም ማሰብ አልነበረብኝም? የእኔና ያንተ ትዳር እኮ በህግ እንጂ በፍቅር የቆመ አይደለም። ህግ ያለፍቅር አቅም ያጣል።»
«አብረሽኝ ደስተኛ አይደለሽም? እኔኮ ደስተኛ ነኝ ሌላ ሴትጋ የምሄድበት ምክንያት የለኝም። ለምን ታወሳስቢዋለሽ? አንቺጋ ጎድሎብኝ ሌላ ሴት የምፈልገው ጉድለት የለኝም።»

ይኼኛው ሁለት አይነት ስሜት ሰጠኝ። ደስተኛ መሆኑ ደስ አለኝ። አታወሳስቢው ያለበት ድምፅ ማስጠንቀቂያ መሰለኝ። እናም ላለማወሳሰብ ዝም አልኩ። በየሆነ ጊዜው የሚያስገርመኝ ባህሪውን አውቃለሁ። ላልወደው አልችልም ነበር። ግን ዝም አልኩ።

«ለምንድነው ይሄን ያህል ኢሞሽናልይ ከሰዎች ጋር መቆራኘትን የምትፈራው? ታዝናለህ ግን እንዳዘንክ ማንም እንዲያውቅብህ አትፈልግም፣ ትራራለህኮ ግን ድክመት ስለሚመስልህ ትሸፍነዋለህ፣ ትወዳለህ ግን መሸነፍ ስለሚመስልህ ትደብቀዋለህ።» አልኩት የሆነ ቀን እሁድ ህፃናቶቹጋ ውለን እየተመለስን።
«ሁሉም በድርብቡ ጥሩ ነው! ኢሞሽን በገዛ እጅሽ ነፃነትሽን በሸምቀቆ መጠፍነግ ነው። ለሀሴትሽ የተደገፍሽው ሰው የነገ ሀዘንሽ ምክንያት እንዲሆን ስልጣን እየሰጠሽው ነው። ማንም ሉጋም እንዲያበጅልኝ አልፈልግም። ተደግፌህ ጥለኸኝ ስትሄድ ወድቄ ተሰበርኩ ብለሽ ማንንም መውቀስ መብት የለሽም። የሰው ልጅ ይቀየራል። ሁሌ ላንቺ ደስታ ምክንያት ለመሆን ሲል ድጋፍሽ ሆኖ ተገትሮ አይቀርም። ይሄዳል። ማወቅ ያለብሽ በህይወትሽ ውስጥ ሰዎች ይመጣሉ። ይሄዳሉ። አብረሻቸው ስትሆኚ ጥሩ ጊዜ አሳልፊ! ሲሄዱ ተንቀሳቀሺ!! ያስተሳሰራችሁ መጠቃቀም ሲሳሳ ኢ,ሞሽን የምትዪው ብን ይላል። »

በተደጋጋሚ በየጨዋታው በኢሞሽን መጠለፍ እንደማይፈልግ እያስረገጠ ይነግረኛል። በቃ ምንም ስሜት የለውም እንዳልል እያንዳንዱ ድርጊቶቹ ለእኔ የሚታዩኝ በፍቅር ተጠቅልለው ነው። ምንም ስሜት የሌለው ሰው ከአራት አመት በኋላ እንኳን የሚስቱን ፀጉር ያጥባል? ምንም ስሜት የሌለው ሰው <ዛሬ የበላሁት ምግብ አልተስማማኝም መሰለኝ። አስመለሰኝኮ> ስለው በደቂቃ ቢሮ ድረስ መጥቶ ደህና መሆኔን ቼክ ያደርጋል? እሺ ምንም ስሜት የሌለው ሰው ከደረጃ ወድቄ እጄ የተሰበረ ቀን የታሸገውን እጄን ደረቱ ላይ አድርጎ ሳይንቀሳቀስ ያድራል? እሺ ምንም ስሜት የሌለው ሰው አራት ዓመት ሙሉ ነፍስ ከስጋዬ የሚያስቃትተኝ ፍቅር ይሰራል? እሺ ምንም ስሜት የሌለው ሰው <አይንሽ ላይ እንባ ሳይ ቀኔ ይበላሻል!> ይላል? እሺ ምንም ስሜት የሌለው ሰው <ጠዋት ሳትስሚኝ ሄጄ ሰራተኞቹ ላይ ተቀየርኩባቸውኮ! ለምን ሳትስሚኝ ሄድሽ?> ይላል።

ከዛ ደግሞ ዓለሜን ድብልቅልቁን ያወጣውና እኔ ከቀኑ ብጎድል ምንም እንደማይጎድልበት ይሆናል። በቃ ምንም እንደሆንኩ። የሆነኛው የህይወቱን ቀኖች አካሂያጅ ብቻ እንደሆንኩ። ምንም እንደማልመስለው። በዚህ ሁሉ ውስጥ የእኔ ነፍስ አንዲት ቀን ብቻ ተሳስቶ «ወድሻለሁኮ» እንዲለኝ ትፀልያለች። በስህተት እንኳን! ከፈለገ አይድገመው። አንዴ ብቻ! እሺ እሱ አይበለኝ እኔኮ «የእኔ ፍቅር » እንድለው እፈልጋለሁ። እሱ አይበለኝ ለምን እኔ የሚነድ ፍቅሬን መግለፅ እከለከላለሁ? ጠዋትኮ ስሜህ ወጥቼ ማታ እስክመለስ እንደቲንኤጀር እቅበጠበጣለሁ> ልለው እፈልጋለሁኮ። መስማት የማይፈልገው ነገር መሆኑን አውቃለሁ። ከአፌ እንዳያመልጠኝ ተጠነቀቅኩ፣ እቅፉ ውስጥ ሆኜ የምትደልቅ ልቤ የምታሳብቅብኝ ይመስል ተሳቀቅኩ!
ከአራት ዓመት በኋላ እንደለመድነው የቀን ውሏችንን እያወራን መኝታችን ላይ እየለፋን የሞላው ስሜቴ ገነፈለ፣ ያባበልኩት ፍቅሬ አመፀ
«እኔ ከዚህ በላይ ማስመሰል አልችልም! ከአቅሜ በላይ ነው የምወድህ!» እያልኩት እናቱ ናፍቃው እንዳገኘ ህፃን መንሰቅሰቅ ጀመርኩ።

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ዘጠኝ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *