Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ሶስት)

ከሳምንታት በኋላ ዝም አለ። በቃ ዝም! በእኔ ቁጥጥር ስር መሆኑን ላለመቀበል መፍጨርጨሩን ተወው። የእኔ እርዳታ የሚሰጠውን የተሸናፊነት ስሜት ላለመዋጥ የሚያደርገውን መንፈራገጥ ተወው። ሳጎርሰው ከምግቡ ጋር የሚውጠውን እልህ ተወው። ሰውነቱን ሳጥበው ከጡንቻው ጋር የሚያፈረጥመውን ትዕቢት አተነፈሰው። መለፍለፉንም ተወው። ዝም ጭጭ አለ። ልክ እንደሌለ ነገር። እንደማይሰማ ፣ እንደማያይ ፣ ምንም ስሜት እንደማይሰጠው ፣ ጭራሽ እዛ እንደሌለ…………. ዝምታው ደስ አይልም ይሸክካል። የተሸነፈ ሲመስል የበቀሌን ጥፍጥና ይቀንሰዋል። ደስ አይልም!
«ወደኋላ ተመልሰሽ ድጋሚ የህይወት ምርጫሽን የማስተካከል እድሉ ቢኖርሽ ታገቢኝ ነበር? ማለቴ ይሄን ትዳር ትመርጪ ነበር?» አለኝ ከብዙ ቀናት ዝምታ በኋላ የገና ቀን ጠዋት መኝታ ቤታችን መስታወቱ ፊት የበዓል ነጭ ልብስ እያለበስኩት ሳለ
«አዎ ሁለቴ ሳላስብ!» አልኩት በልቤ «ያውም መጨረሻው ይሄ መሆኑን አውቄ?» ብዬ ሳልጨርስ የሰማኝ ይመስል
«ላለፉት ዓመታት ስትዪ ወይስ ለመጨረሻዎቹ ወራት?» አለኝ መልሱን እንደሚያውቀው ሁላ ተረጋግቶ
«ለሁለቱም! በእርግጥ መጨረሻው እንደየዋህ ደራሲ ድርሰት መስመሩ ምርጫዬን ያቀልልኛል።» አልኩት! አልከፋውም! እንደውም ፈገግ ነገር አለ። የሆነ የማውቀውን ፈገግታ ፈገግ አለ። የሆነ የድሮው እሱ የሆነ ፈገግታ፣ ያሸነፈኝ ያሸነፈኝ ሲመስለው ፈገግ የሚለው ዓይነት ፈገግታ፣ የሆነ ተንኮል ሲያስብ ፈገግ የሚላት አይነት ፈገግታ………….
«ምን አስበህ ነው?»
«ምንም! ምነው?»
«አውቅሃለሁኮ! የአሁኗን ፈገግታ የምታመጣት ከዲያቢሎስ ጋር የሆነ ነገር ስታንሾካሹክ ነው!»
ከት ብሎ ሳቀ። ከአደጋው በኋላ ለአራት ወራት እንዲህ ስቆ አያውቅም! ዊልቸሩን ወደሳሎን እየገፋሁ እሱ ሳቁን አላቆመም። እንዲህ የሚስቀው ስራ ቦታ የሆነ ፈታኝ እቅድ አቅዶ ሲሳካለት ነው። ወይም በውጤቱ እርግጠኛ የሆነበትን ንድፍ ሲጨርስ
«ምን አስበህ ነው?»
«ራስሽን ግን አይተሽው ታውቂያለሽ? እኔን አንቺ ውስጥ አይተሽው አታውቂም?» አሁንም ሳቁን አላቆመም። «ራሴን አንቺ ውስጥ ሳየው እንዴትኮ ደስ እንደሚለኝ! ያው ክፋትም ደግነትም በሚታየው ድርጊት እንጂ ውስጣችን በተቆለለው ልክ ስለማይመዘን እንጂ ሃሃሃሃሃሃሃ ሙች እኔ እንኳን የምቀናብሽ ክፉ እኮ ነሽ!»

ተመስገን! ከአራት ወር በኋላ ዲያቢሎሱ እሱ ተመለሰ። ዝም ከሚለው ወይም ከሚንፈራገጠው እሱ ይሄ ይሻለኛል። ቢያንስ ይፈትነኛል። እንዳስብ ያደርገናል። ጤንነት አይመስልምኣ? ከምጠላው ሰውዬ ጋር ማውራት መናፈቅ? ለማንም ጮክ ብዬ ባወራው ጤንነት አይመስልም። ጭንቅላቴን የሚፈትነኝ ወሬው ዝም ሲል ይናፍቀኛል።
«ማንም በድርጊቱ እንጂ በሃሳቡ አይዳኝም! ወይም ቢያንስ ሀሳብህ የአፍህን በር ለቆ ካልወጣ ማንም ላይ የክፋት በትርህ አሻራ አያርፍም!»
«ያ ልክ ነው ትያለሽ ታዲያ? ሰው መዳኘት የነበረበት በሃሳቡ እንጂ በድርጊቱ ነበር? ምን እሩቅ ወሰደሽ ራስሽን ምሳሌ አድርጊኣ? አሁን ፀሃይ (ሰራተኛችን ናት። ሳሎን ውስጥ ጉዝጓዙን እየጎዘጎዘች ስሟን ሲጠራ ቀና ብላ አየችን) እንዴት ያለች መልአክ ሴት ብትሆን ነው ይሄን ሰይጣን ባሏን ፈጣሪ ጀምሮ ሰጥቷት እንደማጠናቀቅ እንዲህ የምትንከባከበው? ብላ ነው የምታስበው! አይደለም ፀሃይ? (ፀሃይ ምን መመለስ እንዳለባት ግራ ገብቷት አይኗን ስታጉረጠርጥ እሱ ቀጠለ።) ድርጊትሽ አልሸወዳትም ታዲያ? አንቺ በመልካምነት ጅራፍ በቀልሽን እያሳረፍሽብኝ እንደሆነ እኔም አንቺም ሰይጣንም እግዜርም እናውቃለን። (ሳቅ ብሎ) በነገርሽ ላይ ነገሩን ለምሳሌ አመጣሁት እንጂ እየወቀስኩሽ አይደለም። ታዲያ የሚዳኘው አካል ፈጣሪ በይው ሊዳኝሽ የሚገባው በየትኛው ነው? በድርጊትሽ እንዲዳኝሽ ምኞቴ ነው (ሳቅ ብሎ) ካለበለዚያ እንደተባለው ሲኦል ካለ እዛ ስንሄድ አለቃዬ ሁሉ ልትሆኚ እንደምትችዪ አስበሽዋል?»

ፀሃይ ወሬው ይሁን ግራ የገባት ወይም እኔ ግራ የገባኋት መጎዝጎዟን አቁማ አይኗን ጎልጉላ ቆማ ታየኛለች። እንደማማተብም አደረገች ነገር።
እንዲህ አይነት ወሬዎቹ ናቸው እየጠላሁት እንዲናፍቀኝ ፣ ደሜን በብስጭት እያንተከተከው እንኳን ዝም እንዳይል እንድመኝ የሚያደርጉኝ። አንዳንዴ የሱን ጭንቅላት ሌላ ልብ ላለው ሰው ቢሰጠው ብዬ ተመኝቼ አውቃለሁ። እሱ ጭንቅላት እንጂ ልብ የለውም! ለነገሩ ሰይጣንምኮ ስማርት ነው።
«የሰው ልጅ የሀሳቡ ውጤት ነው። ድርጊቱ የሀሳቡ ልጅ ነው። ያ ማለት መልካምን የሚያደርጉ ሰዎች ሀሳባቸው ውስጥ ክፋት የለም ማለት አይደለም። ተፈጥሮ በሙሉ ሁለቱንም ፅንፎች የያዘች ናት። ውልደት እና ሞት፣ መነሳትና መውደቅ፣ ውሸትና እውነት፣ ፍቅርና ጥላቻ፣ ጨለማ እና ብርሃን፣ ቀንና ማታ፣ ክፉና መልካም……….. የሰውም ልጅ የእነዚህ ነገሮች ስብጥር ነው የጥሩ እና የመጥፎ ፣ የክፉና የመልካም፣ የጨለማ እና የብርሃን……… ጥያቄው የትኛው ያመዝናል ነው። የትኛው አሸንፎ በተግባርህ ይገለፃል ነው ጥያቄው! ሲጥ አድረሽ ጨርሺው የሚለኝን ክፉ ሀሳቤን አቅፈሽ ሳሚው በሚል መልካም ሀሳቤ ከረታሁት ሊቆጠርልኝ የሚገባው ያ ነው። አቅፌ ስስምህ አንተጋ በሚፈጠረው ስሜት ጥቂት ደስታን መቃረሜን ፈጣሪም ይቅር ይለዋል።» ይስቃል።

ከእርሱ ጋር ባሳለፍኩት ሰባት ዓመት የተማርኩት አንድ ነገር የማንም ሀሳብ አሸናፊ የማንም ሀሳብ ተሸናፊ አይደለም። በአብዛኛው ተስማምተን አናውቅም። ለሰዓታት ልንጠቃጨቅ እንችላለን። መጨረሻው ሁለት ፅንፍ ነው። የማሸነፍ እና የመሸነፍ አይደለም። ሙግታችንም የእኔን ልክነት እመን ወይ ተቀበል ግብ ግብ አይደለም። በቃ በህይወት ውስጥ ስላሉን የተለያዩ ምልከታዎች ሀሳብ መቀያየር ነው። ላለመሸነፍ ግብ ግብ የለውም።
«አንቺ ግን ፈጣሪ ብለሽ የምታምኚው በከረሜላ እንደምትደልዪው ህፃን ጅል ነው እንዴ የሚመስልሽ?»
« እ እ! ጅል ሳይሆን መሀሪ ……ተደልሎ ሳይሆን ራርቶ ይቅር የሚል ……እንደዛ ነው የሚመስለኝ።» ብዬ ቁርስ ላበስል ወደጓዳ ልሄድ ስል
«እስኪ ተያት ዛሬ ፀሃይ ትስራው ቁርሱን! »
«ለምን? ምን የተለየ ነገር ተገኘ ዛሬ?» በጥርጣሬ አየሁት
«ምንም! እንጫወት ብዬ ነው። አንቺም የምትፈልጊውን ላታገኚ ድካምሽ በዛ እና አሳዘንሽኝ!»
«ምንድነው የምፈልገው?»
«አንቺ የምታውቂኝን ያህል አውቅሻለሁኮ! »
«እኮ ምንድነው የምፈልገው?»
«ይቅርታ አድርጊልኝ የምትለዋን አረፍተ ነገር ሃሃሃሃ ተሳስቻለሁ! አንቺ መልካም ሴት ነሽ ይቅር በይኝ እንድልሽ? አይደለም በይኝና ተሳስቻለሁ እልሻለሁ።» አሁን መሳቁ የእኔ ተራ ሆነ።
«ስለእውነት የምፈልገው ምን እንደሆነ በትክክል አላውቅም። የሆነኛው ቀን ግን አዎ ይቅርታ ትጠይቀኛለህ ብዬ እጠብቃለሁ።»
«በፍፁም አላደርገውም! <ለምን ደግ እየሆንሽ ለበቀል የተሰጠሽን እድል ታባክኛለሽ? ስልሽ ያልሽን ታስታውሻለሽ? በእኔ ክፉት ክፉትህን ልታቀል? በእኔ ሀጢያት በደልህን ልትሰርዝ? በፍፁም ያን ደስታማ አልሰጥህም!!> ነበር ያልሽኝ። እራሴን አንቺ ውስጥ አየዋለሁ የምልሽኮ ለዚህ ነው። እኔም ያን ደስታ በፍፁም አልሰጥሽም! ተሳስቻለሁ ስልሽ በእኔ ስህተት ያንቺን ልክነት ልታደምቂ? አጥፍቻለሁ ስልሽ በእኔ ጥፋት ያንቺን ፅድቅ ልትፅፊ? በፍፁም ያን ደስታ አልሰጥሽም! Come on you know me better!»
«ፀሃይ ቁርሱን አብስይልንማ!» አልኳት ጉዝጓዙን መጎዝጎዙን ከጨረሰች ብትቆይም ንፁሁን ጠረጴዛ እየፈተገች እያፀዳች የነበረችውን ፀሃይ
«ምን ላብስል?»
«ከአራት ወር በፊት ለበዓል ሳትጠይቂኝ ታበስዪ እንደነበረው የበዓል ቁርስ!» አልኳት ወደወሬዬ ለመመለስ ቸኩዬ ሶፋው ላይ እግሬን ደራርቤ እየተቀመጥኩ። ለወሬ ፊቴን ወደ እርሱ ስመልስ ድክም ብሎ እየሳቀ
«ነርቭሽን ነካሁት አይደል?»
«በተዘዋዋሪ እንደበደልከኝ ማመንህ ግን ገብቶሃል? ይቅርታ በአፍህ አልጠየቅከኝም እንጂ በደልህን እኮ ታውቃለህ! ከደቂቃዎች በፊት አመንክ!» አልኩት
«እ እ! ራስሽን አታፅናኚ እኔ መጀመሪያም እንዳንቺ ጥሩ ሰውነቴን ለመግለጥ ራሴን የማሰቃይ ሰው አልነበርኩም ታውቂኛለሽ። ጥሩም መጥፎም አይደለሁም ራሴን ነኝ! የእኔ ምርጫ እና ድርጊት ከጎዳሽ ተጠያቂዋ ራስሽ እንጂ እኔ አይደለሁም! በምርጫሽ እንጂ አስገድጄሽ የዚህ ህይወት አካል አላደረግኩሽም! ማዘን ካለብሽ በምርጫሽ እዘኚ! በምርጫዬ ተሳስቻለሁ ብለሽ ካመንሽ ራስሽን ይቅርታ ጠይቂው። አንቺ ለራስሽ ያላመንሽውን ጥፋትሽን በእኔ አሳበሽ ራስሽን ነፃ አታውጪ! ይቅርታ የምትጠይቂው ለስህተት ነው። ተሳስቼ ያደረግኩት ነገር የለም። አውቄ እንጂ።» ይሄን ካለ በኋላ እያንዳንዱ ቃላት እኔጋ የሚሰጠኝን ስሜት ስለሚያውቅ ፈገግ አለ በድል አድራጊነት።
«የሰይጣን ጭንቅላት እንዳለህ ግን ታውቃለህኣ?»
«እንዳንቺ የምትፈትነኝ ሴት ኖራ እንደማታውቅ እንደምታውቂው!»
«ብትሞት!»
«እመኚኝ ይደብርሻል። ማን እንዲህ ያለ ሰይጣናዊ ጨዋታ ያጫውትሻል?»
«እመነኝ አይደብረኝም። ሰይጣናዊ ጨዋታህን ለ7 ዓመት ተግቼዋለሁ።»
«እና በተዘዋዋሪ ደቀመዝሙሬ መሆንሽን አመንሽ ማለት ነው?»
በሩ ተንኳኩቶ ፀሃይ የሆኑ የማላውቃቸው ሴትዮ አስከትላ ገባች። ማን እንደሆኑ ከመጠየቄ በፊት የእሱ ድንጋጤ ማንም ይሁኑ ምኑ ብቻ ቅዠቱ እንደሆኑ ነገረኝ!!
«አስወጧት! አስወጡልኝ!» ጮኸ ……..
በሚችለው ሁሉ ተወራጨ። እየሆነ ያለውን ነገር ከመረዳቴ በፊት ዘሎ ከዊልቸሩ ተነስቶ ሴትየዋጋ መድረስ ይችል ይመስል ደምስሮቹ ተገታትረው ባለ በሌለ ሀይሉ ተወናጭፎ ወደፊቱ ወደቀ። ቢችል በዝህችው ቅፅበት አንቆ የሚገድላቸው ነው የሚመስለው! ሴትየዋን ከማስወጣት እሱን ከማንሳት እየሆነ ያለውን ከመረዳት ምኑን እንደማደርግ ግራ ገብቶኝ መሃል ላይ ስዋልል
«በናትሽ አስወጫት! እባክሽ?» አለ አቅም ባጣ ስሜት። ፀሃይ ሴትየዋን እያዋከበች ልታስወጣት ስትሞክር ለሰከንዶች የሴትየዋን ፊት አየሁት። ምንም ስሜት የሌለው ሙልጭ ያለ ፊት ……….. ተከትያቸው ልሄድ አሰብኩ። ያሰብኩት ገብቶታል።
«እባክሽ?» አለኝ። ተስፋ በቆረጠ የልመና ድምፅ
ተመልሼ አጠገቡ መጣሁ። ሴትየዋ ሄደች። ላነሳው ስሞክር። «ተይኝ!» አለኝ።
«እሺ አልተጎዳህም?» አልኩት እንዳወዳደቁ ከአደጋው ሳይሰባበር የተረፈ አጥንት ካለ እንክትክት የሚል ነበር የሚመስለው።
«ደህና ነኝ! እግሬን ብቻ ዘርጊልኝ» አለ! ሲወድቅ የታጠፈ እግሩን ዘርግቼለት ምንጣፉ ላይ በጀርባው ተስተካክሎ እንዲተኛ አድርጌው አጠገቡ በጀርባዬ ጋደም አልኩ። ፀሃይ «አስወጥቻቸዋለሁ» እያለች ወደሳሎን ስትገባ ወለል ላይ በጀርባችን ተጋድመን ስታየን ሳትፈልገው የግርምት ድምፅ አመለጣት። <ሰዎቹ ለይቶላቸዋል> አይነት ነው ግርምቷ።
«እባክሽ? በናትሽ? ቀድቼ ሁላ ደጋግሜ ብሰማው ደስ የሚለኝ ቃል! ጆሮዬን እኮ ነው ያላመንኩት! አንተ? እባክሽ?»
«ደስ አለሽ?» ድምፁ ቅድም እንደዛ የተሸነፈው ሰው ድምፅ አይደለም።
«አልዋሽህም ደስ የሚል ስሜት አለው። ካወቅኩህ ጀምሮ ማንንም ስለምንም ለምነህኮ የምታውቅ ሰው አይደለህም! እኔና አንተ አንወሻሽማ? የሆነ ቦታ ድክመት እንዳለህ ማወቅ ደስ የሚል ስሜት አለው። ተሸንፈህ አይቼህ አላውቅም። እሱኛው የሰጠኝን ስሜት አላውቀውም።»
«እና ተሳሳትኩ? ሲኦል ብንገናኝ አለቃዬ አትሆኚም?»
«ማናቸው ሴትየዋ?»
«ሲዖሌ ናት። ገሃነም! »
«ምንህ ናቸው? እናትህ?»
«ሲዖሌ አልኩሽኮ!»
አውቀው የለ?? በቃ አይመልስልኝም! አይነግረኝም። በጀርባዬ እንደተንጋለልኩ እጁን ፈልጌ እየያዝኩት እሱ ሳያውቅ ሴትየዋን እንዴት ላገኛቸው እንደምችል አስባለሁ።
«እ እ አታባብዪኝ! አትዘኚልኝ! እረፊ !! እኔና አንቺ ይሄን ጨዋታ አንጫወትም!» አለ።እንደሌላ ጊዜው እጁን ሊያስለቅቀኝ ግን አልተወራጨም። ቀጠል አድርጎ «የምታስቢውን ተይው። አይጠቅምሽም ልታገኛት አትሞክሪ»

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አራት)

One Comment

  • yonas birhanu commented on May 8, 2022 Reply

    ኦ ሜሪሻ፡ ሰንበትን እዚሁ ነን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *